ወርቅነሽ ደምሰው
በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሲባል ፀረ ተባይና ፀረ-አረም ኬሚካሎች በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ፀረ አረም ኬሚካሎች ደግሞ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡
በዚህም በአስመጪነት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ በማሟላት ከሚመለከተው አካል የፀረ አረም ኬሚካል አስመጪነት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ኬሚካሉን ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ የሚያደረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አንዳንድ አስመጪዎች እንደሚናገሩት፤ የፀረ አረም ኬሚካል አስመጪነት ፈቃድ ለማግኘት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው ቢገኙም፤ እስካሁን ፈቃድ ማግኘት አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ የፀረ አረም ኬሚካል አስመጪነት ፈቃዱን ለመውሰድ ጥያቄ ካቀረቡ አምስት ወራት ያለፉ ሲሆን፤ እስካሁን ፈቃዱን ማግኘት አልቻሉም፡፡
እንደ አስመጪዎቹ ገለጻ፤ እስካሁን ፈቃድ ማግኘት ባለመቻላቸው ኬሚካሉ የሚፈለግበት የመኸር ጊዜ ሊያልፍ ነው፡፡ ወቅቱ ካለፈ ደግሞ ቢመጣም ገዥ ስለማያገኙ ሊያከስራቸው ይችላል፡፡
በዚህም ምክንያት የንግድ ሥራቸውን ወደ ሌላ ለመቀየር እስከማሰብ ደርሰዋል። ለሚመለከተው አካል ምክንያቱን ለማወቅ ቢጠይቁም አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ቅሬታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን አድርሰዋል፡፡
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሰጡን ዘንድ ያነጋገርናቸው በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃና ኮረንቲን ጀነራል ዳይሬክተር አቶ ግርማ በቀለ እንደሚሉት፤ የቀረበው ቅኔታ ትክክል መሆኑን አምነው የፀረ አረም ኬሚካል ፈቃድ ለማግኘት ያለውን ሂደት እንደሚከተለው ያብራራሉ።
አንደኛ የፀረ ተባይ ኬሚካል ፍተሻ የሚካሄደው በቡድን በመሆን የኬሚካሉን አጠቃላይ ሁኔታ የማረጋገጥ ሥራ ይሰራል፡፡ ሁለተኛ ከአካባቢ ተፅዕኖ አንጻር አካባቢ ይበከላል ወይስ አይበክልም የሚለው የሚታይ ሲሆን፤ ሦስተኛ በሰው ላይ ሊያስከትል የሚችል ተፅጽኖና ሌሎችም በጣም በጥልቀት የሚታዩ ጉዳዮች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች አንድ አመልካች የአስመጪነት ፍቃድ እንደጠየቀ ወዲያውኑ ሊያገኝ ይችላል ይላሉ፡፡ ስለዚህ ፀረ አረም ኬሚካል አስመጪነት ፍቃድ በዚህ ቀንም ይሰጣል ተብሎ መወሰን የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፈቃድ አሰጣጡ በባለሙያዎች ቴክኒካል ግምገማ ከተካሄደ በኋላ መስተካከል ያለበት እንዲስተካከል አስተያየት ይሰጣል፡፡ አንደኛ የተሰጠው አስተያየት ባለጉዳዩ አስተካክሎ በሚያመጣበት ጊዜ ይወሰናል፤ ሁለተኛ ደግሞ በአስተያየቱ አይነት የሚወሰን በመሆኑ፤ ከዚህ አንጻር የሚመላለስ ነገር መኖሩን ይገልጻሉ፡፡
ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ የዘገየበት ምክንያት ግን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ ለስምንት ወር ተቋርጦ ስለነበር እና ሙያተኞች ወደ ስራ ሳይመለሱ በመቆየታቸው የዘገየበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ፡፡ የፀረ ኬሚካል ፍቃድ ለመውሰድ ካመለከቱት ውስጥ ከሰባት ወር በላይ የቆዩ ያሉ ሲሆን፤ ከኮቪድ በኋላ ከመስሪያ ቤቱም ሆነ ከተገልጋዩም አንጻር አንዳንድ አሠራር ላይ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ያሉ መሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ብዙ ፍላጎት ያለበት አካባቢና የመልካም አስተዳዳር ጉዳይ የሚነሱበት ቦታ በመሆኑ ለማስተካከል ጊዜ መውሰዱን ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ስራ የሚገመገመው በቡድን በመሆኑ እና በርካታ ሰዎች አንድ ላይ መሰብሰብ ባለመቻላቸው ምክንያትና በርካታ የወረቀት ዶክመንቶችን ማገላበጥ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡
ሁሉም ነገር ያለቀለትን ዶክመንት እንኳን ቢሆን፤ በግምገማው መሰረት የአስተያየቱ ደረጃ ይለያል፡፡ የጎደለው ነገር ካለ ለባለጉዳዩ ስለጎደለው ጉዳይ በዝርዘር ተጠቅሶ አሟልቶ እንዲመጣ መልስ በፅሁፍ ይሰጠዋል፡፡ ባለ ጉዳይ አሟልቶ የሚያመጣበትና ቀለል ያለ አስተያየት ከሆነ ቶሎ የማምጣት ከበድ ያለና ከአምራቾች ጋር የሚገናኝም ከሆነ አስተያየት ከሆነ ያንን አደራጅቶ እስኪያመጡ ጊዜ ሊወስድ ይችላል በማለት ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ግርማ ገለጻ፤ በጣም በርካታ በግልጽ የሚታወቁ ባለጉዳዮችም የሚያቀርቧቸው የአሰራር ችግሮች አሉ፡፡ የግልጽነት ችግር አለ ብለው ተገልጋዮች የሚያነሱት ጉዳይ ግን ተለይቶ መጠቀስ አለበት፡፡ ማንም ሰው ወይም ባለጉዳይ መስተናገድ ያለበት በመጣበት አግባብ ሲሆን፤ እዚህ ላይ ከመስሪያቤቱ ሆነ ከባለጉዳዮች በኩል ያሉ ችግሮች መፈታት አለባቸው፡፡
ይህንን ለማስተካከልም የአጭር ወይም የረጀም ጊዜ የተሻለ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት መፍትሔ ሊመጣ ይችላል፡፡ አሁን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሠራተኞች ጋር ውይይት ተደርጎ አቅጣጫ ተቀምጧል፤ ነገር ግን በዘላቂነት ዘርፉ መሠረታዊ መፍትሔ የሚፈልግ ነው፡፡
በዚህ ዘርፍ የተሠራ አስመጪ ወይም ካምፓኒ ወዲያውኑ ኬሚካሉ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ ይጠቅማል ተብሎ የሚታሰበው ያህል ጉዳቱም የትየለሌ ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ ይህንን ነገር በጥንቃቄ መከታተል የማይቻል ከሆነ ለትውልድ ጠንቅ ስለሆነ፤ ከኬሚካል ጋር የሚያያዙ በሽታዎች ምን ያህል ችግር እንደሚያስከትሉ ይታወቃል፡፡
ስለዚህ በአጭር ጊዜ መስተካከል ያለባቸው የሚስተካከሉበት ሁኔታ ይኖራል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ መዘግየቱ ችግር ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህንን ለማስተካከል የሚወሰደው እርምጃ ላይ ጥንቃቄ መደረግ ይገባዋል ይላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ የሚሆነው የትውልድ ጥፋት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። አሁን የቀረበው ቅሬታ ትክክል ሲሆን፤ ኬሚካል ገበያ የሚፈልግበት ወቅት ያለው በመሆኑም መልስ ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
አንዱና ትልቁ በዚህ ዘርፍ የሚሰራ ሥራ በሥነ ምግባር መስራት አለበት የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በታማኝነትና ኃላፊነት ባለው መልኩ መሠራት ያለበት ምክንያት የሚመጡ ኬሚካሎች በጣም በርካታ ናቸው፡፡ በጥንቃቄ አገር ውስጥ የማይገቡ ካልሆነ በቢዝነስ እይታ ብቻ የሚታይ ከሆነ ጥፋቱ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የምንም ጊዜም የትውልድ በሽታ ይሆናል፡፡ በዓለም ላይ እየሆነ ያለውም ይሄው ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
በኬሚካል ምክንያት ምን አይነት በሽታ በሰው ላይ እየተፈጠረ እንደሆነና አካባቢ እየበከለ እንደሆነ ይታወቃል ካሉ በኋላ፤ እንደ ተቋም መስሪያቤቱ የሚወስዳቸው ማስተካከያዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ይህንን ኃላፊነት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
ከመስሪያ ቤቱ ጋር ተአማኒና ግልጽ የሆነ አገልግሎት መጠበቅና ማግኘት አለባቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚያጋጥሙ የተለያዩ ጉዳዮች ካሉ በማንኛውም ሰዓት እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታት ዝግጅ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2013