ዳግም ከበደ
ኢንተርናሽናል ሞዴል ፈቲያ መሀመድ ትባላለች። እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2018 በማሌዢያ በተካሄደው ውድድር የሚስስ ቱሪዝም አሸናፊ ነች። በቡልጋሪያ በተካሄደ ውድድር ላይም እንዲሁ በሚስስ ፕላኔት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በአሜሪካ በ2019 በተካሄደ የሚስስ ወርልድ ውድድር በቬጋስ የማህበረሰብ አገልግሎት አሸናፊ ለመሆን በቅታለች።
በአጠቃላይ ፈቲያ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ለ15 ዓመታት መቆየት ችላለች። እነዚህ ውድድሮች በአጠቃላይ እናት ሆነው በሞዴሊንግ ዘርፍ ላይ የሚሠሩ የሚሳተፉባቸው ናቸው። በቅርብ በተቋቋመ የሞዴሊንግ ማህበር ላይ ፕሬዚዳንት ነች።
ሞዴሊንግ ለምን?
ኢንተርናሽናል ሞዴል ፈቲያ ወደ ሞዴሊንግ ሙያ ከዓመታት በፊት የገባችው በሰዎች ምክር ነበር። ሰዎች ቁመቷንና ጠይም ቀለሟን በማየት በሞዴሊንግ ሙያ ብትሳተፍ እንደሚሳካላት ይነግሯታል። በወቅቱ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ፣ ራዲዮ ድራማ፣ ዶክመንተሪዎችና ሌሎች መሰል ፕሮግራሞችን ትሠራ ነበር።
በወቅቱ የፋሽን መፅሄት ላይ ተሳትፎ ነበራት። በተለይ በአገር ውስጥ በትላልቅ መድረኮች ላይ የሚካሄዱ ፋሽን ሾዎች ላይ ተሳትፎ ነበራት። ይህ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት በመሄድ ኢትዮጵያንና ባህሏን ታስተዋውቅ ነበር።
ሞዴሊንግ ድሮና አሁን
በወቅቱ ኢንተርናሽናል ሞዴል ፈቲያ ማህበረሰቡ ለፋሽን ኢንዱስትሪው በተለይ ደግሞ ለሞዴሊንግ የነበረው አቀባበል አነስተኛ እንደነበር ትናገራለች። ቤተሰብም ሆነ ማህበረሰቡ ድጋፍ አያደርግም። እንዲያውም የፆታ ጥቃት የሚደርስባቸውና ሰብዓዊ መብታቸው የሚረገጥበት አጋጣሚ ነበር። አሁን ላይ ግን ይሄ አመለካከት እየተሻሻለ መሆኑን መገናኛ ብዙሃን፣ ህብረተሰቡም ሆነ ወጣቱ ተቀብሎታል። ጫናዎቹም ቀርተዋል።
የፋሽን ሙያ አረዳድ
የፋሽን ኢንዱስትሪው ሰፊ ዘርፍ ነው። በውስጡ በርካታ ሙያዎች አሉት። ይሄ ጥቅል ዘርፍን ሙሉ ለሙሉ የመረዳት ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ይነገራል። ኢንተርናሽናል ሞዴል ፈትያ ቁንፅል ቢሆንም የፋሽን ኢንዱስትሪው በተሟላ ሁኔታ ዕድገት እያሳየ እንዲሄድ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ትገልፃለች።
ከዚህ ቀደም መረጃ በመስጠትና ዘርፉን በማስተዋወቅ ረገድ የፋሽን መፅሄቶች በብዛት ነበሩ፡፡ አሁን ላይ ግን እነዚህ ጠፍተዋል። ይሁን እንጂ በተበታተነ መልኩም ቢሆን በግል ጥረት ትላልቅ ደረጃዎች የደረሱ ባለሙያዎች ተፈጥረዋል። የኢትዮጵያን ባህልና የፋሽን ሀብቶችን ለማስተዋወቅ ጥረት ይደረጋል። ስኬትም እየተመዘገበ ነው ስትል ታብራራለች።
ዓለም አቀፍ ተሳትፎ
ኢንተርናሽናል ሞዴል ፈቲያ በ2015 የአፍሪካ ሚስ ኪውን ላይ በመሳተፍ ዓለም አቀፍ የፋሽን ኢንዱስትሪውን በይፋ ተቀላቅላለች። ከዚያ አውሮፓ ውስጥ የፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ ልምድ ካላቸው ኢሊት ሞዴል ኩባንያዎች ጋር መሥራት ጀመረች። ይህ አጋጣሚ ደግሞ አውሮፓ ውስጥ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች የመሥራት አጋጣሚውን እንድታገኝ አስቻላት።
በአሜሪካም በኢትዮጵያውያን የፋሽን ባለሙያዎች የሚታተሙ መፅሄቶች ላይ የሞዴሊንግ ሥራ ሠርታለች። አጋጣሚዎቹ ለፈቲያ ብዙ ዕድሎችን ከፍተውላታል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የምትወዳትን ኢትዮጵያን አንድታስተዋውቅ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮላታል።
ሞዴሊንግና ማህበራዊ ኃላፊነት
ኢንተርናሽናል ሞዴል ፈቲያ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች። ልምድ ያካበተች በመሆኗ ደግሞ አዲስ በሙያው ላይ የሚመጡ ወጣቶችን ካካበተችው ልምድ አንፃር ለማበረታታት ኃላፊነት እንድትወሰድ አድርጓታል። በዚህም በአሜሪካ በሚካሄዱ የቱሪዝም የሞዴሊንግ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አርአያነቷን አስመስክራለች።
ይህን መሰል ውድድር ላይ የምትሳተፈው ችሎታውና ፍላጎቱ እያላቸው በቤት ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ሴቶችን ለማበረታታት ነው።
ከዚህ ባሻገር ኢንተርናሽናል ሞዴል ፈቲያ በአገራችን የተለያዩ ቦታዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የበኩሏን አስተዋፅኦ ታበረክታለች። በዚህም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርታለች። ከዚህ ውስጥ በድሬዳዋ፣ ሱማሌና መሰል አካባቢዎች ላይ <<ሙከጀላ>> ወይም በዛፍ ጥላ ስር እርቅ ለማድረግ የሚካሄድ የሽምግልና ስነስርዓትን በመጠቀም የሰላም ግንባታ ላይ ስትሳተፍ ቆይታለች። ከዚህ ባለፈ ኢስላሚክ ፋሽን ሾው በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲካሄድ የበኩሏን አስተዋፅኦ አድርጋለች።
ሙከጀላት
«ሙከጀላት እና ጌድ ሆስት» በድሬዳዋ ከተማ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል በዛፍ ጥላ ስር የሚደረግ የሽምግልና ሥነ ሥርዓት ነው። የተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲከሰቱ፤ በግለሰቦች መሃል አለመግባባት ሲፈጠር የአገር ሽማግሌዎች፣ኡጋዞች፣እናቶች እና ወጣቶች በዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበው ምክክር በማድረግ ችግሩን የሚፈቱበት እሴት ነው። በዚህ እውቅ ባህላዊ ሥነ ሥርዓት ነው ዓለም አቀፍ ሞዴል ፈቲያ እና መሰል አጋሮቿ ያደጉት።
ታዲያ አሁን ላይ ባህላዊ እሴቶች ፈር ሲለቁ ከመተሳሰብ እና ከአብሮነት በላይ ጎጠኝነት ሲነግሥ እነዚህን የድሬ ፈርጦች ወደኋላ እንመልከት፣ ማንነታችንን አንዘንጋ፣ ባህላችንን አንርሳ «ኑና በዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበን ልዩነታችንን በምክክር እንፍታ» በማለት እሴቶቻቸውን ለማበልጸግ የተነሱት።
ኢንተርናሽናል ሞዴል ፈቲያ፣ አርቲስት አሊ ቢራ፣ የድሬዳዋ ተወላጅ የሱማሌኛና ኦሮምኛ ዘፋኝ አቶ የኑስ አብዱላሂ፣ ስኬታማው የንግድ ሰው እና የናሁ ቴሌቪዥን ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው እንዲሁም ሌሎች እውቅ የከተማዋ ልጆች እና መላው የድሬዳዋ ማህበረሰብ የተጣላን በማስታረቅ፣ አብሮነትን በማበልጸግ፣ የተሰበረ ማህበራዊ ሕይወትን የሚጠግኑ ሳይንሳዊ ቤተ ሙከራዎች እና ምርምሮች የማይፈቷቸው ባህላዊ ሀብቶች አሉን በማለት ሥራዎችን ሠርተዋል።
በዋናነት ይሄን ማህበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጅቱን ያሰናዳችው ሞዴል ፈቲያ ነበረች።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2013