
በጋዜጣው ሪፖርተር
በናይጄሪያ ሰሜን ምሥራቅ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በገና በዓል ዋዜማ ላይ በአብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታዮች የሚኖሩበትን መንደር በመክበብ፣ ቤተ ክርስቲያን በማቃጥል በፈፀሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ። ኤኤፍፒ የዜና ወኪል በጥቃቱ ቢያንስ 11 ሰዎች መገደላቸውን ከአካባቢው የተገኙ ምንጮቹን ጠቅሶ መዘገቡን ያስነበበው ቢቢሲ ነው፡፡
እንደ ዘገባው፤ የአካባቢው መሪ ለዜና ወኪሉ እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ በቦርኖ ግዛት ወደ ምትገኘው ፔሚ በሞተር ሳይክልና በመኪና በመግባት ማንንም ሳይመርጡ ነው መተኮስ የጀመሩት። ፔሚ የምትገኘው ከስድስት ዓመታት በፊት 200 ሴት ተማሪዎች ተጠልፈው ከተወሰዱበት ቺኮብ አቅራቢያ ነው።
ሐሙስ ዕለት የደህንነት ባለሥልጣናት በክርስቲያኖች በዓል ላይ ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ብለው አስጠንቅቀው የነበረ ቢሆንም ታጣቂዎቹ ፔሚን ድንገት ነበር የወረሯት። ነዋሪዎች ወደ ጫካ የሸሹ ሲሆን የተወሰኑትም የደረሱበት እንዳልታወቀ ተገልጿል።
የአካበቢው ሚሊሻ መሪ አብዋኩ ካቡ በበኩላቸው ታጣቂዎቹ ሰባት ሰዎችን መግደላቸውን፣ 10 መኖሪያ ቤቶችን እንዳቃጠሉና በበዓሉ ለነዋሪዎች ሊከፋፋል የነበረ የምግብ ክምችት እንደዘረፉ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ታጣቂዎቹ «ቤተ ክርስቲያን አቃጥለዋል፤ አንድ ቄስ ጠልፈው ወስደዋል፤ ሆስፒታል ከማቃጠላቸው በፊትም የሕክምና ግብዓቶችን ዘርፈዋል» ብለዋል የሚሊሻ መሪው።
ቦኮ ሃራም የአገሪቷን መንግሥት ለማስወገድና እስላማዊ መንግሥት ለመመስረት በሚፋለምበት ሰሜን ናይጄሪያ በርካታ ጥቃቶችን ፈፅሟል። እስላማዊ ቡድኑ ሙስሊሞች ከእስላማዊ ወግ ባፈነገጠ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፉ የሚከለክል የእስልምና አቋምን ያራምዳሉ። መጠሪያ ስማቸውም «የምዕራቡ ዓለም ትምህርት የተከለከለ ነው» የሚል ትርጓሜ አለው።
ታጣቂ ቡድኑ የፈፀመው እጅግ ዘግናኝ ጥቃት ከስድስት ዓመታት በፊት በቺቦክ ሴት ተማሪዎች ላይ ያነጣጠረው ነበር። በርካቶችንም ለዓመታት አግቶ አቆይቷል። እንደተባበሩት መንግሥታት ከሆነ ለአስርት ዓመታት በዘለቀው የቦኮ ሃራም ግጭት ቢያንስ 36 ሺህ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 2 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ታኅሣሥ ወር ላይ ቡድኑ በካሲና ግዛት ከሚገኝ የወንዶች ትምህርት ቤት ከ300 በላይ ተማሪዎች በመጥለፍ ተጠያቂ ሆኗል። የአገሪቷ ባለሥልጣናት ግን ጠለፋውን የፈፀሙት ከእስላማዊ ቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው የአካባቢው ወንበዴዎች ናቸው ብሏል። የቦኮ ሃራም ተዋጊዎች ባለፈው ወር በርካታ የእርሻ ሠራተኞችን መግደላቸውንም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2013