
አስናቀ ፀጋዬ
የአለማችን ግዙፍ የኢኮኖሚ ቁንጮዎች ቻይናና አሜሪካን ካለፉት ሀያና ሰላሳ አመታት ወዲህ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ እርስ በእርስ ሲፎካከሩ ቆተዋል።
ይህ ፉክክራቸው ጎልብቶ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ወደተፎካካሪ የንግድ ጦርነት ውስጥ እስከመግባት ደርሰዋል። በተለይ ደግሞ የዓለም የንግድ ሚዛን ወደየራሳቸው እንዲደፋ የተለያዩ የንግድ ማእቀቦችን እርስ በእርስ መጣጣላቸው በሁለቱ ሀገራት መካካል ያለው የንግድ እሰጥ አገባ ይበልጥ እንዲባባስ አድርጎታል።
አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ጋብ እያለ እዚህ የደረሰው የሁለቱ ሀገራት የንግድ ጦርነት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላም በዘመነ ጆይ ባይደን አዲስ መልክ ይዞ ብቅ ያለ ሲሆን በተለይ ቻይና በቅርቡ ቁጥጥር በሚደረግባቸውና ወደ ውጪ ሀገር በምትልካቸው ምርቶች ላይ ያወጣቸው አዲስና ጠንካራ ህግ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ውዝግብ ይበልጥ አክሮታል።
ከንግድ ጦርነቱ ባሻገር ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ የመጣው የሁለቱ ሀገራት የዓለም ምጣኔ ሃብታዊ ተቀናቃኝነት አንዴ በአሜሪካ ሌላ ግዜ ደግሞ በቻይና እየተመራ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ከሰሞኑ ደግሞ ዘጋርዲያን አሜሪካን ሀገር የሚገኘው የኢኮኖሚና የቢዝነስ ጥናት ማእከል የሪፖርት ትንበያን መነሻ በማድረግ ባወጣው መረጃ መሰረት በቀጣዮቹ ሰባት አመታት ቻይና ተቀናቃኟን አሜሪካ በመብለጥ የአለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት እንደምትሆን ጠቁሟል።
ሪፖርቱ ቻይና በተለይ በኮቪድ ወቅት ሊከሰት የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመቀነስና ተቀናቃኟን አሜሪካን በመብለጥ ቀጣዩ አስር አመት ከመገባደዱ በፊት የአለማችን ግዙፍ የምጣኔ ሃብት ባለቤት እንደምትሆን አመላክቷል።የቻይና ምጣኔ ሃብታዊ ዋጋ በዶላር ሲለካ በግማሽ አስር አመት ውስጥ እ.ኤ.አ በ2028 ከአሜሪካን ሊበልጥ እንደሚችልም ጠቅሷል።
ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ ያደረገው የአማካሪዎች ቡድን ደግሞ የ193 አገራትን የዕድገት ተስፋን በሚመለከት ባወጣው አመታዊ ሰንጠረዥ ውስጥ ቻይና ከኮቪድ -19 ተፅእኖዎች በፍጥነት በማገገም ኢኮኖሚዋ በሁለት ከመቶ ማደጉን ገልጿል።
አሜሪካ በዚህ ዓመት ኢኮኖሚዋን አምስት በመቶ ለማሳደግ ውል ያሰረች ቢሆንም ቻይና ከዋናው ተቀናቃኟ ጋር ያለውን ልዩነት ታጥባለች ሲል ሪፖርቱ ጠቁሟል።
በዚህ ዓመት በአጠቃላይ በአለም አቀፍ ደረጃ የተጠራ የሀገር ውስጥ ምርት በ4 ነጥብ 4 ከመቶ ዝቅ እንደሚልም ሪፖርቱ ተንብዮ፤ ይህም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአመቱ ትልቁ ውድቀት መሆኑን አመላክቷል።
‹‹በሪፖርቱ ትንበያ ትልቁ ዜና የቻይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ነው›› ሲሉም የአሜሪካው የኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ጥናት ማእከል ምክትል ሊቀመንበር ዳግላስ ማክዊያም የገለፁ ሲሆን በአሁኑ የአምስት ዓመት ዕቅድ ዘመን ማለትም እ.ኤ.አ ከ2020-25 ባለው ግዜ ውስጥ የቻይና ኢኮኖሚ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገባ እንደሚሆን እንጠብቃለን ሲሉም ተናግረዋል።
በዚሁ አምስት አመት ውስጥ ከአመት በፊት አሜሪካ አሳክታው የነበረውን የቻይናው ሙሉ በሙሉ እንደሚወስድም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የሌሎች እስያ ሀገራት ኢኮኖሚዎችም በእድገት ሰንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጡ መሆናቸውን ምክትል ሊቀመንበሩ ጠቅሰው፤ በተለይ ‹‹በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ምንም ላልሰሩ ምእራብያውያን ፖሊሲ አውጪዎች ይህ ትልቅ ትምህርት መሆኑንና እርስ በእርስ ከመተያየት ይልቅ በእስያ እየተረገ ላለው ሙሉ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል›› ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የቻይና የተጣራ የሀገር ውስጥ ምርት አለም አቀፍ ድርሻ እአአ በ2000 ከነበረው 3 ነጥብ 6 ከመቶ በ2019 ወደ 17 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ያሳየና እድገቱም ይቀጥላል ሲል ማእከሉ በተጨማሪ አስታውቆ፤ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋም ከ12 ሺ 536 ዶላር ወይም ከ9 ሺ 215 ፓውንድ እንደሚሻገርና እ.ኤ.አ በ2023 ቻይና ከፍተኛ ገቢ ያላት ሀገር እንደምትሆንም ጠቁሟል።
ምንም እንኳን ከአሜሪካና ከምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የኑሮ ሁኔታ በቻይና አሁንም ዝቅተኛ ቢሆንም በአሜሪካ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ63 ሺ ዶላር በላይ እንደሆነና በእንግሊዝ ደግሞ ከ39ሺ ዶላር በላይ መሆኑን ማእከሉ ለንፅፅር አስቀምጧል።
ማእከሉ አያይዞም የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት እ.ኤ.አ በ2020 የአለም አምስተኛዋ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆንና በቀጣዮቹ አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለባት ሀገር ከመሆን እንደማያግዳትም ገልጿል።
የእንግሊዝ የተለመደው የኢኮኖሚ እድገት በየዓመቱ እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 25 ድረስ 4 ከመቶ፣ ከ2026 እስከ 30 ድረስ 1 ነጥብ 8 ከመቶ እንዲሁም ከ2031 እስከ 35 ድረስ በተመሳሳይ 1 ነጥብ 8 ከመቶ እንደሚሆን እንጠብቃለን ሲልም ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ ያደረገው የአማካሪዎች ቡድን አብራርቷል።
በ2024 የእንግሊዝ የኢኮኖሚ እድገት በህንድ ሊነጠቅ እንደሚችልና ካልሆነ ግን እዛው ባለበት ደረጃ ሊቀጥል እንደሚችልም ይኸው አማካሪ ቡድን ትንበያ ሰጥቷል።
እ.ኤ.አ በ2025 የእንግሊዝ የተጣራ የሀገር ውስጥ ምርት በዶላር 40 ከመቶ በላይ እንደሚሆንና ይህም ከምንግዜም የኢኮኖሚ ተቀናቃኟና ጎረቤቷ ፈረንሳይ የሚበልጥ መሆኑንም አማካሪ ቡድኑ ተናግሯል።
ባለፈው ዓመት ህንድ በኢኮኖሚ ግስጋሴ የፈረንሳይንና እንግሊዝን ቦታ ነጥቃ የነበረ ቢሆንም የህንድ መገበያያ ገንዘብ ሩፒ የመግዛት አቅም መዳከምን ተከትሎ ከእንግሊዝ ኋላ ለመሆን ተገዳለች።
ይሁንና ይህ ለትንሽ ጊዜ እንደሚቆይና በህዝብ ብዛት የአለማችን ሁለተኛዋ ሀገር የሆነቸው ህንድ እ.ኤ.አ በ2035 ሶስተኛዋ ግዙፍ የአለም ምጣኔ ሃብት ባለቤት እንደምትሆን አማካሪ ቡድኑ ጠቁሟል።
የአለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ በቀጣዮቹ አስራ አምስት አመታት የአካባቢ ጉዳዮች በአለም የኢኮኖሚ ቅርፅ ላይ ከባድ ተፅእኖ እንደሚኖራቸውም የአሜሪካን ኢኮኖሚክስና ቢዝነስ ጥናት ማእከል አስረድቷል።
በተመሳሳይ የባህር ጠለል እ.ኤ.አ በ2035 በ45 ሴንቲ ሜትር ከፍ እንደሚል የሚጠበቅ መሆኑና ይህም ከሁለት አመት በፊት እአአ በ 2030 በ20 ሴንቲሜትር ከፍ እንደሚል ከተተነበየው ጋር የተነፃፀረ መሆኑን ማእከሉ ጠቁሟል።
በሚቀጥሉት አስርት አመታት ውስጥ አብዛኞቹ ሀገራት ከካርበን ልቀት ነፃ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር እቅድ እያወጡ ባሉበት በዚህ ወቅት የድንጋይ ከሰል ፍላጎት እየተዳከመ እንደሚሄድና የነዳጅ ዋጋም እንደሚቀንስ ማእከሉ በሪፖርቱ አያይዞ ገልጿል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21/2013