የመለወጥ የተስፋ ጮራ እየፈነጠቀ ነው። መንግስት ግብርናውን ለማዘመንና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት ባደረገው ጥረትም ዛሬ ላይ በርካታ አርሶ አደሮች ከድህነት ወጥተዋል። በምግብ ራሳቸውን ችለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ያፈሩ ትጉህ አርሶ አደሮች ተፈጥረዋል። አርሶ አደሩ የኤክስቴንሽን ስርዓት በአግባቡ በመከተል፤ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፤ በየዓመቱ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግም ላይ ይገኛል::የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ቀደም ሲል አርሶ አደሩ ምርጥ ዘር የመጠቀም ባህሉም አቅርቦቱም አልነበረም።
በአሁኑ ጊዜ ግን በመንግስታዊ የምርጥ ዘር ድርጅቶች ብቻ በዓመት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ ይገኛል። በማህበራትና አርሶ አደሩ እርስ በእርስ የሚለዋወጡት ሲጨመር መጠኑ ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ይሆናል። ይህም ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው የግብርና ዕድገቱ በቂ ማሳያ ነው።
አሁን ባለንበት ወቅት በግብርና ስራ ላይ የተሰማራው ዜጋ በመሰረቱ ከግብርናው ውጪ ሌላ የስራ አማራጭ አለኝ ብሎ የማያስብ እና የግብርና አሰራሩም ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ በመጣ የግብርና ዘይቤ የሚሰራ ነው::አርሶ አደሩ በግብርና ስራ ላይ ለመስራት የተሟላ ዝግጁነት ያለው ነው፤ ይህ በግብርና ሙያ የመሰማራት ዝግጁነት ሌላ አማራጭ ስለሌለ ብቻ የመጣም አይደለም፤ ከትወልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ የስራውና የሙያው ፍቅርም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ስለሆነም በግብርና ሞያ በሰፊው የመሰማራት ፍላጎት መፍጠርን በተመለከተ ነባሩ የአርሶ አደሩ ትውልድ ብዙ የሚጎድለው ነገር አለ::በዝግጁነቱ ላይ ምንም እክል እንደሌለበት እሙን ነው፡፡
አንድ አርሶ አደር ዝግጁነት ኖሮት ታታሪነት ከጎደለው የሰው ጉልበት በግብርና ስራ ላይ አመቱን ሙሉ እንዲሰማራ በስራ ላይ በሚሆንብት ወቅትም ያለመታከት እና ትጋት እንዲሰራ ማድረግ ስለማይቻል የግብርና እድገቱ በሚፈለገው መጠን ሊሆን አይችልም::ምንም እንኳ የህዝቡን ታታሪነት የሚፈታተኑ ጎጂ ልምዶች ቢኖሩም ይህንንም አልፈው በታታሪነት ምሳሌ የሆኑ አርሶ አደሮች አያሌ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኝ አርሶ አደር የጉልበት ስራ ሰርቶ ጥሮ ግሮ ኑሮውን ለማሸነፍ የሚጥር ነው::በስራ ባህል ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን እና ከባህል ልምድ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በሚያሳምን ሁኔታ በማስተማር እና አስተሳሰቡን ለመለወጥ ትግል በማድረግ እንዲህ ያሉ ችግሮችን በማረቅ አርሶ አደሩ ያለውን ትጋት እና ታታሪነት በይበልጥ ማጠናከር ይቻላል ፡፡
በዚህ ስራ ላይ የተሰማራውን ነባሩን የአርሶ አደር ትውልድ በይበልጥ ለማትጋት የሚቻለው በግብርና ስራ ላይ ተግቶ በመሰማራት ኑሮውን ያለማቋረጥ ለማሻሻል እንደሚችል በማረጋገጥ ነው::ምርቱንም ማሳደግ እንዲችል ከሚያመርተው ምርት ዋነኛ ተጠቃሚ እንዲሆን በሚያገኘው ገቢ የኑሮ ደረጃው እንዲሻሻልና ለዚህ የሚያስፈልጉትን ሸቀጦች እና አገልግሎቶች እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ታዲያ በዝግጅትም ሆነ በታታሪነት አንቱ የተባሉ አርሶ አደሮች በሁሉም የአገሪቱ ማዕዘናት ላይ ማግኘት የተለመደ ነው::የስራ ባህልን ወደ ኋላ ሊጎትቱ የሚችሉ ጉጂ ልምዶችን ሰብረው የወጡ ከሰኞ እስከ ሰኞ በማሳቸው ላይ በማሳለፍ የታታሪነት ምሳሌ የሆኑም አያሌ ናቸው::ታዲያ ለዛሬ ከአዋሳ ከተማ ግብርና መምሪያ በሰጣቸው ምርት እና ምርታማነትን የሚጨምሩ ድጋፍ እና ምክር በተግባር በማዋል በታታሪነት በመስራት ለአርሶ አደሩ ምሳሌ የሚሆኑ እናት አርሶ አደር ይዘን ቀርበናል፡፡
ትውውቅ
አርሶ አደር ወይዘሮ አየለች አባቴ ይባላሉ::በአዋሳ ከተማ በቱላ ክፍለ ከተማ ፍንቹዋ በተባለ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው::አርሶ አደሯ እጃቸው እርፍ መጨበጥ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በግብርና ስራ የተሰማሩ ሲሆን አንዴ ተሳክቶላቸው ከዕለት ጉርስ ተርፎ ለገቢያ ሲያቀርቡ የሚበልጠው ጊዜ በዝናብ እጥረት በተለያዩ እክሎች የሚላስ የሚቀመስ ሲያጡ ነበር፡፡
የወይዘሮ አየለች አባቴ እና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ በጋራ ባሳዩት የትጋት በምርት እና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ውጤት ታይቷል::የተገኘውም ውጤት በዚያው ቀበሌ እና በአጎራባች ቀበሌዎች ላይ ከፍተኛ በጎ ተጽህኖ በመፍጠር ብዙ የአሰራር ለውጦችን እንዲመጡ አድርጓል::ለብዙ አርሶ አደሮችም ለለውጥ መነሳሳትና እና መበረታታትም ምክንያት ሆነዋል::የወይዘሮ አየለች የስራ ውጤት ለሌሎች አርሶ አደሮች እንደመማሪያ እና ማሳያ እንዲሆን ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የተቀመረበት ወቅት ታህሳስ ወር 2012 ዓ/ም ነበር፤ አርሶ አደሯ የሚኖሩበት እና የሚሰሩበት ቀበሌ የአየር ፀባይ ከፊል ቆላማ ሲሆን የመሬቱ ከፍታ ደግሞ 1 ሺህ 708 ሜትር ነው፡፡የአካባቢው የአፈር አይነት አሸዋማ ሲሆን ቅመራው የተሰራባቸው የሰብል ዓይነቶች ጥቅል ጎመን፤ቲማቲም እና ቀይ ሽንኩርት ናቸው፡፡
የማሳ ዝግጅት የግብዓት አጠቃቀም
መሬት በግል ተያዘም በመንግስት አጠቃቀሙ የተስተካከለ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፤ እያንዳንዱ ሜትር መሬት ለልማት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት በምትችልበት ሁኔታ ጥቅም ላይ እየዋለች መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል::ለቤት እና ለከተማ ልማት ማዋል የሚገባው መሬት የግጦሽ መሬት ከሆነ የደንና የግጦሽ መሬት መሆን የሚገባው ከታረሰም መታረስ የሚገባው መሬት ከተማን ከተስፋፋበት ወይም ግጦሽ መሬት እንዲሆን ከተደረገ ከመሬታችን ማግኘት የምንችለውንና ማግኘት የሚገባንን ልማት ስለማናገኝ አጠቃላይ ልማቱ መሰናከሉ እና መጓተቱ የማይቀር ይሆናል::እያንዳንዱ ሜትር መሬት የበለጠ ጥቅም ሊሰጥ በሚችልበት ስራ ላይ መዋሉ ዋነኛ ምክንያት ነው። አርሶ አደር አየለች አባቴም ያላቸውን መሬት በአግባቡ ያለአንዳች ማባከን በማረስ የሚጠቀሙ ትጉህ አርሷ አደር ናቸው::ታዲያ ያላቸውን መሬት ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ባስተማራቸው እና ባደረገላቸው ድጋፍ መሰረት ለዘር ምቹ አድርገዋል፡፡
አርሷ አደር አየለች ያላቸው የማሳ ስፋት 4 ነጥብ 5 ሄክታር ሲሆን እርሱንም የማሳ መሬት ሳይንሳዊ በመሆነ መንገድ ለሚፈልጉት ዘር ቦታ አከፋፍለዋል::አርሷ አደሯ ከመምሪያው በአገኙት የእውቀት ድጋፍ ያላቸውን መሬት ለጥቅል ጎመን አንድ ሄክታር፤ ለቀይ ሽንኩርት 1 ነጥብ 25 ሄክታር፤ ቲማቲም 2 ነጥብ 25 ሄክታር በማከፋፈል አዘጋጅተዋል::በአጠቃላይ በማሳው ላይ ጥቅም ላይ የዋለ የአፈር ማዳበሪያ በሄክታር ኤን ፒ ኤስ 7 ኩንታል፤ ዩሪያ 10 ኩንታል እና ኮምፖስት 10 ኩንታል የተጠቀሙ ሲሆን የተዘራው የአትክልት ዓይነትና መጠን ቀይ ሽንኩርት 6ኪሎ ግራም ፤ጥቅል ጎመን 0 ነጥብ 75ኪሎ ግራም፤ ቲማቲም አንድ ኪሎ ግራም ነበር::ይህም የማሳ ዝግጅት እና የግብዓት አጠቃቀም ለሌሎች አርሶ አደሮች እንደ ማሳያ የቀረበ እንዲሁም ተቀምሮ እንዲጠቀሙበት የተደረገ የአርሶ አደር አየለች የትጋት ስራ ውጤት ነው::ዝግጅቱም ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለ በሆኑ ምርታማነት በመጨመር ረገድ ትልቅ ሚና ያለው ነው፡፡
የዘር አዘራርና የአፈር ማዳበሪያ አጨማመር
አርሶ አደር አየለች የዘር አዘራር ወይም የተከላ ሂደት መጠን እንደ ሰብሉ ዓይነት መስመሮችና ዘሮች ተክሎች መካከል ርቀቱን ጠብቆ መዝራትን አከናውነዋል፤ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀማቸውም ሁሉንም ኤን ፒ ኤስ በማሳ ዝግጅት ጊዜ ያደረጉ ሲሆን ዩሪያ ከተከላ ጊዜ ጀምሮ እስከ ሚቀጥሉት 7 ቀናት የሚጨመር ነው::አርሶ አደሯ ቀሪውን ደግሞ ከ45 ቀናት በኃላ “ስሊፕ አፕሊኬሽን” ይጠቀማሉ፡፡
ዘመናዊ የግብርና መሳሪያ ባይኖራቸውም ብርቱዋ አርሶ አደር ወይዘሮ አየለች የኩትኳቶ ክንውናቸውን በእጅ በመኮትኮት የሚሰሩ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ እየተከታተሉ አረምን የማስወገድ ስራ ይሰራሉ::የአረም ቁጥጥር ክንውናቸውም በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት እንደዘሩት የዘር ዓይነት የሚለያይ ሲሆን ለቀይ ሽንኩርት 6 ጊዜ፤ ለጥቅል ጎመን 4 ጊዜ፤ ለቲማቲም 4 ጊዜ ያደርጋሉ:: የውሃ አጠቃቀም በየ3 ቀን እና በየ 4ቀን የሚያጠጡ ሲሆን አርሶ አደሯ የአረም ቁጥጥር በጊዜ መከናወን ለምርት መጨመር ከፍተኛ አዋጭነት ስላለው ከሶስተኛው ሳምንት ጀምሮ አረም ቁጥጥር ያደርጋሉ ::አርሶ አደሯ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ጋር በመተባበር ደግሞ የተባይ መከላከልና ቁጥጥር ክንውን እንደ ማንኮዜብ ዱቀት ፤ዳይመቴኤት፤ አግሮታይት፤ ኮሳይድ እና የመሳሰሉትን ተጠቅመዋል፡፡ሌላው አርሶ አደሯ የተጠቀሙባቸዉ ቴክኖሎጂ ዓይነቶች የዉሃ አማራጭ ሲኖሩ የመጀመሪያው ዓይነት ዘመናዊ ጉድጓድ ብዛቱም 2 ሲሆን 2 የዉሃ መሳቢያ ሞተር ተጠቅመዋል፤ ጉልበት አንዱ ግብዓት ሲሆን ይህም አርሶ አደሯ ብዛታቸው ስድስት የሚሆን የቤተሰብ ጉልበት የተጠቀሙ ሲሆን ወደ 20 የሚሆኑ ወንድ እና ሴት የቀን ሰራተኞችንም ጉልበት ተጠቅመዋል::ይህም ሌላኛው የአርሶ አደር አየለች አባቴ እንደ ምርጥ ተሞክሮ ተወስዶ የተቀመረ የወይዘሮዋ የትጋት ውጤት ነው፡፡
የተገኘው ውጤት
አርሶ አደሯ በአደረጉት ከፍተኛ ትጋት ያገኙት ምርት እጅግ መልካም ነው::በዚህም ቲማቲም 168 ኩንታል ፣ጥቅል ጎመን 244 ኩንታል እንዲሁም ቀይ ሽንኩርት 94 ኩንታል ለማግኘት ችለዋል። ትጋት፣ ላብ መልሶ ይከፍላል የሚባለው በአርሶ አደሮች ቤት እና ማሳ ላይ ይታያል፡፡
በአገኙትም ምርት ልጆቻቸውን ማስተማር ችለዋል፤ በተለያዩ የድጋፍ ዓይነቶች ጎረቤቶቻቸውን ጠቅመዋል ፤ ለከብት መኖነት ጥቅም የሚውል ተረፈ ምርት ያገኙ ሲሆን ይህንን ሁሉ ተጠቅመው ትርፍ ካፒታል ማስመዘገብ ቁጠባ ማስቀመጥ ችለዋል ፡፡
ሌሎች ተግባራት
በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ እንደ አርሶ አደር አየለች አባቴን የመሳሳሉ ትጉህ አርሶ አደሮች የራሳቸው ማሳ ላይ ብቻ የተጠመዱ አይደለም ነገር ግን ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ በመሆኑ የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ስራም ሰርተዋል::እንደሚታወቀው የሀዋሳ ከተማ በአጠቃላይ 152 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ስኬር ስፋት ያለው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 110 ኪሎ ሜትር ስኬር በግብርና ሥራዎች የሚሸፈን ነው። ከዚህ ውጪ ሀይቁ 129 ኪሎ ሜትር ስኬር ይሸፍናል፡፡በአጠቃላይ በእርሻ ማለትም በደን በቋሚና በዓመታዊ ሰብል የሚሸፍን መሬት 9 ሺህ 90 ሄክታር ይሆናል፤ የሀዋሳ ተፈጥሮ ሁኔታ ምቹ ሲሆን ተፈጥሮውን በዘላቂነት ሥነ-ምህዳሩ ባለበት ለማቆየት ብዙ የአረንጓዴ ልማት በገጠሩም በከተማውም እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡
ይህም ሥራ ሥነ-ህይወታዊና ሥነ- አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ሲሆኑ በ2012 ዓ.ም በ20 ተፋሰሶች ላይ 1 ሺ 650 ሄክታር በአዲስ ሥነ አካላዊ ሥራዎች ለመሸፈን ታቅዶ 1 ሺ 80 ሄክታር አዲስ የሥነ አካላዊ ሥራዎች ለመስራት ተችሏል፡፡
ይህ በሥነ አካላዊ የተጀመረው ሥራ ለሥነ ህይወታዊ ማለትም በችግኝ ተከላ መታገዝ ስላለበት ከላይ በተገለጹ 20 ተፋሰሶች ላይና በሌሎች በከተማና በገጠር በግል ይዞታዎች ላይ 3 ሚሊዮን የተለያዩ የደን ዛፎችና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው አቡካዶ ማንጎ ፖፖያ ወዘተ የመሳሰሉትን ለመትከል ያቀደ ሲሆን 30 ሺህ በመትከልም ወደ ተግባር ውስጥ ገብተዋል፡፡
2012 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ቀን እንደሀገር በሀዋሳ ከተማ ላይ ጠቅላይ ሚኒስተር በዶክተር አብይ አህመድ አማካይነት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የተደረገ ሲሆን ያንን ቀን ተከትሎ የመንግስት ተቋማት የግልና የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሐይማኖት ተቋማትና ግለሰቦች ለተከላ የተለየ ቦታ በመውሰድ የተከላ መርሃ ግብር ወቶላቸው እየተከሉ ይገኛሉ::እስከ አሁን 1 ሚሊዮን ችግኝ መትከል የተቻለ ሲሆን ቀሪዎቹን እስከ ሐምሌ 30 ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑ መምሪያው አስውቋል::የእንክብካቤ ሥራ በተመለከተ ሁሉም የተከለውን ችግኝ እንክብካቤ በራሱ እንዲተገብረው እየተሰራ እንደሆነ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2012
አብርሃም ተወልደ