ወይዘሮ አበባ ታምራት ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በባህር ዳር ከተማ ነው። አስር አመት ሲሆናት ወላጅ እናቷ በሞት ተለዩዋት። በዚህ የተነሳ አያቷ ይዘዋት ወደ ዋልድባ ገዳም አቀኑ። እዛም ትንሽ ግዜ ከቆዩ በኋላ ወደ ደብረሊባኖስ ይመጣሉ። ነገር ግን ደብረ ሊባኖስ እንደደረሱ ትንሽ ያማቸውና ህይወታቸው ሲያልፍ አበባ ያላ አሳዳጊ፣ ያለተንከባካቢ ትቀራለች። እናም በቅርብ ወዳለችውና በስም ብቻ በዝና ወድምታውቃት አዲስ አበባ አቀናች። አዲስ አበባ እንደደረደሰችም ሰው ጋር በመጠጋት መስቀል አደባባይ አካባቢ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ ገደል ግቡ የሚባል ሰፈር ያገኘችውን እየሰራች ህይወቷን መግፋት ትጀምራለች። እድሜዋ ከፍ እያለ ሲመጣ ደግሞ በየሆቴሉ እቃ ማጠብ ምግብ ማብሰልና ቀን ስራ የመሳሰሉትን መስራት ትጀምራለች። እንዲህ እንዲህ እያለች ያገኘችውን ተሯሩጣ እየሰራች በተረፋት ግዜ ትምህርቷን በማታው ክፍለ ግዜ ትከታተል ነበር።
በዚህ ሁኔታ እያለች ነበር ከአንድ በወቅቱ በውል ከማታውቀው ወጣት የስንዴ ነጋዴ ጋር ጓደኝነት የጀመረችው። እናም ግንኙነታቸው እየጎለበተ ይመጣና ወደ ፍቅር ተቀይሮ በሰፈር ሽማግሌ ተስማምተው እንዳቅማቸው ሶስት ጉልቻን ለመመስረት ይበቃሉ። ያገኙትን እየሰሩም እሷ አስራ ዘጠኝ አመት ሲሆናት የመጀመሪያ ወንድ ልጇን ለመገላገል ብትበቃም እሷ በማታውቀው ምክንያት ከትዳር አጋሯ ጋር ያለው ግንኙነት እየሻከረ መምጣት ይጀምራል። ውጪ ማደር፤ መጠጣት ገንዘብ ማጥፋት ሲጀምር በመካከላቸው ያለው ጭቅጭቅም እየበረታ ይመጣል። እናም አንድ ቀን መንጃ ፈቃድ ለማደስ ደብረ ብርሃን ሄጃለሁ ብሏት ከቤት ከወጣ በኋላ እሱ እዛው አካባቢ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት ጀምሮ መቀመጡን ስታውቅ ግንኙነቷን ለማቋረጥ ትገደዳለች። ነገር ግን የተወሰነ ግዜ ተለያይተው ከቆዩ በኋላ የሱ ቤተሰቦች ከትግራይ መጥተው ያለውን ነገር አስማምተው አስታርቀዋቸው በድጋሜ በአንድነት ህይወታቸውን መቀጠል ይጀምራሉ። ይህም ሆኖ ትንሽ ግዜ ከቆየ በኋላ አሁንም ባህሪው ያገረሽና ያለፉትን ስህተቶች መድገም ሲጀምር በድጋሜ በመካከላቸው ግጭት ይፈጠራል። እሱም ከትንሽ ግዜ በኋላ አሞኛል ሀገሬ መሄድ አለብኝ ብሎ ወደ ትግራይ ይሄድና በዛው ጭራሹንም ትቷት ይጠፋል።
ይሄ ግዜ ግን ለአበባ ትልቅ ፈተናን ደቅኖባት ይመጣል። እሱ ከሄደ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሁለተኛ ልጇን መጸነሷን ታውቃለች። ግዜው ለአበባ ጥሩ አልነበረም ከወራቶች በኋላ ሴት ልጅ ለመገላገል ብትበቃም እርግዝናዋ ሲገፋ ጀምሮ ስራ አቁማ ስለነበር የሰነበተችው የቆጠበችውን እየበላች ነበር። ልጅቷን ከወለደች በኋላም ለአንድ ወር ያህል ከልብስ ጀምሮ ያላትን እቃ እየሸጠች ስትጠቀም ከቆየች በኋላ ሁሉም ነገር መስመር ይስትና የቤት ኪራይ እንኳን የምትከፍለው ታጣለች። በዚህም ምክንያት የሶስት ወር ውዝፍ እዳ ሲኖርባት የወር ከስምንት ቀን ልጇን ይዛ እዛው ከአስር አመት በላይ የኖረችበት ሰፈር እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ስር የጎዳና ህይወትን “ሀ” ብላ ለመጀመር ትገደዳለች።
ከዛ ግዜ ጀምሮ ለሁለት አመት ከስድስት ወር ላስቲክ እየለበሰች ሁለት ልጆቿን ይዛ በጎዳና አሳልፋለች። የጎዳናው ህይወት ግን እንዲህ በቀላሉ የሚገፋ አልነበረም። ዝናቡ፤ ብርዱ፤ የሌሊቱ ዱርዬ ሁሉ የየቀን ፈተናዎቿ ነበሩ። በዚህ የጨለማ ዘመን ሁለተኛ ልጇንም ክርስትና ያስነሳችው እዛው ጎዳና እያደረች ስለነበር አራስ ስለሆነች ብለው የተወሰነ ግዜ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ባለ መጠለያ ማታ ሁለት ሰአት ገብታ ሌሊት አስራ ሁለት ሰአት እንድትወጣ ፈቅደውላትም የነበረ ቢሆንም ቀሪውን ግዜ ያሳለፈችው ሁለት ሜትር የማትሞላውን ላስቲክ ቤቷ አድርጋ ነበር። ቀን ቀንም ቢሆን በየመኪናው መዞር ከሰው መጣላት የየእለት ትእይንቶች ናቸው።
“አንዳንዶችም ብቻዬን ሲያዩ ወጣት አይደለሽ፤ ለምን ሰርተሽ አትበይም ይሉኛል። ከጀርባዬ ያለብኝን ችግር የሚረዳልኝ የለም። ለሁሉም ደግሞ ተነግሮ አይዘለቅም። መንገር ብችልም የሚያምነኝ የለም። ስለዚህ ሰምቶ እንዳልሰማ ዞር ማለትን አዘወትራለሁ” የምትለው ወይዘሪት አበባ ያኔ ያሳለፈችውን ግዜ እንዲህ ታስታውሳለች። በወቅቱ ግን ስራ የማልሰራው ልጆቼ ህጻናት ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ከአይኔ ሳይርቁ መጠበቅም ስለነበረብኝ ነበር። የጎዳና ህይወት ለሴትና ለህጻናት ፈታኝ ነው። በአንድ ወቅት እኔ እኖርበት የነበረው አካባቢ ተወልዳ ያደገች የማውቃት የአስር አመት ልጅ ተደፍራ አርግዛ በወሊድ ምክንያት ስትሞት በአይኔ አይቻለሁ። ስለዚህ ልጆቼን ትቼ የትም ለመንቀሳቀስ አልደፍርም። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ሴቶች ህጻን ልጅ ተበድረው በየመኪናው እየዞሩ አልያም መንገድ ዳር ተቀምጠው ሲለምኑ ውለው ገንዘቡን ከልጆቹ እናቶች ጋር ይካፈላሉ። ልጆቹን ግን ሙሉ ቀን ሲያሰቃዩዋቸው ነው የሚውሉት። አንዳንዶቹ ምግብ እንኳን አያበሏቸውም። ልጅ እየተቀያየሩ የሚለምኑም አሉ። ወንዶቹም ህጻናት ልጆችን ብቻቸውን ካገኟቸው ሄዳችሁ ለምናችሁ ገንዘብ አምጡ እያሉ ይመቷቸዋል። አንዳንድ ግዜ የሚፈራቸው ካገኙ ከእናቶቻቸው ነጥቀው የሚወስዱም አሉ። ይሄ ነገር እኔንም ገጥሞኛል። አንድ ቀን ልጄን ሲያስለምን ለመዋል የመጣን ወጣት የጎዳና ተዳዳሪ አትወስደውም ስለው ቆይ ማታ አገኝሻለሁ፤ አሳይሻለሁ፤ ብሎ ዝቶብኝ ሄደ። ማታ ስጠብቀው አልመጣም። በሌላ ቀን ግን ጠጥቶ መጥቶ ሊያስፈራራኝ ሲሞክር ሁሌም ኪሴ ውስጥ አሸዋና ሚጥሚጣ እይዝ ስለነበር ሳያስበው ሚጥሚጣውን አይኑ ውስጥ በተንኩበት። ለግዜው አሞት እየጮኸ ሲሄድ የተጎዳ አልመሰለኝም ነበር። በኋላ ትንሽ ቆይቶ ጓደኞቹ ከፖሊስ ጋር መጥተው አይኑን አጥፍተሻል ብለው ጣቢያ ወሰዱኝ። ፖሊሶቹ ያለውን ነገር ጠይቀው ለቀቁኝ። እሱ ግን እስከአሁንም አይኑ በሽተኛ ሆኖ ቀርቷል። እኔ በዚህ አይነት መልኩ ሁሌ እየታገልኳቸው ነበር የምኖረው። በየለሊቱ እያየን የሚደፈሩ ልጆች ስላሉና ልጆቼንም መጠበቅ ስላለብኝም ብዙ ግዜ ሌሊት አልተኛም። የምተኛው ቀን ቀን ነበር። በጣም ይከፋኝም ስለነበፍ ለአመት በአል ራቅ ያለ ቦታ ወይንም ኮሽምና አጥር ስር ተኝቼ ነበር የማሳልፈው ትላለች።
አበባ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ሌላ ተደራቢ አዲስ ችግር ይፈጠርባታል። በማታውቀው ሁኔታ የማህጸን ኢንፌክሽን መታመሟን ታውቃለች። በሽታው በሰውነቷ ላይ ሀይለኛ ሽታ ስለሚፈጥር በማንኛውም ሰዓት ከሰው እንድትቀርብ የሚያደርጋት አልነበረም። ህክምና ለማድረግም አልቻለቸም። በዛ ላይ ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ ስላልነበራት ወደ ልጆቼም ይተላለፍ ይሆናል በሚል ስጋት እየተሰቃየች ሳለች አንድ ቀን የእለት ጉርሷን ለእሷና ለልጆቿ ለመለመን ወደ አንዲት መኪና ስትጠጋ ባለመኪናዋ ወይዘሮ የተለመደውን ልጅ ነሽ ሙሉ አካል አለሽ ለምን ሰርተሽ አትበይም? ጥያቄ ታቀርብላታለች። አባባ በሽታውም ችግሩም እየተባባሰባት ስለመጣ መፍትሄ ባታገኝም ለግዜው የምትመጸውታትን ለመቀበል ነገር ግን እውነቱን ትነግራታለች። ወይዘሮዋ ግዜ ሰጥታ ስታዳምጣት ከቆየች በኋላ እውነት የጎዳና ህይወትን ለመላቀቅ ከፈለግሽ ልተባበርሽ፤ አሁን ልጆችን ይዘሽ ከእኔ ጋር መሄድ ትችያሽ ትላታለች። አበባ በአንድ ወገን እየሆነ ያለው ነገር ህልም ህልም እየመሰላት በሌላ በኩል ያንን ጠረን ይዛ እንዴት መኪና ውስጥ መግባት እንዳለባት እየጨነቃት ልጆቿን ይዛ በድፍረት ወደመኪናው ትገባለች። ወይዘሮዋ እሷንም ልጆቿንም ወደ ቤቷ ይዛቸው ከሄደች በኋላ ገላቸውን አስታጥባ ልብሳቻውን አስቀይራ የህይወት ምዕራፍ ሁለትን እንድትጀምር ታደርጋታለች። አበባ ግን ምንም እንኳ በውስጧ ካለችበት የጎዳና ህይወት የመላቀቅ ተስፋ ቢኖራትም እንዲህ በአንድ ቀን ጀምበር ታሪክ ይቀየራል ብላ ስላላሰበች ያላመነችውንም ያልተማመነችበትንም አጋጣሚ መጨረሻ በትእግስት መጠባባቅ ጀመረች። ሴትየዋ (ወይዘሮ መሰረት) የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ እንደሆነች ለአበባ ነግራት ከዚህ በኋላም ድርጅቷ በተቻለ አቅም እንደሚደግፋት በመንገር እሷም ራሷን ለመለወጥ አንድትዘጋጅ ትመክራታለች።
ከቀናት በኋላም ሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት አካባቢ ቤት ትከራይላትና የሶስት ወር ክፍያ ከፍላላት አዲስ የህይወት ምእራፍ እንድትጀምር ታደርጋታለች። እጇ ላይ ቀርታት የነበረችው አንዲት ብረት ድስት ብቻ ስለነበረችም ወይዘሮ መሰረት ሁሉንም የቤት እቃ አሟልታ የእለት ቀለብም ትሰፍርላት ትጀምራለች። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በየቀኑ የማህጸን ህክምና እንድታገኝ እያደረገቻት ስለነበር አበባ ጤናዋም ተስፋዋም ተያይዘው እየለመለሙ ነበር። ጤናዋ ወደነበረበት መመለሱ ሲረጋገጥም አበባ ወደ መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ትወስዳትና ስልጠና እንድትከታተል ታደርጋታለች። ስልጠናው ሲጠናቀቅም በሰለጠነችው መሰረት ስራ እንድትጀምር አንድ ሺ አምስት መቶ ብር ተሰጥቷት ስለነበር ያንን ጥሪት አድርጋ ትንሿን ልጅ አዝላ ትልቁን እየጎተተች አብዮት አደባባይ አካባቢ እየዞረች በፔርሙዝ ሻይና ቡና እያዞረች መሸጥ ትጀምራለች። ግን ለሷ ያለው አልነበረምና ከአንዴም ሁለት ግዜ በደንብ አስከባሪዎች ንብረቷን ስለተወረሰባት ስራውን መቀጠል ሳትችል ትቀራለች። ሁለተኛ ዙር ሌላ ድጋፍ ይደረግላትና በሷው አሳቢነት ከጀሞ ላርጎ (ፈሳሽ ሳሙና በማምጣት) በየቤቱና በየቢሮው እየዞረች መቸርቸር ትጀምራለች።
በዚህ ወቅት ኦሎምፒያ አካባቢ የሚኖሩና ከልጅነቷ ጀምሮ የሚያውቋት አንድ ቄስ የቀበሌ መታወቂያ አውጥተውላት ስለነበር “ነገን ማን ያውቃል” ብላ በ2005 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝግባ ነበር። በሌላ በኩል የምትኖርበትም ቀበሌ ከሴቶች ጉዳይ ባጻፈችው የትብብር ደብዳቤ የደሃ ደሃ ብሎ በመመዝገብ የቀበሌ ቤት እንዲሰጣት ፈቅዶላት በመጠባበቅ ላይ ነበረች። እናም በ2008 አንዲት ለእሷ የተባረከች ሳምንት ሰኞ የኮንዶሚንየም እጣ እንደደረሳት ይነገራትና ተደስታ ሳትጨርስ ማክሰኞ ጠዋት የቀበሌ ቤት እንድትረከብ ጥሪ ያደርጉላታል። በመጀመሪያ ሁለቱም የሚሰጣት መስሏት ደስ ብሏት ነበር። ነገር ግን ሁለቱንም መቀበል እንደማትችል ሲነገራት ከሁለት ደስታዎች መካከል አንዱን መምረጥ ብታስብም ፍላጎቷ የጋራ ቤቱን ይሆንና ለሰድስት ወር የቆጠበችው 900 ብር ብቻ ስለነበር ሌላ ሀሳብ ይፈጠርባታል። እናም አውጥታ አውርዳ ክፍያው የማይቀመስ ሲሆንባት ወደቀበሌው ለመዞር እያሰበች ለሁሉም መላ አይጠፋም ብላ ነገሩን የክፉ ቀን ደራሽ እናቴ ለምትላት ለወይዘሮ መሰረት ታማክራታለች።
ወይዘሮ መሰረት እንድትመርጥ አድርጋ በድርጅቱ በኩል የኮንዶሚንየሙን የቅድሚያ ክፍያ አስራ ሶስት ሺ ብር ትሰጣታለች። እናም ጥቅምት ሀያ አምስት 2009 ዓ.ም የቤት ባለቤት ለመሆን ትበቃለች። አበባ በአሁኑ ወቅት ደረቅ ቆሻሻ ተደራጅታ መስራት ከጀመረች ስምንት ወር የሆናት ሲሆን በወር አንዳንዴ 1ሺ500 አንዳንዴም 2000 ብር እየተከፈላት በመስራት ላይ ትገኛለች። ከዛ በፊት የነበሩትን ግዜያት ግን ያሳለፈችው በግንባታ ስራ ላይ ለተሰማሩት ውሃ በማቅረብ ነበር። በእነዚህ ግዜያት በየቀኑ ከሚገኘው ገቢ በየወሩ ለቤቱ ኪራይ 740 እየቆጠበች ትከፍላለች። በአንድ ወቅት ግን አሟት ስለነበር ይሄም አልሳካ ብሎ ባንክ ማስጠንቀቂያ አምጥቶ ይለጥፍባትና በመደበኛ ከሚደረግላት ባለፈ የመሰረትን ድርጅት ለድጋሚ ድጋፍ ትጠይቅና የስድስት ወር ተከፍሎላታል። በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ልጇ አራተኛ ክፍል ሁለተኛ ልጇ ደግሞ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ሆነዋል። ወይዘሮ አበባ በቀን ስራ ባሳለፈችው ግዜ ያገኘችው ልምድ ለገንዘብ ማስገኛ ባይጠቅማትም የደረሳትን ስቱዲዮ የጋራ መኖሪያ ቤት ራሷ ግምበኛ ራሷ ለሳኝ ራሷ ቀለም ቀቢ በመሆን ባለ አንድ መኝታ አድርጋ አሳምራታለች። አበባ «ጤናዬ እንደተጠበቀ ልጆቼ ትንሽ ከፍ ካሉ ቢያንስ አንድ እናት አባት የሌለው ህጻን ለማሳደግም የልብ ሀሳብ አለኝ ትላለች።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ