የመላመድ አባዜ
በአገራችን የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የመረዳዳት ባህላችን አንድ ደረጃ ከፍ ሲል ተፋዞ የነበረው ማህበራዊ መደጋገፋችንም እንዲያንሰራራ ዕድሉን አግኝቷል፡፡ በዋናነት በወቅታዊው ጉዳይ ሥራቸውን ላጡ፣ ለተቀዛቀዘባቸውና ለአቅመ ደካሞች አስፈላጊውን ሁሉ ለመደጎም በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች ድጋፍ ሲያደርጉ እያስተዋልን ነው፡፡ ይሄ የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡
እውነታው ይሄ ቢሆንም ግን አንዳንድ የሚያሳዝኑ ነገሮችንም ከበጎ ተግባሩ ጎን ለጎን አብረን መታዘባችን አልቀረም፡፡ ለእርዳታ የቀረቡ ዕቃዎች ርቀታቸውን ጠብቀው የሚወስዳቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሆኖም በተግባር የተመለከትነው በአንዳንድ የድጋፍ መስጫ ቦታዎች ሰዎች ጥንቃቄ ካለማድረጋቸውም በላይ የእርዳታ አስተባባሪዎች አቅመ ደካሞችን ሲጨብጧቸው ነው። ይሄን መመልከት ጥሩ ስሜት አይፈጥርም፡፡
ይህን ስንመለከት «በቃ! ኮሮናን ተላመድነው» የሚል ጥያቄ ይደቅንብናል። ጎበዝ መዘናጋት ይቅርብን እንጂ፡፡ እርዳታ ስናደርግ በሽታ አብረን እንዳንለግስ መጠንቀቅን አንዘንጋ፡፡ ጥረታችን «ግንጥል ጌጥ» አይሁንብና።
ይህ ብቻ አይደለም ብዙዎቻችን ቀደም ሲል እናደርገው የነበረውን ጥንቃቄ አቁመናል፡፡ ተዘናግተናል። በየቀኑ በርከት ያለ የኮሮና ተጠቂ ቁጥሮች ሪፖርት ሲደረጉ የምንሰማ ቢሆንም ደንገጥ ብሎ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ የሚወስደው ሰው እየቀነሰ ነው፡፡ እርግጥ ነው ይሄ የመዘናጋት ጉዳይ በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ የሚታየው በኮሮና ወረርሽኝ ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሌም አዳዲስ ነገሮች ሲከሰቱ ጭምር ነው። መርሳት ሳይኖርብን ከአንድ ሳምንት በኋላ የተላመድናቸው ነገሮች በርክተዋል፡፡
እስኪ አብነት እናንሳ። ለቀናት ሲያከራክር የነበረው የአልኮል መጠጥ ዋጋ ጭማሬ ዛሬ ምን ደረጃ ላይ ነው። በወቅቱ ቢራና የመሳሰሉት መጠጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ «እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል?» በማለት የተቃወሙ ብዙዎች እንደነበሩ እናስታውሳለን።
የፋብሪካ ባለቤቶችም «ተጠቃሚ አይኖርም፤ ፋብሪካችንን ልንዘጋ እንችላለን በውስጣችን ያሉ ሠራተኞችም ይበተናሉ…» ሲሉ ተደምጠው ነበር። እውነትም ለጊዜውም ቢሆን በርካታ ግሮሰሪዎች ቀዝቅዘዋል፡፡ አንድ ሁለት ብለው የሚገቡ ደንበኞች በጊዜ ወደ ቤታቸው (እያጉረመረሙም ቢሆን) ገብተዋል። አላስችል ያላቸው ከኮታቸው ቀንሰው ከሁኔታው ጋር እራሳቸውን ለማላመድ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
ከሳምንት በኋላ የተፈጠረው ግን ተቃራኒው ነው። ሁለት የምጠጣበትን አንድ፣ አራት የምጠጣበትን ሁለት ወዘተ እያሉ መጠጣት የጀመሩ ደንበኞች ከቀን ወደ ቀን ቃላቸውን እየሰበሩ በመምጣታቸው የመጠጥ ቤቶች በድጋሚ ወደነበሩበት ቦታ ተመለሱ። አፈር ነህና ወደ አፈር … ይሏል ይሄኔ ነው። ፍርሃት ሲያንዘፈዝፋቸው የነበሩ የአልኮል ፋብሪካዎች፣ ደንበኛ ስላጣሁኝ ሥራዬን አቁሜያለሁ ብለው ሪፖርት ያደርጋሉ ተብለው የተጠበቁ መጠጥ ቤቶች በፌሽታ ተሞሉ። ሁሉም ወደ ቀድሞው ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመለሳ፡፡ ዛሬ ላይ ማንም ሰው የመጠጥ ዋጋ አያሳስበውም። በየመጠጥ ቤቶች የሚታየው ሰው ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ድርጅታችን ይዘጋል፤ ሠራተኞቻችን ይበተናሉ ያሉ ሁሉ አሁን ተረጋግተዋል። ድራፍቱን በእስትሮ እያሉን ነው። ይሄ ታዲያ የመልመድ አባዜ ማሳያ አይሆን ይሆን?
አሁንም እየተስተዋለ ያለው በቀላሉ ወረርሽኙን የመላመድ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለበሽታው መስፋፋት መልካም አጋጣሚን ፈጥሮለታል፡፡ የኮሮና ወሬ አዲስ እንደሆነ አካባቢ ሁሉም ሰው በቤት ውስጥ መዋል ጀምሮ ነበር፡፡ አብዛኞች የከተማችን አውራ መንገዶች ሰው አልባ መሆን ችለው ተመልክተናል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የከተማችን አውቶቡሶች ትኬት ሻጩና ሹፌሩ ብቻ ሲመላለሱ ለጥቂት ቀንም ቢሆን ታዝበናል፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ በሁለት ሰዎች መካከል አንድ ወንበር ክፍት አድርገው ወደ ማጓጓዝ ተሸጋገሩ፡፡ አሁን ይሄ ተቀይሯል። በወንበሮች ሙሉ መጫንን ተለማምደዋል፡፡ እንዲሁም ከኮሮና ጋር ከመላመዳችን በፊት ወደ አውቶቡስ ውስጥ የሚገባ ሁሉ እጅ ማፅጃ ይደረግለት ነበር፤ አሁን ይሄ ቀርቷል። ኮሮናን ተላመድነው ማለት አይደል። እሱ ግን ቂም በሆዱ ቋጥሮ ሥራውን ቀጥሏል።
ታክሲዎችም የወጣውን አዋጅ ተከትለው ከስድስት ሰው በላይ አይጭኑም ነበር፡፡ በሽታውን ከተላመዱ በኋላ ግን መጠንቀቁና ሕግ ማክበሩ ለጊዜው ብቻ መሆኑን የወሰኑ ይመስላሉ። ሕግ አስከባሪ መኖር አለመኖርን እየተጠባበቁ አንድ ሰው ወደ መደረብ መሸጋገራቸውን በዓይናችን አይተናል። ምን ይሄ ብቻ መንገዶችም በሰዎች ተሞልተዋል፡፡
በርካታ የምግብና የመጠጥ ቤት አስተናጋጆች በኮሮና ምክንያት ተጠቃሚ አጥተው አብዛኛውን ጊዜያቸውን በድብርት ነበር የሚያሳልፉት፡፡ ይሄ ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር እስኪውል አልቀጠለም፡፡ አሁን ምግብና መጠጥ ቤቶች መቀመጫ እስኪጠፋ ድረስ በሰዎች ተጨናንቀዋል። አስተናጋጆችም እንኳን ሊደበሩ ቁጭ የሚሉበት ጊዜ የላቸውም፡፡ አስፈሪው ነገር ግን ወረርሽኙ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ቅብጠት ምን ልንለው እንችላለን? የመላመድ አባዜ?
የመዘንጋት እና የመላመድ ተግባራትን ልናርቅ ይገባል። ቢያንስ ቢያንስ የቢራ ዋጋ መናሩን መልመዳችን አይከፋም። ኮሮናና መጠጥ ለየቅል ናቸው፡፡ ኮሮናን መልመድ በዚህ ምድር ላይ የመቆየት ያለመቆየት እጣፈንታችንን ይወስናል፡፡ አሁን አሁን እንደ በፊቱ እጅን በፍጥነት መታጠብም አቁመናል፡፡ አንድን ነገር እንዲህ በቀላሉ መልመድ ከቻልን ምን አለበት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ መተሳሰብን፣ አብሮ በጋራ መኖርንና በጥቅሉ የዕለት ተዕለት ኑሮአችንን የሚያቀሉልንን ነገሮች መልመድ ተሳነን፡፡ ሁኔታው ትንሽ ግራ ያጋባ ይመስላል። አእምሯችን የተከለከለውን እንደሚፈልግ ሕፃን ልጅ፤ ከሚጎዳን እንድንላመድ ይገፋፋናል።
ወዳጄ ጊዜው ከኮሮና ጋር መላመድ ሳይሆን መጠንቀቅ ይጠይቃል። ባላወቅነው ጸባይ እጅ ከምንሰጥ እዚያው በሩቁ ብለን ብንራራቅ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም ይበጃል፤ የትራንስፖርት አጠቃቀማችንም ይስተካከል፡፡ የግዴታ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር እንቅስቃሴያችን በቤታችን ይገታ፡፡ ከኮሮና ጋር ሳይሆን እቤት ከመዋልና ከመጠንቀቅ ጋር እንላመድ፡፡ ሰላም!
ሞገስ ፀጋዬ
ከእርሶ ለእርስዎ
ቤት መዋል ከጀመርኩ ጀምሮ እየወፈርኩ ነው ምን ትመክረኛለህ?
ቤዛዊት ለማ (ከሳሪስ)
መልስ፡- ከምትበይው ለሌሎች አካፍዪ
ግብፅ ወደ ድርድሩ የተመለሰችው ለምን ይመስልሀል?
ሙሉጌታ ተገኝ (ከመርካቶ)
መልስ፡- ጣሊያን መክራት
ከምግብ የሚጥምህ ምን ዓይነት ነው?
ሳቤላ (ከ4 ኪሎ)
መልስ፡- ተጋብዤ የምበላው
ማንበብ አልወድም ግን ደግሞ ብዙ መፃፍ እፈልጋለሁ ምን ላድርግ?
ወርቅነህ ቱፋ (ከአዳማ)
መልስ፡- መሰረት የሌለው ቤት ልትሰራ አስበሀላ
ኮሮና በዚሁ ከቀጠለ ምን ልታደርግ አሰብክ?
ሙሉ ሰው (ከጎንደር)
መልስ፡- መደበቅ
ኮሮና እንደገባ በየመንገዱ እጅ ሲያስታጥቡ የነበሩ ልጆች የት ሄዱ?
መልስ፡- ውሃ ፍለጋ
የፊት ጭንብል ሁሉም ካደረገ እኔ ሳላደርግ ብዞር ኮሮና ሊዘኝ ይችላል?
ቶማስ ነኝ (ከቤላ )
መልስ፡- የዚህን መልስ እንኳን እኔ ኮሮናም አያውቅ
የኮሮና የቅርብ ወዳጅ ማን እንደሆነ ታውቃለህ?
ዘላለም ዘርጋው (ከካራ)
መልስ፡- መዘናጋት
አሜሪካ ግን የዴሞክራሲ መብት እኔ ጋር ተረጋግጧል እያለች፤ በጥቁሮች ላይ የሞት መከራ ለምን ይደርሳል?
ኢሳያስ ሞጆ (ከባህርዳር)
መልስ፡- ዴሞክራሲ ተረጋግጧል ነው ተረግጧል ያለችው? እስኪ አረጋግጥ
በትርፍ ሰዓትህ አብዝተህ የምታደርገው ምንድነው?
መልስ፡- እጄን መታጠብ
ተገኝ ብሩ
አስደናቂ እውነታዎች
ወፎች አይሸኑም፡፡
• ጉንዳኖች ፈፅሞ አይተኙም፤ሳንባ የላቸውም፤
• ጉንዳን እስከ 7 ዓመት ሊኖር ይችላል ንግስቷ ግን እስከ 15 ዓመት ልትኖር ትችላለች::
• ሻርክ ብቸኛው የማይታመም እንስሳ ነው። ምንም ዓይነት በሽታ አያጠቃውም ካንሰርን ጨምሮ::
• ፈረሶች እና ላሞች ቁመው ነው የሚያንቀላፉት::
• የማር ንብ ሁለት ሆድ ሲኖራቸው አንዱ ለማር ሲሆን ሁለተኛው ለሚመገቡት ምግብ ማስቀመጫ ያገለግላቸዋል::
• ትልቁ ነጭ ሻርክ ከሦስት ወር በላይ ሳይበላ መጓዝ ይችላል::
• አብዛኞቹ ዝሆኖች በክብደት ከሰማያዊ ዓሣነባሪ (Blue whale) ምላስ ያንሳሉ::
• በረሮ በረሀብ እስኪሞት ድረስ ለሳምንት ያህል ጭንቅላቱ ተቆርጦ በሕይወት መቆየት ይችላል::
• የአህያ ዓይን አቀማመጥ በአንድ ጊዜ አራቱንም እግሮች ማየት ያስችሉታል::
• ዶልፊን ውሃ ውስጥ ከ24ኪ.ሜ ርቀት ያለ ድምፅ በቀላሉ መስማት ይችላል::
• የወባ ትንኝ (Mosquito) 47 ጥርስ አላት::
• ማንኛውም ሁለት የሜዳ አህያ(zebra) አንድ ዓይነት መስመር አይኖራቸውም::
• ቢራቢሮ የሚቀምሱት (taste) በኋላ እግራቸው ነው::
• የወንድ ሸረሪት የወሲብ አካል በአንዱ የእግሩ ጫፍ ላይ ይገኛል::
• ንቦች አምስት ዓይን አላቸው::
• አሳማ በተፈጥሮ(physical) ወደ ሰማይ ማየት አያስችለውም::
• አይጥ ከተራበች የራሷን ጅራት ትበላለች።
• ለሚስቱ ታማኝ የሆነ እንስሳ ቀበሮ ብቻ ነው።
• ሰማያዊ ዓሣነባሪ (Blue whale) በመጠን እስካሁን በዓለማችን ከነበሩ እና ካሉ እንስሳዎች ትልቁ ነው::
• የሌሊት ወፍ ብቸኛዋ ከአጥቢዎች መብረር የምትችል ስትሆን የእግር አጥንቶቿ ከመቅጠናቸው የተነሳ መብረር እንጂ መራመድ አይችሉም::
• የሌሊት ወፍ ምንጊዜም ከዋሻ ሲወጡ ወደ ግራ ይበራሉ::
• እባብ ዓይኖቹ ቢከደኑም በዓይኖቹ ቆብ ማየት ይችላል::
• ወንድ የወባ ትንኝ አይናደፍም ሴቷ ብቻ ናት መናደፍ የምትችለው::
• የዱር አይጥ በፍጥነት መራባት የሚችሉ ሲሆን በ18 ወራት ብቻ 2 አይጦች 1 ሚሊዮን ዘመዶችን ማፍራት ይችላሉ::
• አንድ ንብ አንድ የሾርባ ማንኪያ ማር ለማዘጋጀት ከ4000 በላይ አበቦችን መጎብኝት አለባት::
• ቀንድ አውጣ ለ3 ዓመት መተኛት ይችላል::
• አንድ ላይ የተያያዘ የሸረሪት ድር ተመሳሳይ ወፍረት ካለው አንድ ላይ ከተያያዘ የብረት ሽቦ ይጠነክራል::
• ዝሆኖች ከ3ማይል ላይ ያለ ውሃ ማሽተት ይችላሉ::
• ኦይሰትር የተባለ የዓሣ ዝርያ ከአንዱ ፆታ ወደ ሌላኛው እንዲሁም ወደ ነበረበት ለወሲብ በሚመቸው
• ፆታውን መቀየር ይችላል::
• በየዓመቱ 1/3 የሚሆነው የዓለማችን ሰብል በተባይ/ ነፍሳት ይወድማል::
• ምንጭ ፡-New Information
ዲጂታል የኔቢጤ ‹‹ጎፈንድሚዎች››
ሰው ከክብሩ ወርዷል። ሂሳዊና የሞራል ውድቀት የገጠመው በዝቷል። ከልክ ያለፈ ራስ ወዳድነት ተጭኖ በግል ፍላጎቱ የናወዘውን ቤት ይቁጠረው። ሙሉ አቅሙን ለጥፋት፤ ለቅጥፈት ያውለዋል። ይገርማል! ደግሞ በዚህ ቢያበቃ ጥሩ። ክፋት እንዴት እንጀራ ይሆናል? ቁጭ ብሎ ነገር እንደ ዳንቴል እየጠለፈ፤ ሌላው ለግብሩ ይከፈለዋል። ረብጣ ገንዘብ በባንክ ደብተሩ ውስጥ ሰተት ብሎ ይገባለታል።
ስለተንኮል ፀልዮ ጠዋት ከአልጋው ይነሳል። ለክፋት ይበላል፤ ለእኩይ ያጌጣል። ይገርማል! ምን እሱ ብቻ…ልቦናው የታወረውስ? መልካሙን የሚጠየፍ፤ ለጥላቻ ጆሮው ክፍት። እርሱም እንደሌላው ዓይኑን በአይበሉባው እያሸ በግራ ጎኑ ይነሳል።
ድሮ ድሮ እጁ ለስንፍና የቀረበ፤ በየጥጋጥጉ ምእመን አጭበርብሮ ሆዱን ይሞላ ነበር። ይሄ በየመንገዱ የምናየው ሃቅ ነው። ለልመና መኪናና ድምፅ ማጉያ ስፒከር የሚከራይ አይተናል። እውነት የያዘው በሃሳዊው ጉሮሮው ይዘጋል። አሁን አሁን ከዚህም የባሰ መጥቷል። ዲጂታል የኔ ቢጤዎች ….ጎ-ፈንድ-ሚ-ዎች በዝተዋል። የማህበራዊ መስኮቶች በነዚህ የልመና ጠበብቶች ተሞልተዋል። ‹‹የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል›› አይደል አባባሉ።
‹‹የምሰራበት የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደልቤ ለማናከስ ስላልተመቸኝ በግሌ ዩትዩብ ልሰራ ስላሰብኩ ጎ ፈንድሚ አካውንቴ ላይ ያላችሁን ጣል ጣል አድርጉልኝ›› ይሄ በየዕለቱ የምንሰማው ሃቅ ነው። ጥላቻን ለመዝራት የሰው ኪስ ውስጥ የሚገቡት ስንቶች ናቸው? ክቡር ሕይወት በእርሱ ምክንያት ጠፍቶ በነጋታው የድረ ገፅ ገንዘብ መሰብሰቢያ ከፍቶ በመቶ ሺህ ዶላሮች ይሸቅላል። ይገርማል!
‹‹የእከሌን ብሔር ወክዬ ከእከሌ ጋር እሰጣ አገባ ውስጥ ነው ያለሁት። እኔ እሟገትላችኋለሁ እናንተ ደግሞ ያላችሁን ጣል ጣል አድርጉልኝ›› ይሄ በየደቂቃው በድረ ገፆች የምንሰማው ሃቅ ነው። ከእነዚህ እኩያን የባሰ ግን ሰጪው አብዝቶ ይገርመኛል። ለመልካሙ ጊዜ የማይፈታው እጁ ተዘርግቶ ሳይ ‹‹ምን ነክቶን ይሆን?›› እላለሁ።
የስንቱ ህሊናው ታወረ፤ ማስተዋሉ የሰለለ። ለጠብ ደረቱን ነፍቶ፤ በዘመን አመጣሽ አጥር ታጥሮ፤ ሰው ለአጥፊው ይከፍላል። የአንድ ሃሳብ ግዞት ቁራኛ ይሆናል። ያሳዝናል። የተዘረጉ እጆች ሁሉ መልካም ፍሬ የያዙ የሚመስለን ስንቶቻችን ነን? ይገርማል!
ለመልካም እጃቸውን የዘረጉ መኖራቸውን አልሳትኩም። ነጠላ ዘርግተው ለምነው ወገናቸውን የሚረዱ ሞልተዋል። እኛ ግን እንዴት እኩዩን ከመልካሙ መለየት አቃተን? ማህበራዊ መስኮት ብዙ እያሳየን ነው። የወገን ድጋፍ የሚሹ መንገድ የወጡ ምስኪን የኔ ቢጤዎች እንዳሉ ሁሉ፤ ሞፈሩን ጥሎ፣ ሥራ ንቆ ልመናንና ማጭበርበርን መርጦ መንገዱን የሞላው እልፍ ነው። እዚህም ሰፈር ያው ነው። ስማቸውን ቀየሩ እንጂ ግብራቸው ግን አንድ ነው። ‹‹ሃሳዊ ዲጂታል ጎ-ፈንድ-ሚዎች›› ዘመናዊ የኢንተርኔቱ ዓለም አጭበርባሪዎች። እንጠንቀቅ!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2012
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2012