ሲመሽ የሚራወጠው አዲስ አበቤ ሁኔታው ለእንግዳ ግር ያሰኛል። ያገኘውን መጓጓዣ ተጠቅሞ ወደ ቤቱ የሚሮጠው የከተማዋ ነዋሪ፤ ከአንዳች ነገር አምልጦ እስከ መጨረሻው የሚሸሽ እንጂ ነግቶ ወደ ስራ ገበታው የሚመለስ አይመስልም። ሲነጋ ወደ ስራው ሲመሽ ወደናፈቁት ቤተሰቦቹና ማረፊያ ጎጆው ይራወጣል።
መኖሪያዬ ከመስሪያ ቤቴ ስለማይርቅ አምሽቼ መስራት አዘወትራለሁ። ዛሬ ግን አንዳች ጥሪ ያለብኝ ይመስል በስራ መውጫ ሰዓት ኮምፒዩተሬን አጠፋፍቼ ወጣሁ። የሀገሪቱ ታላላቅ ጉዳዮች ማስተናገጃ የሆነው መስቀል አደባባይ ጠዋትና ማታ በእግር ሽር የምልበት ሰፊ ጎዳና ነው። የእግር ጉዞ ማድረግ እጅግ እወዳለሁ። በተለይ ምሽት ላይ ድካም ካልሆነ ርቀት ለይቼ ከመንገዴ አልገታም።
ከፊላሚንጎ ወደ መስቀል አደባባይ በሚወስደው መንገድ እጄን በኪሴ ሸጉጬ በእርጋታ ወደፊት እየተጓዝኩ ነው። የሰማዕታት ሀውልት ጋር ስደርስ ከፊት ለፊቴ ባየሁት ነገር ሳላስበው ጉዞዬ ተገታ። ከወደ ኡራዔል አቅጣጫ እኔ ወዳለሁበት ከሌሎች የበዙ እግረኞች ጋር በአጀብ ስትሻገር ባየኋት ልዕልት ፈዘዝኩ፤ ከፍ ያለ ስሜት ውስጥ ተዘፍቄ ደነዘዝኩ እንጂ። ሁለመናዬ ተደናግሮ የሚሰራው ልቤ ብቻ ይመስል ደረቴ ላይ ሲደልቅ ይሰማኛል።እራሴን ለመቆጣጠር ሞከርኩ አልሆነልኝም።
“እንዴ ምን ነክቶኝ ነው?” ለራሴ የሆንኩትን መጠየቅ ያዝኩ ምላሽ ሳጣ እራሴን ታዘብኩት። ሌላኛው የመንገዱ በኩል ነበረችና ለመሻገር ወደኔ ስትቀርብ ይበልጥ ብርክ ያዘኝ። ባማረ ተክለ ሰውነትዋ ላይ የዘነጠ አለባበስ ተጎናፅፋ በመጠነ በቄንጠኛ አረማመድ ሰበር ሰካ እያለች ወደኔ ስተቀርብ ሰውነቴን አንዳች የማላውቀው ድብልቅልቅ ያለ የስሜት መናጥ ውስጥ ተዘፈቀ።
ጎላ ጎላ ብለው በኩል የደመቁት አይኖቿ ያሳሳሉ። የጠዋት ፀዳል የመሰለው ውብ ፊትዋ ሲያዩት ያፈዛል።ብቻ አምላክ ሳይሰስት በውበት ያስጌጣት ልዩ የውበት አክሊል የደረበች ልቅም ያለች ቆንጆ ናት።የራስ ማድረግ የሚመኝዋት አብረዋት ሊኖሩ የሚጓጉላት ልዕልት።የግሌ በሆነች ብዬ ሳለውቅ ተመኘዋት።
አልፋኝ ስትሄድ አንገቴ ተጠማዘዘ። እግሬም ሳላዛው ቆሜ ከነበረበት ወደ ኋላ ዞሮ ማጣቱን ያልወደደው ውበት መከተል ጀመረ።እራሴን እንደምንም ተቆጣጥሬ ከኋላዋ መከተል ተያያዝኩት። በሁኔታዬ ግራ ብጋባም ስለስዋ ብዙ ማሰብ ጀመርኩ።
ከራሴ ጋር ሙግት ጀመርኩ።ጭንቅላቴ መልስ የሌላቸው ጥያቄዎችን እራሱን እየጠየቀ ፋታ አጥቷል። ሁለመናዬ ለዚህ ቅጽበታዊ ስሜት እጁን ሰጥቶ የእግሬን እርምጃ ብቻ መቆጣጠር ጀምሯል።ሳላናግራት መመለስን ጠላሁ። በምንም መልኩ ይህቺን ልጅ ማውራት አለብኝ። የፍቅር ስሜቱ ባውቀውም ዛሬ ተለይቶብኛል። ፍላጎቴን መግደል አልፈለኩም። ልጠጋት ወሰንኩ።
ቁና ቁና እየተነፈስኩ ከኋላ ደረስኩባት። ከእርምጃዎች በኋላ ታክሲ ተራ ደርሳ ሁሉ ነገር ቅጽበታዊ ገጠመኝ ብቻ ሆኖ ሊያልፍ ይችላል። መፍጠን አለብኝ። በምንም መልኩ ይሄን ስሜት የፈጠረብኝን፣ ውስጤን ተቆጣጥሮ ያራወጠኝን፣ እራሴን ከቁጥጥር ውጪ አድጎ ያለ ቦታዬ ያስገኘኝን ስሜት እንደ ቀልድ ማለፍ ውስጤ አልፈቀደውም።
በሆነ መልክ በድጋሚ እስዋን ማግኘት የምችልበትን ዘዴ መፍጠር አለብኝ። ፊላሚንጎ ሬስቶራንት ፊት ለፊት ታክሲ መያዣ ጋር ቆመች ። ቦታው ላይ ሌሎች ሁለት ሰዎች ታክሲ ጥበቃ ቆመዋል። መፍጠን አለብኝ አዎ ታክሲ መቶ ሁሉ ነገር እንዲበላሽ መፍቀድ የለብኝም።
ይበልጥ ተጠጋኋት “ሰላም እህት” ፊትዋን ቅጭም አድርጋ ዞራ አይታኝ ሳታናግረኝ አንድ እርምጃ ወደፊት ተራመደች። ድንጋጤዬ ቢጨምርም ጀምሬዋለሁና መጨረስ ግድ ይለኛል። እኔም ተጠጋኋት ። የመጣው ታክሲ አንድ ሰው ብቻ ጭኖ ሄደ። ወደ ኋላ ተመለሰች። ይቅርታ እህት፤ ግድ ሆኖብኝ ነው የማስቸግርሽ። ብር ሳሊዝ ጓደኞቼ ቀጥረውኝ ተጣድፌ ከቤት ወጣሁ ዋሌቴን እንኳን አልያዝኩም ኤቲኤም እንዳልጠቀም። ሶሪ ግን የግድ ቢሆንብኝ አንቺን መጠየቄ ደሞ ለውጥ ነው።
ከላይ እስከታች ገረመመችኝ። አቤት ሰው ተኮሳትሮም ያምራል፤ስታምር። “ስታለቅሺ ደስ አልሽኝ” የሚለው ዘፈን ልክ መሆኑ ያኔ ነው የገባኝ። ጭራሽ ውበትዋ ስትገረምመኝ የጎላ ያህል ተሰማኝ። አለባበሴን ስታይ ቀፋይ አይደለም ብላ አሰበች መሰለኝ ፊትዋን መለስ አድርጋ “የት ነው ምትሄደው?” ብላ ስትጠይቀኝ ውስጤ ፈካ።
“እ..ቦሌ ቦሌ ነው ያሉት ጓደኞቼ እዚያ መድረሻ ብቻ.” ቦርሳዋን ከፈት አድርጋ የአስር ብር ኖት መዛ አውጥታ ዘረጋችልኝ። ደግነትዋ ገዝፎ ታየኝ። “አመሰግናለሁ ግን ስጦታ አይደለም የፈለኩት ስልኬ ላይ ብር አለ ወደ ስልክሽ ብር ልላክልሽና የላኩት ያህል ትሰጪኛለሽ ለውጥ ነው የፈለኩት። ይቅርታ ግን። “ኧረ ግድ የለም ይገጥማል፤ ችግር የለም ወንድም እንካ ውሰድ”
“አመሰግናለሁ ለትብብርሽ እህት ግን የምቀበልሽ ከስልኬ ላይ ወዳንቺ ብር ካስተላለፍኩ ነው ደሞ የጠየኩሽ 3 ብር ነው።” እርግጥ አድርጌ ነገርኳት መች የታክሲ ብር መለመን ሆነና አላማዬ። “ አረ ግድ የለም ይሄ የሚካበድ አይደለም እኮ እንካ ተቀበለኝ።” እጅ መስጠት አላማን ያስነጥቃልና ፈጽሞ መምረር እንዳለብኝ ተረዳሁ። “ይቅርታ በዚያ መልክ መለዋወጥ ካልሆነ አልቀበልም ስለተረዳሽኝ አመሰግናለሁ። በቃ በእግር ወደ ቤት ልመለስ ምንም ማድረግ አልችልም።” ብዬ ፊቴን አዞርኩ በውስጤ ነገሩ እንዳይበላሽ አምላኬን እየተማጸንኩ።
ወዲያው “እሺ ና ቆይ ይሄ ገንዘብ ሆኖ ነው እንዲሁ ብትቀበለኝ ምን አለ?” ፈገግ ብዬ “አይ ግድ የለም ቀና ሰው ነሽ የእውነት በቃ አላስቸግርሽ እህቴ” አልኳት “ሆ ምኑ ደረቅ ነህ እሺ በቃ ላክ” አለችኝ። ውስጤ በደስታ ተሞላ፤ ሃሳቤ ሊሳካ ነው። ቁጥርዋን ነግራኝ 5 ብር አስተላለፍኩላት።ስልክዋን አይታ 5 ብር አውጥታ እጅዋን ወደኔ ዘረጋች።
በዘዴ ቁጥሯን መቀበል ነበረና የፈለኩትን ተሳካልኝ። መሄድ አሰኝቶኝ ነበር ግን ደግሞ በፈጠርኩት ውሸት ተናዳ ስልክ ባታወራኝስ ብዬ በማሰብ አበሬያት ቆሜ ታክሲ እየጠበኩ ቁጥሯን ብር ልኬላት ከመጣልኝ መልዕክት ላይ አውጥቼ መዘገብኩ።
ታክሲ መጣና አብረን አንድ ታክሲ ውስጥ ገብተን ጎን ለጎን ተቀመጥን። ስለስዋ ብዙ እያሰብኩኝ ነው። የተሳፈርንበት ታክሲ ደንበል አደባባይ እንደተሻገረ ስልክዋ ተጣራ። አንስታ ማውራት ጀመረች። “ ወዬ ውዴ ታክሲ ውስጥ ነኝ መጣሁ፤ እኔም በጣም ናፍቀኸኛል ውዱ ባሌ እየደረስኩ ነው። ” ተደናገጥኩ ስልክ የያዘችበት ጣትዋ ላይ ቀለበት መኖሩን ተመለከትኩ። ሰውነቴ በድንጋጤ ቅዝቃዜ ተሰማኝ። ከዚያ በኋላ ያወራችውን መስማት አልቻልኩም። ለረዳቱ “ወራጅ አለ” አልኩት። ከታክሲ እንደወረድኩ እራሴን እንደምንም አረጋግቼ ከኪሴ ስልኬን አውጥቼ የአንድ ሰው ቁጥር አጠፋሁ። ከደቂቃዎች በፊት የመዘገብኩትን።
ተፈፀመ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2012
ተገኝ ብሩ