ዳግም ከበደ
ዲዛይነር ዮርዳኖስ አበራ ትባላለች። የዮርዲ ዲዛይን ባለቤትና መስራች ነች። ባህላዊ አልባሳትን በዘመናዊ መንገድ ዲዛይን በማድረግ ምቹና ተለባሽ እንዲሆኑ ትሠራለች። የኢትዮጵያን አልባሳት ለማስተዋወቅም እንዲሁ። ይህን ሥራ ከ12 ዓመት በፊት የጀመረች ሲሆን፤ እውቅ ዲዛይነሮች ከሚባሉት ተርታ የምትሰለፍና ለሙያው ማደግ የድርሻቸውን ከተወጡት ውስጥ የምትመደብ ናት።
ወደ ፋሽን ሙያ
ወደ ፋሽን ዲዛይን ሙያ የተሳበችው የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን፣ ፋሽን ሾው ታዘጋጅ በነበረበት ወቅት ሲሆን፤ ይህ ጥረቷ የባህል አልባሳትን ዲዛይን ወደማድረግ አድጓል። ቤተሰቦቿ ወደ አርቱ ያዘነበለ ሙያ ውስጥ መሆናቸውም ከልጅነት ጀምሮ በዚህ መሰል ሙያ እንድትማረክ አጋጣሚውን ከፍቶላታል።
የሙያው ፈተናዎች
ባህላዊ አልባሳትን በዘመናዊ መንገድ ዲዛይን አድርጋ ለማስዋብ በምታደርገው ጥረት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በርካታ ፈተናዎች ገጥሟታል። የመጀመሪያው ባህላዊ ተፅኖውንና የተለመደውን የአለባበስ ዘይቤ ሰብሮ መግባት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በጊዜው የዲዛይን ሙያ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደና በስፋት ስለሌለ ነበር። እነዚህን ፈተናዎች ግን አሸንፋ አሁን ላይ ስኬታማና በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈላጊ ከሚባሉ ዲዛይነሮች ተርታ ተመድባለች።
ዲዛይኒንግ እና ጥበብ
ዲዛይነር ዮርዳኖስ ባህላዊ አልባሳትን በዘመናዊ መንገድ ማዘጋጀትም ሆነ የፋሽን ሙያ የጥበብ አንድ ዘርፍ እንደሆነ ታምናለች። በዚያም ሥራዎቿ ጥበብ የታከለበት፣ ከተለመደው ወጣ ብሎ የዘናጩን ፍላጎት የሚያረካ፣ወቅቱን የጠበቀና ከአየር ሁኔታው ጋር የተስማማ፣ ከተክለ ሰውነት ጋር የሚሄድና ለእይታ ምቹ እንዲሆን የራሷን ሙያዊ እውቀት ተጠቅማ ተወዳጅ ሥራዎችን ታቀርባለች።
ኢትዮጵያዊነት፣ ባህልና ፋሽን
በዲዛይነርና የፋሽን ባለሙያዋ ዮርዳኖስ እምነት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሙያውን የመረዳትና በዲዛይነር የተሰሩ ማራኪ አልባሳትን የመጠቀም ፍላጎት በእጅጉ አድጓል። በተለይ በዚህ ሁለት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እየታየ ነው። አዲሱ ትውልድ አዲስ ነገርን በቶሎ ለመቀበል ፈጣን ነው።
ሆኖም ኢትዮጵያዊ ባህሎቹ ወጣ ያሉና ከማህበረሰቡ የማንነት ስሪት ጋር የማይሄዱ የፋሽን አልባሳትን አይቀበሉም። ይሄ በጎና የሚበረታታ አስፈላጊም ነው። በተለይ አለባበስ ከባህል፣ የአየር ፀባይ፣የተለያዩ ዝግጅቶች ከሚፈልጉት ስነ ስርዓቶች አንፃር የተዋሃዱ መሆናቸው ተገቢ ነው። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያዊ ማንነትን የተከተሉ አልባበሶች ከዘመናዊው ዓለም ጋር ሳይፋቱ የታረቀ ውህደት እንዲይዙ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ነው የምትገልጸው።
ዮርዲ ዲዛይን አሁን
የዲዛይንና የፋሽን ባለሙያዋ ዮርዳኖስ አበራ ከ12 ዓመት በላይ በዘርፉ ቆይታለች። ዓለም አቀፍ ተሳትፎም ታደርጋለች። በዓለማችን ላይ በተካሄዱ ትላልቅ የፋሽን ሾውና የዲዛይን ፌስቲቫሎች ላይ ትካፈላለች።
የዲዛይንና ፋሽን ሙያ በዓለማችን ላይ እጅግ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሙያው አደጉ የሚባሉ አገራት የኢኮኖሚ መሰረታቸው በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም ከሚያደርጉት ዘርፎች መካከል የሚመደብ ነው። ከዚህ አንፃር ዮርዳኖስ ዘርፉ በአገራችን መሰል አስተዋጽኦ እንዲኖረው ጠንክረው ከሚሠሩ ባለሙያዎች መካከል ነች። በዮርዲ ዲዛይን ድርጅቷ ውስጥም በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች። የፋሽንና ዲዛይን ሙያ አሁን ካለው ደረጃ በላይ እድገት እንዲያሳይም ከሙያ አጋሮቿ ጋር በመሆን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ትሠራለች።
አሁን ላይ በዘርፈ ብዙ የአልባሳት ዲዛይኒንግ ሙያ ላይ ትሳተፋለች። መንግሥት ሙያውን ትኩረት ሰጥቶት ድጋፍ እንዲያደርግ ከሚሞግቱ ሙያተኞች መካከልም ቀዳሚዋ ነች። በዚህ ጥረቷ አሁን ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪዎች ዩኒፎርም ሲያሰፋ በዲዛይነር እንዲሠራ ሲወሰን ለዚህ ታላቅ ሥራ ታጭታ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እያቀረበች ነው።
የመንግሥት ድርሻ
ዲዛይነርና የፋሽን ባለሙያዋ ዮርዳኖስ በተለያዩ አገራት የፋሽን ሾው የማሳየት አጋጣሚው ነበራት። በዚያ መልካም ተሞክሮ አይታለች። እዚያ የታዘበችው በአገሯም ቢኖር ትሻለች። በተለይ መንግሥት የቱሪስት መዳረሻ በሆኑ አካባቢዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የፋሽን ኢንዱስትሪ ማሳያ ቦታዎች ማዘጋጀት እንዳለበት ታምናለች።
ለባለሙያዎቹም ቢሆን መሰል ምቹ አጋጣሚዎች መፍጠር የአገርን ኢኮኖሚ ከማሳደጉም በላይ የማንነታቸው መሰረት የሆኑ ባህሎችን ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል ብላ ታምናለች። መንግሥት ሃሳባቸውና ራእያቸው እውን እንዲሆንም ከምንም በላይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው አበክራ ትጠይቃለች። እሷና መሰል ባለሙያዎችም በማህበር ተደራጅተው የፋሽን ኢንዱስትሪው ወደፊት እንዲራመድ እየሠሩ መሆኑንም እንደዚያው።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013