አያንቱ ተሾመ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው ነቀምት ሲሆን፤ ታላቅ እህቷን ተከትላ ከታናሽ እህቷ ጋር አዲስ አበባ ከገባች ሰባት ዓመታት ተቆጠረዋል። የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናን ከታናሽ እህቷ ጋር የወሰደችው አያንቱ፤ ውጤት አምጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲ ባትገባም ኮሌጅ ለመማር አዲስ አበባ መግባት ፈለገች። ታናሽ እህቷ ደግሞ ልትለያት ባለመውደዷ አብረው ወደ አዲስ አበባ አቀኑ።
የአያንቱ ታላቅ እህት ትዳር መስርታ ቡራዩ አካባቢ በኪራይ ቤት ትኖር ስለነበር፤ እርሷ ቤት ለመግባት ባይፈልጉም አዲስ አበባ የቤት ኪራይ ውድ በመሆኑ አብረው መኖሩ ግዴታ ሆነባቸው። ታላቅ እህቷ ከነባለቤቷ ‹‹ ሁለት ሰዎችን ለጊዜውም ቢሆን ማኖር ይከብደናል›› ብለው ለማስጠጋት ባይከለክሉም የእነርሱ አከራይ ግን ሁለቱ እህትማማቾች ከታላቅ እህታቸው ጋር እንዳይኖሩ ለማድረግ ያልሞከረችው አልነበረም።
‹‹አከራዩዋ ‹ሁለት ልጆች መጥተዋል፤ ስለዚህ 500 ብር መጨመር አለባችሁ።› ብላ በአንድ ሺህ 500ብር ይከራዩ የነበረውን በ2ሺህ ብር እንዲከራዩ አስገደደቻቸው።›› የምትለዋ አያንቱ፤ አከራይዋ በዚህ ሳታበቃ በቂ ባልሆነ ምክንያት እንደገና በ2ኛው ወር ‹‹የመብራት ዋጋ ጨምሯል›› ብላ 200 ብር ተጨማሪ የመብራት እንዲከፍሉ አስገድዳቸዋለች ትላለች።
እንደ አያንቱ ገለፃ፤ ታላቅ እህቷ እንጀራ የምትጋግረው በእንጨት፤ ወጥ የምትሰራው በከሰል ቢሆንም፤ የመብራት 200 ብር እየከፈሉ የአምፖል መብራት እንኳ ለማግኘት በሰዓት ይወሰኑ ነበር። አያንቱ ሌሊት ማጥናት ብትፈልግም በሻማ እንጂ በመብራት የማይታሰብ ነው። ከአራት ሰዓት በኋላ መብራት መጠቀም ፈፅሞ ተከልክሏል። ስለዚህ አያንቱ የቤት ሥራ (አሳይመንት) ሲኖርባት መነጋጋት ሲጀምር ውጪ ቁጭ ብላ ፈጣሪ የሰጣትን ብርሃን ተጠቅማ ትሰራ እና ፈተና ሲደርስም ሌሊት እየወጣች ታጠና ነበር። በዚህ መልኩ ሁለት ዓመታት አሳልፋለች።
አያንቱ ወንድ ጓደኛ ስለነበራት፤ እህቷ ቤት እያለች አረገዘች። እርሷም ከጓደኛዋ ጋር ትዳር መስርታ ከእህቷ በቅርብ ርቀት ቤት ተከራየች። ቤቱን ስትከራይ አከራይ ‹‹ቤት የማከራየው ልጅ ለሌለው ነው። ልጅ ካላችሁ አላከራይም›› ብትልም፤ አያንቱ ሌላ ቤት ባለማግኘቷ እና ሌላ አካባቢንም ባለማወቋ ነፍሰጡርነቷን ሳትናገር በደፈናው ቤቱን ተከራየች። እንደ አያንቱ ገለፃ የዛ ቤት ኑሮ ግን ሲኦልን ያስመርጣል።
አያንቱ ሥራ ጀምራለች። ከነባለቤቷ ጠዋት ወጥታ ማታ ትመለሳለች። ስትገባ እና ስትወጣ ሆዷን በጃኬት ትሸፍናለች። በእረፍት ቀናት ቤት ውስጥ ሆና ሥራ ስትሰራም ተጠንቅቃ ነው።አከራይዋ ትንሽ ለየት ያለች ነች። ከቤት ኪራይ ውጪ የመብራት በሚል ስለሚከፍሉ የኤሌክትሪክ ምጣድ እና ስቶቭ መጠቀም ቢቻልም፤ አከራይ ስትፈቅድ ብቻ ነው። በፈለገችው ሰዓት ማንኳኳት ሳይጠበቅባት ባከራየችው ቤት ዘው ብላ መግባት ትችላለች።
ውሃ የሚቀዳው በጎማ ቱቦ በ150 ሊትር በርሜል እና የሚጠጣ ውሃ ደግሞ በ5 ሊትር ጀሪካን ብቻ ነው። ከዛ ውጪ አይፈቀድም። ውሃው ውሃ እስከሚመጣ ለሳምንት ወይም ከዛ በላይ ሊቆይ ይችላል። አንዳንዴ ለአስራ አምስት ቀንም ‹‹ውሃ የለም›› በሚል ውሃ አያገኙም። ውሃ መምጣቱን ቧንቧ ከፍተው ማረጋገጥ አይችሉም። አከራይዋ ‹‹ውሃ መጥቷል ዕቃችሁን አዘጋጁ›› ትላለች። ሁሉም ዕቃውን አጣጥቦ ያወጣል። ከዛ ራሷ ትቀዳለች። አምና የውሃ ጎማውን አትሰጥም የምትለዋ አያንቱ፤ ‹‹ምናልባት የውሃ ስርቆት ይካሄዳል ብላ ትሰጋለች›› በማለት እየሳቀች የነበረውን ታስታውሳለች።
አያንቱ እንደምትናገረው፤ የስምንት ወር ነፍሰጡር እያለች አንድ ቀን ልብስ ለማጠብ በባልዲ ውሃ ይዛ ስትወጣ አቅቷት አስቀመጠችው። አከራይ አይታ ስለነበር ተጠራጥራ ‹‹ አንቺ እርጉዝ ነሽ?›› ብላ አፈጠጠች። አያንቱ ከዚህ በላይ መዋሸት አልቻለችም‹‹ አዎ›› አለች። ‹‹በይ በይ እኔ የልጅ ለቅሶ መስማት አልፈልግም፤ ቶሎ ውልቅ በሉ›› ብላ ግቢውን ስትዞር ዋለች።
አያንቱ ቅዳሜ ነፍሰጡር መሆኗ ታውቆ ሰኞ ሌሊት 12 ሰዓት ላይ እንጀራ ስትጋግር፤ አከራይ ‹‹እንፋሎቱ ምንድን ነው? ›› ብላ እንደለመደችው ዘው ብላ ገባች። ‹‹እንጀራ እየጋገርሽ ነው›› ብላ እንጀራውን ‹‹አንድ፣ ሁለት…ሰባት›› ብላ ከቆጠረች በኋላ ‹‹ይበቃል አጥፊው›› አለች። አይንቱ የኤሌክትሪክ ምጣዱን ማብሪያ እና ማጥፊያ እያየች ‹‹አንድ እንጀራ ላስፋ›› ብላ ስጠይቃት፤ አከራይዋ በሰማበት ጋግሪ ብላ ራሷ አጠፋችው።
‹‹ለሁለት ቤተሰብ ሰባት እንጀራ በቂ ነው፤ ከፈለግሽ ሳትለኩሺ አንድ እንጀራ ጨምሪ›› ብትልም ምጣዱ ብዙም ባለመሞቁ አያንቱ ያሰፋችው ስምንተኛ ሊጥ ሳይበስል እዛው ምጣዱ ላይ ቀረ። ነገሩን ሁሉ የሰማው የአያንቱ ባለቤት ከስራው እረፍት ወስዶ ስራ እንደሚገባ ሰው፤ ጠዋት የወጣ እስከ ማታ እየዞረ ‹‹የሚከራይ ቤት አለ›› እያለ በየቤቱ ደጃፍ ቢያንኳኳም የሚከራይ ቤት ማግኘት አልቻለም።
አያንቱ አባቷ ሊያዩዋት ከነቀምት መጡ። አከራይ በቤት ስላልነበረች የሽማግሌውን መግባት አላወቀችም። እነአያንቱ እራት በልተው ቡና ጠጥተው ለመተኛት ሲሰነዳዱ ከምሽቱ 4ሰዓት አከራይ የተለየ ድምፅ ሰማሁ ብላ ዘው አለች። የአያንቱን አባት ስታይ አበደች። ‹‹ውጡልኝ እኔ እንግዳ ብሎ ነገር አልፈልግም። እናንተንም ቤቱን ልቀቁ ብያለሁ።›› እያለች ሌሎቹን ተከራዮች ሳይቀር ቀስቅሳ ‹‹አስወጡልኝ›› አለች። እባክሽ መሽቷል ተብላ ብትለመንም ‹‹ አልሰማም ቢፈልጉ የትም ይደሩ ይውጡ›› አለች። አባት ከምሽቱ አራት ሰዓት ከአያንቱ ባል ጋር የአያንቱ እህት ቤት ሄደው አደሩ። ለቀናት ለመቆየት እና ልጆቻቸውን ለማየት የመጡት የአያንቱ አባት በመጡ በማግስቱ ወደ አገራቸው ተመለሱ።
አንድ ቀን አያንቱ ስለደከማት ጋደም ብላ ባለቤቷ በስቶቭ ጎመን እየሰራ አከራይ እንደልማዷ ዘው ብላ ገባች። ‹‹ምን እየሰራችሁ ነው? ስጋ ስለማይበስል በስቶቭ አይሰራም። የሚሰራው በከሰል ነው።›› ብላ ድስቱን ስትከፍት ጎመን ነው። የአያንቱ ባል ፈዞ ያያት ነበር። ጎመንም ቢሆን ያው ነው። ‹‹በስቶቭ መሰራት ያለበት ሽሮ ብቻ ነው።›› ካለች በኋላ፤ ጎመኑን አየት አድርጋ ደግሞ እየበሰለ ነው። በሞቀው ይበስላል ብላ በድጋሚ እንዳይለኮስ አስጠንቅቃ ስቶቩን አጥፍታው ወጣች።
የአያንቱ ባል የዛን ቀን ከልቡ አዝኖ አለቀሰ። ከቤት ወጥቶ የሚከራይ ቤት ሲፈልግ አገኘ። ቀብድ ከፍሎ ተመለሰ። ለአያንቱ ሊያሳያት ሲሄዱ አዲሷ አከራይ የአያንቱን ነፍሰጡርነት ስታይ ‹‹ውይ ይቅርታ ልጅ ላለው አናከራይም›› አለች። የአያንቱ ባል ‹‹ልጅ የለንም›› አለ። ‹‹ያው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይኖራችኋል።›› አለች። ‹‹ ታዲያ ምን አለበት? ልጅ እርግማን አይደል›› በማለት አያንቱ ጥያቄ ስታቀርብ‹‹ ልጅ ያላቸው ሴቶች ሁል ቀን ልብስ ያጥባሉ። ከውሃ ውስጥ አይወጡም። ሁልቀን ልብስ ያሰጣሉ ኮተታቸው ብዙ ነው።›› ብላ ለቀብድ የተሰጠውን ብር መለሰች። እነአያንቱ ልጅ ሊኖራቸው መሆኑ ቢያጓጓቸውም የት እንደሚያሳድጉት እያሰቡ ተጨነቁ።
ተስፋ ያልቆረጠው የአያንቱ ባል የዘጠኝ ወር ነፍሰጡር ለሆነችው ሚስቱ የተመቸ ማደሪያ ለማግኘት ሲታትር ዕድል ቀናው። ሁለት ክፍል ቤት በአንድ ሺህ ሰባት መቶ ብር አገኘ። ቤቱ የፀዳ የብሎኬት ሲሆን ግቢው ውስጥ ብዙ ተከራይ እንዳለ ያስታውቃል። ልጆች ይጫወታሉ። ‹‹የሚከራይ ቤት አለ?›› ብሎ ሲጠይቅ ‹‹ልጅ አለህ?›› የሚል ጥያቄ አልቀረበለትም። ጠዋት አግኝቶ ከሰዓት አያንቱን ይዞ ሲሄድ ሌሎች ሰዎች ቤቱን በ3ሺህ ብር እንከራይ ሲሉ ደረሰ። አከራይዋ ሴት አያንቱን ስታይ አዘነች። ‹‹አንደኛ በሰዓታት ቢሆንም ቀድመው ቀብድ የከፈሉት እነርሱ ናቸው። በዛ ላይ ልጅቷ ነፍሰጡር ስለሆነች ቤቱን እነርሱ ይግቡበት›› አለች። የአያንቱ ባል ተደሰተ። ነገ ዛሬ ሳይል እቃውን እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት አመላልሰው አልጋ እንኳ ገጣጥመው ሳያሰናዱ ዕቃው እንደተኮለኮለ ፍራሽ ላይ ተኝተው አደሩ።
አያንቱ ቤቱን በቀየሩ በአምስት ቀን ውስጥ ወንድ ልጅ በሰላም ተገላገለች። ብዙም ሳትቆይ በዓመቱ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች። አሁን የተከራዩት ቤት ተሸጧል። ገዢው ‹‹ቤት መስራት እፈልጋለሁ ውጡ›› እያለ ነው። ሆኖም የእርሷ ልጆች ወንዶች ስለሆኑ በጣም ያስቸግራሉ። በዛ ላይ የልጅ አሳዳጊነት ህይወቷ አሳዝኖት ‹‹በቃ ትንሽ ቆዩ›› በማለት ቤቱን የገዛው ሰው ፈቅዶላቸው እየኖሩ ነው።
አያንቱ እንደምትለው አሁን ልጆቿ የዘጠኝ ወር እና የሁለት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆኑ እጅግ ያስቸግራሉ። እነርሱን ከክፉ አከራይ ጭቅጭቅ ጋር ማሳደግ ያሳብዳል። ዛሬ ላይ ሆና የነገን ስታስብ እየተጨነቀች ነው። ሆኖም ግን ለጊዜው ተፈቅዶላት እየኖረች ነው። ከዚህ በኋላ ያለውን ደግሞ ፈጣሪ ያውቃል ትላለች። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
ምህረት ሞገስ