በኃይሉ አበራ
ቱርክ እና እንግሊዝ በፈረንጆቹ ዘመን መለወጫ ከዓርብ ጥር አንድ ጀምሮ ተግባራዊ የማድረግ ታሪካዊ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነት መፈራረማቸውን ዘ-ጋርዲያን ዘግቧል።
የቱርክ የንግድ ሚኒስትሯ ሩህሳር ፔክካን በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ ለሚመሰረተው ነጻ የንግድ ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ባደረጉት ንግግር ለቱርክ እና ለእንግሊዝ ታሪካዊ ቀን መሆኑን ገልጸው፣ ስምምነቱ በቱርክ እና በእንግሊዝ መካከል ጠንካራ የንግድ ልውውጥ ከማድረጉም በተጨማሪ የሀገራቱን የንግድ መዋቅር ከጥርጣሬ ነጻ ያደርጋል ሲሉ ሩህሳን ፔክካን አስረድተዋል።
እንግሊዝ በአሁኑ ጊዜ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት የመጨረሻ ጥረት እያደረገች ሲሆን ፔክካን በበኩላቸው እ.ኤ.አ 1995 የተጀመረውን የቱርክና የአውሮፓ የጉምሩክ ህብረት በመጥቀስ፣ የህብረቱን የ25 ዓመታት ግቦች በማስቀጠል ትስስራችንን በበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል የመጀመሪያ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ በአዲሱ ስምምነት ቱርክ እና እንግሊዝ የንግድ ሰዎችን ፍላጎት በማሟላት የተፈራረሞትን ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ በቁርጠኝነት እንዲሰሩም ተናግረው፣ ከዚህ በፊት ቱርክ ወደ እንግሊዝ ከሚልኩት የቱርክ ምርቶች 75 ከመቶ ያህል ታሪፍ ለመክፈል እንደምትገደድ፣ ይህም ወደ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ እንደሚያዳርጋት ነገር ግን ስምምነቱ ይህንን ኪሳራ ያስወግዳል ብለዋል። በእቅዱ መሠረትም ሁሉንም የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶችን ያካተተ ከታሪፍ ነፃ ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
በዚህ መነሻነት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ መጠን 15 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደደረሰ በመግለጽ፣ ቱርክ ወደ እንግሊዝ ከላከቻቸው ምርቶች ሁለተኛው ትልቁ የወጪ ንግድ እ.ኤ.አ. በ2019 ሲታይ 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የነበረ ሲሆን፤ የገቢ መጠን ደግሞ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነበር።
በተመሳሳይ መልኩ በቱርክ የእንግሊዝ ኢንቨስትመንት ፍሰትም ወደ 11 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ሲሆን ስምምነቱ በሁለትዮሽ ኢንቨስትመንቶች በአዎንታዊ መልኩ ታይቷል። ቱርክ ስምምነቱን በኢንቨስትመንቶችና በአገልግሎቶች በመሳሰሉ ዘርፎች ለማስፋት ፍላጎት እንዳላትና ወደ እርሻ ገበያው ለመግባት በምን መልኩ ማሻሻል እንደሚገባ እንነጋገራለን ሲሉ ፔክካን አክለዋል።
የብሪታንያ የንግድ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ በበኩላቸው ስምምነቱ በቀጣዮቹ ቀናት የበለጠ ለታቀደው የእንግሊዝ እና የቱርክ የንግድ ግንኙነት መሠረት ይጥላል ብለው፣ ስምምነቱ እንግሊዝን ከተለዋጭ ኢኮኖሚዎች ጋር በዘመናዊ ስምምነቶች ትስስር ለማስቀመጥ የእቅዳቸው አካል በመሆኑ በገንዘብና በባዮቴክኖሎጂ ዘርፎች የበለጠ የንግድ አቅም አለ ብለዋል።
ሁለቱ አገራት በንግድ፣ በምርቶች፣ በቴክኖሎጂ፣ በአገልግሎት፣ በተሽከርካሪዎችና በሌሎች ዘርፎች እንዲሰሩ ተግባብተዋል። በተጨማሪም እንግሊዛውያን በቱርክ የሚመረቱ የጋርመንት ምርቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች መግዛት እንደሚችልና ተመጣጣኝ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ለተገልጋዮች ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ተገልጸዋል።
ትሩስ እንዳሉት እንግሊዝ በብሬዚት ወደ ኋላ በተቆ ጠረው ባለፉት ሁለት ዓመታት ለመሸፈን ከ62 አገራት እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር 885 ቢሊዮን ፓውንድ (አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር) ስምምነት ላይ ደርሳለች። የእንግሊዝ አገራቸው ነጻ የንግድ ቀጠና ፊርማውን ተከትሎ ባወጣችው መግለጫ እንደገለጸች በስምምነቱ ከ18 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ (24 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር) የሚያወጣ ንግድ ይሸፍናል።
ለ7 ሺህ 500 ሰዎች የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያላቸው እንደ ፎርና የመሳሰሉ የአውቶሞቲቭ አምራቾች የእንግሊዝና የቱርክ ትስስር በበለጠ ለማጠናከር ወሳኝ ናቸው።
የዓለም-አቀፍ ንግድ ጸሐፊ ሊዝ ትሩስ በስምምነቱ እለት በሰጡት ሀሳብ “የዛሬው ስምምነት ለንግድ ሥራ በጣም አስፈላጊ የሆነ ማረጋገጫ ይሰጣል፤ እንዲሁም በመላው እንግሊዝ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአውቶሞቲቭ እና በብረት ኢንዱስትሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሥራዎችን ይደግፋል” ብለዋል።
እንግሊዝ ከቱርክ ጋር ያደረገችው ስምምነት ከጃፓን፣ ካናዳ፣ ስዊዘርላንድ እና ኖርዌይ በኋላ አምስተኛው ትልቁ የነፃ ንግድ ስምምነት ነው። እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ነጠላ የንግድ ስምምነት እ.ኤ.አ ከጥር 1 ጀምሮ በይፋ ለመውጣት በተዘጋጀችበት በአሁኑ ወቅት ከ62 አገራት ጋር የንግድ ስምምነቶች ትፈርማለች።
አዲስ ዘመን ታሕሣሥ 22/2013