
በኃይሉ አበራ
በጀኔቫ በሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት የሚመራውና የኮቪድ -19 መነሻ የሚያጠና የባለሙያዎች ልዑካን ቡድን ወደ ቻይና እንዳይገባ በመከልከሉ ገና ከጅምሩ እየተሰናከለ መሆኑን በመግለጽ የዓለም ጤና ድርጅት ቅሬታ አሰምቷል።
ልዑኩ በመጨረሻው ሰዓት ወደ ቻይና እንዳይገባ በመከልከሉን ባልተለመደ መልኩ ከቤጂንግ የተባበሩት መንግስታት አካል በኩል መስማቱ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምን እንዳበሳጫቸው ጃፓን ታይምስ የተባለ ድረገጽ ዘግቧል።
በዘገባው መሰረት ለወራት ያህል በጥንቃቄ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አስር ጠንካራ የልዑካን ቡድን በዚህ ሳምንት ወደ ቻይና ለመድረስ ተስፋ አድርጎ ነበር። ቤጂንግ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት የዳረገውን እና የዓለም ኢኮኖሚን ወደ አዘቅጥ የጣለውን የቫይረሱን መነሻ ታሪክ ብቻዋን ለመቆጣጠር ቆርጣለች ይላል ዘገባው።
እኤ.አ በ2019 ማብቂያ አከባቢ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ኬዝ በማዕከላዊ የቻይናዋ ውሃን ከተማ መመዝገቡን ተከትሎ የማስፈራሪያ ክሶች ሲሰሙ ቢቆዩም የቻይና ባለስልጣናት ጉዳዩን በሚስጥር ይዘውታል፤ ቫይረሱም ከቻይና ውጪ በዓለም ሀገራት ተሰራጭቷል።
ነገር ግን ቤጂንግ ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው የመጀመሪያ ቀናት ጀምሮ ሙሉ ገለልተኛ ቡድን ምርመራ እንዲደረግ የሚለውን ስትቃወም ቆይታለች፤ ድንገተኛ ወረርሽኙ በግዛቷ ውስጥ መጀመሩን በተመለከተ ጥርጣሬን እንዲፈጠርም አድርጓል።
የዓለም ጤና ድርጅት ልዑክም ጥርጣሬን ለማስወገድና ቫይረሱ እንዴት ከእንስሳት ወደ ሰው እንደመጣ የጠራ መልስ ለማግኘት በሚል ሂሳብ ተሰይሟል። ነገር ግን የተወሰኑ የልዑኩ ቡድን በጉዞ ትራንዚት ቢገኙም ቤጂንግ እስካሁን የመግቢያ ፍቃድ እንዳልሰጠቻቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ገልጸዋል።
ዶክተር ቴዎድሮስ ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ዛሬ የቻይና ባለሥልጣናት ወደ ቻይና ለሚመጡ የቡድን አባላት አስፈላጊ ፈቃዶችን እንዳላጠናቀቁ ተገንዝበናል። ሁለት አባላት ቀድሞውኑ ጉዞአቸውን ስለጀመሩ እና ሌሎች በመጨረሻው ሰዓት መጓዝ ባለመቻላቸው በዚህ ዜና በጣም አዝኛለሁ፤” ብለዋል።
“ተልዕኮው ለዓለም ጤና ድርጅት እና ለዓለም አቀፍ ቡድን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን” ግልጽ ለማድረግ ከቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በአጽኖት ለመነጋገር መጣራቸውን ተናግረዋል። አክለውም “ቻይና የውስጥ አሰራሯን በማስተካከል ለማሰማራት በተቻለ ፍጥነት እየሰራች መሆኑን አረጋግጫለሁ” ብለዋል። ተልዕኮው በጣም አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን የዓለም ጤና ድርጅት ሆነ ቻይና እስካሁን መቼ እንደሚጀመር እንዳላረጋገጡ ዘገባው አስቀምጧል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዳይሬክተር ማይክል ሪያን ማክሰኞ ዕለት ባደረጉት ገለፃ ችግሩ የቪዛ ማረጋገጫ ችግር ነው ብለዋል። በኛ እምነት ይህ በፍጥነት ሊፈታ የሚችል የሎጂስቲክስ እና የቢሮክራሲያዊ ጉዳይ ብቻ ነው ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ ከቻይና የተሰጠ አፋጣኝ አስተያየት የለም።
“ሁላችንም ቡድኑ ዛሬ መሰማራቱን እንደሚጀምር በመረዳት እንሰራ” ያሉት ሚኒስትሩ ማክሰኞ ማለዳ ከሩቅ የሚመጡ ሁለት የቡድን አባላት አስፈላጊ ማረጋገጫዎች አለመቀበላቸውን ከማወቃቸው በፊት መነሳታቸውን ተናግረዋል። የተልእኮውን “ፍጹም ተጨባጭ ባህሪ” አፅንዖት ሰጥተው “የሚያበሳጭ እና… ተስፋ አስቆራጭ” መሆኑን አስረድተዋል።
የኮቪድ-19 አመጣጥ መነሻ ተጨባጭ ጭምጭምታ እና ግምታዊ ጭብጥ በመጥፋቱ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የከረረ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል። እንዲሁም የቫይረሱን መነሻ ትርክት ለመቆጣጠር የወሰኑ የቻይና ባለሥልጣናት እውነታዎችን ለማድበስበስ ላይ ተወስነዋል።
የሳይንስ ተመራማሪዎች ቫይረሱ መጀመሪያ በውሃን ከተማ ውስጥ ልዩ እንስሳትን ለስጋ በሚሸጥ ገበያ ወደ ሰው ተላልፏል ብለው ያምኑ ነበር። ነገር ግን ባለሙያዎቹ አሁን ገበያው የበሽታው ቀጥተኛ መነሻ ሳይሆን ምናልባትም የተጠናከረበት ቦታ ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ። ቫይረሱ በመጀመሪያ ከሌሊት ወፎች የመጣ መሆኑ በሰፊው ይታሰብ ነበር፤ ነገር ግን ከሌሊት ወፎች ወደ በሰዎች ያስተላለፈው መካከለኛው እንስሳት የትኛው እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013