አብርሃም ተወልደ
የአንዳንድ ሰዎች ጽሞና ማን ወሰደው? ምን ዋጣው? ሰው እንዴት የጽሞና ጊዜ ያጣል።በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ትችት፣ ስድብ ፣ማጉረምረም … የለመደባቸው ጥቂት አይደሉም።ትዕግስት የሚባል ነገር አጥተናል፤ ሲሆንልም ሲሆንብንም አንድ አይነት ሆነናል።
ባለፈው ሳምንት ከብዙ ጊዜ መለያየት በኋላ ከአንድ ወዳጄ ጋር ተቀጣጥረን በአንድ ምግብ ቤት ተገናኘን፤ የዚያ ቤት ምግብ ጉዞ ፍታት/ረጅም ጊዜ የሚወሰድ የፍታት አይነት ነው/ የሚሉት አይነት ስለሆነ መጨዋወት ጀመርን፤ ባለመገናኘታችን የተነሳ ብዙ ያልተወያየንባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩና መወያየት ጀመርን።
እንዳው ለወጉ ተወያየን አልኩ እንጂ አንዱን ስናነሳ ሌላውን ስንጥል እና ስንተች ነው የቆየነው።በእርግጥ አንዱን ማንሳት ሌላውን መጣል ተፈጥሯዋዊ ናቸው።ግን ያዢያቸውን ይመስላሉ።
ውይይት ካደረግንባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በትግራይ ሲካሄድ የቆየው ህግን የማስከበር ዘመቻ ነው፤ በዚህም ላይ ወዳጄ በአብዛኛው የሚችለውን ያህል ነቀፈ፤ አቃቂር አወጣ፤ ትንሿን ችግር ዘርፍ አበጃጅቶና አግዝፎ ገለጻት፤ ተቸ።በቃላት መተቸት ያልሆነለትን ደግሞ ቀኝ እጁን በማወናጨፍ ፣ ፊቱም በማንጠልጠል ጭምር ልክ አለመሆኑን ገለጸ፤ ለተነሳው ጉዳይ ድምቀት ለመስጠት ሞከረ።
የተናገረው አስፈርቶት ይሁን አላውቅም ደግሞ በረድ አለ።የህዝቡና የመንግስት አይንና ጆሮ እኮ እኛ ነን አለኝ፤ አየህ አንከኖችን እና ችግሮችን ነቅሶ በመውጣት የሚተች ባይኖር፣ ሁሉም ልክ ነው ቢል አንደኛ መንግስታትን አምባገነን እናደርጋቸዋለን ሲል አብራራልኝ።የፈለገውን ያህል ብናገር አስፈልጋለሁ ማለቱ ነው።
በጨወታችን መሐል ምግቡ ቀረበ፤ ቀመስኩት፤ ሸጋ ነበር፤ የገበታ ስነ ስርአት ባይሆንም አሁንም ጨዋታችንን ቀጠልን።እኔ የምልህ፤ የምትሰራበት አካባቢ የመመገቢያ ቦታ እና የምግብ አማራጮች ብዙም ያሉበት አይደለም።የት ትመገባለህ ስል ጠየኩት?
ምን እባክህ! በሚል ሃሳቡን ጀመረ።የትስ ቢሆን ያው ነው፤ ምን ደህና ነገር አለ፤ ሌላ ዘንድ አትሂድ፤ አሁን እየባለነው ያለውን እንጀራ ብቻ ተመልከት፤ ከእንጀራው ስንት በመቶው ጤፍ እንደሆነ አናውቅም፤ በቅርቡ ከባልደረቦቼ ጋር ምግብ እየበላን ስንጨዋወት አንዱ ጓደኛችን አያችሁ ይህን እንጀራ ሲል አመለከተን፤ ምን ሆነ አለነው፤ ዛሬ ገና ጤፍ ያለበት እንጀራ አየሁ ሲል አስተያየቱን ሰጠ።
አሁንስ ተሳክቶልሃል አልኩት በልቤ፤ መቶ በመቶ የጤፍ እንጀራ የሚበላው መኖሪያ ቤት ሲዘጋጅ ብቻ ነው።ሆቱል ቤቱም፣ አንጀራ ሻጩም ጥራጥሬ የተቀየጠበት የጤፍ እንጀራ ነው የሚያቀርቡት።መኖሪያ ቤትም የሆነው እጁ ጤፍ ይሆንና የተቀረው ጥራጥሬ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አለ፤ ይሄ ምን ችግር አለው፤ እህል ነው፤ ችግሩ የሚከፋው የጄሶ እንጀራ መሆኑ ላይ ነው አልኩት።
ወደ ገበታው ተመለሰን፤ ወጡን እየው፤ እየው! በበርበሬ ይሰራ በሸክላ … አለኝ፤ ያነሳቸው ሀሳቦች ምግቡን ይበልጥ እንዳጣጣም አረጉኝ።ስጀመር ያገኘሁትን ጥፍጥና ከወዳጄ አስተያየት በኋላ እያጣሁ መጣሁ።
ሁሉም ነገሩ የሰው ልጆችን ሆን ተብሎ ለመጉዳት ታስቦ የሚደረግ አርጎ እየወሰደ መሆኑ አሳሰበኝ፤ የወዳጄ ትችት እኔን ፍርሃት ውስጥ ከተተኝ።ቃላት እና ሃሳቦች እንደ አጥንት እና መቅኒ ናቸው፤ አንድ አምሳል አንድ አካል የሆኑ፤ ልንለያያቸው እጅጉን የሚያዳግቱ።ሀሳቦቻችን ማለትም እኛ ብቻ የምንሰማቸው ደምጽ አልባ ቃላት በውስጣዊ ማንነታችን፣ በጤናችን፣ ደስታ እና አመለካከታችን ላይ ተጽእኖ ይፈጥራሉ።እኔም የሆንኩት እንዲሁ ነው፤ ለካ ወዳጄ በአነሳው የነቀፌታ ሀሳብ ተወስጄ ነበር።እውነት እኮ ነው፤ አንድም ደህና ነገር የለም ማለት ጀምሬ ነበር።
ጸሐፍት ከአፋችን የምናወጣው ያሰብነውን ነው ይላሉ።አንደበታችን እኛን እንደሞኝ የሚያስቆጥርበት አጋጣሚ አለ፤ በመረጃ ላይ ሳይመሰረቱ መፍረድ፣ መተቸትና መላምት መስጠት ከማዋረድ እና ከማጥፋት ባሻገር መቼም ቢሆን ደስታ እና ሰላም አይሰጥም።
የወዳጄ አንዳንድ ሀሳቦቹ መልካም ናቸው፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር መንቀፍ እየጉረመረሙ መግለጽ ለምን? ሁሉንም ነገር አለሚዛኑ መተቸትስ ተገቢ ነውን ስል ራሴን ጠየቅኩ፤ አእምሮዬ ይሆናል ያለውን የመፍትሔ ሀሳብ ለገሰኝ።እውነት እኮ ነው፤ የሚጨበጨብላቸው የአዋቂነት እና የንባባቸው ስፋት ልኬቱ ከፍ ያለ ነው የሚባልላቸው “ምሁራን” ጀግኖች ጎበዞች የሚባሉት ትችት ሲያቀርቡ ብቻ ነው፤ ለዚያም ነው በጨለማ የሚታያቸው፤ በሄዱበት ሁሉ መልካም ከመናገር እና ከመዝራት ይልቅ ሁሌም ጨለማውን ሲያዩ ሲያትቱ እና ሲናገሩ የሚታዩት ከዚህ በፊት ባቀረቡት ሃሳብ ባገኙት ሙገሳ ተገፍተው እንደሆነ እገምታለሁ።
ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ማዕዘናት ስለአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳይ የትምህርት ዝግጁቱም ሆነ ለነገሩ መረጃው የሌለው ነገር ግን በሆነ አንድ የትምህርት መስክ ሶስተኛ ዲግሪውን የተማረ ይመጣና ዶክተር እገሌ እባላለሁ፤ ለአገሬ ይህንንና ያንን አድርጌያለሁ፤ የቀድሞ መንግስት… መከራ ሲያደርስብኝ ነበር ሲሉ ያመለክታሉ።እነዚህን ለማረም ፣ ለማስተካከል እንዲሁም አንዳንዱን ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ አሁን ያለውም መንግስት አቅም ያለው አይመስለኝም።
አሁን አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው መንግስት “ሰባኪ” ነው፤ አገርን ለመምራት ሳይሆን በእምነት ተቋም ነው መገኘት ያለበት ሲል ይቆይና፤ መንግስት ህግ ማስከበር አለብኝ ብሎ ሲነሳ ደግሞ ይሄው ግለሰብ /“ዶክተሩ”ተብዬው/ ወንድም ወንድሙን ገድሎ አሁን ይህ ምን የሚሉት ጉዳይ ነው ይልሃል፤ ብቻ የምንም ነገር ሱስ አይያዝህ፤ በተለይ አለሚዛኑ የመተቸት እንዲሁም የመንቀፍ ሱስ፤ በጎ አይታይህማ!
ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መወያየት፤ ለመፍትሄውም መምከር የሚበረታታም የሚፈለግም ጉዳይ ነው፤ ከብዙ መልካም ነገሮች ይልቅ ጥቂት ስህተቶችን እየለቃቀሙ አንድም መፍትሄ ሃሳብ ሳይዙ ነቀፌታ ላይ ማተኮር ግን የበሽታ ነው።
የህይወት ገጠመኜ (life evenet) የተባለ አንድ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ሶቅራጦስ አለ ብሎ ያነበብነውን እስቲ እንመለክት።አንድ ሰውዬ ወደ ታዋቂው ፈላስፋ ሶቅራጦስ ይቀርባል፤ “ስለ ጓደኛህ አንድ ወሬ ልነግርህ ነበር…” ይለዋል።ሶቅራጦስም “ቆይ አንዴ! ምንም ነገር ሳትነግረኝ በፊት ሶስቱ ወንፊቶች ወይም ማጥለያዎች ብዬ የምጠራቸውን ጥያቄዎቼን ላንሳልህ…”ሲል ይጠይቀዋል።
“ሶስቱ ወንፊቶች?”ሲል ሰውዬው ራሱን ጠየቀ።“አዎ!” ሲል ሶቅራጦስ መለሰ።የመጀመሪያው ወንፊት እውነታ ነው፤ አሁን የምትነግረኝ ነገር እውነት መሆኑን እርግጠኛ ነህ?” ሲል ሶቅራጦስ ሰውዬውን ይጠይቀዋል።ሰውዬውም “እርግጠኛ አይደለሁም! እኔ እንጃ! ሰው ነው የነገረኝ…”ሲል ይመልሳል።
ሶቅራጦስ “ስለዚህ… እውነት ይሁን አይሁን አታውቅም!” ብሎ በሁለተኛው ወንፊት ላይ ተመስርቶ ጥያቄውን ያስከትላል።ሁለተኛው ወንፊት መልካም ዜና ወይም ወሬ ነው? የሚል ነበር፤ አይደለም ሲል ሰውየው ይመልሳል፤ እንደውም በተቃራኒው ነው አለው።ሶቅራጦስ “በአጭሩ… ልትነግረኝ የመጣኸው… ስለ ጓደኛዬ እውነት መሆኑን ያላረጋገጥከውን መጥፎ ነገር ነው ማለት ነው›› ሲል መለሰለት።
አንድ ወንፊት ይቀራል! በሱ ወንፊት ካለፍህ ወሬውን ልሰማህ እችላለሁ…” ሲል ሶቅራጦስ ይገልጻል።በ“ሶስተኛው ወንፊት የምትነግረኝ ለኔ ይጠቅመኛል?” ሲል ሰውዬውን ይጠይቀዋል።ሰውዬውም “ይጠቅምሃል ለማለት አልደፍርም! ግን…” ይላል።ሶቅራጦስም “የምትነግረኝ ነገር እውነት ካልሆነ እንዲሁም የማይጠቅመኝ ከሆነ ለምን ልትነገርኝ መጣህ?” ሲል ሰውዬውን ይጠይቀዋል።ሰውዬው ምላሽ አልነበረውም።
ቀደም ሲል ለተጠቀሰው አይነት በሽታ አንዱ መፍትሄ የሶቅራጦስ አይነት ማንጠሪያ ማዘጋጀት ነው፤ ሌላኛው ደግሞ ማንኛውም ሰው ችግር አየሁ ብሎ አንዳች ነቀፌታን በሚሰነዝርበት ቅጽበት የመፍትሄ አካልም እንዲሆን መጋበዝ ነው፤ በዚህም አይነት መንገድ ክፉ ብቻ የሚታያቸውን በመተቸት የተካኑ ግለሰቦች ላመጡት ነቀፌታ መፍትሄ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ በጎንም ለማየት ይሞክራሉ፤ አሊያም ለአንደበታቸው ልጓም ያበጃሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2013