በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው የተቃውሞ ሰልፍ ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ከአንድ ወር በፊት የዳቦ፣ የነዳጅና የሸቀጣሸቀጥ ወጋ መጨመርን ምክንያት አድርጎ የተቀሰቀሰው ይህ የተቃውሞ ሰልፍ በጥቂት ግዜ ውስጥ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ከስልጣን ይልቀቁ ወደሚል ጥያቄ መቀየሩ ይታወሳል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከሶስት ሳምንታት በፊት በመላ ሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማብረድ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ መልዕክት ቢያስተላልፉም ተቃዋሚዎቹ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዚህም ፖሊስ በተቃዋሚዎቹ ላይ በሚወስደው እርምጃ የሟቾቹ ቁጥር እጨመረ፤ ተቃውሞውም እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ በዚህ ሁለት ቀን በተለያዩ ከተሞች የአልበሽርን መንግሥት በመቃወም ላይ ባሉ ሰልፈኞች ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከሞቱት ሰዎች መካከል አንድ የሃያ አራት ዓመት ወጣትና አንድ ጎልማሳ ይገኙበታል፡፡
የሟቹ ጎልማሳ ልጅ የህያ ማዊያ በሽር ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደገለጸው፤ አባቴ የተገደለው የመንግሥት ታጣቂ ሃይሎች የሚያባርሯቸው ተቃዋሚዎች ሸሽተው እቤቱ ለመግባት በሞከሩበት ወቅት ነው፡፡ ሁኔታውንም እንዲህ ያስረዳል አባቱ ከጸሎት ቤት ወደ ቤቱ እየገባ ሳለ የመንግሥት ታጣቂዎች የሚያባርሯቸው ተቃዋሚዎች ከኋላው ተከትለውት ወደ እቤት ውስጥ ይገባሉ፡፡ እነሱን ለማዳን በሩን ዘግቶ እንደተቀመጠ በበሩ ስር በተተኮሰ ጥይት መገደሉን አስረድቷል፡፡ አባቱ ለተቃውሞ እንዳልወጣ የሚናገረው ወጣቱ እራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ተከትለውት ወደ ቤቱ የገቡትንም ሰዎች በወቅቱ ውጡ ማለት እንደማይችል ተናግሯል፡፡ ከበሩ ላይ ትንሽ ግርግር ተፈጠረ ፤ ወዲያውም የጥይት ድምጽ ተሰማ፤ መጨረሻ ላይ አባቴ መሬት ላይ ተዘርሮ አየሁት ይላል፡፡
የሟቹ ሴት ልጅ ሰሀም ማዊያ በሽር በበኩሏ ‹‹እኔ አሁን የምፈልገው አባቴን የቀሙኝ የሱዳን መንግሥት ታጣቂ ሃይሎች ለፍርድ እንዲቀርቡና ፍትህም እንዳገኝ ብቻ ነው›› ብላለች፡፡
የአልጀዚራው ጋዜጠኛ ሞሀመድ ቫል ከካርቱም ለአልጀዚራ ባስተላለፈው መልዕክት ባለፈው ሀሙስ ብቻ አስር በሚሆኑ የሀገሪቱ ከተሞች ተቃውሞ እንደነበር ዘግቧል፡፡ ተቃውሞው ቀደም ሲል በካርቱም ከተካሄዱት ሰልፎች በጣም ጠንከር ያለ እንደነበር እና የሱዳን የወደብ ከተማን ጨምሮ በትልልቅ ከተሞችና በገጠር መንደሮችም ተመሳሳይ ሁኔታ መታየቱን ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ተቃውሞው መላ ሀገሪቱን እያዳረሰ እና እየጠነከረ መምጣቱን ተናግሯል፡፡
በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በተለይም በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገም ይገኛል፡፡ መንግሥት እስከ አሁን የተቃውሞው አቀንቃኞች ናቸው ያላቸውን ቁጥራቸው ስምንት መቶ የሚደርስ ግለሰቦችን ያሰረ ሲሆን፤ ከነዚህም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የህግ ባለሙያዎች እና ግንባር ቀደም የተባሉ ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡
ምንም እንኳን የሱዳን ባለስልጣናት ተቃውሞውን ለማክሰም የተለያዩ የሃይል እርምጃዎችን ቢጠቀሙና የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ቢያወጡም ይህ በኑሮ ውድነት ምክንያት የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ የሃያ ዘጠኝ ዓመት እድሜ ያስቆጠረውን የአልበሽርን ወንበር በማነቃነቀና ባለስልጣናቱንም አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡
የመብት ተሟጋቾች ሕጻናትን ጨምሮ እስከ አሁን በግጭቱ የሞቱት ሰዎች ብዛት አርባ እንደሚደርስ ሲያስረዱ የመንግሥት መርማሪ ኮሚቴ ቃል አቀባይ አሚር ሞሀመድ ኢብራሂም ከታህሳስ አጋማሽ ጀምሮ ይህ ሰው እስከ ተገደለበት ግዜ ድረስ የሟቾቹ ቁጥር ወደ ሃያ ዘጠኝ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
ኢያሱ መሰለ