በኢትዮጵያ ባለፉት መታት የተከሰቱት ቀውሶች በርካታ ዜጎችን ለእንግልትና ለህልፈተ ህይወት ሲዳርጉ ቆይተዋል። ከአመታት በፊትም ሀገሪቱን በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ከአለም ቀዳሚ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል። እንደሀገር የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎም መንግስት የዲሞክራሲውን ምህዳር ለማስፋት በማለት ባመቻቻቸው ሁኔታዎች በመከለል በርካቶችን ከቤት ንብረት ያፈናቀለ፤ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለውን ዜጋ ለሞት የዳረገና ምንአልባትም ለመመለስ ዓመታት የሚፈጅ የመንግሥት የግለሰብና የድርጅቶችን ንብረት ውድመት አስከትሏል። የዚህ ችግር ገፈት ቀማሾች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያካተቱ ቢሆንም ከችግሩ ተሻጋሪነት አንጻር የበለጠ ተጋላጭና ተጎጂ የሆኑት ግን ሴቶች በተለይም እናቶች ናቸው።
በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውና ኢትዮጵያንም መዳረሻው ያደረገው የኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለውም ጉዳት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሴቶችን በተለይም እናቶችን የሚመለከት ነው። በእነዚህ ክስተቶች ዛሬም ድረስ በርካታ እናቶች ከደረሰባቸው አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ባለፈ በተለያዩ ቦታዎች የማይለዩዋቸውን ልጆቻቸውን ይዘው በችግር ውስጥ ይገኛሉ። እንደዚህ ሳይታሰቡ በሚፈጠሩ ቀውሶች ወቅት የሴቶችን ለችግር ተጋላጭነት ለመቀነስ ምን መሰራት አለበት ስንል የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ወይዘሪት ገነት ስዩም አነጋግረን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተውናል።
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ በደሎች ቤተሰብ ያፈርሳሉ፤ ቤተሰብ ሲፈርስ ደግሞ ማህበረሰብ ብሎም ሀገር ይጎዳል። በተጨማሪም እንደ ህግም እንደ ሞራልም የማህበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑትን ሴቶችን ከጥፋት መጠበቅ ግዴታ ነው። በመሆኑም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ለሴቶች ከምንሰጠው ትኩረት ልንዘናጋ አይገባም። እስካሁን እንደ ሀገር የሴቶችን በኢኮኖሚ በማህበራዊና በፖለቲካ መስክ ያላቸውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰሩና እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ከዓመት ወደ ዓመት ለውጥ እየታየ ቢሆንም ከሚጠበቀው አንጻር ግን በቂ ነው ሊባል አይችልም። ባለፉት ዘመናት ሴቶች ከነበሩበት ሁኔታ በሁሉም መስክ የተመዘገቡ የተሻሉ ለውጦች አሉ። ለምሳሌ በኢኮኖሚው ዘርፍ ትላንት ለምሳሌ ለመጥቀስ እናጣቸው የነበሩ የሴት ኢንቨስተሮች ዛሬ በብዛት በመንቀሳቀስ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ አድል በመፍጠር ዜጎችን ተጠቃሚ ሲያደርጉ ለመመልከት በቅተናል። በተመሳሳይ የሴቶች መብት በጣም ይጣስበታል በሚባለው በገጠሩም አካባቢ በማህበር ተደራጅተው በትራክተር አስከማሳረስና በምርታቸው በመጠቀም ላይ ያሉት በርካቶች ናቸው።
ከማህበራዊ ተሳትፎ አንጻርም በርካታ ሴቶች የትምህርት አድል ማግኘት በመቻላቸው በርካታ የሴት ዶክተሮች፤ ኢንጅነሮችና አብራሪዎችን አንዲሁም በተለያየ መስክ የተሰማሩና አንቱ የተባሉ ሴቶችን እያየን እንገኛለን። በፖለቲካውም መሰክ ከፍተኛ የፌደራል ተቋማትን መምራት ብቻ ሳይሆን ከማንም በተሻለ ውጤታማ እያደረጉ ያሉም አሉ። ከዓመት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራርም የሚኒስትሮች ሹመት ግማሽ በግማሽ ለሴቶች ማድረጉ እየተመዘገበ ላለው ለውጥ አንዱ ማሳያ ነው። ይህም ሆኖ ግን ከሚፈለገውና ወቅቱ ከሚጠይቀው አንጻር የመጣው ለውጥ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም። በመሆኑም ወቅታዊ ሁኔታዎችን መሰረት አድርጎ እታች ድረስ የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጡ ረገድ እንደ ሀገር ብዙ ስራ ይጠበቃል።
የተለያዩ ሀገራዊ ቀውሶች ሲከሰቱ ቀዳሚ ተጎጂና የገፈቱ ቀማሽ ከሚሆኑት መካከል ሴቶችና ህጻናት ቀዳሚዎቹ ናቸው። ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተከሰተውን ለወጥ ተከትሎ በተፈጠሩ ግጭቶችና መፈናቀሎች ለተለያዩ ጉዳት የተዳረጉት ሴቶች በተለይም እናቶች በርካታ ናቸው። በእነዚህ ግዜያት ከመኖሪያቤት ከመፈናቀል እስከ የኑሮ ውድነት የተፈጠሩት ችግሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የችግሩ ሰለባ አድርጓቸዋል። መፈናቀል ሲከሰት ልጆች ይዘው በመሰደድ ትልቁን እዳ የሚጋፈጡት ብሎም ዋናውን መስዋእትነት የሚከፍሉት ሴቶች እናቶች ናቸው። በአንዳንድ ቦታዎችም በጣም አስጸያፊ በሆነ አካኋን ከአራስ አስከ ህጻን የመደፈር ብሎም በአስከፊ ሁኔታ አስከተፈፀሙ ግድያዎች የደረሱ ወንጀሎች በእናቶች ላይ ተፈጽመዋል። በዚህም ረገድ በመንግሥት በኩል ህግ የማስከበርና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ስራዎች በስፋት ሲከናወኑ የነበረ ቢሆንም ከችግሩ ውስብስብነት አንጻር ውጤቱ አመርቂ ነበር ለማለት አይቻልም። እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ ዛሬም ብልጭ ድርግም እያሉ እየተደጋገሙ ይገኛሉ። በመሆኑም እነዚህን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች እነዚህ ወንጀሎች እንዳይደገሙ ሊያደርጉ የሚችሉ ተመጣጣኝና አስተማሪ እርምጃዎችም ሊወሰዱ ይገባል። የሄ ደግሞ የመንግሥት የህግ አስከባሪ አካላት ስራ ብቻ ሳይሆን ጥቃት አድራሾቹ የራሳችን ሰዎች እንደመሆናቸው መላው ህዝብ ችግሩ የኔም ነው እኔንም ይመለከተኛል በማለት ከአንድ ወቅት ርብርብ አልፎ የዘወትር የህይወቱና የስራው አካል በማድረግ ሴቶችችን ከጥቃት መከላከል ይጠበቅበታል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የኮቪድ አስራ ዘጠኝ ኮሮና ቫይረስ መከሰት ደግሞ ችግሩን ይበልጥ የባሰና የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጎታል። የመንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ወደ ኮሮና መሆኑ በሌሎች ስራዎች ላይ እንዳጠቃለይ ጫና ተፈጥሯል። የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ከተፈጠሩ ክስተቶች መካከል የሰዎች የእንቅስቃሴ መገደብ፤ የስራ ማቆም፤ ልጆች ከትምህርት መቅረት፤ የኑሮ ውድነት፤ (በተለይ ለእለት ፍጆታ በሚውሉ እቃዎች ላይ)…..ና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሴቶች ላይ እየፈጠሩ ያሉት ተጽእኖ ከፍተኛ ነው። ይህም ሆኖ የበሽታው ስርጭት በቀጥታ ለይቶ ሴቶችን የሚያጠቃ ባይሆንም የሚያደርሳቸው ተጽእኖዎች ግን በቀጥታ ሴቶችን በተለይም እናቶችን የሚመለከቱ ናቸው።
የኮሮና ቫይረስ ያደጉትንና የዳበረ ኢኮኖሚ አላቸው የሚባሉትን ሀገራት ለማንበርከክ የበቃ ነው በመሆኑም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እንደ ሀገር ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።
የተቸገሩትንም በመደገፍ ረገድ በመንግሥት፤ በድርጅቶችና በግል ባለሀብቶች የሴቶች ፌዴሬሽንን ጨምሮ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ቢኖሩም ከችግሩ ስፋትና የቫይረሱ ስርጭት መቼ ሊያቆም እንደሚችል በማይታወቅበት ሁኔታ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም። በዚህም የተነሳ ዛሬም የእለት ምግብ ከማጣት ጀምሮ በጣም በችግር ወስጥ ያሉ ቤተሰቦች ብዙ ናቸው። የተጀመሩት ድጋፎች በአሁኑ ወቅት እየተቀዛቀዙ በመሆናቸው እንደ እጅ ማስታጠቡ እልም ብለው እንዳይጠፉና በርካታ ቤተሰቦች ለከፋ ችግር እንዳይዳረጉ የኢትዮጵያዊነት መለያችን የሆነውን የመረዳዳት ባህል አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ኮሮናን በተመለከተ በበርካታ ቦታዎች የመዘናጋት ነገር እየመጣ በመሆኑ ቫይረሱ ብዙ መስዋእትነት ሊያስከፍለን ይችላል። በመሆኑም በመንግሥት የሚተላለፉ ትእዛዞችንና በህክምና ባለሙያ የሚሰጡ ምክሮችን በመተግበር ራስን ቤተሰብን ብሎም ማህበረሰብንና ሀገርን ከኮሮና ቫይረስና የሚያስከትለው ጉዳት መከላከል የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ ወይዘሪት ገነት አስገንዝበዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአስከፊነታቸው ለህዝቡ ከተነገሩት የአባት ልጅን መድፈርና መሰል ታሪኮች ባለፈ በሴቶች ላይ በርካታ ጥቃቶች በቤት ወስጥ እየተፈጸሙ ይገኛሉ። እነዚህ ጥቃቶች ከጤና ጉዳት ባለፈ በተጠቂዎች ላይ የሚፈጥሩት የስነልቦናና ማህበራዊ ተጽእኖዎች ሴቶቹን የቀራቸውን ህይወት በሙሉ የሚከተላቸው ነው። ይህም ሆኖ የጉዳቱ ሰለባዎች ከአቅም ማነስ፤ ተስፋ ከመቁረጥና በህግ ላይ ካለመተማመን አብዛኞቹ ፍትህ ከመፈለግ ይልቅ ከነጉዳታቸው እቤታቸው መቀመጥን ይመርጣሉ። ሌላው ቀርቶ ከተማ ውስጥ ተቀምጠው እንኳን በርካታ ሴቶች የት አቤት ማለት እንዳለባቸው የማያውቁ አሉ። በመሆኑም በሴቶች ፌዴሬሽን እየተሰጠ ያለውን አይነት ነጻ የህግ የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አቅማቸው በፈቀደ መሰል ችግሮችን እያነፈነፉ በማወጣት ህጋዊ ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመንግሥትም በኩል ህግ አስከባሪ አካላት ከፖሊስ እስከ ፍርድ ቤት የፍትህ ስርዓቱን በማስተካከል ተጎጂዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት።
በተጨማሪም መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ ስላለበት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወቅቱንና ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ ፖሊሲዎችና ህጎችንም በመፈተሽ ማሻሻል፤ መውጣት ያለበትንም በማውጣት እንደየጊዜው ነባራዊ ሁኔታ መራመድ ይጠበቅበታል።
ሴቶችን ከጥቃት የመከላከልና ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ ወቅት እየጠበቁና ችግር ሲፈጠር ብቻ ከማርገብ ባለፈ በዘላቂነት ሊሰራ ይገባል የሚሉት ወይዘሪት ገነት እንዳጠቃለይም በአንድ በኩል በቀጥታ በአሁኑ ወቅት በችግር ውስጥ ያሉ ሴቶችን ለመታደግ፤ በሌላ በኩል ለቀጣዩ ትውልድ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በተግባር ለማረጋገጥ መሰራት አለባቸው ያሏቸውንም ተግባራት እንደሚከተለው አስቀምጠዋል። ዛሬ በርካታ ዜጎችን ለመፈናቀል ለሞትና ለአደጋ ያጋለጡትን የሰላም እጦት ተግዳሮቶች ከማንም ቀድመው ህዝብ በማንቃት የመከላከል የህሊና ኃላፊነት ያለባቸው ቤተ እምነቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀይማኖቱና ለሀይማኖት አባቶች ትልቅ ክብር አለው ከማንምም በተሻለ የሚሉትን ይሰማል ይተገብራልም።
በመሆኑም ከምንም ነገር ቅድሚያ በመስጠት ከጸሎቱ ባልተናነሰ ስለ ሰላምና አንድነት ሳይሰለቹ ያለማቋረጥ መስበክ የሚጠበቅባቸው የሀይማኖት ተቋማትና የሀይማኖት አስተማሪዎች ናቸው። የሀይማኖት መሪዎች ይህ የሰላም መታጣትና ስነ ምግባር የጎደለው ትውልድ መፈጠር ለራሳቸው ለሀይማኖት ተቋማትም ይዞ የሚመጣው ዳፋ መኖሩን መገንዘብም አለባቸው። አስካሁንም በቂ ስራዎች ባለመሰራታቸው ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም የተመለከትናቸው ቤተ እምነቶችን የማቃጠል ተግባራት ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው።
አገር ያቀናሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው የትምህርት ተቋማትም ዛሬ የብዙ ችግሮች መነሻ ሲሆኑ እየታየ ነው። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጸሙ ተግባራት መማር ለምኔ የሚያሰኙ ህዝቡ በተማረው ሀይልም ሆነ በትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን ተስፋ የሚያጨልሙ ናቸው። ዛሬ በአንዳንድ ቦታዎች የሚደርሱ ጥፋቶች ላይ እየተሳተፉ ካሉት መካከል የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወጣቶችም መታየታቸው አንዱ የልጆች የትምህርት ቤት ቆይታ ችግር ያለበት መሆኑን አመላካች ነው። በመሆኑም ከመንግስት በኩል የሚመለከታቸው አካላት ከስር ጀምረው የትምህርት ፖሊሲውንም ሆነ የትምህርት አሰጣጡን መፈተሽ ይጠበቅባቸዋል። እያንዳንዱ መምህርም ሀገሩን የሚወድ የታረቀ ስነ ምግባር ያለው ተማሪ ለማፍራት የግድ የስነ ምግባርና ስነ ዜጋ አስተማሪ ብቻ መሆን አይጠበቅበትም። የትኛውንም የትምህርት አይነት የሚያስተምር ቢሆንም እግረ መንገዱን የተማሪዎቹን ስነ ምግባር ለመቆጣጠርና ለማረቅ እድሉ ስለሚኖረው ስለሰው ልጅ ክብር ስለ ማህበረሰቡ ሞራልና የሀገር አንድነት የህዝቦች ህብረት ማስተማር አለበት።
ማህበረሰቡም ዝምታውን መስበር አለበት የሚሉት ወይዘሪት ገነት በሴቶች ላይ እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች መባባስ አንዱ ምክንያት ችግሮቹ በማህበረሰቡ ውስጥ ባሉ አጥፊዎች መፈጸማቸው ብቻ ሳይሆን እያወቀም ሆነ ሳያውቅ ማህበረሰቡ ከለላ እየሰጣቸው መሆኑ ነው። ድሮ የሴቶችን መደፈር ስናስብ ቅጠል ለቀማ ሲወጡ፤ አልያም ትምህርት ቤትና በጉዞ ላይ ሆነው ነበር። ዛሬ ግን እየተፈጸመ ያለው የኛ በሚሏቸው ይጠብቋቸዋል ከለላ ይሆኗቸዋል በሚባሉ የቅርብ ሰዎችና የቤተሰብ አባላት ነው። እነዚህ አካላት የሚያደርሱትን ጥቃትን መከላከል ደግሞ ለየትኛውም ተቋም አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ማህበረሰቡ ለዚህ ምስጢር ቅርብ ነው። ስለዚህ በማህበረሰቡ በኩል እኔንም ይመለከተኛል በሚል ስሜት ችግሩን መጋፈጥና ይፋ ማውጣት ካልጀመረ የቤት ወስጥ ጥቃት የመቀነስ እድሉ ጠባብ ነው። አስካሁንም ችግሩ እንዲባባስ አንዱ ምክንያት የማህበረሰቡ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፉ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በእንደዚህ አይነት ስራ የሚሰማሩ የማህበረሰቡ አካላትን ማውገዝ ማግለል መጀመር አለበት። ከማህበረሰቡም ቀን የወጣላቸው በአመራርና በውሳኔ ሰጪነት ላይ ያሉ ሴቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ከመወጣት በተጓዳኝ ችግሩን ከወንዶች ይልቅ ችግሩን በመረዳት ባሉበት ሆነው ተሰሚነት ስለሚኖራቸው የአቅማቸውን መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ10/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ