የዘንድሮ ትምህርት በኮሮና ምክንያት ከተቋረጠ ከአራት ወራት በላይ ተቆጥረዋል። ተማሪዎችም በቤታቸው ውስጥ ሆነው የቀረውን ትምህርት በማጠናቀቅ ለቀጣዩ ጊዜ እንዲዘጋጁ መንግስት ከብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች ውጭ ወደቀጣዩ ክፍል እንዲዛወሩም አድርጓል። በመሆኑም በቀጣይ ትምህርት ሲከፈት ተማሪዎች የበለጠ ትጋት እንደሚጠበቅባቸው ሊረዱ ይገባል።
በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ከማል ሙሰማ እንደሚሉት በአናጺነትና በረዳት ግንበኛነት ሁለት ልጆቻቸውን በማስተማር ላይ ይገኛሉ። አንዱ ሰባተኛ ክፍል ሲሆን ሌላኛው 12ኛ ክፍል ይማሩ ነበር ትምህርት እስከ ቆመበት ጊዜ ድረስ። በኮቪዲ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት መቋረጡ በጣም ትክክል ነበር። ምክንያቱም ወላጆችን ከስጋት ልጆችንም ከወረርሽኙ መከላከል እንዲቻል አድርጓልና።
ትምህርት ቢዘጋም ተማሪዎች ስራ እንዳይፈቱ መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ለማስተማር ሲሞክር ነበር የሚሉት አቶ ከማል ነገር ግን በቂና የተሳካ ነበር ብሎ መውሰድ ያስቸግራል ይላሉ። ልጆች ለማጥናትና የቤት ስራዎችን ለመስራት ሲሞክሩ እንኳን ለእነሱ ለወላጆችም ደስ ያሰኝ ነበር። ይሁን እንጂ ልጆቼም ሆነ እኔ ስናስብ የነበረው የዘንድሮው የትምህርት ዘመን ሊደገም እንደሚችል ነበር።
ሁሉም ተማሪዎች ወደሚቀጥለው ክፍል እንዲዛወሩ መወሰኑን ከሰፈር ነዋሪዎች(ከጎረቤት) መስማታቸውን የሚናገሩት አቶ ከማል፤ መረጃውን እንደሰሙ ማጣራታቸውንም ተናግረዋል። “በየትኛውም አካባቢ በየትኛውም የስራ አይነት በወረርሽኙ የተነሳ እንደልብ መስራት እየተቻለ አይደለም። በዚህ የተነሳ ገቢም ቀንሷል። ለሚማሩ ልጆቼ የመንግስት ድጋፍ እንዳለ ቢሆንም የአንድ አመት የትምህርት ቤት ወጪ ድጋሚ እንዳለብኝ እያሰብኩ ነበር። ብዙ ሰዎች የሚቸገሩ ይኖራሉ።ተማሪዎችም በራሱ ወደሚቀጥለው ክፍል አልፋችኋል ሲባሉ ሞራላቸው በጣም ነው የተነቃቃው። ስለዚህ በዚህ ውሳኔ የማይደሰት
ብዬ አላስብም። ነገር ግን ክረምቱን እንዲያጠኑ ማድረግ አስፈላጊ ነው። 12ኛ ክፍል የሚማረው ልጄ በኢንተርኔት ፈተና አለ ተብሎ አሁንም በማጥናት ላይ ነው። በአጠቃላይ በመንግስት ውሳኔ ተደስቻለሁ።” ይላሉ።
የኢቢሳ የኤስ ኦ ኤስ የመንግስት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ ተሻለ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ችግሮች ቢኖሩም ውሳኔው በጎ ጎኑ እንደሚያመዝን ይናገራሉ። ወደ አንድ ውሳኔ መምጣቱ ተገቢ ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ይሄ የተለየም ብቻ ሳይሆን አዲስ ውሳኔ ነው። የገጠሙት ችግሮች ከግንዛቤ ውስጥ ገብተዋል በውሳኔው። የራሱ የሆኑ ችግሮችም አሉት። ያልተሸፈኑ የትምህርት አይነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በጎ ጎኑ ያመዝናል ባይ ናቸው።
የመማር ማስተማሩ ሂደት ምን እንደሚመስል ሲያብራሩም፤ ይሄ ያልተጠበቀ ክስተት ነው። የተለያዩ ወርክ ሽቶችን ቢያንስ ለስድስተኛ ጊዜ በቴሌ ግራም ለተማሪዎች መላካቸውን ይገልጻሉ። ያ ሲደረግ እንደአገርም ያልተለመደ ክስተት በመሆኑ ከወላጆች ጋር በመደዋወል ጭምር የተሰራ እንደሆነ ያስረዳሉ። የቴሌግራም ተጠቃሚ ላልሆኑት ተማሪዎች ተለይቶ እንዲባዛላቸው በማድረግ ከወረርሽኙ የመከላከያ ስልቶችን በተከተለ መንገድ እንዲደርሳቸውና ሰርተው እንዲመልሱ ሲደረጉ የነበሩ አሰራሮች መኖራቸውንም አንስተዋል። በዚህ መንገድ ለማስተማር ጥረት የተደረገ ሲሆን ፈተናውንም በቴሌግራም ነው የተፈተኑት። ፕሮግራም ወጥቶ ወላጆች ኃላፊነት እንዲወስዱ በማድረግ የተሰራ ነው። ምንድን ነው የሚፈተኑት?፣መቼ ነው የሚፈተኑት? እና እንዴት ነው የሚፈተኑት የሚሉ ጉዳዮችን በቅደም ተከተል አዘጋጅቶ በማሳወቅ ወላጆች ኃላፊነት እንዲወስዱ ተደርጎ ነው የተከናወነው። ፈተናውን ተፈትነው እንደጨረሱ በአስር ደቂቃ ውስጥ በፎቶ አንስተው ምላሽ እንዲሰጡ በማድረግ የተከናወነ ነበር። እንዲሁ ከሚቀር የተሻለ መፍትሄና ጥረት ተደርጎ የሚወሰድ እንጂ ተመራጭ አለመሆኑንም ርዕሰ መምህሩ አብራርተዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ከ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በስተቀር ሌሎቹ ወደ ቀጣዩ ክፍል እንዲዛወሩ የወሰነበትን
ምክንያት የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ሀረጓ ማሞ እንዳሉት፤ በዋናነት ተማሪዎችን ለማበረታታት ታስቦ የተደረገ ነው። በቤት መቀመጥ በራሱ የሚፈጥረው የስነልቦና ጫና በመኖሩ ተማሪዎች ከዚህ ችግር ይላቀቃሉ። ወደ ሚቀጥለው ክፍል ተዛውራችኋል ሲባሉ እና በሚቀጥለው ዓመት በነበራችሁበት ነው የምትቀጥሉት ተብሎ ሲለጠፍ ሁለቱ በተማሪዎች ስነልቦና ላይ የሚፈጥረው ጫና ይለያያል። ስለዚህ ወደሚቀጥለው ክፍል ተሸጋግራችሁ ነው ወደትምህርት ቤት የምትመለሱት ተብሎ መገለጹ በራሱ በቀጣይ ትምህርት ቤት ገብተው በሚማሩበት ወቅት ከፍተኛ ጉጉት እንደሚፈጥርባቸው ጭምር ታሳቢ ተደርጎ መሰራቱን ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ሀረጓ እንደሚሉት ከትምህርት ውጪ ላለ ሰው ከባድ ቢመስልም ተማሪዎችን በአንድ ወር ተኩል በሚሰጥ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት የባከነውን የትምህርት ጊዜ ማካካስ ይቻላል ይላሉ።
በአንድ ወር ተኩል እንዲዘጋጁ የተፈለገው የስምንተኛ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኞችን የሚመለከት እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ትምህርቱን የሚዘጋጁት ተማሪዎች ብቻቸውን ሳይሆን መምህራን ትኩረት አድርገው ተማሪዎቻቸው ምን ማወቅ እንደሚጠበቅባቸው በመለየት በየትኞቹ ይዘቶች ሊተኮር እንደሚገባ ወስነው ዝግጅት የሚያደርጉበት ነው። በዚህ መንገድ መምህራን ለተማሪዎቻቸው መሰረታዊ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይኖርባቸዋል። በሰላሙ ጊዜም ቢሆን በበጎ ፈቃደኝነት ለተማሪዎች ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መምህራን አሉ። ያንን ተሞክሮ ነው ለዚህ የችግር ወቅትም በመፍትሄነት የሚተገብሩት። በአጭር ጊዜ ካሉበት የክፍል ደረጃ አኳያ ምን መሰረታዊ እውቀት መጨበጥ አለባቸው በሚል በተገቢው ታስቦበት እንደሚሰራ ተናረዋል።
በኦንላይን ይሰጣል የተባለው የ12ኛ ክፍል ፈተናስ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል? ሊሰጥ የታሰበው በተመሳሳይ ጊዜ ነው? የኮምፒውተር አቅርቦቱስ በበቂ ሁኔታ አለ ወይ?፣የተማሪዎችስ የመጠቀም ችሎታ እንዴት ታይቶ ነው? በሚል ለቀረበላቸው
ጥያቄ ወይዘሮ ሀረጓ ሲመልሱ፤ የኢንተርኔት አቅርቦቱ በዋናነት የሚታሰብበት ሲሆን ለዚህ አሰራር ያስፈልጋሉ የተባሉ ዝግጅቶች ሁሉ እየተደረጉ ስለመሆናቸው ገልጸዋል። በየክልሎች አመቺ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ የመፈተኛ ጣቢያዎች ተለይተዋል። በተለዩት ጣቢያዎች አማካኝነት ተማሪዎች በየጣቢያዎች ተገኝተው የኦንላይን ፈተና ስርዓቱ ይከናወናል። ለኦን ላይን ፈተናው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራው እየተሰራ ይገኛል። በዚህ መንገድ እንጂ በቤታቸው ሆነው የሚፈተኑበት አግባብ አለመኖሩን ተናግረዋል።
በኮቪዲ 19 ምክንያት የተስተጓጎለው የትምህርት ስርዓት የአገሪቱ አቅም በፈቀደው መጠን የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ለማስቀጠል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በዚህ የተነሳም የመማር ማስተማሩ ተግባር ከነአካቴው ከሚቀር በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ መገናኛ ስልቶች እንዲከናወን ተደርጓል። በመሆኑም የስምንተኛ እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊና አገራዊ ፈተናዎች በኦንላይን በሚሰጥ ፈተና የሚቋጭ ሲሆን በሌሎቹ ክፍሎች በመማር ላይ የነበሩት ግን ሁሉም ተማሪዎች ወደሚቀጥለው ክፍል ይዛወሩ ዘንድ ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ አሳልፏል።
የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችን በተመለከተም ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲዎቻቸው እንዲመለሱ በሚወሰንበት ወቅት በርካታ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ተጠቁሟል። የገጽ ለገጽ ትምህርቱ ሲጀመር በቅድሚያ የሚገቡት ተመራቂዎች እና ከአራተኛ ዓመት በላይ ያሉ ተማሪዎች እንደሚሆኑም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራትም በ2012 ዓ.ም ያላጠናቀቋቸውን ቀሪ ትምህርቶች እንዲያጠናቅቁ ይደረጋል። በሁለተኛ ዙር ደግሞ ከመጀመሪያ ዓመት እስከ ሶስተኛ ዓመት የሆናቸው ተማሪዎች ገብተው እንዲማሩ ይደረጋል። ተማሪዎቹ መቼ እንደሚመለሱ ባይገለጽም ከወረርሽኙ በሚጠበቁበት አሰራር መማር ማስተማሩ በሁለት ዙር እንደሚከናወን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2012
ሙሐመድ ሁሴን