ዳግም ከበደ
ጀግና ከፊት እንጂ ከኋላ ጠላት አያጠቃም ይላል ያገሬ ሰው። ጊዜ የማያሳየን ጉድ የለምና እዚሁ እደጃፋችን ላይ ግን ጀግንነት ብርቅ ያልሆነባት ኢትዮጵያ ከጀርባ እንደ ፈሪ አድብቶ የሚያጠቃ የእናት ጡት ነካሽ መጣባት። ጥንትም የፈሪ ምሱ ሽንፈት ነውና ያደረሰው ጉዳት እጅጉን መሪር ቢሆንም ፣አገር የማትረፍ ወኔን ሰንቀው ለተዋደቁ ጀግኖች ሆነ።
አስገራሚው ደግሞ የተራዘመ ጦርነት አድርጌ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የመከራ ማቅ አለብሳለሁ በማለት ጁንታው የደገሰው እኩይ ተግባር እንደጉም ተኖ በአስደናቂ ጀብዱ በሶስት ሳምንት ውስጥ ተገባደደ።
ለመሆኑ ወር እንኳን ያልፈጀው ድል እንዴት ተጀምሮ በምን መልኩ ተጠናቅቆ ይሆን? ህግን የማስከበር፤ ፍትህን የማስፈን ትልም ያነገበው ኦፕሬሽን ምን መልክ ነበረው?
በዛሬው የእንወራወር አምድ በጥቂቱ ወደኋላ ወስጃችሁ መላው ኢትዮጵያዊ ልባቸው ያበጠባቸው ዘራፊዎችና ወንበዴዎችን እንዴት ማስተንፈስ እንደቻለ ላስታውሳችሁ ወደድኩ።
በዚህ መንገድ ፅሁፌን ለማሰናዳት መነሻ ምክንያት የሆነኝ ደግሞ ይህ ድል በትብብርና በአንድነት ለሚሰሩ የልማት እና የብልፅግና ጉዞ ዳግም የስኬት መንተራሻ እንደሚሆን በማመን ነው።
የጥቃቱ ማግስት
ውጊያ የራሱ ስልት፣ ስነምግባር እንዳለው የጦር ጄኔራሎች ይናገራሉ። በትህነግ ላይ በመንግስት የተወሰደው እርምጃም በዚህ መንገድ ነበር የተከናወነው።በጁንታው በኩል ለጥበቃ የተሰማራ ኃይል፣ በታጠቀና ለውጊያ አስቀድሞ በሴራ በተዘጋጀ ኃይል ከበባ በማድረግ እንዲሁም በመከላከያ ውስጥ ከሀዲዎችን በማዘጋጀት እርምጃ መውሰድን ነበር ምርጫው ያደረገው። ክስተቱ በጣም አሳፋሪ ነበር።
ይህ ድርጊት ቁጭት ውስጥ የከተተው የመከላከያ ሰራዊት በመጨረሻም የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሂደቱን በድል እና በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፀጥታ አካላትና ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል የሚለውን በመለየት ባፋጣኝ ነበር የመመከት ብሎም የማንበርከክ ስራ የተሰራው።
የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስና በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላትን እንዲሁም ሕዝባዊ አደረጃጀት ያላቸው የሚሊሺያ አደረጃጀቶች፣ በአንድ ላይ ተደራጅተው አካባቢያቸውን በአግባቡ ለመጠበቅ በተዋረድ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ሆኑ። በከተማ፣ በገጠር፣ በመንደርና በትንንሽ አካባቢዎች ይህ አረመኔ ቡድን አድብቶ ሊወስድ የሚችለውን ጥቃት እንዴት መመከት እንደሚቻል ከማስረዳት ጀምሮ የጁንታውን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍ የሁሉንም አካላት ሥነ ልቦና ለአንድ አላማ በጥንካሬ ተገነባ።
በእኩይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ኃይሎችን በቂ ጥናት በማድረግ መንቀል ያስፈልጋል የሚለው ጉዳይ በሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት መግባባት ላይ ተደርሶበታል።የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ተግባር የሚከናወነው ሁለት ቦታ መሆኑንም መገንዘብ ተችሏል። ይህም ትግራይ ላይና ከትግራይ ውጪም ባሉ የተለያዩ ከተሞችና ስምሪት በተሰጠባቸው ቦታዎች ላይ ነው፡፡
በዚህም የሕዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሳይውል ሳያድር መንግስት ማወቁና በአፋጣኝም እርምጃ መውሰዱ ድሉን ያፋጠነው አንዱ ትልቅ ሥራ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ሁለቱን ተልዕኮዎች በደንብ ከመረዳት ባሻገር ሁሉም ዜጎች በአንድ መንፈስ ተረድተውት ድጋፍ ቸረውታል።
የሠራዊቱ የመፈፀም አንድነት
«በሠራዊት ውስጥ ምንጊዜም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን እያረጋገጡ መሄድ ያስፈልጋል። ሰራዊቱ በተበታተነ አመለካከት ምንም ስራ መስራት አይችልም» በሚል መንግስት በለውጡ ማግስት ቁርጠኛ አቋም በመውሰድ የተለያዩ ማሻሻያዎችን/የሪፎርም ስራዎች/ ማድረጉ ይታወቃል። ይህ መልካም ስራ ቀድሞ መሰራት መጀመሩ ጁንታው ጥቃት በፈፀመበት ማግስት ሠራዊቱ በአንድ ረድፍ ቆሞ ለመከላከልና በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል ለመንሳት ያስቻለው ፅናት እጅግ በጣም የሚደነቅና ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ነው።
ጁንታው የክፋት አላማውን ለማስፈፀም በጎንደር፣ በአፋር፣በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ በጋምቤላና በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በመሃል አገር ጨምሮ የተለያዩ ሙከራዎች አድርጋል። ይሄን ሰራዊቱ ከሌሎች የፀጥታ መዋቅሮችና ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን እያንዳንዱን የጥፋት ሴራ ማምከን ችሏል። ይህም ለወደፊቱ ተጠናክሮ የሚቀጥልና ኢትዮጵያዊነትን በፅኑ መሰረት ላይ እንድትቀጥል የሚያስችል እርሾ ነው።
ተቋማትና የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ሂደት
የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ዘመቻ በመንግስት በአጭር ጊዜ በድል የተደመደመው የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማትን በጠበቀ እና ብዙም ኪሳራ ባላስከተለ መልኩ ነው። ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ትልልቅ የኢንዱስትሪ መንደሮች፣ቅርሶችና ታሪካዊ ቦታዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥበብ የተሞላበት ጥንቃቄ ሲደረግ አስተውለናል።
ኢንቨስተሮች ሕዝቡንና የፀጥታ ኃይሉን አምነው በየቦታው የጀመሯቸው ትልልቅ ስራዎች አንዳችም ጉዳት አልደረሰባቸውም። መንግስት በነዚህ የአገር ሃብቶች ላይ ጥቃት ማድረግ በአገር ላይ ከተቃጣው ጦርነት እኩል የሚታይ መሆኑን በማመን ድልን ከማፋጠን በላይ ጥንቃቄ አድርጎላቸዋል።
የዜጎችና የመንግስት አንድነት
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት በሚሰጠው መመሪያ መሰረት በመንቀሳቀስ ሕግ የማስከበር ስራው እንደተሰራ በድሉ ማግስት መንግስት አብስሮናል። መላው ዜጎች የመጀመሪያ ጉዳያቸውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በመለየትና በእርሱ ባለመስማት ከሰራዊቱ እኩል በጋራ ድሉን ለማምጣት ችሏል።
ከበርካታ ዓመታት በፊት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተከናወኑ አሰቃቂ ወንጀሎችንና ድርጊቶችን ሳይቀር «በዲጅታል ወያኔ» ቡድን በማደራጀት ህብረተሰቡን ለማሳሳት ቢሞከርም፣ በተቃራኒው ግን የትህነግን የሃሰት ለቅሶ የተረዳው መላው ሕዝብ ሴራውን አክሽፎታል። ህብረተሰቡ ከመንግስት ብቻ የሚሰጠውን መግለጫ እየተከታተለ በየቀኑ ራሱን በመረጃ እያበለፀገ በመሄድ ሊፈጠር የሚችለውን ውዥንብር አምክኖታል።
ዜጎች መንግስት ላቀረበው ሕዝባዊ ጥሪ በቂ ዝግጅት አድርገዋል። ለዚህም የአማራ ሚሊሺያ እና ልዩ ኃይል የነበረውን ዝግጁነትና የሰራውን ጀብዱ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎችም ሰራዊቱን በተለያየ መንገድ በጀግንነት ለድል እንዲበቃ እገዛ አድርገዋል።
ይሄ የተሳካው መንግስትና የፀጥታ አካላት በተደራጀ ሁኔታ ለሕዝቡ ጥሪ በማቅረባቸው ነው።በተለይ በየአካባቢያቸው በአግባቡ ተደራጅተው በመስራት ውጤታማ ተግባር አከናውነዋል። እኩይ ተግባር ለመፈፀም የተሰማራ ኃይልን ተደራጅቶ መጠበቅ ኢትዮጵያውያን እንደሚያውቁበት አስመስክረዋል። እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ላይ ኮሽታ እንዳይኖር በማድረግ በኩል የህብረተሰቡ ሚና የላቀ ነው።
ከሁሉም በላይ ሕዝቡ በጋራ ተደራጅቶ አካባቢውን ጠብቋል፤እየጠበቀም ይገኛል። በአካባቢው ላይ ሊፈጸም የሚችል ማንኛውም ሴራ እና ጥቃት ከሕዝብ አይን ሊሰወር አይችልምና ሕዝቡ ከፀጥታ ኃይሎች በተቀበላቸው አድራሻዎች መሰረት በርካታ ሺ ጥሪዎችንና ጥቆማዎችን በማድረግ የታሰቡ እኩይ ሴራዎችን ማክሸፍ ችሏል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም የሕዝቡን ጥቆማ መሰረት አድርጎ እጅግ በጣም ውጤታማ ስራ ማከናወኑንና ለድሉ መፍጠን ዜጎች ጉልህ ድርሻ ስለማበርከታቸው በተለያየ አጋጣሚ በመገናኛ ብዙኃን አስታውቋል ። ይሄ በአዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ ሀዋሳም ሆነ ሁሉም ከተሞች ላይ የተስተዋለ በጎ ተግባር ነው።
እንደ ማጠቃለያ
ጁንታውን ቀብሮ አፈር የማልበስ ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል። ይሄ ለመላው ኢትዮጵያውያን እረፍት ነው። ከቀናት በፊት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የጥፋት ቡድኑ መበታተኑንና ከዚህ በኋላ ህልውናው ማክተሙን መቀሌ ላይ ተገኝተው አብስረውናል።
የቀረው በየቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ የተወሸቁትን ለቃቅሞ ህግ ፊት ማቅረብ መሆኑንም አስረድተውናል።
ከዚህ መረዳት የምንችለው ኢትዮጵያውያን ጠላት አጥቅቷቸው እንቅልፍ የማይወስዳቸው መሆኑን። እጅ የመስጠት ታሪክ የማያቁ ናቸው። ድል በሄዱበት ቦታ ሁሉ ይቀናቸዋል።
ለእዚህ ሁሉ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆማቸው ነው፡፡ ይህ አንድነት ከዚህም ባሻገር ለዘመናት የተጫነንን ድህነት በተመሳሳይ መንገድ መቀነስ ብሎም ማጥፋት እንደምንችል ትልቅ ትምህርት እንደሚሆነን ማሳያ ነው።
ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሁለት ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ በእብሪት ልቡ አብጦ ሀገር ለማፍረስ ሲዘጋጅ የነበረን ማፊያ መገርሰስ ከቻልን በቀጣይ ጊዜያት ፊታችንን ወደ ስራ አዙረን በልማቱም መስክ ድልን ለመጎናፀፍ በአንድነት መጓዝን ይጠይቀናል፡፡
ይህንኑ እርምጃ ለመውሰድ ዛሬ ነገ ሳንል መተባበር የሁላችን ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2013