ራስወርቅ ሙሉጌታ
ኧረ ጎበዝ የማስታወቂያችን ነገር ወዴት እያመራ ይሆን፤ በቅርቡ ከአንድ ወዳጄ ጋር ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ ሳቀና የገጠመኝ ነገር አካባቢየን በአግባቡ መቃኘት እንዳለብኝ በር የከፈተልኝ ነበር። በእለቱ የተፈጠረውን ነገር ልጠቁማችሁና ወደ ዋናው ጉዳዪ ምልከታዬን መነሻ አድርጌ ልግባ።
እንደ ቻይና ባቡር ተጠማዞ ተጠማዞ መጨረሻው የማይታወቀው የታክሲ ወረፋ ተስፋ አስቆራጭ ስለነበር የቻልነው ድረስ የአመሻሹን አየር እየወሰድን በእግር ለመጓዝ ወክ ለማድረግ ተስማምተን ማዝገም ጀመርን። ጥሩ ርእሰ ጉዳይ መርጠን እየተጨዋወትን ስለነበር ሳናውቀው ብዙ መንገድ ከተጓዝን በኋላ እረፍት ለማድረግም መክሰስ ብጤ ለመቅመስም ከአንድ የፍራፍሬና ጭማቂ መሸጫ ቤት ጎራ አልን።
አንዲት ቆንጅዩ ምታሳሳ ልጅ እግር መጥታ ከታዘዘችን በኋላ የሚጠጣው ነገር እስኪመጣ አይኔን ወደ አንድ ጎን ግድግዳ ስወረውር ቀልቤን የሳበውና ያስገረመኝን ነገር ለማየት በቃሁ። ብዙ ግዜ በጭማቂ ቤቶች ተሰቅለው የማያቸው የአትክልት ቦታ፤ መናፈሻዎችን የፍራፍሬና የጭማቂ ምስሎች አልያም ሀይማኖታዊና ማህበራዊ ይዘት ያላቸውን ጥቅሶች ነበር። ይህኛው ግን ለየት ያለ ነበር በእርግጥ ጋደኛዬ ይሄ ምንም እንዳልሆነና ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሌሎች ቦታዎች ማየቱን ቢነግረኝም እኔን ግን ከመገረም ሊታደገኝ አልቻለም።
በአትክልት ቤቱ የቀኝ ጎን ግድግዳ ላይ በትልቅ ፍሬም ውስጥ በመስታወት ተሸፍኖ የተቀመጠ ማስታወቂያ አለ።
ማስታወቂያው በመግቢያው ላይ “የእነዚህን አትክልቶች ጥቅም ያውቁ ኖሯል?” ሲል ጠይቆ ይጀምርና ከስሩ በቤቱ ውስጥ የሚሸጡት አትክልቶች በሙሉ ያላቸውን የጤና ጥቅም ይዘረዝራል። ፍራፍሬዎቹ በስምና በምስል በአንድ ጎን የተደረደሩ ሲሆን በትይዩ በአሁኑ ወቅት የህዝብ ቀዳሚ የጤና ችግር የተባሉት እንደ ኩላሊት ስኳርና ደም ግፊት ሆድ ድርቀት ለጨጓራ ተደርድረዋል ታዲያ ጽህፎቹ ያግዛል ይረዳል የሚሉ የደከሙ ቃላቶችን የያዙ ሳይሆን በድፍኑ «ለመከላከል ይጠቅማል» ብለው ነው የዘጉት።
እንግዲህ ልብ በሉ እነዚህ ሰዎች መቼም በዚህ ዘመን ያመመው ባይኖር አንድ በሽታ ይኖርብኛል ብሎ የማይሰጋ ስለማይኖር እዛ ቤት ከገባ የእነሱን ህክምና ሳይወድ ለመቀበል ይገደዳል ማለት ነው።
በጣም ተገርሜ ለመሆኑ የትኛው ዶክተር አዟቸው ነው። አንድ ሀኪም በስንት ጥረት የሚደርስበትን ምርምር እነሱ አትክልት ከመላጥና ከመፍጨት የዘለለ ሞያ ሳይኖራቸው እንዲህ የሚያዙት። ለሰው ልጅ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ያለው ፋይዳ አትክልትና ፍራፍሬ ያላቸው የበሽታ መከላከል አቅም ከፍተኛ መሆኑ በጥናት የተረጋገገጠ ቢሆንም እንደዚህ የሚሸጡትን ምርት ከህመም ጋር አያይዞ ማዋደድ ግን ተገቢ አይመስለኝም። ለነገሩ ማተሚያ ቤት መሄድ ደብሯቸው ካልሆነ ለኮሮና የሚሆንም ፍራፍሬ ሳያዘጋጁልን አይቀሩም ነበር አልኩኝ በሆዴ ነገር እየበላሁ። ጓደኛዬ የኔ በነገሩ መብሰልሰል አልተዋጠለትም እናም ይሄማ ምን ችግር አለው በሚል ስሜት አይኔ ሲያያቸው ኖሮ ያላስተዋልኳቸውን ነገሮች ይዘረግፍልኝ ጀመር።
…. ይሄ ምን ይገርማል እኛም እኮ የምንሸጠውን ምርት ባንናገርም እከሌ እንትን አመመው ስንባል ከዳማከሴ ጀምረን የማናዘው መድሀኒት የለም። እኛ ሄደን ወይንም በቅርብ የምናውቀው ሰው ታክሞ የዳንበት ሆስፒታል ካለ የታመመ ሰው ስናገኝ ወደዛ መምራታችን አይቀርም ምግቡም እኮ እንደዛው ማለት ነው።
ጨጓራችንን አሞን ስንበላው የተስማማን ነገር ካለ ጨጓራ ያመመው ስናገኝ ጠቆም ማድረጋችን አይቀርም። በእርግጥ በዚህ ደረጃ የሚያቀርቡትን ምርት በህመም አሳቦ አዋዶ መሸጥ ይከብዳል።
ለስንቱ የማላውቀውን መድሀኒት ሳዝ ቆይቺያለሁ ብዩ ራሴን መፈተሽ ጀመርኩ። ጓደኛዬ ጨዋታውን ቀጥሏል።
ይልቅስ ካነሳሀው አይቀር አለ የቀረበለትን አትከልት በሹካ እያባረረ እየለቀመ። ይልቅስ ካነሳሀው አይቀር እነዚህ ቤተክርስቲያንና መስኪድ ስር አንዳንዴ ደግሞ በየመንገዱ ዳር ከካንሰር እስከ ቡዳና ሰላቢ መድሀኒት አለን ብለው በየብልቃጡ የሆነ ያልሆነውን ነገር እየከተቱ የሚቸረችሩትን መንግስት ለምን መላ እንደማይልልን አይገባኝም።
በስንቱ ህይወት እየቀለዱበት መሰለህ። እነዚሁ ሰዎች በሬዲዮ በጋዜጣና በየግድግዳው ላይ በሚጽፏቸው ማስታወቂያዎች የማያቀርቡልህ የመድሀኒት አይነት የለም። በነገራችን ላይ የሌላውን አለም ባላውቅም እኛ ሀገር የሀበሻ መድሀኒት አዋቂ እንደዘመናዊ ህክምና ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ ሀገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጪ ሪፈር አይልክህም።
አፍንጫህ ድረስ ተስፋ እየሰጠ መቃብርህ ተምሶ ልጥህ ተርሶ ጉድጓድ እስክትገባ ድረስ እንደ ቆላ ፍየል ያገኘነውን ሁሉ ቅጠል እየደቆሰና እየጨቀጨቀ ሲያበላህ ይኖራል። በጣም ተጨንቀህና ደፋር ሆነህ ደግሞ መፍትሄ አለማግኘትህን ከነገርከው ያመናፍሰውና (መንፈሳዊ ያደርገውና) ከጎረቤትህ አልያም ከጓደኛህ ካሰኘው ደግሞ ከቤተሰብህ አንዳች ነገር ያቀመሰህ እንዳለ ጠቆም ያደርግህና ብቻህን እያወራህ እንድትሄድ ይፈርድብሃል።
ብቻ መቼም ይሁን በምንም ጉዳይ ይሁን አንችልም አናውቅም አይሉህም በጣም ጎበዝና ብልህ ስለሆኑ የሚነግሩህና የሚሰጡህ ነገር አያጡም። የባሰ አለና ሀገርህን አትልቀቅ አልኩ የሚነግረኝን ነገር እንዴት እስካሁን እንዳላስተዋልኩ ለራሴ እየገረመኝ።
ጓደኛዬ ብዙ ነገር ሲያጫውተኝ ቢቆይም እኔ የተረዳሁት የሰውን ችግር በዛ ላይ ህመምን በሽታን ያህል ክፉ ነገርን ለገቢ ማስገኛነት መጠቀም ሃላፊነት የጎደለው ስራ አንደሆነ ብቻ ነው።
ለሱ ግን ምንም ልለው አልፈቀደኩም እናም ሂሳባችንን ከፍለን ከወጣንና ትንሽ ከተጓዝን በኋላ አካባቢ ያሉትን ሳላስተውል እያነበብኳቸው ሳላውቅ ተጽእኖ ሲፈጥሩብኝ የነበሩትን የመንገድ ላይ የስልክ እንጨትና የህንጻ ማስታወቂያዎች እየገመገምኩ ጉዞዩን ቀጠልኩ።
ለካ ከተማችን የማስታወቂያ ሀብታም ናት ድልድይ ላይ ሳይቀር የሚለጠፉና የሚንጠለጠሉ በርካታ ማስታወቂያዎች በየመንገዱ ዳርቻ አሉ።
ምን አልባትም በየትኛውም አቅጣጫ በአውራ ጎዳናዎች ላይ ብንጓዝ በየሀያ ሜትር ርቀት ማስታወቂያ ሳናገኝ የምናልፍ አይመስለኝም።
በተለይም በሰው ቁመት ተመጥነው በኤሌክትሪክና በስልክ እንጨቶች ላይ እላይ በላይ እየተለጠፉ የተደረቱት ወረቀቶች የእለት ከእለት ትእይንታችን ስለሆኑ አላስተዋልናቸውም እንጂ ምን ያህል ከተማችንን እንዳበላሿት ብናውቅ ስንቶቻችን ስንፍቃቸው በዋልን ነበር።
ሌላው ቀርቶ በየቀኑ ክፍት የስራ ቦታ እየተባለ የሚለጠፉት የጠየቁትን ያህል ሰራተኛ ቢቀጥሩ ኖሮ መንግስት ስራ ፈጠራ ብሎ ጥቃቅንና አነስተኛን ባላደራጀ ኧረ ኤጀንሲውንም ባላቋቋመ ነበር።
አንዳንዶቹ ማስታወቂያዎች ደግሞ የኮንሰርትና የባዛር ጥሪን የሚያውጁ እጅግ በጣም ግዜቸው ያለፈ ነገር ግን የሚያወርዳቸው የሚፍቃቸው አጥተው አይናችንን ማረፊያ ያሳጡታል። እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው እኔም ቀለል አድርጌ ያየኋቸውና ከተማችንን ከማቆሸሽ የዘለለ በቀጥታ ከእኛ ጋር ብዙ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው።
እንዲህ እንዲህ እየታዘብኩ ሾላ ገበያ አካባቢ ስደርስ ከእንድ ሚኒባስ ላይ በሞንታርቦ የተለቀቀልኝ የጥሪ ማስታወቂያ ደግሞ በብርሃን ቅጽበት በሀሳብ መገናኛና አራት ኪሎ እንድገኝ አረገኝ።
ረፋድና አመሻሽ ላይ መገናኛና አራት ኪሎ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር በሚኒባስና መሰል መኪናዎች አንዳንድ ግዜም እንደ ልጅ በትከሻና በደረት በታቀፉ (የድምጽ ማጉያ) ስፒከሮች ሲያደናቁሩን የሚውሉት በርካቶች ናቸው።
የሀይማኖት መዝሙር፤ ስብከት የእቃ ሽያጭ የእርዳታ ማሰባሰቢያ …. ምኑ ቅጡ። እንግዲህ እነዚህን ሁሉ ማስታወቂያዎች እያንዳንዱ ሰው የሚሰማው ሶስት ቃላቶችን በአንድ (ዋጋ፤ የእቃ ጥራትና አጋጣሚና እድለኝነትን) ደራርበው ከሚጠሩት የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በተረፈው ጆሮ ነው።
ያው የታክሲ ረዳቶች ልፈፋና ከየልብስ መደብሩ የሚወጣው ዘፈን የየለት ቀለባችን ስለሆነ የሚዘነጋው አይኖርም ብዬ ነው። እንዲህ እንዲህ እያልኩኝ በትዝታና በምልከታ እዚህና እዛ ስዘል ቆየሁ በኋላ ሁለት ሌላ አዳዲስ ተከታተይ ሀሳቦች በአእምሮዩ ድቅን አሉብኝና።
የመጀመሪያው ሀሳቤ ግን መንግስት ለምንድነው ይህንን ነገር ስርአት የማያሲዘው ከተማዋና ነዋሪዎቿ እኮ የድምጽ ብክለት እያሳቀያቸው ነው የሚል ሲሆን። ሁለተኛው ደግሞ ለእንደዚህ አይነት ሰላምን የሚነሱ ተግባራት የህብረተሰቡ ምላሽ ምን ሊሆን ይገባል የሚል ነበር።
መንግስት በፖሊስም ሆነ በደንብ አስከባሪ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚሰራቸው ስራዎች እንዳሉ ባውቅም በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አለማምጣታቸው ግን ገሀድ የወጣ ሀቅ ነው። ለነገሩ ትናንት በህጋዊ መንገድ ሱቅ ከፍተው ግብር ከፍለው የሚሸጡ ሰዎች በር ላይ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ተመሳሳይ ምርት ይዘው በርካሽ ዋጋ እየጠሩ ሲሸጡ እርምጃ ባለመወሰዱ ዛሬ መንገዱ ሁሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ እቃ የሚቸረቸርበት ገበያ እየሆነ መጥቷል።
እዚህ ላይ በጣም የሚገርመው መንግስት በየጎዳናው ዳርቻ የተኮለኮሉትን አሯሩጦ ሳይጨርስ ጥቂት ብልጣብልጦች በቴክኖሎጂ መግግባት ጀምረዋል። ግብር መክፈል የለ? ፖሊስ እያባረራቸው? ጸሀይና የሰው አይን አይበላቸው ? ….. ምን አለፋችሁ መንግስት ያሰማራቸው ደንብ አስከባሪዎችና ፖሊሶች መሀል ከተማ ላይ ሲተራመሱ እነ ህገ ወጥ ነጋዴዎች በቴሌግራም በኢሞ በፌስቡክ ቀን ከሌት ሳይሉ ቤታችን ገብተው ቁጭ!!! አይገርምም። ልብሱ…. ቅባቱ…. ቴሌቪዥን…. ፍሪጅ…. ቤት ….. ምን ቀረ?።
የሚገርመው እነዚህ ሰዎች ከሩቅ ምስራቅና አውሮፓ እንዲሁም አሜሪካ የሚመጡ ውድ እቃዎችን በኮንትሮባንድ መቸብቸባቸው ሳያንስ «እቤትዎ ድረስ እናደርሳለን እያሉ» በስንት መከራ በማህበር ተደራጅተው እዳ ገብተው ስራ የጀመሩትንም ባለ ታክሲዎች ከጨዋታ እያስወጧቸው ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ሳወጣ ሳወርድ ከቆየሁ በኋላ መንግስት መሆን በጣም ከባድ መሆኑን ስለተረዳሁ እንደ ዜጋ ላስብ ብዬ ወደ ማህበረሰቡ ሃላፊነት በሀሳብ ተሸጋገርኩ።
ግን ለምን ከመንገድ ላይ መግዛት አናቆምም ? አልኩ ለራሴ በእርግጥ ዋጋ ይቀንሳል ቢሆንም እንደ ህዝብ በስርአት መቀጠል ስለሚኖርብን ስርአት ይዘው ለሚሰሩት ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባ ነበር።
ነገር ግን ህግ ለማክበር ብሎ መቶ ብር መንገድ ላይ የሚሸጥን እቃ ከሱቅ ሁለት መቶ ብር መግዛት …. እኔ እንጃ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡን ለተሳሳተ ውሳኔ የሚያበቃው የነጋዴዎቹ ውትወታ ሃሳቡን እያስቀየረው መሆኑ ግን በግሌ በጣም አስከፋኝ። ምክንያቱም ሰው ፕሮግራም አውጥቶ እቃ ለመግዛት ገበያ እስካልወጣ ድረስ ማንም ስለጮኽ ሀሳቡን መቀየር የለበትም የሚል ጽኑ አቋም ስላለኝ ነው።
ረጅሙንና ጸጥ ያለውን የሰፈራችንን መግቢያ በሰላም ከተጓዝኩ በኋላ ወደ ቤቴ መገንጠያ ላይ ስደርስ ከአንዲት የጎረቤት ግሮሰሪ እጅግ የሚያምር ድምጽ ወደ ጆሮዩ ይዘልቅ ጀመር። ዘፋኙ ስሜቱን ለመግለጽ አልያም ገቢ ለማግኘት እንደዘፈነው ባወቅም ባለ ግሮሰሪዎቹ ለማስታወቂያ እንደከፈቱት እርግጠኛ ነበርኩ። ስፒከሩ አዲስ ስለሆነ ይሁን ወይንም እኔ ዘፈኑን ስለማውቀው አላውቅም ግጥሞቹ ጥርት ብለው ነበር የሚሰሙኝ።
ድምጻዊውም በሚያምር ድምጹ በጥሩ የሙዚቃ መሳሪያ ታጅቦ እንዲህ እያለ ያዜማል።
ሳናሞናሙነው ሳናሞናሙነውስንሸላለመው ነግቶ ሊቆጨነው እናም ረጅም መንገድ ስለተጓዝኩ ይሁን ወይንም ለማስታወቂያ አልያም ለመወስወሻ የተከፈተውን ሙዚቃ ስለሰማሁ አላውቅም ብቻ ያንን ሁላ የከተማ ጫጫታ ከእቁብ ሳልቆጥር የመጣሁት ሰው በድንገት የድካም ስሜት ሲሰማኝ አረፍ ለማለት ወደ ግሮሰሪው አቀናሁ።
ግሮሰሪው ገብቼ እንደተቀመጥኩ ከቀረበለኝ ነገር እኩል ሌላ አዲስ ሀሳብ ብልጭ አለልኝ። ለካስ የማስታወቂያዎቻችን ሁላ ጉልበት ከእነሱ ሀይል የመነጨ ሳይሆን ከእኛ ፍላጎትና ምኞት የተቀዳ ነበር።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 2013