ኢትዮጵያ በፍቅርና በአንድነት የሚኖርባት ሰፊ የባህል ውቅያኖስ ናት፡፡ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ መነሻዋ እስከ ምስራቅ መዳረሻዋ በርክተው የሚገኙት ሀገረ ሰባዊ ባህላዊ ትውፊቶች፣ እሴቶች፣ ወጎች፣ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓቶች የዚህች ውብና ድንቅ አገር መገለጫዎች ናቸው፡፡ ባህል ለባህሉ ባለቤት መገለጫና ማህበረሰቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በዕለት ተዕለት ተግባሩ የሚከውነውና የሚያምነው ትልቅ ሀብቱ ነው፡፡
አንድ ማህበረሰብ የእርስ በእርስ ትስስሩን ለማጠንከርና ችግሮችን ለመፍታት የራሱ የሆኑ ሥርዓቶች ያበጃል፡፡ ዛሬ ዓለም ከምትገኝበት ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት በፊት ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ባህላዊ አስተዳደራዊ ሥርዓት ባለቤት መሆናቸው ቀዳሚ ያደርጋቸዋል፡፡ ሀገራችን በልዩነት ቀድማ በተለያየ ብሄረሰብ ከተገበረችው ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓቶች ውስጥ ዛሬ በሀገራችን ደቡባዊ ክልል የሚገኘውን የ‹‹ሞስዬ›› ብሄረሰብ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓትን ማስቃኘት ወደድን፡፡
በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ ከሚገኙ 56 ብሄረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ሞስዬ ብሄረሰብ በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን በደራሼ ወረዳ ከሚገኙ አራት ብሄረሰቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ የሞስዬ ብሄረሰብ በአብዛኛው በናሎ፣ በቡሳ ቅላና በቡሳ ባሶ ቀበሌዎች ውስጥ ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን፤ የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ታሪክና ልዩ ልዩ መገለጫዎች አሉት፡፡
ብሄረሰቡ ዘጠኝ የተለያዩ ጎሳዎች ያሉት ሲሆን፤ ካንስቻ፣ እሽላይቻ፣ ካሪቻ፣ ኤላይቻ፣ ከላይቻ፣ ካላይቻ፣ አርጋማይቻ፣ ማሊቻ እና ከተይቻ ይባላሉ፡፡ የብሄረሰቡ መግባቢያ ቋንቋ ‹‹ሞስታቻ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ግብርናና ከፊል አርብቶ አደርነት የማህበረሰቡ መተዳደሪያ ነው፡፡ መልክዓ ምድሩ ተራራማ ሲሆን፤ ቆላ፣ ደጋና ወይና ደጋ የአካባቢው የአየር ንብረት መገለጫ ነው፡፡
የብሄረሰቡ ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት
አቶ ፍሬው ተስፋዬ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪ ሲሆኑ፤ በብሄረሰቡ ታሪክና ባህል ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀጣዩም መረጃ እርሳቸውን ዋቢ በማድረግ ተሰናድቷል፡፡
የሞስዬ ብሄረሰብ የረጅም ዓመት ታሪክ፣ የብሄረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ መሰረት ያደረገና ማህበራዊ ሥርዓት የሚመራበት ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ያለው ነው፡፡ ብሄረሰቡ ከጥንት ጀምሮ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀቶችን በመትከል እራሱን በእራሱ የሚያስተዳድርበት የሚመራበት የስልጣን ተዋረድ ያለው ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ሲመራ እንደቆየ የብሄረሰቡ ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡
የብሄረሰቡ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ንጉሳዊ ሲሆን፤ ባህላዊ አስተዳደሩም የሚመራው የሁሉም ስልጣን የበላይ በሆነው ንጉስ ‹‹ዳማ›› ነው፡፡ በስሩም የተለያየ ሥልጣንና ተግባር ያለችው ሌሎች ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅሮች አሉት፡፡ እነዚህ የሥልጣን እርከኖች ከላይኛው ስልጣን ዳማ (ንጉስ) ጀምሮ ንጉሱን ከህዝብ ጋር የሚያገናኘው ‹‹ማካ›› የተባለ የስልጣን ደረጃ ጋር ይደርሳል፡፡
ከማካ ዝቅ ብሎ ደግሞ «ፖልዓ» የተባለ የመጨረሻ የሥልጣን እርከን አለ፡፡ በዚህ የባህላዊ አስተዳደር መዋቅር ተመራጭና መሪ የሆነው ባለስልጣን የማህበረሰቡ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና ችግሮችን በየደረጃው የመለየትና የመፍታት ግዴታና ሃላፊነት ይጣልበታል፡፡
በሞስዬ ብሄረሰብ የዳማ ድርሻ
በሞስዬ ብሄረሰብ ዳማ (ንጉስ) ባህላዊ አስተዳደሩን በበላይነት የሚያስተዳድር፣ የህበረሰቡ ተጠሪ ሆኖ የሚመራ የስልጣን ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡ ንጉሳዊ ስልጣን ህዝብ ፈልጎና መርጦ የሚሾመው ሳይሆን በዘር ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍና ንጉስ የሆነው አባት ሲያልፍ ለልጁ ንግስናውን አውርሶ የሚያስቀጥለው ነው፡፡ ንጉሱ ሲሞት ንግስናውን ወይም ስልጣኑን የሚያወርሰው ልጅ እንደሌላው ባህል ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ አልያም ደግሞ ለንግስናው ለመረጠው ልጁ አይደለም፡፡ የንጉሱ ልጅ ሲወለድ በምጥ ላይ ያለችው የንጉሱ ሚስት በእጅዋ የተለያየ እህል ወይም ጥራጥሬ ትጨብጣለች። በባህሉም መሰረት እህል ተጨብጦ የተወለደው ልጅ ንግስናውን ይረከባል። ንጉስ የምትወልደው እንስት ከማልቻ ጎሳ የተገኘች መሆን አለባት። ንጉስ ለሚሆነው ሰው የሚታጭለት ሚስት ከማልቻ ጎሳ እንዲሁም ባለሙያና ቆንጆ ኮረዳ መሆን ይጠበቅባታል።
በብሄረሰቡ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ቀጥተኛ ባይሆንም ንጉሱን በመደገፍ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የንጉሱ ሚስት ንጉሱ ድንገት ከሞተና የንጉሱ ልጅ ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ከሆነ ለአቅመ አዳም እሲኪደርስ ብሄረሰቡን የመምራት ስልጣን አላት፡፡
የንግስና ስነ ስርዓት
ንጉሱ ከማልቻ ጎሳ ካገባት ሚስቱ የወለደው ልጁን እሱ ሲሞት የንግስና ቦታውን ያወርሰዋል፡፡ ንጉሱ ልጁን ከመሞቱ አስቀድሞ ለንግስና ያጨዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሱና ለንግስና የታጨው ልጅ ከእጩነት በኋላ ከንጉሱ ጋር መተያየትና አንድ ላይ መኖር የለባቸውም በሞስዬዎች ሥርዓት፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከተለያዩ ንጉሱ ቶሎ ይሞታል ተብሎ በብሄረሰቡ አበላት ስለሚታመን ነው፡፡ ለንግስና ከታጨ በኋላ ከአካባቢው ርቆና ተደብቆ ንጉሱ (አባቱ) እስኪሞት ድረስ ይጠባበቃል፡፡
ለንግስና የታጨው ልጅ ዳማው (ንጉሱ) ከሞተ በኋላ ከተደበቀበት ያስወጡትና በአካባቢው ወደሚገኘው ላባሼ ወንዝ ወስደው ገላውን ያጥቡታል፡፡ ከዚያም ወደ ‹‹በጃሌ›› (ደንብ ማስፈጸሚያ ቤት) ይወስዱታል፡፡ በደንብ ማስፈጸሚያው አካባቢ የተዘጋጀ ለንጉስ መቀመጫነት የሚያገለግል በአካባቢው አጠራር ‹‹በዳኤ ዳማ›› የተሰኘ ከድንጋይ ተጠርቦ በተዘጋጀ የንጉስ መቀመጫ ላይ ያስቀምጡታል፡፡ ህዝቡም ወደ ንጉሱ እየቀረበየንጉሱ ስልጣንና እድሜ እንዲረዝም ፀሎት ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ንጉሱ በፍትሀዊነት እዲያስተዳድር ‹‹ወዜ…ወዜ…›› እያሉ ይማጸኑታል፡፡
የንጉሱ ቤተሰብ መጠሪያ ‹‹ኮዋኔ›› የሚባል ሲሆን፤ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በንጉሱ ሹመት ጊዜ ቦታው ላይ በመገኘት ለንጉሱ ክብርና ንጉስነቱን በክብር መቀበላቸው ለመግለጽ ወንድ በግ ያርዱለታል፡፡ የንጉሱ የንግስና ሥርዓት እንዲያስፈጽሙ የተመረጡ የአካባቢው ሽማግሌዎች ከታረደው በግ ደም በመውሰድ በዳኤ ዳማ (የንጉሱ መቀመጫ) አጠገብ የሚገኝ ድንጋይ ላይ ይቀቡታል፡፡ ይህም የንግስና ሥርዓቱ ማጽደቂያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ንጉሱም የተቀባውን ደም ተረማምዶ ወደ ንጉስ መኖሪያ ያቀናል፡፡ የንጉሱ መኖሪያ ቤት ከሌሎች የብሄረሰቡ መኖሪያዎች ለየት ተደርጎ የሚታነጽ ሲሆን፤ ምሶሶው ጫፍ ላይ የሰጎን እንቁላል ይቀመጥበታል፡፡ ይህም የንጉሱ ልዕልናና ትልቅነት ይገለጽበታል፡፡ መኖሪያ ቤቱ ‹‹ካያ›› ይባላል፡፡
የንጉሱ ስልጣንና ተግባር
ንጉሱ በብሄረሰቡ የላኛው ወይም የበላይ ስልጣን ባለቤት ሲሆን፤ ህዝቡን የመምራትና የማስተዳደር ሌሎች ከሱ ስር ያሉ ሁለት የስልጣን እርከኖች የማዘዝ፣ የመምራትና ከባድ ወንጀሎችና ግጭቶች ሲኖሩ ውሳኔ የማስተላለፍ ስልጣን አለው፡፡ ሁሉም የሙስዬ ብሄረሰብ አባላት ንጉሱን የመታዘዝ፣ የማክበርና ንግስናውን የመቀበል ግዴታ አለባቸው፡፡
በብሄረሰቡ ልማድ መሰረት ንጉስ በህይወት እያለ ብቻ ሳይሆን ከሞተም በኋላ ይከበራል፤ ይወደሳልም፡፡ ለክብሩም የተቀበረበት ስፍራም ሰፊ ተደርጎ ይታጠርና ማንም በአጥር ግቢው ገብቶ ዛፍ ወይም ሌላ ዕፅዋት ሳይነካ አካባቢው ጥብቅ ሆኖ ለዘመናት ይቆያል፡፡ መካነ መቃብር ስፍራ እንዲሆን ከተከለለው አጥር ግቢ የዛፍ ቅርንጫፍ ወይም ሌላ ንብረት ወደ ውጪ ቢወድቅ እንኳን በመንገዱ ያለፈ ሰው አንስቶ ወደ ውስጥ ይጥላል እንጂ መጠቀምም ሆነ መውሰድ የተከለከለ ነው፡፡ ምክንያቱም የንጉሱን ክብር መንካት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
በጥንት ዘመን በጦር ሜዳ ጀግንነቱና በአስተዳደራዊ ጥበቡ በብሄረሰቡ ተወዳሽ ለነበረው ንጉስ ካርሞ (ዳማ ካርሞ) የተቀበረበት ሰፊ የመቃብር ስፍራ ዛሬ ድረስ በቡሳ ቀላና ባሶ ቀበሌዎች መካከል በጣም ሰፊ በሆነ ይዞታ ጥቅጥቅ ደንና እድሜ ጠገብ ዛፎች ይገኙበታል፡፡ ይህ ለዘመናት ፈጽሞ ሳይነካ የቆየው ጥብቅ ደን ለአካባቢው የአየር ንብረት መጠበቅ ጉልህ አስተዋጾኦ አበርክቷል፡፡
ማካ (ሁለተኛው የሥጣን እርከን)
በሞስዬ ብሄረሰብ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ሁለተኛው የሥልጣን እርከን ‹‹ማካ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ከዘጠኙም ጎሳ አንድ ማካ የሚመረጥበትና ጎሳውን የሚመራው የሥልጣን ክፍል ነው፡፡ የሚመረጠውም በህዝብ ድምጽ ነው፡፡ ይህ የሞስዬ ብሄረሰብ የምርጫ ሥርዓት ለዘመናዊ ውክልና ምርጫ መሰረት የጣለ ነው፡፡ ለዚህ መስፈርቱ በጦር ሜዳ ውሎው በጀግንነት የታወቀ፣ በማህበራዊ ህይወቱ ከሰዎች ጋር ጥሩ መስተጋብር ያለው፣ በህብረተሰቡ የሚከበርና የአመራር ብቃት ያለው መሆን አለበት፡፡
የማካ ሥልጣንና ሃላፊነት በዋናነት ንጉሱን (ዳማን) ከህዝቡ ጋር የማገናኘት፣ የተወከለበትን ጎሳ በበላይነት የመምራትና የማስተዳደር፣ ወደ ንጉሱ የማይደርሱና ከታችኛው የስልጣን ክፍል (ፖልዓ) አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን መምራትና ውሳኔ መስጠት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ከንጉሱ መልዕክቶችን እየተቀበለ ወደ ፖልዓ በልዩ ልዩ ዘዴዎች የሚያስተላልፈውም እርሱ ነው፡፡ ለአብነት እንደ መግባቢያ ተለምዶ የነበረው የተቆጣጠረ ገመድ በመለዋወጥ እና ገመዱ የተላከለት ማካ ወይም ከሱ ቀጥሎ ያለው ፖልዓ ቋጠሮውን በመፍታት ንጉሱ ህዝቡን ሰብስቦ ማወያየት የሚፈልግበት ጊዜ በእርግጠኝነት የማወቅ ልምድ ነበራቸው፡፡
ፖልዓ (የመንደር ተቆጣጣሪ)
በብሄረሰቡ የመጨረሻው የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኘው ደግሞ ፖልዓ ይባላል፡፡ መንደሮችን (ጎጦችን) የመምራትና የማስተዳደር፣ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠር ቅራኔና ግጭት እየተከታተሉ የመፍታት፣ የሽምግልና ስራዎችን የመስራት ሃላፊነት የተሰጠው ነው፡፡ ከህዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ወደ ላይኛው የስልጣን እርከን (ማካ) መረጃዎችን በማድረስ ከላይ ከንጉሱ ዳማና ከማካ የሚተላለፍ ትዕዛዝና አዋጅን ወደ ህዝቡ በቀጥታ በማድረስ የነቃ ሳትፎ ያደርጋል፡፡
ብሄረሰቡ በሸንጎ መልክ የፍትህ ሥርዓት የሚካሄድበት ባህላዊ አደባባይ ሌላው መገለጫው ነው፡፡ አደባባዩም በተለያዩ የአስተዳደር ቀበሌዎች የሚነሱ ግጭቶች ይዳኙበታል፤ ማህበራዊ ጉዳዮች ይመከሩበታል፡፡ በልዩ መልክ ክብ ተደርገው የታነጹ አደባባዮች በብሄረሰቡ አጠራር ‹‹ሞራ›› የሚባሉ ሲሆን፤ በብሄረሰቡ አባላት ጥብቅ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ ከንጉሱ ዳማ ጀምሮ እስከ ፖልዓ ድረስ ፍትህ የሚዳኘው እዚህ ባህላዊ አደባባይ ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011
ተገኝ ብሩ