ወይዘሪት ፍሬህይወት ጉልላት ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በተለምዶ መስቀል ፍላወር የሚባለው አካባቢ ነው። እናቷ የስድስት ወር ልጅ እያለች ትታት ጠፍታ ስለሄደች እናትም አባትም ሆነው ያሳደጓት አያቷ ናቸው። እናቷን ምን አይነት እንደሆነች ለማየትም እንኳን እድሉን ያላገኘች ቢሆንም አያቷ የሚያስፈልጋትን ሁሉ አሟልተው በማቅረብ የእናት ምትክ ሆነው እንደማንኛውም ህጻን በደስታ እንድታድግ አድርገዋታል። ለአቅመ ትምህርት ስትደርስም በድሮው ምስራቅ በአሁኑ ሀምሌ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል አንቀባረው አስተምረዋታል። አስራ ሰባት አመት ሲሞላት ግን ባላሰበችው አጋጣሚ የህይወቷ መስመር ሌላ አቅጣጫ የሚይዝበት አጋጣሚ ተፈጠረ። በወቅቱ ትምህርት ቤት ከተዋወቀችው የልጅነት ጓደኛዋ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ቀስ በቀስ ወደ ፍቅር ያድግና በአንዲት ያልተጠበቀች እለት በተፈጠረ ግንኙነት ለመጸነስ ትበቃለች። ማርገዟን ካወቀች በኋላ ነገሩ ግራ ሲያጋባት ውሎ ሲያድር የተፈጠረውን ነገር ለጓደኛዋ ስታዋየው ለእሱም እንግዳ ነገር ስለሆነበት ምን አልባትም የመጣውን ነገር ለመጋፈጥ የሚያስችል ዝግጅት ስላልነበረው በነበረው ግንኙነት ለመቀጠል ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል። ጭራሹንም ራሱን ያርቅና በአካልም መገናኘት የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ይህ ጊዜ ለወይዘሪት ፍሬህይወት የመጀመሪያው ከባዱን የህይወት ምእራፍ የጀመረችበት ወቅት ነበር። እሷ የጓደኛዋን አይመለከተኝም መልስና መጥፋት ከሰማች በኋላ ሁሉም ነገር ተጭበርብሮባት የምትይዘው የምትጨብጠው ነገር ታጣለች፤ ሆዷ ደግሞ ቀን መሽቶ በነጋ ቁጥር እየጨመረ እርግዝናዋን እያሳያት ሲመጣ የእሷም ጭንቀት በእጥፍ ማደጉን ይቀጥላል። ጊዜው እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ስለነበር ደፍራ ባታደርገውም በተደጋጋሚ ብር ብላ ከቤት ለመጥፋትም አስባ ነበር ። ሆኖም አያቷ ነገሮችን በአስተውሎት ይከታተሉ ስለነበር እንደ ምንም አቅርበው ያለውን ነገር ለመረዳት ይሞክራሉ፡፡ እናም እንደፈሩት ማርገዟን ያረጋግጣሉ። እሳቸው ነገሩን በጸጋ ቢቀበሉትም እሷ በድብቅ ታደርግ የነበረውን ነገር ስላወቁ በወዳጅ ዘመድ ልጁን እንድትወልድ በማስነገር ሌላውን ነገር እሳቸው እንደሚወጡት ቃል በመግባት እሷን ማባበልና መንከባከብ ይጀምራሉ። ወይዘሮ ፍረህይወትም በዛ ወጣትነት እድሜዋ የልጅ እናት ላለመሆን የሞከረችው ነገር ሁሉ ሳይሳካ ይቀርና የበኩር ልጇን በሰላም ለመገላገል ትበቃለች።
ልጇን በሰላም ለመገላገል በቅታ በአያቷ አራሽነት ለስድስት ወር ያህል ከቆየች በኋላ አያቷ በማረፋቸው ሌላ አዲስ ድርብ ድርብርብ ችግሮች ከፊቷ ይደቀኑባታል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ ለምንም የማይመቹ የዓመታት ትእግስትን የሚሹና የጊዜን ዳኝነት የሚጠይቁ ነበሩ። የመጀመሪያ ጭንቅ ፍሬህይወት ማርገዟን ካወቀችና የልጅነት ጓደኛዋ ከራቃት ጊዜ ጀምሮ በዛ የቀን ጨለማ ወቅት ልጅ ወልዳ ማሳደጉ እንደ ተራራ የማይገፋ ሲሆንባትና ጭንቀቷ ሲበረታባት ያገኘችው ሰው ሁሉ የሚነግራትንና በሰሚ ሰሚ የሰማችውን በመቀመር በተደጋጋሚ ጽንሱን ለማስወረድ የተለያዩ ነገሮችን ስትጠቀም ቆይታለች። እናም እነዚህን ነገሮች ተጠቅመው ጽንሱ ሳይወርድ ቀርቶ ልጅ ከተወለደ ከአእምሮ ዝግመት እስከ የአካል መጉደል ሊያስከትል እንደሚችል ስትረዳ ልጄ ምኔ አድጋ ጤነኝነቷን ባረጋገጥኩ በማለት ጊዜ ለሚፈታው እውነት በጭንቀት ስትታመስ ዓመታትን ለማሳለፍ ትገደዳለች። በእነዚህ ጊዜያትም የበኩር ልጇ በመሆኗና ስለ ልጅ አስተዳደግና ባህሪ የምታውቀው ነገር ስላልነበር በልጇ ላይ አንዲት የተለየ ባህሪ ባየች ቁጥር በጭንቀት ታሳልፋቸው የነበሩት በርካታ ሌሊቶች ዛሬም ከአእምሮዋ አልተፋቁም።
ሁለኛው ለጊዜ ዳኝነት ብቻ የቀረበው የወይዘሪት ፍሬህይወት ችግር የምትወዳቸው አያቷ አደራ ነበር። የእናትም የአባትም ምትክ ሆነው ሲያሳድጓት የነበሩት አያቷ አንድ መስማትና መናገር የማይችል የአካል ጉዳተኛ ልጃቸውንና በተመሳሳይ መስማትና መናገር የማትችል እህታቸውን ትተው ነበር ወደማይቀረው ዓለም የሄዱት። እናም ካሳደጓት አያቷ ኀዘን በተደራቢ አራስነትና እነዚህን ሁለት የቅርብ እንክብካቤ የሚፈልጉ ቤተሰቦቿን ካለማንም ረዳት የመታደግ ሃላፊነት ጫንቃዋ ላይ ያርፋል። በተለይም የአያቷ ልጅ አጎቷ ራሱን ችሎ መብላት መጠጣት መንቀሳቀስና መጸዳዳት የማይችል በመሆኑ ጊዜ ሰጥቶ ሰአት ጠብቆ እሱን መርዳት የዘወትር ስራ ከመሆኑ ባሻገር የገቢ ምንጭም እሷው ብቻ ነበረች። እናም በእነዚህ ሁለት የተራራቁ እውነታዎች ውስጥ በመሆን ለዚያውም መጨረሻው እስካልልየለት ጊዜ የህይወትን መንገድ መግፋት እንዳለባት ትገነዘባለች። አጎቷ ከልጅነቷ ጀምሮ አብሯት ያደገ በመሆኑ እንኳን በአካል የሚፈልገውን ቀርቶ ህሊናውንም ለማስደሰት አብራው መሆን እንዳለባትም ለራሷ ታሳምናለች። በዚህ ላይ ለጨዋታ እያለ በአካባቢው ያለውን ነገር አላግባብ ሊነካካ ሊወረውርና ሊያጠፋ ስለሚችል ብቻውን እንዲውል ማድረግ አስቸጋሪ ነበር።
በተመሳሳይ የአያቷ እህት አክስቷም መንቀሳቀስ ቢችሉም መናገር የማይችሉ በመሆኑና ስራ ስለሌላቸው የአራት ሰዎች ሃላፊነት የወደቀው ወይዘሮ ፍሬህይወት ላይ ነበር። ያም ሆኖ እሷም ቤተሰቡም ቢያንስ በልቶ እንዲያድር መስራት ስላለባት በየሰአቱ እቤቷ እየተመላለሰች ከልብስ አጠባ ጀምሮ በአቅራቢያዋ ያገኘችውን ሁሉ የጉልበት ስራ መስራቷ ትቀጥላለች። በነዚህ ጊዜያት የነበሩት እያንዳንዶቹ ቀናት ግን እንዲህ በቀላሉ የሚገፉ አልነበሩም፡፡ በአንድ ወቅት ራሷን ለማጥፋት እስከ ማሰብ ደርሳ ነበር፡፡ ሰምጣ ባትቀርበትም የተለያዩ ሱሶች ውስጥ ለመግባትም ተገዳ ነበር። የአያቷ ስራ ፈትል መፍተልና አንዳንድ ዝግጅቶች ሲኖሩ ምግብ ማብሰል ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ቤታቸው አንድም ቀን ጎሎ አያውቅም ነበር። እንኳን የአዘቦቱ በበኣዓላትም ከሚበላውም ከሚጠጣውም ቤተሰቡ የሚቀርበት ነገር አልነበረም። እሳቸው ካረፉ በኋላ ግን ምንም ቢሰራ ምንም ቢለፋ ቤቱ ሊሟላ አልችል ይላል፡፡ እናም አንድ ቀን ነገሮች ሁሉ ሲደራረቡባት በፍጹም ተስፋ መቁረጥ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ሄዳ ታድራለች። እዛ ያያትና ሁኔታዋ ያላማረው አንድ የአካባቢዋ ነዋሪ የሆነውን ነገር ሁሉ ይጠይቃትና በአያቷና በእሷ መካከል ያለውን ይህይወት ልምድ በቀላሉ ማየት እንደሌለባት ነግሮ ወደቤቷ እንድትመለስ ያደርጋታል።
በዚህ ሁኔታ አራት ዓመታትን ካሳለፈች በኋላ ደግሞ ከልጇ አባት ጋር ተገናኝተው ልጅ እንዳለው ብትነግረውም የሆነውን ለማመንና ላለመቀበል በመፈለጉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመለያየት ይበቃሉ። በዛው ዓመት ወይዘሪት ፍሬህይወት በአንድ አጋጣሚ ከተዋወቀችው ልጅ ጋር ትዳር ለመመስረት ትበቃና አንዲት ልጅ ትወለዳለች። የባሏ ቤተሰቦች ሁለተኛ ልጇን ከህጻንነቷ ጀምረው እያሳደጉላት ቢሆንም ባለቤቷ መጠጥ ያዘወትር ስለነበር ከአራት ዓመት በኋላ ትዳራቸው መቀጠል ሳይችል ይቀራል።
ከምንም በላይ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ እሷን ብቻ ሳይሆን በአካል የማታውቃትን እናቷንም እያነሱ ይናገሩት የነበረው ሀሜት ሌላ ራስ ምታት ነበር። ይሄ ደግሞ ከወለደችም በኋላ የተከተላትና ሁሌም ሰላሟን የሚነሳት ነገር ነበር። «ሰው እንኳን ሊለውጥህ ጥረህ ግረህ እንኳን ብትለወጥ መለወጥህን አይቀበልም፤ ቢቀበልም ረጅም ጊዜ ይወስድበታል። የሚቀለው ስምህን ማጥፋትና ሞራልህን ማድቀቅ ብቻ ነው፤ ስለዚህ ሁሌም ጠንካራ መሆን ነበረብኝ» ትላለች ከዓመታት በፊት የነበረውንና ያሳለፈችውን ነገር ወደኋላ ተመልሳ ስታስታውስ ።
በዚህ የጭንቅ ህይወት ውስጥ እያለች ነበር የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ህይወቷን መስመር የሚያሲዝላት አጋጣሚ የተፈጠረው። በምትኖርበት ወረዳ በኩል «መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት» ከሚባልና በሴቶችና ልጆች ላይ ከሚሰራ ድርጅት ጋር ለመገናኘት ትበቃለች። ድርጅቱ ያለችበትን ሁኔታ ካጠና በኋላ መጀመሪያ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንድትወስድ ያደርጋል። ከስልጠናውም በኋላ ከእለት መሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦት ጀምሮ ድጋፎች ማግኘት ትጀምራለች። በመሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ለእለትና ለመቋቋሚያ ከሚደረገው ድጋፍ ባለፈ የሚሰጣቸው የህክምና አገልግሎት ትልቅ እረፍት እንደሰጣትም ትናገራለች። በተለይ በአንድ ወቅት ልጇ ትርፍ አንጀት ሲያማት በፍጥነት ህክምናውን ባታገኝ ሊደርስ የሚችለው ነገር ለእኔ የዘላለም ጸጸት ነበር ትላለች። ከትምህርት ቁሳቁስ ግብአት ድጋፍ ባለፈ በድርጅቱ ለልጆቹ በየወሩ ሃያ ሃያ ብር ተቀማጭ ይቀመጣል፡፡ ይሄ ለእሷም ለልጆቿም ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነም ትናገራለች።
ከሁሉም በላይ ግን የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅትን በመቀላቀሏ ሌላ ህይወቷን የቀየረ አጋጣሚም ይፈጠርላታል። በአንድ ወቅት ለድርጅቱ ስራ በመንቀሳቀስ ላይ እያለች ግድግዳ ተደግፎ በተሰራ የጎዳና ላይ የላስቲክ ቤት ውስጥ ሁለት ልጆቿን ይዛ የምትኖር እናትን ታያለች። ሴትየዋ ሁለት ልጆቿን በዛች ጣራ ግድግዳዋ የላስቲክ በሆነች ጠባብ ክፍል ውስጥ እሳት አያይዛ ምግብ አብስላ አልጋ አንጥፋ እየተኛች ታገኛታለች ልጅቱን ቀርባ ስታናግራት ደግሞ ብዙ ተስፋ እንዳላት ይሄ ቀን እንደሚያልፍ ትነግራታለች። ያን ጊዜ ፍሬ ህይወት በርካታ መከራዎችን ያሳለፈች ቢሆንም የተሻሉ ነገሮች እንዳሏትና ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ከፊቷ እንደማይኖር ትገነዘባለች።
ወይዘሮ ፍሬ ህይወት ዛሬ «ማን ያውቃል» ብላ የተመዘገበችው የጋራ መኖሪያ ቤትም አያት ጨፌ እጣ ወጥቶላት የቤት ባለቤት ለመሆን ትበቃለች። የኮሮና መከሰት እንቅፋት ቢሆንባትም በድርጅቱ በተሰጣት ስልጠና መሰረት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች ትንሽ ትንሽ ትቆጥብ ስለነበር ቅድሚያውን ከፍላ አሁንም በየወሩ የሚጠበቅባትን እየከፈለች ቤቱንም አከራይታ እየኖረች ትገኛለች። የመጀመሪያ ልጇም ሃያ አመት የሞላት ሲሆን በአንድ ኮሌጅ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ስትሆን ሁለተኛ ልጇ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ናት። ካሳለፍኩት አስቸጋሪ ህይወት ይልቅ ዛሬ በልጆቼ ላይ ያለኝ ተስፋ ከምንም በላይ ብሩህ ነው የምትለው ወይዘሪት ፍሬህይወት ያለፉትን ስድስት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ አካሉን መቆጣጠር የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረውና እንደ ወንድሟ የምታየው አጎቷ ከወራት በፊት ህይወቱ ማለፉ ኀዘን ውስጥ እንደ ከተታት ትናገራለች። በተጨማሪ እኛን ከእሷ ጋር በደንብ የሚግባቡ ነገር ግን ድምጽም የማያወጡ የምልክት ቋንቋም የማይችሉት አክስቷ ነገር ግን የዘወትር ጭንቀቷ እንደሆነባት እንዲህ ትገልጻለች። «ያለንበት ሁለት ክፍል ቤት የቀበሌ ነው፤ አያቴ ስትሞት በሞተው አጎቴ በልጇ ስም አዛውሬው ነበር፤ አሁን ህመምተኛ አክስቴን ይዤ ልቆይ የምችልበት ቤት ይሄ ብቻ ነው፤ መንግስት ካስወጣኝ ያሳልፍኩት የመከራ ህይወት እንዳይደገም እፈራለሁ»።
«ሴቶች መንቃት አለባቸው» የምትለው ወይዘሮ ፍሬ ህይወት በተለይ በወጣትነት ዘመን ለችግር ላለመዳረግ የእያንዳንዷ ቀን እርምጃ ጥንቃቄና ማስተዋል የተሞላበት መሆን አለበት። ችግርም ሲከሰት ተስፋ ቆርጦ ለሽንፈት እጅ ከመስጠት ይልቅ ቀኑ እንደሚያልፍ አውቀው መታገስ አለባቸው፤ ያገቡም ቢሆኑ ከመፋታትና ልጆችን ለችግር ከመዳረግ አስር ጊዜ ሊያስቡና ሊታገሱ ይገባል ስትል ትመክራለች።
የመሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሰረት አዛገ «ሴቶችን መደገፍ ቤተሰብን መታደግ ነው፤ በትንሽ ድጋፍ ብዙ ማትረፍም የምንችለው ሴቶችና ልጆች ላይ ትኩረት አድርገን ስንሰራ ነው፤ ወይዘሪት ፍሬ ህይወትም ለዚህ አንድ ማሳያ ናት» ይላሉ። ዳይሬክተሯ እንደተናገሩት ወይዘሪት ፍሬህይወት ራሷን ከነበረችበት ችግር ለማላቀቅ ትንሽ ቀዳዳ ስትፈልግ የነበረች ናት። እናም እኛ ጋር ስትመጣ የተነገራትንም የተሰጣትንም በአግባቡ መተግበርና መጠቀም ስለቻለች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ችላለች። ዛሬ ከራሷም አልፋ እኛ ጋር ለሚመጡትም ሆነ በአካባቢዋ ላሉት የጽናት ዓላማ ናት ይላሉ። ወይዘሮ መሰረት በሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ስለሚሰራው የበጎ አድራጎት ድርጅታቸውም ሲናገሩ። መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት የተቋቋመው ተገደውና ተታለው ልጅ የወለዱና የቤተሰብ ሃላፊ የሆኑ ሴት ልጆችን ለመታደግ ነው። በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ለ711 እናቶችንና 1097 ልጆችን የእለት ደራሽ ምግብ የትምህርትና የስነ ልቦና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። አንድ እሽግ ለአንድ ልጅ በሚል ፕሮግራምም በአምስት ክልሎች በሚገኙ 47 ጣቢያዎች 15 ሺ የገጠር ልጆችን ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን እስካሁን በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑት ተማሪ ልጆች ቁጥር ከ አንድ መቶ ሺ በላይ ደርሷል።
የአካባቢ ጥበቃንም ከሴቶች አቅም ግንባታ ጋር በማያያዝ በተሰራው ስራ በኮንሶ 81 ሺ ሄክታር ጠፍ መሬት ከመንግስት በመቀበል በእጽዋት እንዲሸፈን ያደረገ ሲሆን በአምቦ ከተማም ተመሳሳይ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ጥበቃ ስራ እየሰራ ይገኛል። የሴቶች ቁጠባ፤ ባዮ ጋዝ ማምረት፤ የወጣቶች አቅም ግንባታና ማህበራዊ ተጠያቂነትን ጨምሮ ሌሎች ህብረተሰብ ተኮር ችግር ፈቺ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። ሴቶችና ህጻናትን ጎዳና እንዳይወጡ ከመከላከል ባሻገር የወጡትንም መልሶ ለሟቋቋም ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን 172 እናቶችን ከነልጆቻቸው ከጎዳና በማንሳት በሁለት አመት ውስጥ ለማቋቋም የጀመሩት ፕሮጀከት የኮሮና ስርጭት ከተገታ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ወደ ተግባር እንደሚገባ ዳይሬክተሯ ወይዘሮ መሰረት ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ