የትምህርት ተቋማት የእውቀት መሸመቻ ገበያዎች ናቸው። በዚህ የተነሳ ላለፉት እልፍ ዘመናት በባህላዊ መንገድ ፊደል መቁጠሪያ የሆኑት ትላልቅ የዛፍ መጠለያዎች ጭምር ክብራቸው ወደር የለውም። የኔታንማ በሙሉ ዓይን ቀና ብሎ ማየትም ከድፍረት ይቆጠር ነበር። ዘመናዊ የቀለም ትምህርት መቅሰሚያ የሆነው አስኳላ ከመጣም ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እስከ አስተማሪዎቻቸው ክብራቸው የትየለሌ ነው። በልጆችና በማህበረሰቡ ተቋማቱ የእውቀት ገበያ አስተማሪዎች ደግሞ የእውቀት አባት ተደርገው ተከብረውና አድባር ሆነው ለእልፍ ዘመናት ኖረዋል።
አሁን አሁን የሚሰማው ግን ለጆሮ የሚሰቀጥጥ እየሆነ ነው። ትምህርት ቤቶች የእውቀት ምንጭነታቸው ነጠፈ፤ የዘረኝነት ምንጭነታቸው አቆጠቆጠ። ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማህበረሰቡ ልጆቹን ልኮ በእውቀት ከሚታነጹለት የሚቀጠቀጡበት ጊዜ በመስፋቱ ወደ ጦር ሜዳ የሚልክ እንጂ ወደ እውቀት ገበያው የሚልክ አልመስል እያለው ተላቅሶ ይሸኛል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቆዩባቸው ዓመታት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሄርተኝነትን፣ ከአገር ይልቅ ዘርን፣ ከእውቀት ቀንድነት ክብር ይልቅ የአድርባይነት መረዳታቸውን የሚናገሩ ወጣቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ከእውቀት አውድማነታቸው ይልቅ የፖለቲካ መራኮቻነታቸው በገሃድ እየታየና እየተገለጸ እንደመጣ ግልጽ በመሆኑ ለማንም አዲስ ጉዳይ አይሆንበትም። በዚህ የተነሳ እስካለፉት ጥቂት ዓመታት ድረስ የአገር ተተኪና ተረካቢ ምሁር ማፍሪያነታቸው ተዘንግቶ የፖለቲካ እጩ ምልምሎች የሚፈሉበት ችግኝ ጣቢያ በመሆኑ በአባልነት ከመታቀፍ እስከ ሕዋስ አመራርነት ለመያዝ ሽኩቻው አይጣል ነበር። በመመረቂያ ዓመት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይጦፍ እንደነበርም ይነገርለታል።
በሌላ ገጽታው በየአካባቢውና በየወረዳው በተከፈቱልንና በመጡልን ሲባሉ የነበሩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሁን አሁን የግጭት አውድማ እየሆኑ በመምጣታቸው ባልተከፈቱብንና ባልመጡብን ሲባሉ እየተደመጠ ነው። ከዚያም አልፎ ከእርሻ ማሳቸው ሳይቀር ቆርጠው እየሰጡ ለእውቀት መቅሰሚያዎች መክተሚያ የግንባታ ቦታ በመስጠት እንዲለመልሙና እንዲስፋፉ ሲያደርጉ የኖሩ አባቶች በየአካባቢው ሞልተዋል። እነዚህን የዋህ አባቶች አፈር ሳይጫናቸው የእውቀት ተቋማቱን ይዞታና ቦታ በመንጠቅ የግል ይዞታቸው ለማድረግ ግብግብ የሚገጥሙ ገልቱና ስግብግቦች እየተመለከቱ ነው። የዚህ አይነቱን መጥፎ ድርጊት ለማስቀረት እንባቸውን እያፈሰሱ ቢመክሩም ሰሚ ጆሮ ያለው ትውልድ እያገኙ ባለመሆናቸው ልባቸው ሲሰበር፣ አእምሯቸው ሲያዝን እና ስብዕናቸው የተነካ ያህል እየተሰማቸው ሞታቸውን ሲለምኑ ማየት እየተለመደ መጥቷል።
ይሄን ሁሉ ትውስታ ወደ ቀሰቀሰብኝ የሰሞኑ ጉዳይ ልውሰዳችሁ። የእርስ በርስ ግጭት መጠንሰሻ እና የወጣቶች ሕይወት መገበሪያ የሆነው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መዘጋት የወለደው ጦስ ይመስላል። የተንኮል የፖለቲካ እንቁላላቸውን ጥለው በብሄር ኩብኩባቸው ጠቅልለው የሚያሳድጉበትና ያልበሰለውን ለጋ ወጣት ጭነው የሚጋልቡበት ሜዳ ሲያሰሉ ኖረዋል። ዛሬ እነሱን ያስፈነደቀ መላው ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ተግባር በኦሮሚያ ክልል ፣በአዲስ አበባና በአማራ ክልሎች እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መፈጸም ችለዋል። መነሻቸው የተወዳጁ የጥበብ ሰው የሃጫሉ ሁንዴሳ በአረመኔዎች እጅ መገደልን ለማስመሰል ጥረዋል። በእነዚህ ኃይሎች በሻሸመኔ ከተማ የተፈጸመው የጥፋት ወንጀል ንብረትን ማውደም ትንሹ ነው። ከፍ ሲል ሕይወትን ያጠፋና እጅግ ከፍ ሲል ደግሞ የትውልዱን ማፍሪያ የትምህርት ተቋማትን ጭምር ያወደመ የክፉዎች ደባ የተገለጸበት ነበር።
እነዚህ የትምህርት ተቋማትን ያቃጠሉ ርጉማን ጀግናው አርቲስት ሃጫሉ ለኢትዮጵያውያን መብትና ነጻነት ፊት ለፊት ቆሞ ከመጋፈጥ ባለፈ በእስር ቤት አጥር ተሸብቦ እንኳን ለወገኑ የታገለ እንደሆነ አያውቁም?፣ በአምቦ ከርቸሌ እስር ቤት ትምህርት ቤት ማስከፈቱን አልሰሙም?፣ በሴራ የሚታሰሩ ወጣቶች በአንቦ ከርቸሌ ዲግሪዎች እስኪያጠልቁ ድረስ እውቀት እንዲቀስሙ ማስቻሉን አልሰሙም? አዎ! እንዲህ አይነቱን የጀግና ተግባር ጆሯቸው አይሰማም።
በሻሸመኔ ከተማ በጥፋተኞች የወደመው የሉሲ አካዳሚ ላለፉት 22 ዓመታት በላይ ለአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል።
የሉሲ አካዳሚ ባለቤት አቶ ዮሐንስ ወልዴ እንደሚሉት ፤ ትምህርት ቤቱ ምንም ነገር የቀረ አለው ማለት አይቻልም። የአስተዳደር ሕንጻው ወድሟል። ምንም አይነት የቀረ ዶክሜንት በትምህርት ቤቱ የለም። መረጃዎች፣ የፕሪንተር ማሽኖች፣ ኮምፒዩተሮች፣ የቢሮ አጠቃላይ ቁሳቁሶች ከነሙሉ መገልገያዎች ወድሞ ባዶ ፍርስራሽ መቅረቱን ተናግረዋል።
የእቃ ግምጃ ቤት (ስቶር)፣ የኢ-ቤተመጽሐፍት ያላቸው ሁለት የኮምፒዩተር ክፍሎች፣ ኮምፒዩተር ማስተማሪያ ክፍሎች፣ ቤተሙከራዎች (ላቦራቶሪዎች)፣ ደረጃውን የጠበቀ ትልቅ ቤተ መጽሐፍት (ላይብረሪ)፣ የተማሪዎች መመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ አንድ አውቶቡስ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ መቃጠሉን ገልጸዋል። ከዚያም አልፎ በመኖሪያ ቤታቸው በመሄድ ዶልፊን መኪና አቃጥለዋል። በከተማው መሐል ላይ የሚገኘውን አፖስቶ ቅርንጫፍ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በአስተዳደር ሕንጻው ላይ አምስት ክፍሎች ከነመረጃዎቻቸው፣ ሙሉ ሙሉ ተቃጥለዋል። ማዕከሉን፣ቤተ-መጽሐፍት ክፍሉን አቃጥለውታል ይላሉ።
ትምህርት ቤቱን ማቃጠል የጀመሩት ማክሰኞ እለት (ሰኔ 22) ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ ዮሐንስ፤ ይሄን ሁኔታ ሲሰሙ ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን ይዘው በቅርብ ርቀት ወደሚያውቋቸው ቤተሰቦቻቸው ቤት በመሄድ ተደብቀው ሕይወታቸውን እንዳተረፉ ይናገራሉ። የመኖሪያ ቤታቸውንም የቻሉትን ያህል ዘርፈው ቀሪውን በማቃጠል እንዳወደሙባቸው አብራርተዋል።
በዚያች የበሬ ግንባር በምታህል ሻሸመኔ ከተማ ከ153 በላይ ሰዎች ተመርጠው በስም ዝርዝር ተገድለዋል። ከ35 በላይ ሕንጻዎች ተመርጠው ወደ ፍርስራሽነት ተለውጠዋል። ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች በርካታ የንብረትና የአካል ጉዳቶች መድረሳቸው ተሰምቷል።
ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ የትውልድ ማፍሪያ በሆኑት የትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት ያደረገው ጥፋት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባይዘጉ ኖሮ ሊደርስ የሚችለውን ችግር መገመት አይከብድም።
“በፍሮይድ አገላለጽ የሰው ልጅ፣ ኢአመክንዮአዊ (እንስሳዊ ባህሪ) ወይም ደመ-ነፍሳዊ፣ ረብሸኛ፣ እና ስሜታዊ (ሴክሽዋል) ነው፤ በዚህ የተነሳ ጨለምተኛው ቲዎሪስት እየተባለ ይጠራል”
ሁሉም ዜጋ በአንድነት ተሰልፎ የራሱንና የአገሩን ንብረት ከጥፋት መታደግ ይኖርበታል። አጥፊና ዘራፊዎችን ለሕግ በማቅረብ የዜግነት ግዴታውን መወጣት አለበት። ትውልድ አላፊ ነው፤ ታሪክና አገር ግን ይቀጥላሉ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ10/2012
ሙሐመድ ሁሴን