ከሀያ አመት በፊት ተከስቶ የነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ለሁለቱም ሀገራት ጥቁር ጠባሳን ጥሎ ያለፈ አጋጣሚ ነበር። ጦርነቱ ካስከተለው ከፍተኛ የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ባሻገር ለዘመናት አብረው በኖሩት ሁለቱ ህዝቦች መካከል ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስንም አስከትሎ ቆይቷል። በዚህም የተነሳ በርካታ ቤተሰቦች ለመለያየት ብቻ ሳይሆን ከፍቅር እስከ የዕለት ጉርስ ማጣት ለችግር እንዲጋለጡም አድርጓል። ከሁለት አመት በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የመንግስታቱ ግንኙነት ወደህዝብ ለህዝብም ተሸጋግሮ ለአሰርት አመታት አይደለም በአካል በድምጽ ያልተገናኙ ቤተሰቦች ለመተያየት በቅተዋል። የዛሬ የቤተሰብ እንግዳችንም ለስራ ምክንያት ወደ አስመራ ባቀኑበት አጋጣሚ ጦርነቱ በመጀመሩ እንደወጡ ቀርተው ከሀያ አመት በኋላ ያለፉት አልፈው የቀሩ ቤተሰቦቻቸውን በህይወት ለማግኘት የበቁ አዛውንት ናቸው።
አቶ ተስፋ ልደት ዝክታ ገብረማርያም ይባላሉ። የተወለዱት የዛሬ ሰማኒያ ሶስት አመት በ1929 አ.ም በዛሬዋ ሀገረ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ አካባቢ ነው። የልጅነት ጊዜአቸውን በተወለዱበት አካባቢ ያሳለፉ ሲሆን እስከ አምስተኛ ክፍልም እዛው ተምረዋል። የህይወት መንገዷ አይታወቅምና በ1952 አ.ም ወደ አዲስ አበባ በማቅናት አዲስ የህይወት ምዕራፍ ለመጀመር ይበቃሉ። አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ የነበራቸውን ሞያ በመጠቀም በወቅቱ ኢትዮጵያ ሲኒማ ህንጻ ስር የነበረ አንድ የቻይና ምግብ ቤት ውስጥ በመቀጠር በቅደሚያ ሼፍነት ከዛም በተለያዩ ደረጃዎች አስተዳደር እስከመሆን ደርሰው ተቀጥረው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ ቆይታቸውም በተለያዩ ቦታዎች የኖሩ ሲሆን አብዛኛውን ግዜ ያሳለፉት ጨርቆስ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ ሀያ አምስት ቀበሌ ሀያ አንድ የሚባል አካባቢ ነው። ትዳር የመሰረቱበትን ወቅት በቅጡ ባያስታውሱትም ወይዘሮ አብርሃጽዮን ገብረክርስቶስን አግብተው የሞቀ ትዳር መስርተውም ስምንት ልጆችን ወልደው አሳድገዋል። «አዲስ አበባ በነበርኩ ግዜ በጣም የሚያስደስት ህይወት ነበር የምንኖረው፤ ከህዝቡ ጋር እንፋቀራለን፤ የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የጎረቤትና የሰፈርም ቅርርብ ስለነበረን ለእኔ በርካታ ትዝታዎች አሉኝ።» የሚሉት አቶ ተስፋ ልደት ጨርቆስ አካባቢ ከሰላሳ አመታት በላይ ያሳለፉትን ግዜ ዛሬም ድረስ አሁን ያለ እስኪመስላቸው ያስታውሱታል።
በዚህ ሁኔታ እያሉ ነበር አዲስ አበባ ሲያሰራቸው የነበረው ምግብ ቤት አስመራ አዲስ በመክፈቱና ሆቴሉ ልምድ ያለው ሰራተኛ ያስፈልገው ስለነበር እሳቸው ከአንድ ቻይናዊ ጋር በመሆን አዲሱን ሆቴል ለማጠናከር በ1986 አ.ም ወደ ትውልድ አካባቢያቸው አስመራ ያቀኑት። ለአመታት ተለይተዋቸው የነበሩትን ቤተሰቦቻቸውን አግኝተው የሄዱበትም ስራ ተሳክቶላቸው ጥቂት አመታትን በሰላም ቢያሳልፉም ነገሮች በነበሩበት ሊቀጥሉ አልቻሉም። እሳቸውም ሆነ ቻይናዊው ጓደኛቸው ወደ አስመራ ያቀኑት ከሆቴሉ ጋር የአራት አመት ኮንትራት ውል ገብተው የነበረ ሲሆን ከእሳቸው ጋር የተጓዘው ቻይናዊ ውሉ ሲጠናቀቅ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ሀገሩ ያቀናል። እሳቸው ግን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ግጭት የተነሳ መንገዶች ሁሉ ተዘግተው ስለነበርና ትውልዳቸው ኤርትራ በመሆኑ ያለ አንዳች ዝግጅትና ቅድመ ሁኔታ እዚያው አስመራ ለመቅረት ይገደዳሉ። በሁለቱ ሀገራት መካካል የተጀመረው ጦርነት ጦስ ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን በአጋጣሚ አባቷን ለማየት ወደዛው አቅንታ ለነበረችውም ልጃቸው ይተርፍና ባለቤታቸውና ሰባት ልጆቻቸውን ለማግናኘት ወደ አዲስ አበባ የመምጣቱ ነገር የማይታሰብ ይሆናል። በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው ችግርና ያስከተለው የድንበር መዘጋት የአየሩንና የመኪናው መንገድ ብቻ ሳይሆን ስልክ መደወልም ደብዳቤ መጻፍም የማይታሰብ አድርጎት ስለነበር አቶ ተስፋልደትና ልጃቸው ከዚያ ግዜ ጀምሮ ከአስራ ስምንት አመት በላይ ቤተሰባቸውን ለማየት ሳይታደሉ ይቆያሉ።
አቶ ተስፋ ልደት በአስመራ ቆይታቸው ይበሉት ይጠጡት ባያጡም፤ የስጋ ዘመዶቻቸውንም በቅርብ የሚያገኙ ቢሆንም መሽቶ በነጋ የሚያስቡት የሚጨነቁት አዲስ አበባ ትተዋቸው ስለሄዱት ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ነበር። የጭንቀታቸውና የሀሳባቸው መነሻ ደግሞ ከቤተሰባቸው ጋር የመገናኛቸው ግዜ መርዘሙ አልያም አለመታወቁ ብቻ ሳይሆን ከናፍቆት
ባለፈ እንደ ቤተሰቡ አባወራነት ቤተሰቡን ደግፎ የሚያኖር አለመኖሩ ነበር። ባለቤታቸው ይሄ የሚባል ስራ የሌላቸው የቤት እመቤት ሲሆኑ ልጆቻቸው ደግሞ ለአቅመ ስራ ያልደረሱ ገና በትምህርት ገበታ ላይ ያሉ ናቸው። ጦርነቱ እስከ ተጀመረበት ግዜ ድረስም ቤተሰቡ ይተዳደር የነበረው አቶ ተስፋ ልደት ሰርተው ወር ቆጥረው በሚልኩት ገንዘብ ነበር።
አቶ ተስፋ ልደት በሰላሙ ቀን ወደ አስመራ ከማቅናታቸው በፊት በአንድ ወቅት ጠንከር ያለ የአስም ህመም ገጥሟቸው ስለነበር ለክፉም ለደጉም ብለው ባንክ ያስቀመጧትን ትንሽ ገንዘብ ቤተሰቦቻቸው እንዲገለገሉበት በማሰብ ከባንክ አካውንታቸው ገንዘብ ማውጣት እንዲችሉ ፈቅደውላቸው ነበር። ያቺ ገንዘብ ደግሞ ረዘም ላለ ግዜ የዘጠኝ ቤተሰብ ወጪ ይዛ የምትዘልቅ ባለመሆኗ አቶ ተስፋ ልደት ዘወትር ባለቤቴና ልጆቼ ምን ሆነው ይሆን እያሉ በስጋት ለመቆየት ዳርጓቸዋል። የሚፈይዱት ነገር ባይኖርም በአንድ ወገን ሰላም ወርዶ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጀመር የሁለቱን ሀገራት መንግስታት መግለጫ ሲከታተሉ በሌላ በኩል ደግሞ በሰሚ ሰሚ ከሁለቱም ሀገራት ውጪ ያሉ የሚያውቋቸው ሰዎች ስለቤተሰቦቸቻው የሰሙት ነገር ካለ በማለት መረጃ ሲያፈላልጉ ኑረዋል። እንደየሁኔታው በተለያየ ግዜ ቤተሰቦቻቸው በህይወት መኖራቸውንና ደህና እንደሆኑ ሲያጠያይቁ ኖረው አንድ ቀን የሴት የልጃቸውን ሞት ተከትሎም የባለቤታቸውን ሞት በአንድ አመት ግዜ ውስጥ ካረፉ ከወራቶች በኋላ በሰሚ ሰሚ ውጪ ሀገር ባሉ ሰዎች በኩል መርዶ ይደርሳቸዋል። ይሄ አጋጣሚ ለአቶ ተስፋ ልደት ለሞቱት እንዲያዝኑ ብቻ ሳይሆን ያሉትስ ከዚህ በኋላ ምን ሊገጥማቸው ይችላል በሚል ሌላ የሰቀቀን ዘመን ይዞባቸው ይመለሳል። እዛው አስመራ እያሉም እህትና ወንድማቸው አርፈው ስለነበር ሀዘናቸው ድርብ ድርብር ይሆንባቸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ችግር አነሱ እንዳልታሰበ እንዳልታወቀ ሁሉ መጨረሻውም ያልለየለት በመሆኑ ከሶስት አመት በፊት የመጣው ይምጣ ብለው ቀላል የማይባል ገንዘብ በዶላር ከፍለው በሱዳን አቋርጠው አዲስ አበባ ይመጣሉ። ነገሩ እንዲህ እንደ ቀላል የተፈፀመ ባይሆንም ለሶስት ወር ያህል አዲስ አበባ ተቀምጠው ልጆቻቸውን አይተውና ናፍቆታቸውን ተወጥተው ተመልሰው በመጡበት አኳኋን በሱዳን ወደ አስመራ ያቀናሉ። ይህም ሆኖ አጋጣሚው የቆየ ናፍቆታቸውን ቢያስታግስላቸውም ልጆቻቸውን ትተው ወደ አስመራ ማቅናታቸው ግን የግድ ስለሆነባቸው እንጂ ልባቸውም ሀሳባቸውም እዚሁ አዲስ አበባ ከልጆቻቸው ጋር መኖር ነበር።
በዚህ ሁኔታ ለይ እያሉ ነበር ለእሳቸውም፤ ለሁለቱ ሀገራት ህዝብም ብሎም ለአለምም ያልታሰበ የደስታ ዱብዳ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ስምምነት የተከናወነው። ስምምነቱን ተከትሎም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሁለቱን ሀገራት ድንበር ሲያስከፍቱ ከሀያ አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ መላውን ቤተሰባቸውን በነጻነት ለማግኘት እንደሚችሉ ያምናሉ። ምኞታቸውም መና አልቀረም ነበር፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ሲጀመር አስመራን ከስም ውጪ የማታውቃት ልጃቸው ሳይታሰብ ሄዳ ልትጎበኛቸው ትበቃለች። እሳቸውም ያለውን ነገር አስተካክለው ጓዛቸውን ጠቅለው አንዷን ልጃቸውን ይዘው ወደአዲስ አበባ ያቀናሉ። «ሁሌም ስጋት ውስጥ ነበርኩ፤ ቤተሰቤን በህይወት አገኛቸዋለሁ ብዪ አላሳብኩም ነበር፤ እንደገና የተወለድኩ ያህል ነው የተሰማኝ፤ የማላውቃቸውን የልጅ ልጆቼንም ለማየት በቅቻለሁ።» የሚሉት አቶ ተስፋልደት ከቤተሰባቸው ተነጥለው ያሳለፉትን ግዜ እንዲህ ያስታውሱታል።
“አስመራ በስራ ላይ እያለሁ እኔም ሆነ ቻይናዊው የስራ ባልደረባዬ የየራሳችን አንዳንድ ክፍል ያለን ቢሆንም
ተገናኝተን እንጨዋወት ነበር ከሌሎች ሰዎች ከዘመዶቼም ጋር እገናኘለሁ ነገር ግን እኔ ሁሉ ነበር እንደጨለመብኝ ነበር የኖርኩት። በተለይ አውደ አመት ሲመጣና አንዳንድ ግዜም ቤተሰብ ተሰብስቦ ስመለከት ሁሌም የሚረብሽ ስሜት ይሰማኝ ነበር። ሁሌም ስለምናደድና መጠጥም አዘወትር ስለነበር ጨጓራዪን እስከመታመም ደርሼ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለሁለቱ ሀገራት ባደረጉት የእርቅ ስራ አንዱ ተጠቃሚ ነኝ። በህይወቴ ተደሰትኩባቸው ከምላቸው ቀኖችም አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ የገቡ ቀን ነው። እሳቸው ሲገቡ ከአስመራ ህዝብ ጋር ወጥቼ እየጨፈርኩ ነው የተቀበልኳቸው፡፡ ያቺን ቀን የለበስኳት የሁለቱን ሀገራት ጥምረት የምታሳይ ቲሸርትም እስካሁን በእጄ ትገኛለች። ስራ የሌለን አዛውንቶች ሌሎች ወጣቶችም በአንዳንድ መናፈሻ ቦታ ተገናኝተን ስንጫወት ኢትዮጵያ ቤተሰብና ዘመድ ያለንም ሆንን ሌሎቹ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በመገናኘት አብረው መኖር እንዳለባቸው እንነጋገር ነበር። አሁንም ድረስ ለአመታት በርካታ ቤተሰብ ተበታትኖ እናትና አባት ተለያይተው በብዙ ሰዎች ላይ በርካታ ችግር ሲደርስባቸው ቆይቷል። ይሄ መቀጠል የለበትም። አሁንም ህዝቡ መቀራረብ ይፈልጋል።ዶክተር አብይ ብዙውን ስራ ሰርተውታል። አንዳንድ የተመረጡ ትልልቅ ሰዎችም ግዜ ወስደው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አጠናክረው ማስቀጠል አለባቸው። ሶስቱ ልጆቼ ከኢትዮጵያ ወጥተው ሲውዲን፤ ካናዳና እስራኤል ናቸው ያሉት፡፡ ከሀገር የወጡትም የእናታቸውን ወርቅ ሳይቀር ሸጠው ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው ነው፡፡ ዛሬ እኔንና ሌሎቹንም ቤተሰቦች የሚደጉሙት እነሱው ናቸው” ይላሉ።
አቶ ተስፋ ልደት ከሀያ አመት ቆይታ በኋላ ያገኟትን አዲስ አበባንና ነዋሪዎቿንም እንዲህ ይገልጿቸዋል። “አዲስ አባባ እኔ ከማውቃት በጣም ሰፍታለች፤ በርካታ ህንጻዎችና መንገዶችም ተገንብተዋል፡፡ እንደ ስሟ አዲስ እየሆነች ነው። ድሮ የኖርኩበት ሰፈር «ጨርቆስ» አካባቢው ስለተነሳ ሁሉንም ጎረቤቶቼን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ግን የማገኛቸው አሉ፡፡ ብዙ ነገር አሳልፈናል፡፡ ተነፋፍቀን ስለኖርን ስንገናኝ በጣም ነው ደስ የሚለን። አሁን ከምኖርበት ፈረንሳይ ለጋሲዎን አካባቢ ኮሮና ከመከሰቱ በፊት እየወጣሁ እዘዋወራለሁ። የህዝብ አቀባበልና እንግዳ አክባሪነት የድሮ ትዝታዪን እያጫረብኝ በጣም ደስ የሚል ግዜ ነው የማሳልፈው። በፊት ጨርቆስ እያለሁ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሃይለማርያም ወንድም ጋር ጎረቤትም ሆነን ነበር፡፡ የቀበሌ ቤት ነበረኝ፡፡ አሁን እጄ ላይ ያሉትን መረጃዎች አጠናክሬ መታወቂያ ለማውጣት እየተንቀሳቀስኩ ነው። ሁሉም ሰው የእኔ እድል ደርሶት የተበታተነ ቤተሰብ ሁሉ እንዲገናኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ያሰቡት ነገር ተሳክቶላቸው የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በሰላም በፍቅር እንዲኖሩ ምኞቴም ጸሎቴም ነው” ይላሉ።
«የቤተሰብ መለያየት የሚፈጥረውን ስቃይ የሚያውቀው የደረሰበት ብቻ ነው» የምትለው የአቶ ተስፋልደት አምስተኛ ልጅ ወይዘሮ ሃና ተስፋልደት ቤተሰቡ ያሳለፈውን ግዜ እንዲህ ታስታውሳለች። “ከአባታችን ተለይተን ረጅም ዘመን አሳልፈናል፡፡ ዛሬ ግማሾቻችን ትዳር መስርተናል፡፡ ግማሾቹም ከሀገር ወጥተዋል፡፡ ያለፈው ግዜ ግን እንዲህ በቃላት ብቻ የሚገለጽ አልነበረም። አባታችን አብሮን እያለ እቤት ውስጥ የሚያስቀና ፍቅር ነበረን፡፡ እሱ ያደርግልን የነበረ በርካታ ልምዶችም ቀርተውብናል። አመት በዓል በመጣ ቁጥር በጣም እናዝን፣ እንከፋም ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ እናታችንና እህታችንን አጥተናል። እናታችን በአንድ በኩል እኛንም ከሀገር እንዳያስወጡን በሌላ በኩል እኔ አንድ ነገር ብሆን እያለች ትጨነቅ ነበር። አባቴን በህይወት አገኘዋለሁ ብዪ አስቤ አላውቅም ነበር። አባታችን በሱዳን መጥቶ ከጠየቀን በኋላ ግን ብዙ ነገሮች መለወጥ ጀመሩ። በህይወት ባገኘውም አርጅቶ ወይንም ታሞ ሊሆን ይችላል ብዪ አስብ ነበር፡፡ እሱ ግን ደህና ሁኔታ ላይ ሆኖ ነበር የመጣው። ተመልሶ ከሄደ ደግሞ አመት ሳይሞላው በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም በመስፈኑ ቤተሰባችን ዳግም ለመሰባሰብ በቃ” ትላለች።
እነሆ ይህ ቤተሰብ ከረጅም አመታት በኋላ በዚህ ሁኔታ ለመገናኘት መብቃቱ አስደሳች ቢሆንም ከዚህ ልንማር የሚገባቸው በርካታ ቁምነገሮች ግን እንዳሉ አንዘ ነጋም፤ በተለይ ሰላም ለሰው ልጆች ያለው ዋጋ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የዚህ ቤተሰብ ተሞክሮ ትልቅ ትምህርት ነው። ቸር እንሰንብት፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ