ዳንኤል ዘነበ
በጋዜጠኝነት ሙያ በተለያዩ የራዲዮ ጣቢያዎች ውስጥ ለበርካታ አመታት አገልግሏል። በሙያው ብዙ ውጣ ውረዶችን ቢያጋጥሙትም፤ ጠመዝማዛውን የህይወት መንገድን አልፎ ለስኬት በቅቷል። የጋዜጠኝነት ሙያን አክብሮ መስራቱ፤ ወርቃማው ድምጹ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ አድርጎታል።
በተጨማሪም ሀገራችን በአካል ጉዳተኝነት ላይ ያለውን የተሳሳተ እሳቤ ወደ ትክክለኛው መስመር ለማምጣት በሙያው እያደረገ ባለው ትግል ብዙዎች አድናቆታቸውን ይለግሱታል፤ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረማርያም።
የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አብይ ጉዳይ አድርጎ ለአመታት እየሰራ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተስፋዬ፤ አካል ጉዳተኛ መሆኑ ህልሙን ማሳካት እንዳይችል እንዳላገደው ይናገራል። በባሌ ጎባ ከተማ ተወልዶ ያደገው ጋዜጠኛ ተስፋዬ የመጀመሪያና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል።
«አካል ጉዳተኝነቴ ውበቴ ነው» የሚል አባባል የሚያዘወትረው ጋዜጠኛ ተስፋዬ፤ ከልጅነቱ ያልመው የነበረው ጋዜጠኛ የመሆን ህልሙን ለማሳካት ወደ ኮሌጅ በመግባት፤ጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን አጥንቶ ለመመረቅ በቅቷል።
በሙያው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ከመቻሉ ትይዩ፤ አሚንስ መልቲ ሚዲያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በመመስረት በድርጅቱ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚያጠነጥን የሬዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ የተለያዩ ዶክመንተሪዎችንና ፊልሞችን በመስራት ትዳር መስርቶ ልጅ ወልዶ ህይወቱን በተሳካ ሁኔታ እየመራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በአሀዱ 94.3 ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ የራሱን አየር ሰዓት ገዝቶ ‹አዲስ መንገድ› የተሰኘ ፕሮግራም እያዘጋጀ መሆኑን ተገንዝበናል።
ጋዜጠኛ ተስፋዬ ሲወለድ ጉዳት አልባ የነበረ ሲሆን በስድስት አመቱ የገጠመው የጤና እክል ተከትሎ ሁለት እግሮቹን ማጣቱን ያስታውሳል። መንፈሰ ጠንካራው ተስፋዬ፤ በሁለት ክራንች መጓዙና አካል ጉዳተኝነቱ የልጅነት ህልሙን እንዳያሳካ ባያግደውም፤ አካል ጉዳተኛ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ ተፅእኖዎች እንደነበሩበት ይገልፃል።
ማህበረሰባችን አካል ጉዳተኞች ተምረው፣ ሰርተው፣ሀብት አካብተው፣ ቤተሰብ መስርተው ለመኖር የታደሉ አይመስላቸውም።
በተለይ ወላጆች አካል ጉዳተኝነቱን እንደ መቅሰፍት በመቁጠር፤ ልጆቹን ከቤት እንዳይወጡና ተምረው ከፍተኛ ደረጃ እንዳይደርሱ በተሳሳተ እሳቤ ሲጎዷቸው ማየቱን በትዝብት ይናገራል። ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች የራሱን የህይወት ተሞክሮ በምሳሌነት በማንሳት እንዲህ ይላል፤ «ቤተሰቦቼ ይህ ጉዳይ ‹የሰይጣን ሥራ ነው› የሚል የተሳሳተ አመለካከት የነበራቸው ሲሆን አንዴ በመርዝ በሌላ ጊዜ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በራፍ ላይ በመጣል ሕይወቴን ሊያጠፉኝ እስከ መሞከር ደርሰው ነበር።
ግን ሳይሳካ ቀረ» ይላል። የጋዜጠኛ ተስፋዬ ቤተሰቦች በተሳሳተ አመለካከት አካል ጉዳተኝነቱን ተከትሎ ጫናዎቹን እንዳላቋረጡ ይናገራል።
በተደጋጋሚ ተስፋ የሚያስቆርጡ ንግግሮች፣ ከንፈር መምጠጥና የመሳሰሉት ኋላቀር አስተሳሰቦች ‹ተስፋዬ እንደ ስሙ ተስፈኛ ከመሆን ይልቅ፤ ተስፋ ቢስነቱን ጮክ ብሎ እንዲሰማው› እና ህልሙን እንዳያሳካ ወደኋላ ሊጎትቱት የሚችሉ ተፅዕኖዎች ነበሩ። ጋዜጠኛ ተስፋዬ መፅሀፍትን በማንበብና ተፈጥሮ ባደለችው የመንፈስ ጥንካሬ ተምሮ ራሱን ለፍሬ ማብቃት መቻሉን ነው ያብራራው።
ማህበረሰቡ አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ ከማወቅ ይሁን ካለማወቅ የሚያደርሱትን ጫናዎች እኔ በመቋቋም ለዛሬ መድረስ ብችልም፤ ብዙ ሺህ አካል ጉዳተኞች ግን ቤት ተቆልፎባቸው የእውቀተ ብርሀን ሳያዩ እያለፉ መሆኑን ይገልፃል።
በሀገራችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች የመማር መብታቸውን አጥተው፤ የእውቀት ብርሃን እንደራባቸው ተስፋ በመቁረጥ መንፈስ ውስጥ እንደሚገኙ በቅርበት የሚያውቅ መሆኑን ይናገራል።
የጋዜጠኝነት ሙያን እንደ መሳሪያ በመጠቀም እርሱና ጓደኞቹ ባለፉት አመታት በአካል ጉዳተኝነት ላይ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ተሰብሮ፤ ወላጆች አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራዎች መስራታቸውንና በቂ ባይባልም የተወሰኑ ለውጦች መታየታቸውን ይገልጻል።
«በአዲስ አበባና በተወሰኑ ከተሞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወላጆች አካል ጉዳተኛ ልጆችን የመላክ ልምድ እያዳበሩ የሚገኝ ቢሆንም፤ ስለ ብዙሀኑ ስናስብ በገጠራማ የሀገራችን ክፍል ዛሬም ኃላቀሩ አስተሳሰብ ሳይለወጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኛ ህጻናት የትምህርት እድል ማግኘት አልቻሉም» ብሏል።
ጋዜጠኛ ተስፋዬ በማህበረሰቡ ዘንድ አካል ጉዳተኛ ህጻናት የትምህርት እድል በአግባቡ የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅ ማድረግ ላይ ትልቅ የቤት ስራ መኖሩን በመጠቆም ሃሳቡን ይቋጫል።
«በሀገራችን ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተያይዞ የሚታዩት መሰናክሎች ደረጃቸው ይለያይ እንጂ የሚሊዮን አካል ጉዳተኞች የጋራ ችግሮች ናቸው» የሚሉት በዊልቸር የሚንቀሳቀሱት ወይዘሮ ሙሉእመቤት ጌታነህ ናቸው።
በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች ትምህርት ካለማግኘት አንስቶ እስከ ሥራው ዓለም ድረስ ያሉ ተደራራቢ ውጣ ውረዶች መሆናቸውን ይናገራሉ። በሀገራችን ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተያይዞ የሚደርሱ መገለልን ጨምሮ ሌሎች ከአመለካከት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮች በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ ጎልቶ የሚታይ መሆኑን ጨምረው ይገልፃሉ።
በሀገራችን አካል ጉዳተኞች ትምህርት የመማር ሰብዓዊ መብታቸው በጭራሽ እየተከበረ አለመሆኑን ያመላከቱት በዊልቸር የሚንቀሳቀሱት ወይዘሮ ሙሉእመቤት፤«ስለ አካል ጉዳተኝነት በማህበረሰቡ በኩል ባለው የተሳሳተ አመለካከት ብዙ ሺህ አካል ጉዳተኞች ቤት ተቆልፎባቸው ይገኛሉ።
ወላጆች አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አይፈልጉም። በኢትዮጵያ እንዲህ በመሰለ ኋላቀር እሳቤ ሰለባ የሆኑ ብዙ ሺህ አካል ጉዳተኞች «ካሉት በታች ከሞቱት በላይ» የጨለማ ህይወት ውስጥ እየገፉ ነው የሚገኙት» ሲሉ ነበር አካል ጉዳተኞች ከትምህርት አለም ምን ያህል እንደራቁ ያብራሩት።
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው ዐመዲን እንደገለጹት፤ በሀገራችን የአካል ጉዳተኛና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎችን በሁሉም የትምህርት ዘርፎች እነዚህን ህጻናትና ወጣቶች አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራው ስራ አመርቂ ነው የሚባል አይደለም። ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ ቁጥር መካከል 17.5 በመቶ የሚሆኑት ወይም 15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትና ወጣቶች የትምህርት እድል ያላገኙ መሆናቸውን ያነሳሉ።
በትምህርት ተደራሽነቱ ላይ ሰፊ ክፍተትና ጥልቅ ችግሮች መኖራቸውን ያመላከቱት አቶ አሳልፈው፤ የፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው የአስር አመት ስትራቴጂክ ፕላን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ታሳቢ ተደርጓል። በስትራቴጂክ እቅዱ ላይ የአካል ጉዳተኛና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎችን በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል የሚል ተስፋን የሚያሳድር መሆኑን ያብራራሉ።
«ነገር ግን መታሰብ የሚገባው ስትራቴጂም ቢወጣ፣ ፍኖተ ካርታም ብናዘጋጅ በጉዳዩ ላይ ከልብ ካልተሰራ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም» ሲሉ ወረቀት ላይ ያሉ እቅዶችን ወደ መሬት ማውረድ እንደሚገባ ያመላክታሉ።
አቶ አሳልፈው በመጨረሻም ስለዚህ የአካል ጉዳተኞች የትምህርት ተሳትፎ እየጎለበተ እንዲሄድ ትምህርት ቤቶቻችንን ምቹ ማድረግ ይኖርብናል።
ጉዳት አልባ ለሆኑት እንደሚታሰበው ሁሉ ለአካል ጉዳተኞችም ዜጎች ስለሆኑ ትምህርት ቤቶቻችንን ለእነሱም ምቹ እንዲሆኑ ማድረግና በልዩ ፍላጎት ትምህርት የሰለጠኑ መምህራንን በስፋት ማፍራት እንዲሁም፤ የተለየ ድጋፍ ለሚሹ አካል ጉዳተኞች እንደ መንግስት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች እንዲሟሉላቸው ማድረግ የሚገባ መሆኑን ነው ያሳሰቡት።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2013