ኢትዮጵያ ሰፊ ሀብት አላት። በዓለም ማህረሰብ ጭምር እውቅና የተቸራቸው የቱሪስት መስህቦች፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች፣ ለበርካታ አመታት የዘለቁ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች፣ ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። ነገር ግን እነዚህን ሃብቶች የምጠቀምበት መንገድና የሃብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ አለመሆን በርካታ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች እንዲኖሩ አስገድዷል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌሎች አገራት የምንሰማቸው የራስ ወዳድነትና ግለኝነት ባህርያት ተዛምቶብን ከመተዛዘን ይልቅ መጠፋፋት፣ ሌሎችን ከመርዳት ይልቅ ለራስ ከልክ ያለፈ ህይወት እስከመኖር የደረስንባቸው አጋጣሚዎችን እንመለከታለን። ለዚህም አንዱ ማሳያ በድህነት በምትታወቀው አገራችን ውስጥ የምናያቸው ከልክ ያለፉ የቅንጦት እቃዎችና ከልክ ያለፈ የአኗኗር ዘይቤ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የሚላስ የሚቀመስ ያጡ በርካታ ህጻናትና አረጋውያን እና ከ80 ሺህ የሚልቁ የጎዳና ተዳዳሪዎች ባሉባት አገራችን በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት ቅንጡ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ የሚያስገቡ፤ አንድ ውስኪ እስከ 85 ሺህ ብር የሚሸጥበት፣ ለልደት አስከ 200 ሺህ ብር ለልደት የሚመደብበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ስንሰማ ምን ያህል በህይወት ተቃርኖ ውስጥ እንደምንኖር ያመላክታል።
በዓለም ላይ በስልጣኔያቸው ቀዳሚ የነበሩት ግሪኮች በዘመናቸው ከሚመሩባቸው የህይወት መርሆዎቻቸው ውስጥ ግንባር ቀደሙ “በልክ መኖር” የሚል ነበር። ይህ ማለት ሃብት ማፍራትን ወይም ባለፀግነትን መከልከል አይደለም። ይልቁንም ያለንን ሃብት በአግባቡ መጠቀምን፣ ከተረፈም ለሌላቸው ማካፈልንና ለመዝናናትም ሆነ ለደስታ ከልክ በላይ እንዳንሄድ የሚያሳስብ ነው።
ነገር ግን የመረዳዳትም ሆነ በልክ የመኖር ባህሎች ዛሬም እንዳሉ የሚያሳዩ ተግባራት እንዳልጠፉ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በተለይ በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን።
ለአብነትም በአገራችን በእርጅና፣ በበሽታና በአዕምሮ ህመም ምክንያት ረጂ አጥተው ለጎዳና ህይወት የተዳረጉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ዋስትና መሆን የቻሉት መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል፣ ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እና ሌሎች በርካታ በህሊናቸው በተገዙ ዜጎች የሚካዱ የበጎ ስራዎች ማሳያዎች ናቸው።
ከዚህም ባሻገር በአገራችን በርካታ ወጣቶች ያለምንም ክፍያ በጎዳና የወደቁና አቅመ ደካማ እናቶችና አባቶችን በመርዳት፣ ገላቸውን በማጠብና ልብስ በማልበስ፣ የፈራረሱ ቤታቸውን በመጠገን፣ እንዲሁም ለምነው በማብላት የበጎ አድራጎት ስራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ወጣቶችም አሉ። ለዚህም በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ ጎጃም በረንዳ አካባቢ የተሰማሩት ወጣቶች የበጎ አድራት ተግባር አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
በቅርቡ የተቋቋመው ባቡል ኸይር በሚል የሚታወቀውና በየቀኑ እስከ ስድስት መቶ ለሚደርሱ ችግረኛ ወገኖች ቁርስና ምሳ የመመገብ የበጎነት ስራ ላይ ትልቅ አሻራ እያሳረፈ ያለው ድርጅትም ሌላው የበጎነት ተምሳሌት ነው። ይህ ተቋም በተለይ በኮሮና ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ደራሽ በመሆን እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ትልቅ የኢትዮጵያዊነት ተምሳሌት ነውና ምስጋና ይገባዋል።
በሌላ በኩል አገራችን የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉ ዜጎች በጋራ የሚኖሩባት አገር ናት። በእያንዳንዱ ሐይማኖት ውስጥ ደግሞ መረዳዳት አንዱ የእምነቱ አስተምህሮ ነው።
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓልም ለመረዳዳት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ በዓል ነው። የእርድ በዓል እየተባለ በሚጠራው በዚህ በዓል ወቅት እያንዳንዱ የእምነቱ ተከታይ በዓሉን የሚያሳልፈው ከራሱና ከቤተሰቡ ጋር ብቻ ሳይሆን የተቸገሩትንም በመርዳትና ደስታቸውን በመጋራት ነው።
በአረፋ ወቅት የሚደረገው እርድ ሁሉ በሶስት ቦታ እኩል እንደሚከፈል የእምነቱ አባቶች ይናገራሉ። ከዚያ በኋላ አንዱ ለቤተሰብ፤ አንዱ ለጎረቤት ሌላኛው ደግሞ ለድሆች ይሰጣል። በዚህም መሰረት በዓሉን ብቻ ሳይሆን የበዓሉን ሰሞንም ሁሉም በእኩልነት የሚያሳልፍበት ትልቅ የመረዳዳት ተምሳሌት ነው።
ዛሬ አንተ የዚህ አካባቢ አይደለህምና ውጣ ሳይሆን አቅፎና ደግፎ የሚይዝና የሚንከባከብ ማህበረሰብ ያስፈልገናል። ከአቅም በላይ በልቶ በቁንጣን የሚጨናነቅ ሳይሆን ካለው ላይ ቀንሶ ያጡትን የሚታደግ ዜጋ ያስፈልገናል። በወሬ ሳይሆን በስራ የሚያምን ዜጋ ያስፈልገናል። ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን አሻግሮ የሚያይና ሉሎችንም አቅፎ ለመሻገር የሚስችል ራዕይ የሰነቀ ዜጋ ያስፈልገናል። ይህ ሲሆን ከዛሬ ይልቅ ነገ የተሻለ ቀን እንደሚሆን አይጠረጠርም !
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012