የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀደምት ዘገባዎች በእጅጉ ተነባቢ ዛሬም ላገኛቸው በእጅጉ ተነባቢ ናቸው።እኛም ከእነዚህ ዘገባዎች ጋዜጣው በ1950ቹ ያስነበባቸውን ወጣ ያሉ ዘገባዎች ለዛሬ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
በዛሬው የአዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1950ዎቹ ይዟቸው ከወጣ ዘገባዎች በአዘጋገባቸውና በይዘታቸው ተነባቢ ናቸው ያልናቸውን እና ሌሎች አስደናቂ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል።
ማገጃ ምልክት ይሰጠው
ማንኛውም የሥራ ድርጅት በብዙ ድካም ከተቋቋመ በኋላ አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገለት የተሠራው እንዳልተሠራ የነበረው እንዳልነበር መሆኑ የማይጠረጠር ነው።በሲዳሞ ጠ/ግዛት ዋና ከተማ ይርጋዓለም የቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ ያቋቋመው ከፍተኛ መሥሪያ ቤት ይገኛል። የተቋቋመውም በትልቁ መኪና መንገድ አጠገብ ስለሆነ ፤ተሽከርካሪዎች የሚመላለሱበት ቦታ ነው።
አንዳንድ ጊዜም ከባድ ጭነት የያዙ መኪናዎች ለምሳሌ አውቶቡስን የመሳሰሉት በሁለተኛው መንገድ እንዲያልፉ የሚታዘዙበት ቀን ስለሚያጋጥም በተጠቀሰው መሥሪያ ቤት አደባባይ የሚገኙትን ሽቦዎች ሳይመለከቱ ለማለፍ ሲሞክሩ በብዙ መጯጯህ ስልኩ ሽቦ ከመጣስ የዳነበትና መኪናውንም ለመመለስ የቻለበትን ጊዜ ለማታወስ የማይችል የለም፤ ታናናሽ መኪናዎችን ለማሳለፍ የቦታው ስፋት ይፈቅዳል።ስለ ታላላቅ መኪናዎች ግን የክፍሉ ባለሥልጣን የማገጃ ምልክት ቢያደርግበት የሚሻል መሆኑን አስታውሳለሁ።
አቧራ አዋዜ አይደለም።
በዚሁ ከተማ ትልቁን መንገድ በመከተል አልፎ አልፎ በሚገኙት ሰፈሮች ብዙዎች የልኳንዳ ሥጋ የተሰቀለባቸውና
ፉርኖ ይህንንም የመሳሰሉት ምግቦች የተደረደረባቸው ቤቶች ይገኛሉ። ሥጋው የሚገኝበት ብዙ ቦታ በረንዳ ስለሆነ ማናቸውም ተንቀሳቃሽና ይልቁንም በማይቋረጠው የመኪና ኃይል ከመንገዱ ላይ የሚነሳው አቧራ በሥጋውና በማናቸውም ምግብ ላይ ሲሰፍርበት ይታያል።
ለማስረጃ ያህል በመንገዱ ዳር የሚገኘውን የቡና የሌላውንም ቅጠል የተመለከትን እንደሆነ በአንዱ ቅጠል ላይ ብቻ አንድ ጥርኝ የሚሞላ አቧራ ስለምናገኝ በየቀኑ በያንዳንዱ ብልት ሥጋ ላይ ተደባልቆ ወደ ሆድ የገባውን አቧራ ለመገመት እንችላለን።
ስለዚህ ሥጋና ፉርኖ ይህንንም የመሳሰለ ምግብ የሚያሰናዱ ነጋዴዎች ለዚሁ አገልግሎት በዘመናዊ ዕቅድ በተሰናዳው መስታወት ውስጥ ማኖር ይገባቸዋል።ይህም ባይቻል አቧራ ወደሌለበት ሁለተኛው መንገድ እንዲዛወሩ ማድረግ ስለሚገባ ፤ሥራው የሚመለከተው ባለሥልጣን ያስብበት ዘንድ ሳስታውስ በትሕትና ነው።
መመሳሰል ይገባዋል
በዚሁ ከተማ የሚገኘው የጠቅላይ ግዛቱ በጅሮንድ ጽ/ቤት በሦስት ቦታ ተከፋፍሎ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ ቤቱም በጠላት ጊዜ የተሠራ አሁን መፍረስ የጀመረ ነው።ስለ የውስጥ ዕቃውም አጠባበቅ ከቤቱ ይልቅ ዘበኞቹንና ካዝናውን ማመን ግድ ሳይሆን አይቀርም።
ይኸውም ሆኖ ለሥራው የተመጠነ ስፋት ያለው አይደለም። በአካባቢው የሚገኙት ቢሮዎች በአማረና በጥሩ ሕንፃ የተሠሩ ሲሆኑ፤ የተጠቀሰው መሥሪያ ቤት እርጅና የእነሱን ውበት ግርማ አሳንሶታል።ስለዚህ ጓደኞቹን እንዲመስል የክፍሉ ባለሥልጣን ይተጋበት ዘንድ ማሳሰብ የጋዜጣው ፋንታ ነው።
የሲዳሞ ጠ/ግዛት አዣንስ
ኃይለ መስቀል ወልደየስ (የካቲት 20 ቀን 1951 የወጣው አዲስ ዘመን)
ሁለት ወንዶች ልጆች
እናት በአስር ቀን ልዩነት ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደች። በወቅቱ ዜናው ጋዜጣችን ላይ ሲወጣ ርዕሰ ዜናው ከላይ እንደተጠቀሰው ሁለት ወንዶች ልጆች ብቻ ነበር የሚለው በሚከተለው መልኩ ተዘግቦ ስለነበር እንድታነቡት እንጋብዛለን።
በደብረ ታቦር ከተማ ዙሪያ ቃናት ማርያም ከተባለው አገር የአቶ መኰንን ካሳ ባለቤት ያልጋነሽ አድማሱ የተባለችው ፤ጥር 22 ቀን 51ዓ.ም ከሌሌቱ 8 ሰዐት ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ ከወለደች በኋላ 10 ቀን ቆይታ የካቲት 2 ቀን 1951 ዓ.ም ከጥዋቱ 1 ሰዐት ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ ደግማ መውለዷንና ሁለቱም ልጆች እስካሁን በሕይወታቸው መኖራቸውን የነዚሁ ልጆች አባት አቶ መኰንን ካሳ አስታውቀውናል።
የደብረ ታቦር ከተማው ዙሪያ ምክትል ገዥ ባላምባራስ ኃይሌ ታምራት በቁጥር100/1951የካቲት 10 ቀን በተጻፈ ደብዳቤ አረጋግጠውልናል።እኒህ የምክትል ወረዳ ገዥ እንደዚህ ያለው ሁኔታ በጋዜጣ እንዲገለጥ በቶሎ ለአውራጃው ግዛት አዣንስ ጽ/ቤት በማስተላለፋቸው እናመሰግናለን።
ሌላዎችም ምክትል ገዥዎች የርሳቸውን አርአያ ተከትለው ይህን የመሰለ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው በፍጥነት የሚያስታውቁን ቢሆን ከፍ ያለ ምስጋና የሚያገኙበት መሆኑን እንገልጻለን።
የደብረ ታቦር አውራጃ አዣንስ
አሰፋ ረታ (የካቲት 17 ቀን 1951 የወጣው
አዲስ ዘመን)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2013