ዳግም ከበደ
በፊልም፣ በቲያትር፣ በመፅሄት፣ በፋሽን ሾው ኢንዱስትሪው እጅግ ተፈላጊ ከሆኑ ሙያዎች መካከል ነው። እነዚህ የጠቀስናቸው ሙያዎች ያለእሱ ባዶ ናቸው ብንል ማጋነን አይሆንም። በዚህ ምክንያት ባለሙያዎቹም ቁልፍ ከሚባሉ የእጅ ጥበብ ሙያተኞች መካከል ይመደባሉ። ሜካፕ እና ሜካፕ አርቲስቶች።
ለዛሬ በዚህ ሙያ ላይ ዝናን ካተረፉ ባለሙያዎች አንዷ የሆነችውን እንግዳ ጋብዘናል። ሜካፕ አርቲስት አትክልት ለማ ትባላለች። በኢትዮጵያ ውስጥ የሜካፕ አርቲስት ፅንሰ ሃሳብን በትምህርት ደግፈው ማስተዋወቅ ከጀመሩ እውቅ ባለሙያዎች ውስጥ የአትክልት ስም ቀዳሚው ነው። ለዚህ ነው እኛም ይህን ሙያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ እየጣሩ ከሚገኙ ባለሙያዎች የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ለመገንዘብ የወደድነው።
አርቲስቷ ማን ናት
ወደ ሜካፕ አርቲስትነት ሙያ የገባችው በትምህርት ነው። ፋሽን፣ ፈጠራ (creativity) ፣ ፊትን በተለያየ መንገድ መቀየር (special effects)፣ የመፅሄት ፋሽን ሜክአፕና ሌሎች መሰል የዘርፉ ስራዎችን አጠቃላ ተምራለች። ይህች ተወዳጅ ሙያው በውስጧ መፀነስ የጀመረው ግን በልጅነቷ በእናቷ ፀጉር ቤት ውስጥ በትርፍ ሰአቷ በመዋሏና ለስራው ፍቅር እያደረባት በመምጣቱ ነው።
የሙያው ፈተናዎች
የሜካፕ አርቲስትነት ሙያውን ስትቀላቀል የመጀመሪያ ፈተና ሆኖ የገጠማት የፋሽን ኢንዱስትሪው በአገር ደረጃ ገና ጅምር መሆኑ ነበር። ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረትም ትንሽ ነበር። በተጨማሪም ሙያው የሚፈቅዳቸውን አዳዲስ የፋሽን ፈጠራዎች ለማስተዋወቅ የተቀባይነት ፈተናዎች ይገጥሟት ነበር።
ቀስ በቀስ ግን ሜካፕ አርቲስት አትክልት ነገሮች እየቀለሉላት መጡ። በተለያዩ ታዋቂ የፋሽን ሾው ትርኢቶች ላይ ሙያዋን ለማስተዋወቅ ቻለች። የፈጠራ ስራዎቿም በሞዴሎች እና በፋሽን ሾው አዘጋጆች ተወዳጅነትን እያተረፉ ሙያውም እድገት እያሳየ መጣ። በተለይ ስራዎቿን ተወዳጅ ያደረገው ኢትዮጵያን የሚወክል መሆኑና የፈጠራ ስራውም ይህንኑ ማካተቱ ነው። አሁን ላይ አትክልት ብቻ ሳትሆን ባጠቃላይ በሜካፕ አርቲስትነት ሙያ ላይ የፈጠራ ክህሎት እያደገ መጥቷል ፤የፋሽን ኢንዱስትሪው ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሻገር ጉልህ አስተዋፆኦ ማድረግ ተችሏል።
ከዓመታት በኋላ
ሜካፕ አርቲስት አትክልት ለማ ሙያው ላይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ ላለፉት አስር ለሚደርሱ ዓመታት ቆይታለች። ይህ ዘርፍ በቀዳሚነት አሁን ለደረሰበት ደረጃም የራሷን ጉልህ ሚና ተጫውታለች።ከዚህ በመነሳት የቀደመውንና አሁን ላይ ያለውን የሙያውን ለውጥ በሚገባ ማብራራት ትችላለች።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ማለትም እርሷ ወደ ሙያው ሙሉ ለሙሉ ስትገባ አጠቃላይ ማህበረሰቡ ለሜካፕ አርቲስትነት ሙያ እንዲሁም ባጠቃላይ ለሜካፕ ያለው ምልከታ በእጅጉ አናሳ ነበር። ለፈጠራ ውጤቶች የሚሰጠው ትኩረትም እንዲሁ የደከመ ነበር። ለሜካፕ አርቲስት ብቻ ይሆን በፈጠራ ስራ ላይ ባጠቃላይ በአርት ላይ የነበረው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ሙያው ላይ የሚገቡ ሰዎችም በልምድ የሚሰሩ ነበሩ።
አሁን የፋሽን ኢንዱስትሪውም ሆነ ተከታዩ ስለ ሜካፕ ያለው ምልከታ በእጅጉ ተቀይሯል። ከ90 በመቶ በላይ ባለሙያዎች ስራቸውን የሚያከናውኑት በትምህርት ታግዘው ነው። በመፅሄት፣ በፊልም፣ በፋሽን ሾው እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ሜካፕ አርቲስት ተፈላጊና የጀርባ አጥንት ነው። በጥቅሉ እንደ አርቲስቷ ምልከታ አሁን ላይ ለሙያው ቦታ ተሰጥቶታል።
ሜክአፕ አርቲስት አትክልት በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ በዓለም አቀፍ የፋሽን ሳምንቶች ላይ ከመድረክ ጀርባ የሜካፕ ዋና ስራዎችን በመምራት ትታወቃለች። ‹‹African Mosaique›› ላይ ለሁለት ዓመት ያህል በዚሁ ሙያ ሰርታለች፤ በተለይ ‹‹Hub of Africa Addis fashion week›› ላይ በኢትዮጵያም ሆነ በተለያዩ አገራት በመሳተፍ ትላልቅ ዝግጅቶችን በዚሁ ሙያ የመምራት ብቃቷን አስመስክራለች። የሜክአፕ አርቲስትነት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፋሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግ በጎ አስተዋጽኦም እያደረገች ትገኛለች።
ሶረቲ ስፓ
ሜካፕ አርቲስት አትክልት ለማ ራሷን በምትወደው ሙያ ከማብቃት ባሻገር መሰል ፈለግ ለመከተል የሚፈልጉ ወጣቶችን ለማበረታታት ጥረት ታደርጋለች። የኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪ ቀሪው ዓለም ከደረሰበት እድገት ላይ እንዲደርስ ከሙያ አጋሮቿ ጋር እየሰራች ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ የብዙሃንን ቀልብ መያዝ የቻለ ‹‹ሶረቲ ስፓ›› የተሰኘ የመዝናኛና የመዋቢያ ድርጅትን ከፍታለች። አጋጣሚውም ለበርካታ ወጣቶችና ባለሙያዎች የስራ እድል መፍጠር ችሏል። ከዚህ ባሻገር በዚህ ስፍራ የሚሰሩ ባለሙያዎች ብቁ እንዲሆኑ የተለያዩ ትምህርታዊ ስልጠናዎችን ይሰጣል።
ወጣቶችና ፋሽን
ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አሁን ላይ ለፋሽን ልዩ ቦታ የሚሰጡ መሆናቸውን ሜካፕ አርቲስት አትክልት ትገልፃለች። ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊ (ሃበሻ) መዘነጥና መልበስን የሚወድ ማህበረሰብ መሆኑንም ታምናለች።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያውያን በባህላቸውና ባላቸው የራሳቸው የፋሽን ስልት ተውቦ ለመታየት ይጥሩ ነበር። አሁን ደግሞ በተለየ መንገድ በማህበራዊ ድረ ገፅና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይህን ልምድ በማስፋት የፋሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግ እየሰሩ መሆኑን ታነሳለች።
ኢትዮጵያውያንን ለዓለም ልናስተዋውቀው የምንችለው ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብና ሌሎች በርካታ ነገሮች እንዳሏቸው ጠቅሳ፤ ይህን በፋሽን ኢንዱስትሪው አማካኝነት ለማስተዋወቅ ቃል በመግባት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር የነበራትን ቆይታ ቋጭታለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2013