ዋቅሹም ፍቃዱ
ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በሊቢያ ህዝብ መካከል ከፍተኛ መከፋፈል በመከሰቱ አገሪቱ እስከ ዛሬ ድረስ የማያባራ የእርስበርስ ጦርነት ለማስተናገድ ተገዳለች። አገሪቱ በመጪው ዓመት 69ኛውን የነጻነቷ ቀን ስታከብር የአገሪቱን ሰላምና አንድነት የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ምርጫ እንደምታካሄድ ሊቢያውያን ተስፋ አድርገዋል ሲል የቻይና ዜና አውታር ዥንዋ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ሊቢያ እ.ኤ.አ ታህሳስ 24 ቀን 2021 ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችበት 69ኛው ዓመት ስታከብር በአገሪቱ የሰፈነው መከፋፈልና አለመረጋጋት ለማስወገድ ይረዳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ምርጫ ለማካሄድ አቅዳለች። ዋሊድ ካረህ የተባለው የ68 ዓመት ጎልማሳ ለሶስት ወንድ ልጆቹና ከልጆቻቸው ጋር በአገሪቱ ርዕሰ መዲና ውስጥ በመገኘት የማርትሪስ አደባባይ በሚጎበኝበት ወቅት 69ኛው የአገሪቱን ነጻነት እያከበረ በምርጫው ላይ እንደሚሳተፍ በደስታ ተናግሯል።
አክለውም የነጻነት ቀኑ ለሁሉም ሊቢያውን የብሄራዊ ኩራትና የጀግንነት ተምሳሌት በመሆኑ በአደባባዩ ተገኝተው አባቶቻቸው ለነጻነቱ ያደረጉት ተጋድሎና የከፈሉት መስዋዕት መስማትና በዓሉን መታደም ምንኛ መታደል እንደሆነም ተናግሯል።
ዋሊድ ልጆቹ የትናንቱን ሊቢያ ጠንቅቀው እንዲያውቁ፣ በዚሁ ልክ ደግሞ ለአገሪቱ ሰላምና አንድነት እንዲሰሩ ጽኑ እምነት እንዳለው ዘገባው ያትታል። ዋሊድ ልጆቹም በተጨማሪ የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን ለመምጣት እንዲሁም ጠባብ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ህዝቡን የመከፋፈል አጀንዳቸውን ወደ ጎን በመተው ለሊቢያውያን አንድነትና ሰላም ዘብ እንዲቆሙ፣እንደ ትናንቱ የአገሪቱ አርበኞች ለዛሬይቱ ሊቢያ ታላቅነት ያለምንም አድሎ እንዲሰሩም ጥሪ ማቅረቡን ዘገባው ያወሳል። የሊቢያ ሰንደቅ ኣላማም በአባቶቻቸው ደም የተወጠነ በመሆኑ ሊቢያውያን የማንነታቸውና የነጻነታቸው መገለጫ አድርገው እንዲያዩ እና እንዲሰሩለት ዋሊድ አበክሮ ይጠይቃል።
እንደ ዘገባው ሊቢያ ከነጻነቷ 1951 እስከ 1969 በንጉስ ኢዲሪስ አስ ሰኑሲ ትተዳደር ነበር። ኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ በ1969 ጀምሮ አገሪቱን ሲያስተዳድሩ ከቆዩ በኋላ በ2011 በወታደሮቻቸውና በምዕራባውያን በሚደገፉ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰው የእርስበርስ ጦርነት ጋዳፊ ከሰልጣን ተወግደው የስልጣን ዘመናቸው በሞታቸው ተደመደመ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ አገሪቱ በፖለቲካ ክፍፍል፣የኑሮ ውድነትና ከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ ለመውደቅ ተገዳለች።
የአገሪቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ታዓር ዳርዱር እንዳሉት መጪው ምርጫ ለአገሪቱ መረጋጋትና አንድነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በምርጫ ቅስቀሳ የሚንጸባረቁ ሀሳቦች የፓርቲዎች የግል ጥቅም ሳይሆን አገሪቱን አንድ የሚያደርጉ እንዲሆኑ የሁሉም ሊቢያውያን ምኞት ነው። ለስኬቱ ደግሞ በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ሊቢያውያን ተሳትፎ ያስፈልጋል።
በቅርብ የተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ህዝቡ ማንን መምረጥ እንዳለበት አቅጣጫ ጠቋሚ ክርክር እንደነበረ ታዓር መናገራቸው ዘገባው ጠቁሟል። የአገሪቱ ጸጥታ አደጋ ላይ እያለና ኑሮ ውድነቱም ተባብሶ ባለበት በአሁኑ ወቅት በህዝቡ መከራ ጠባብ የግል ፍላጎታቸወን ለመጫን የሚታትሩ ፓርቲዎች በክርክሩ እንደ ተለዩ ታዓር መናገራቸው ዘገባው አልሸሸገም።
በተመሳሳይ መልኩ የአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችም የሊቢያ ፖለቲከኞች ልዩነታቸውን በማጥበብ መጪውን ምርጫ ፍትሐዊና ሰላማዊ በማድረግ አገሪቱን አሁን ካለችበት ቀውስ እንዲያወጡ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ዥንዋ ዘግቧል።
ተማሪዎቹ ከዚህ በኋላ መከፋፈልን የሚያመጣ፣ ለህዝብ ያልወገነ፣ የህዝብ አመኔታ የሌለው መሪ በሊቢያ ምድር ማየት አይፈልጉም። ይልቁንስ የህዝቡን እንባ የሚያብስ ፣አንድ የሚያደርግ፣ ልማታዊ አስተሳሰብ ያለውና ለአገሪቱ ሰላምና ብልጽግና የሚሰራ መሪ እንዲመረጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማድረገም ዝግጁ መሆናቸው ዘግባው ያስረዳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013