ሰላም የህጻናት መንደር የተመሰረተው በአንዲት ሀገር ወዳድ እናት እ.አ.አ በ1986 አ.ም ነበር። መስራቿ ወይዘሮ ጸሀይ ሮሽሊ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ኑሯቸው ግን በጉዲፈቻ ሊያሳድጉ ከወሰዷቸው የስዊስ ዜጎች ከሆኑት ከዴቪድ ሮሺሊ እና ከማርያ ሮሺሊ ጋር በሲውዝ ሀገር ነበር። ወይዘሮ ጸሀይ በ1977 አ.ም በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ የነበረው ድርቅ ያስከተለውን ሰቆቃ በሲውዝ አገር በቴሌቪዠን ፕሮግራም ሲተላለፍ ይመለካታሉ። የእናት ሀገር ፍቅር አንጀታቸውን አላስችል ሲላቸው ነገሩን በአይን ለማየትና አቅም የፈቀደውን በመርዳት ለወገን ደራሽ ለመሆን ወደትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ያመራሉ። ኢትዮጵያም ደርሰው ወደ ሰሜኑ ክፍል በማቅናት ያለውን ነገር ከዜናና ከቴሌቪዥን ፕሮግራም ባለፈ በአይናቸው ተመልክተው የበለጠ ልባቸው ይነካል። እናም ወደ መኖሪያ ሀገራቸው በመመለስ በዚህ ጉዳይ ላይ በተለይም ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን ለመታደግ እንደ ሚሰሩ ለራሳቸው ቃል ይገባሉ። ሲውዝ ሲመለሱም እናትና አባታቸውን ብሎም እህትና ወንድሞቻቸውን አነጋግረው እነሱም ፈቃደኛ ስለሆኑላቸው እርዳታ ወደማሰባሰቡ ይገቡና እ.አ.አ በ1985 አ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለመንግስት ስለስራቸው ነግረው የቦታ ጥያቄ ያቀርባሉ። መንግስትም ቀና ሀሳባቸውን በመገንዝብ ሰላሳ ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ይሰጣቸዋል እሳቸውም ቀድመው ተዘጋጅተው ስለነበር በዛው አመት የህጻናት መኖሪያ መንደር በማስገንባት ሰላሳ ሁለት በድርቁ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በማስመጣት በቀጣዩ አመት ዛሬ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገውን ፕሮጀክት ለመጀመር ይበቃሉ።
እናት ሂሩት ከበደ በሰላም የህፃናት መንደር ለአስራ ሶስት አመታት ያህለ አገልገለዋል። የመጀመሪያዎቹን ሰባት አመታት በትመህርት ቤት ወስጥ ከሰሩ በኋላ አሁን በሚሰሩበት የስራ መስክ በእናትነት ወደሌላ ድርጅት በመሄድ ሲሰሩ ይቆያሉ። ከስድስት አመት በፊት ደግሞ የቀድሞ ድርጅታቸው ሰላም የህጻናት መንደር ለእናትነት ያወጣውን ማስታወቂያ ተመልክተው በመወዳደር በተሻለ ነጥብ ለሁለተኛ ግዜ ተቋሙን ህይወት ይቀላቀላሉ። እናት ሂሩት ያለፉትን ስድስት አመታት ከአስራ ሁለት ልጆቻቸው ጋር ያሳለፉትን እንዲህ ያስታውሱታል።
እኔ ለእናትነት ብቻ የተፈጠርኩ ይመስለኛል። የአብራኬ ክፋይ የሆኑ ሶስት ልጆችና ሁለት የልጅ ልጆች አሉኝ እነዚህን ቤተሰቦቼን ያለፉትን ስድስት አመታት የማገኛቸው ከሳምንት አንድ ቀን ብቻ ነው። ነገር ግን አንድም ቀን ከእነሱ የተለየሁ ሆኜ ተሰምቶኝ አላውቅም። ዛሬ ስንት ልጆች አሉሽ ስባል መልሴ ብዙ ናቸው የሚል ነው በምንም የማልለያቸው እጅግ የሚያሳሱኝ አስራ አምስት ልጆችና ሁለት የልጅ ልጆችን እንዳሉኝ ነው የማውቀው። ድሮ ለልጆቼ እንደማደርገው ሁሉ ዛሬም የየለት ተግባሬ እንደዛው ነው ጠዋት ተነስቼ ልጆች ተነስተው እንዲተጣጠቡና እንዲለባብሱ እቀሰቅሳለሁ እነሱ እስኪነሱ የምሳ እቃቸውንና ቦርሳቸውን አዘጋጃለሁ። ወደ ትምህርት ቤት ከሄዱ በኋላ የቤት ማዘጋጀቱ ስራ ይቀጥላል እሱን እንዳጠናቀኩ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ የሚበሉትን ምግብ አቀራርቤ እጠብቃቸዋለሁ። እንደ መጡም የደንብ ልብሳቸውን ቀይረው አብረን ገበታ እንቀርብና ስንጨርስ እነሱ ወጥተው የሚጫወቱበት የእረፍት ሰዓት ይሆናል።
ምሳ ስንበላም ሆነ በእረፍት ሰዓታቸው የቀን ውሏቸውን ምንም ሳያስቀሩ ያጫውቱኛል እኔም ማረም ያለባቸውን እንዲያርሙ መቀጠል ያለባቸውን እንዲቀጥሉ ስመክራቸው እቆያለሁ። አመሻሽ ላይ ተቋሙ የቀጠራቸው አስጠኚዎች ስለሚመጡና ስለሚያስጠኗቸው እኔ እራትና ወደ ማዘጋጀቱ እዞራለሁ። ከራት መልስ ሁሌም ስንጸልይ እንቆይና ከጸሎት በኋላ በሶፋ ዙሪያ ተሰብስበን ሳሎን ውስጥ ቴሌቪዠን እንመለከታለን። እያንዳንዱን ፕሮግራም አብረን እናያለን ባየነውም ላይም እንወያያለን እኔም እንደእናት በመገሰጽ መምከር ብሎም በማስተማር ስንሳሳቅ እናመሻለን። አንዳንድ ቀን ደግሞ የትምህርት ቤት ደብተራቸው ወላጅ እንዲያየው ከታዘዘ እሱን አይቼ ፈርሜ አስተካክላለሁ።በዚህ ሁላ ሂደት ግን ስራዎችን የምሰራው ብቻዩን አይደለም ትልልቆቹ ልጆች የታናናሾቻቻውን የቤት ስራ በማየትና በማሰራት ብሎም አልጋቸውን በማነጠፍ በማጫወትና በመቆጣጠር ሁሌም ከጎኔ ናቸው። ከትምህርት ቤት መልስ በእረፍት ሰዓታቸውና ጠዋት ጠዋት ስፖርት ይሰራሉ እኔ ስፖርት የሚሰራና ምግብ ደፍሮ የሚበላ ልጅ ጤነኛና ደስተኛ እንደሚሆን ስለማውቅ ሁሌም አበረታታቸዋለሁ።
ዛሬ ልጆቼ ምን እንደሚያስቡ ምን እንደሚፈለጉ ፈጥኜ እረዳቸዋለሁ። እንኳን የእኔን ልጆች ጎረቤት ያሉትንና አክስት የሆንኳቸውንም በደንብ ነው የማውቃቸው ምን እንደሚፈልጉም እረዳለሁ። እነሱም ከእኔ የሚሸሽጉት ነገር የላቸውም ሌላው ቀርቶ የስጋ ልጆቼ ደፍረው የማይጠይቁኝን ሳይቀር ይጠይቁኛል። እኔም መድረስ ያለባቸው ጥሩ ቦታ እንዲደርሱ ስለምፈልግ የማወቀውን ሁሉ ያለሰስት እነግራቸዋለሁ ለልጆቼ የማደርገውን አደርግላቸዋለሁ የምላቸውን እላቸዋለሁ። በተለይ ለአቅመ ሄዋንና ለአቅመ አዳም ከደረሱት ጋር የበለጠ እንቀራረባለን የማቀርባቸው የማዋራቸውና የማዳምጣቸው እንደ አንድ የእድሜ እኩያቸው ሆኜ ነው።በማንኛውም ሰዓት ፊታቸውን አይቼ የጎደለ ነገር ካለ የደበራቸውም፤ ያመማቸውም ከሆነ በቀላሉ እረዳቸዋለሁ አንድ ልጅ ካተኮሰው ካመመው ከትንንሾቹም ሆነ ትልልቆቹ በምንም ነገር ከእኔ ተለይተው እንዲያድሩ አልፈቅድም።ከቁሳቁስ አቅርቦትም ሆነ ከህክምናው ተቋሙን ጠይቀን የሚጎልብን ነገር አለመኖሩ ደግሞ እኛም ትክክለኛ እናት እንድንሆን ረድቶናል ብዪ አስባለሁ እኛም በነጻ ነው የምንታከመው።
በአሁኑ ወቅት ከልጆቼ መካከል ሁለቱ መዋዕለ ህጻናት የሚማሩ ሲሆን አራቱ አንደኛ ክፍል ናቸው ቀሪዎቹ የስድስትኛና የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ሁሌም ትልልቆቹ የራሳቸውን የቤት ስራ ከሰሩ በኋላ ትንንሾቹን ያስጠናሉ ወደ መኝታ ሲሄዱ ደግሞ እኔ ተረት አነብላቸዋለሁ። በቤት ውስጥ ሙያቸውም ጎበዞች እንዲሆኑ እንሰራለን አመት በዓል ሲሆን ሴቶቹ ጸጉራቸውን እንዲሰሩ ወንዶቹ እንዲስተካከሉ ይደረጋል እቤትም በጉም ዶሮውም አይቀርም።ለእያንዳንዱም የበዓል ስራ ከፍ ከፍ ያሉት ከእኔ ጋር አብረው የሚሰሩ ሲሆን ትንንሾቹም አብረውን ቁጭ ብለው ያያሉ። በግቢያችን ውስጥም እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የአትክልት መደብ አላቸው ባቄላ፤ በቆሎ፤ ቆስጣ፤ አበባና የመሳሰሉትን ተክለው ሲንከባከቡ ይውላሉ። በእረፍት ቀናቸው ከቤተ ክርስቲያን መልስ ግዜአቸውን የሚያሳልፉት በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ነው። ዘወትርም ፈጣሪን በዚህ ቦታ ስላስቀመጠኝና የብዙ ልጆች እናት ስላደረገኝ እያመሰገንኩ ዛሬም ልጆቼ ምኔ ትምህርታቸውን ጨርሰው የራሳቸውን ህይወት ሲጀምሩ ባየሁ አያልኩ እናፍቃለሁ ይላሉ እናት ሂሩት።
«ሁላችንም የተቋሙ ሰራተኞች ሁለት ቤተሰብ እንዳለን ይሰማናል» የሚሉት ደግሞ በሰላም የህጻናት መንደር የህጻናት ክትትልና ድጋፍ ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው በዙ ናቸው። አቶ አስቻለው ከስራ አስኪያጅነታቸው በተጨማሪ የልጆቹም አባት ናቸው። በየቀኑም በተቋሙ ከሚሰሩት ስራ ጎን ለጎን የአባትነት ድራሻቸውን ይወጣሉ። ልጆቻቸውን በአካል ያገኛሉ፤ ውሏቸውን ይጠይቃሉ፤ ሀሳባቸውን ይሰማሉ አንዳንድ ቀን ደግሞ ከስራቸው አስቀምጠው ስለ ብዙ ነገር ያዋዩዋቸዋል። ልጆቻቸውም የከበዳቸውም ሆነ ግራ ያጋባቸው ነገር ካለ የአቶ አስቻለውን ቢሮ እንደቤታቸው ባሰኛቸው ሰዓት ይጎበኙታል። አባት አስቻለው እንዲህ አይነቱ ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን ያደረገው የተቋሙ አሰራር መሆኑን እንደሚከተለው ያብራራሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ልጆችን የሚቀበለው ከአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሲሆን የሚቀበለውም እድሜያቸው ከአራት እስከ ስድስት አመት የሆናቸውን ብቻ ነው። ነገር ግን እህትማማች፤ ወንድማማችና ወንድምና እህት ከሆኑ መለያየት ስለሌለባቸው እስከ አስር አመትም ይቀበላል። ከዚህ ውጪ አንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩም የሚቀበላቸው ልጆች አሉ። ልጆቹ ተቋሙን ከተቀላቀሉም ጀምሮ አንድ ልጅ በወላጆቹ እጅ ሲያድግ የሚያገኛቸው ነገሮች በሙሉ ተሟልተውላቸው እንዲያድጉ ይደረጋል። ለምሳሌ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆች እድሜያቸውና ጾታቸው እንደሚለያይ ሁሉ በሰላምም በእያንዳንዱ ቤት ያሉት ልጆች ይህንን ስብጥር የጠበቁ ናቸው። የምትመደብላቸውም እናት በሳምንት ውስጥ ስድስቱን ቀናት የምታሳልፈው ሙሉ ለሙሉ ከእነሱ ጋር ሲሆን በእነዚህ ግዜያትም አንዲት እናት ለልጆቿ የምታደርገውን በሙሉ ታደርጋለች። በሳምንት አንድ ቀን ለ24 ሰዓት ስትወጣም አክስታቸው (የሌላው ቤተሰብ እናት) ትተካለች። ተቋሙም የተቋሙን ሰራተኞች ፍላጎት ማሟላት የልጆቹን ደህንነት መጠበቅ መሆኑን ስለሚረዳ ለልጆቹ ብቻ ሳይሆን ለሰራተኞቹም አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
ልጆቹ የስነ ልቦናና የማህበራዊ ጉዳይ ተግዳሮት እንዳይገጥማቸውም በስነ ልቦናና በማህበራዊ ሳይንስ የተመረቁ የበቁ ባለሙያዎች አሏቸው። ለትምህርታዊ ድጋፍም በትምህርት መስክና በህጻናት አስተዳደግ የተመረቁ ባለሙያዎች ከእናቶችና አክስታቸው ጋር በመሆን በየእድሜያቸው የሚያስፈልጋቸው ነገር እንዲሟላ ያደርጉላቸዋል። እነዚህ ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉት ግን ለልጆቹ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰራተኛ ነው። በቤተሰብ ቅልቅል ፕሮግራምም ሲገቡ የሚሰበሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግና በማፈላለግ ከወላጅ አልያም ከዘመድ አዝማድ ጋር እንዲገናኙ ይደረጋል።
በጤናው በኩል ሰላም የራሱ የተሟላ ክሊኒክ አለው ከዚህ ካለፈ ደግሞ አጠቃለይ ህክምና ሲያስፈልግ ስምምነት ስላለ ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ይሄዳሉ። የተለየ ሲሆን ደግሞ እንደ ህመሙ የሚመለከተው ሆስፒታል ሄደው እንዲታከሙ ይደረጋል። በዚህ በኩል ባለፉት ሁለት አመታት ህንድ ደረስ በመሄድ የህክምና አገልግሎት ያገኙ ልጆች አሉ። በአመት ሁለት ግዜ አንድ ሺ ሁለት መቶ ሀምሳ ብር ለልብስ ግዢ ይመደባል ከዚህ ገንዘብ የተረፋቸው ካለ ሁሉም በስማቸው በእናታቸው ሞግዚትነት በተከፈተላቸው አካውንት እንዲቆጥቡ ይደረጋል። ይህም የራሳቸው ጥሪት እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ ከልጅነታቸው ጀምሮ ቁጠባን እንዲማሩ ያስችላቸዋል።
ሌላው ልጆቹን ከውጪው ማህበረሰብ ጋር በቀላሉ እንዲዋሃዱ የሚያደርጋቸው የሰላም ትምህርት ቤት ነው። ተቋሙ ከአጸደ ህጻናት እስከ ቴክኒክና ሞያ ኮሌጅ ትምህርት ቤት ያለው ሲሆን በትምህርት ቤቱ ከሚማሩት ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው። ለምሳሌ በሰላም ህጻናት መንደር ቁጥር አንድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1200 በላይ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የሰላም ልጆች 98ቱ ብቻ ናቸው። ከአስራ ስድስት አመት በላይ ሲሆኑ ወንዶች በወንዶች ሴቶች በሴቶች ቤት የሚገቡ ሲሆን እስከ አስራ ስምንት አመታቸው ለሁለት አመት የመሸጋገሪያ ግዜ በመሆኑ የኪስ ገንዘብና የጽዳት መጠበቂያ እቃዎች ራሳቸው እንዲገዙና ሌሎች እንቅስቃሴዎችንም ራሳቸውን ችለው እንዲከውኑ ይደረጋል። ይህም ከማህበረሰቡ ጋር የበለጠ የሚያቀራርባቸው ሲሆን ከአስራ ስምንት አመት በላይ ደግሞ በከፊል ራስን መቻል ፕሮግራም ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ቁሳቁስና የምግብና የልብስ ወጪ እንዲሁም የቤት ኪራይ ተከፍሎላቸው ህክምና ተሟልቶላቸው ውጪ መኖር ይጀምራሉ።
የሰላም የህጻናት መንደር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ጫሊ በበኩላቸው ተቋሙ ሲመሰረትም ሆነ ዛሬ አላማው በተለያዩ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን ከጎዳና በማንሳት ሁለንተናዊ ሰብዕናቸው የተሟላ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ማድረግ ነው። እስካሁንም በዚህ ረገድ ውጤታማ መሆን ችለናል ይላሉ። እንደ ስራ አስኪያጁ ማብራሪያ ተቋሙ ልጆቹን ተንከባክቦ ለአቀመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ማብቃት ብቻ ሳይሆን የተስተካከለ የህይወት መሰረት እንዲኖራቸው ይሰራል። ለዚህም ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ባላቸው የትምህርት ግዜ ቆይታ ሁሉም ነገር እንዲሟላላቸው ይደረጋል። በኢትዮጵያ መማር ብቻ ሳይሆን ስራ መፈለግም አንድ ፈተና በመሆኑ ከምረቃ በኋላ ለስድስት ወር የሚደረግላቸው ቋሚ ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ ተቋሙም በስራ ማስተሳሰር ባለሙያ በኵል ልጆቹ ገና ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ጀምሮ በየኢንዱስትሪው በመሄድ ስራ ያፈላልጋል። በዚህ አካሄድም በየአመቱ ከስልሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት ወረቀታቸውን እንደያዙ ስራ ለመቀጠር ይበቃሉ። ቀሪዎቹም ከመመረቃቸው በፊት እንዲቆጥቡ ስለሚደረግ ከራሱ ከተቋሙ ከ «ሰላም ብድርና ቁጠባ» የመነሻ ጥሪት ተሰጥቷቸው የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ ስራ የተቀጠሩትንም ሆነ በራሳቸው የሚሰሩትንም ተመርቀው ከወጡበት ግዜ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ አመትም ክትትል ይደረግላቸዋል።
የሰላም ልጆች በጥሩ ስነምግባርና በትምህርት የታነጹ በመሆናቸው በግል ስራ የተሰማሩት አብዛኛዎቹም ባለሀብት ለመሆን በመብቃት በአሁኑ ወቅት ሁለት የተቋሙ የቦርድ አባል በመሆን እያገለገሉ ያሉም አሉ። የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውም ጠንካራ በመሆኑ የሰላም ፍሬዎች የሚል ማህበር በማቋቋም በየወቅቱ በመገናኘት ይደጋገፋሉ።
ሰላም የህጻናት መንደር በማህበራዊ ሀላፊነትን በመወጣት ረገድም በትምህርት ቤቱ ካሉት ሶስት ሺ የሚደርሱ ተማሪዎች ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የነጻ እድል ተማሪዎች ናቸው። ከቀሪዎቹም የትምህርት ቤት ክፍያው ትልቁ 700 ብር ቢሆንም በኮሮና ምክንያት እሱም ወደ ሀምሳ በመቶ የተቀነሰ ሲሆን እሱንም አቅሙ ለሌላቸው ነጻ ተደርጓል። በአስር የሙያ መስኮችም በአማካይ በየስድስት ወሩ ለአንድ ሺ ሁለት መቶ ወጣቶች አጫጭር ስልጠናዎችን ይሰጣል። ይህን የሚሰራው የሰላም የቴክኒክ ሙያ ኮሌጅም በ2017 በአፍሪካ ከሚገኙ ምርጥ አስር ኮሌጆች መካከል ከኢትዮጵያ ብቸኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ በመሆን ለመሸለምም በቅቷል። በአካባቢው ያሉ ህመምተኛ እናቶችን እየደገፈ ሲሆን አንዳንደ ፕሮጀክቶች በማጠፍ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 እስካሁን ለሶስት መቶ ቤተሰቦች ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በተመሳሳይ ለመቀጠል እቅድ አስቀምጧል።ተቋሙ እስካሁንም ከ46 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በተለያዩ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለ408 ዜጎች የስራ እድል ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ይህም ሆኖ ሰላም የህጻናት መንደር ሁለት ፈተናዎች ከፊቱ ተጋርጠውበታል የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ የመጀመሪያው ዛሬም የህብረተሰቡን ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ቁጥር በርካታ መሆኑና የአቅም ውስንነት መኖሩ ሲሆን ሁለተኛ ተቋሙ ከመንግስት የተሰጠውና በእጁ ያለ ቦታ ቢኖረውም ካርታ ያለው የተወሰነው ቦታ ብቻ በመሆኑ የዛሬ ሰላሳ አመት ክሊኒክ የተገነባበትን ቦታ ጨምሮ ለቀሪው ካርታ የማግኘቱ ነገር አስቸጋሪ ሆኖበታል። በዚህም የተነሳ በርካታ ለጋሾች ጤና ጣቢያ፤ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ፈቃደኛ ሆነው በዚህ ምክንያት ብቻ እየተመለሱ ይገኛሉ። የከተማው መሬት ማኔጅመንት ቢሮም ካርታ እንዲሰራ ደብዳቤ ቢጽፍም በየካ ክፍለ ከተማ በኩል ባለመፈጸሙ ለሁለት አመት በእንግልት ላይ እንገኛለን። ይህንን ችግራችንን መንግስት ቢቀርፍልን አሁን የምንሰጠውን አገልግሎት ከማሳደግ ባለፈ በርካቶችን ተጠቃሚ የምናደርግበት ሁኔታም ይመቻች ነበር ይላሉ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ