የቤት ውስጥ ጥቃት የቅርብ ቤተሰብ በሆኑ በአዋቂዎች ወይንም በጎልማሶች በቤት ውስጥ በሚኖሩ በአብዛኛው ሴቶችና ልጆች ላይ የሚፈፀም አካላዊ ድብደባ፣ ወሲባዊ ጥቃትና ትንኮሳ፤ ሥነ ልቦናዊና የኢኮኖሚ ጥቃትና ጫናን የሚያካትት ወንጀል ነው። የዚህ አይነቱ ጥቃት ከዚህ ቀደምም የነበረ ቢሆንም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት እየተወሰደ ባለው እርምጃ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ ደግሞ በዓለም ዙሪያ እየተባባሰ መምጣቱ እየተነገረ ይገኛል። በኢትዮጵያም የኮሮና መከሰትንና ሥርጭትን ተከትሎ በመንግሥት በተወሰደው በቤት የመቆየት ውሳኔ ተከትሎ ቁጥሩ እየጨመረ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አራጋው ተናግረዋል። በዚህ መነሻ የቤት ውስጥ ጥቃትን ለመከላከል መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምንድ ናቸው ስንል የሕግ ባለሙያና በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አማካሪ የሆኑትን ወይዘሮ ቤተልሄም ደጉን አነጋግረን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
ባለሙያዋ እንዳብራሩት የቤት ውስጥ ጥቃት ከሌሎች የጥቃት አይነቶች ለየት የሚያደርገው በቤት ውስጥ መፈፀሙና ጥቃቱን የሚፈፅመው አካልና ተጠቂው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የቅርብ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ነው። የቅርብ የምንላቸው የቤተሰብ አባላት ደግሞ የትዳር አጋር፤ ወንድም ዘመድና አብሮ የሚኖር ማንኛውንም የቤተሰብ አባል የሚያካትት በመሆኑና በአካል ራስን በማራቅ ችግሩን መከላከል የሚያስችል ሁኔታ አይኖርም። ጥቃቱ በአብዛኛው የሚፈፀመው በሴቶች በተለይ ሚስቶች ላይ ሲሆን እንደየደረጃው ሴቶች ልጆችና ህፃናትና ሌሎችንም ያካትታል። የቤት ውስጥ ጥቃት ለዘመናት አብሮን የኖረ ቢሆንም በአብዛኛው ጥቃት ፈፃሚዎች ከቤት በማይውሉበት የጥቃቱም መጠን የቀነሰ ነበር።
ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መገኘቱን ተከትሎ በየትኛውም የዓለም ክፍል እንደተደረገው ሁሉ ቫይረሱን ለመከላከል የመጀመሪያውና የተሻለው አማራጭ በቤት ወስጥ መቆየት በመሆኑ በመንግሥት ትእዛዝ እየተተገበረ ይገኛል። በዚህም አብዛኛው የቤተሰብ አባል ከሌላው ጊዜ በተለየ ረጅም ሰዓት በቤት ውስጥ ለማሳለፍ ተገዷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የመገናኘት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ በቤት ውስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እየጨመሩና ተደጋጋሚ እየሆኑ መምጣታቸው እየተነገረ ይገኛል። ከላይ እንደተጠቀሰው የጥቃት አድራሾችና የተጠቂዎች ግንኙነት ደግሞ ከሥጋ ዝምድና ጀምሮ የተቀራረበ በመሆኑና የአቅምና የግንዛቤ ከፍተት እንደማህበረሰብም ስላለ ችገሩ ይፋ ሳይወጣና የሕግ ውሳኔ ሳያገኝ እንዲቆይ እያደረገው ይገኛል።
የቤተሰብ ጥቃትን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን አስቸጋሪ ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከልም በመጀመሪያ ደረጃ ጥቃቱ የሚፈፀመው በተለምዶ ለቤተሰቡ ከለላና ጥበቃ ያደርጋሉ በሚባሉት እንደ ባል፣ አባትና ወንድም በመሆኑ ወደ ሕግ የሚደረገውን ጉዞ የተወሳሰበ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የማይታሰብም ያደርገዋል። በሁለተኛ ደረጃ ችግሩ ተከስቶም ከታወቀ በኋላ እንደ ባህል ተችሎ ነው የሚኖረው:: ትእግስት ማድረግ ያስፈልጋል በሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሩን ከሥር መሠረቱ የማይቀርፉ ሽምግልናዎች ስለሚደረጉ ተጠቂዎች እንደታፈኑ በጫና ውስጥ የመቆየት አድላቸው ሰፊ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትዳር አጋር የሚፈፀም ሲሆን ደግሞ በተለይ በሴቶች በኩል ልጆችን በማሰብ በኢኮኖሚውም ጥገኝነት ስላለ ወደ ሕግ ከመሄድ ይልቅ በችግር ውስጥ ለመቆየት የሚገደዱት በርካቶች ናቸው። አብዛኞቹ የቅጣቱ ሰለባዎች በኢኮኖሚ ጥገኛ የሆኑ ናቸው:: በተለይ ሚስቶች ለመፋታት ቢወስኑ እንኳ በወንጀል ቢከሰሱ ባል ቢታሰር ዞሮ ዞሮ የገቢ ምንጯ ስለሚቋረጥ የወንጀል ክሱን ጨክነው የሚገፉበት ብዙ አይደሉም።
በሕግ ረገድም የቤተሰብ ጥቃት ከላይ የተጠቀሱት የራሱ የሆኑ ገጽታዎች እንዳሉት ቢታወቅም የሚስተናገደው እንደማንኛውም ጥቃት በመሆኑ በቀላሉ መረጃና ማስረጃ ማቅረብ ስለማይቻል ተንጠልጥለው የሚቀሩት ጉዳዮች ብዙ ናቸው። አንዲት ሴት ወይንም ልጅ በአንድ መንገደኛ የሚደርስባት ማንኛውም አይነት ጥቃት ትንኮሳና የመብት ገፈፋ በሚዳኝበት ሕግ በቤት ውስጥ የሚፈፀመውምመዳኘቱ የራሱ ችግር ያለበት ነው። በዚህ መልኩ በሕጉ በኩል ያለው ክፍተት ጥፋቱን ለሚፈፅሙት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሕግ አስከባሪ አካላትም የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ አንዳንድ ጊዜ ጉዳዩ ለዳኝነት ከመቅረቡ በፊት በፖሊሶችና በሌሎች የሕግ አስከባሪ አካላት በኩል ጥቃቱን አቅልሎ በማየት እንደ ወንጀል የሚታዩ ጉዳዮችን እንደባልና ሚስት ጉዳይ እንደ ፍትሐብሔር ክስ ብቻ በመውሰድ ተስማምታችሁ ፍቱት የሚል ተገቢ ያልሆነ ምላሽ ሲሰጡም ይታያል።፤ ለማግኘትም ለማቅረብም አስቸጋሪ መሆኑ እየታወቀ ምስክር አቅርቢ የመሳሰሉትን ጥያቄዎችን ስለሚያቀርቡ ጉዳዩ ለውሳኔ የመቅረብ እድሉ ጠባብ ይሆናል። ምስክር እንዲቀርብ ማድረግ የሕግ አስከባሪ አካላት ሥራ ቢሆንም በተጠቂዎች በኩል ምስክር ቢገኝም ከጥቃቱ ባህሪ አንፃር ብዙ ጊዜ ጎረቤትና ዘመድ ስለሚሆን ዘላቂ ግንኙነት እንዳይነካ በመፍራት ደብድቧል፣ ተሳድቧል ብሎ ከመመስከር ይልቅ ለመሸምገል አልያም አላየሁም፣ አልሰማሁም ለማለት እንደሚገደዱ ከግምት በማስገባት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የማህበረሰብ ግንዛቤ ማነስና የቤተሰብ ጣልቃ ገብነትም ለመባባሱ ሌላው ምክንያት የሚሉት ወይዘሮ ቤተልሄም መቻቻል አንዱ የማህበረሰባችን እሴት ቢሆንም አንድ ሰው በተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰበት ቻል ወይንም ቻይ ብሎ መሸምገል ተገቢ አይደለም። አንዳንዶች ቤተሰብም ጎረቤትም ሆነው ጥቃት እየተፈፀመ መሆኑን እያወቁ ዝም የሚሉ መኖራቸው ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። እንደ ማህበረሰብ ለወንድነት ለሴትነት የሚሰጠውም ትርፍጓሜ የራሱ ተጽዕኖ ፈጥሯል። በስፋት እንደሚስተዋለው አንዲት ሴት ልጅ እከሌ ተናገረኝ ወይንም መታኝ ብላ ለራሷ ቤተሰብ ሳይቀር ስሞታ ብታቀርብ ወንድ ልጅ አይደል ወይንም ታላቅሽ አይደል ቢናገርሽ ምን አለበት? የሚል ምላሽ መስጠት የተለመደ ነው። ከዚህ ጀምሮ መታረም ያለባቸው አስተዳደጎች አሉ:: ወንድ ልጁን እንደ ሴት ተመተህ እቤትህ እንዳትመጣ ብሎ የሚመክር ቤተሰብ ለሴት ልጁም ማንም ሊነካሽ አይገባም፤ የሚነካሽ ካለ ለእኔ ንገሪኝ እያለ በግልጽነት የራስ መተማመን አዳብራ እንድታድግ በማድረግ፤ ከችግር ራሳቸውን እንድትከላከል ብቻ ሳይሆን ችግር ሲፈጠርም በሴትነቷ የደረሰባት የእሷ ጥፋት አለመሆኑን አምና ያለምንም ፍራቻና ማመናታት ለቤተሰቧም ሆነ ለሚመለከተው አካል በድፍረት እንድትናገር ማብቃት ይጠበቅበታል ይላሉ።
የኮሮና ወቅትን የቤት ውስጥ ጥቃት ከሌላው ጊዜ የተለየና አስቸጋሪ የሚያደርገው ሌላው ነገር ረጅም ጊዜ ከቤት ውስጥ ጥቃት ፈፃሚውና ተጠቂው መቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን አስቸጋሪ ነገር ቢገጥምና ወደዘመድ አዝማድ ለመሄድ ቢፈለግ እንኳን ከቫይረሱ የመተላለፊያ ባህሪያት ጠንካራነት የተነሳ እንደልብ ወደፈለጉበት ለመሄድ አለመቻሉ ነው። ጎረቤት እንኳን እንደልብ መሄድ የማይቻልበት ወቅትም ነው። የተፈጠረውም የኢኮኖሚ መዳከም እንደልብ ሰው ቤት ሄዶ ለመቀመጥ አይፈቅድም:: በመሆኑም ከኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በዚህ አዋጅ አንደሚታዩት ሁሉ ይህም በተለየ ሁኔታ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ የጥቃቱ አይነትና ባህሪ ልዩ መሆኑን መገንዘብ፤ ለምሳሌ ሙስና እንደ ማንኛውም ወንጀል ሳይሆን በልዩ አዋጅ የሚታይ ነው:: ይህ የተደረገው ወንጀሉ አዲስ የተፈጠረ ሆኖ ሳይሆን ከቴክኖሎጂ፤ ከጊዜ ጋር በተያያዘ በጣም እየተራቀቀና እየጨመረ በመምጣቱ በበፊቱ የሕግ ማዕቀፍ በማስተናገድ ተገቢውን መፍትሄና ፍትህ ማስድገኘት ባለመቻሉ ነው። በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ በሚሊየን የሚቆጠር ሰው ተይዟል በየሀገሩ ግን የዚህን ቁጥር እጥፍ የሚደርሱ ዜጎች የቤት ውስጥ ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል።
በተጨማሪ አብዛኛዎቹ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በሕግ እውቅና ያልተሰጣቸው በመሆኑ ለራሱ በተቀመጠ ሳይሆን ከዚህም ከዛም የተውጣጡ አንቀጾችን በማጣቀስ ነው ውሳኔ የሚሰጣቸው። አንዲት ሴት ባሌ ደበደበኝ ብላ ወደ ሕግ ብትሄድ ልትጠይቅ የምትችለው ሌላ አንድ ሰው ድብደባ ቢያደርስባት በምትሄደው አካሄድ ነው። ነገር ግን መታየት ያለበት የአንድ ቀኑ ድብደባ ወይንም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከጥቃቱ በፊት ያሉትንም ከጥቃቱ በኋላ የሚኖሩትንም ባገናዘበ መልኩ መሆን ነበረበት። በመሆኑም ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ የቤት ውስጥ ጥቃት ያላቻ ጋብቻ አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉትን ያካተተ እንደ ፍትሐብሔር፤ የቤተሰብ፤ የንግድ ሕግና ወንጀለኛ መቅጫ ሁሉ ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍና የሕግ እውቅና ያስፈልገዋል።
የቤተሰብ ጥቃት የግል ድብደባን ብቻ መታየት የለበትም:: ይሄ በቀጣይም የሚሠራ መሆን አለበት:: ይሄ በመሆኑ ነው የጥቃት መጠኑም አይነቱም የሚጨምረው:: ግንዛቤውም በተገቢው ደረጃ የማይሻሻለው። ማንኛውም ሰው ራሱን ከጥቃት ከሚከላከልባቸው መንገዶች አንዱ ወደ ቤት መሄድ አልያም እቤት ውስጥ መሆን ነው። ይሄ ጥቃት ደግሞ በዚህ ወቅት በቤት እየተፈፀመና እየተባባሰ ሲመጣ በመንግሥት በኩል እናወግዛለን እያሉ ከመናገር ባለፈ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ይጠበቃል። ስለዚህ በመንግሥት በኩል ሕግ አውጭውም ሕግ አስፈፃሚውም አካል የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በመረዳት ተመጣጣኝ ሕጎችን ማውጣትና መተግበር ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ የሕግ ምርምርና ጥናት ኢንስቲትዩት የሚባል ተቋም አለ:: ይህ ተቋም በሀገሪቱ ሕግ ሊወጣባቸው የሚገቡ ሊሻሻሉ የሚገቡ ነገሮችን እያጠና እንዲሻሻሉ የሚያቀርብ ነው:: ከዚህ ተቋምም ችግሩ አሳሳቢ መሆኑንና ሥር መስደዱ የሚጠበቁ ሥራዎች አሉ። የሲቪል ማህበራትም ዓመት ጠብቀው ቀናት ከማክበር ባለፈ የሕግ ማሻሻያ እንዲደረጉ በመገፋፋት የግለሰብ ጉዳዮችንም በመከታተል ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል። ከወረዳ ጀምሮ የሚቋቋሙትን ህፃናትና ሴቶችን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ክፍሎችን በማጠናከር ሙሉ ጊዚያቸውን ለዚህ ሥራ ብቻ እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባል።
ሕብረተሰቡም ጉዳዩ የሚመለከተው መሆኑን በመረዳትና አሁን ያለው አካሄድ ስህተት መሆኑን በመረዳት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ይጠበቃል። ጎረቤትና ቤተሰብ ሽምግልና ሲጠራ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጉዳዩ ወደ ሕግ እንዲቀርብ ማድረግ እንጂ መቻቻል አለባችሁ በሚል የተለመደ ብሂል ጥቃቶችና መገፋቶች እንዲቀጥሉ ማድረግ የለባቸውም። እንግዳ መቀበል መተሳሰብ ባህላችን ነው:: እንደምንለው ሁሉ ሴትን መስደብ ሴት ልጅና ህፃናት ላይ ጥቃት ማድረስ ባህላችን አይደለም ብሎ ማውገዝና መቃወም መጀመር ይገባል። በተመሳሳይ በኢኮኖሚውም ከወንድ እኩል ለሠራች ሴት ለሥራዋ እኩል አለመክፈልና ተመሳሳይ መድሎዎችን ማድረግን ባህላችን አይደለም በማለት እኩልነትን አንዱ የባህሉ አካል ማድረግ ይጠበቅበታል። በተለይ የቤት ውስጥ ጥቃት በልጆችና ሴቶች ላይ በማንኛውም ሰዓት በየትኛውም ቦታ ሊፈፀም ስለሚችልና ጥቃቱ በማታለልና በማስፈራራት የሚፈፀም በመሆኑ ጎረቤትና የአካባቢ ነዋሪ ሁሌም በጥንቃቄና በንቃት ሰፈሩ ያለውን እንቅስቃሴ መከታተል ይጠበቅበታል። የሃይማኖት ተቋማትና አባቶችም የሚጠበቅባቸው ሥራ አለ።
በሃይማኖት አባቶች በኩል በሃይማኖቱ አስተምህሮ ለሴትና ለወንድ የሚሰጠው ቦታ እይታ እንዳለ ሆኖ የየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ የሴቶችን የልጆችን ለጥቃት ተጋላጭነትና ተጎጂነት የሚፈቅድ አይደለም። በመሆኑም ምዕመኖቻቸው እነሱን ስለሚሰሙ ባገኙት አጋጣሚ በጎነትን፣ ፍቅርን፣ ርህራሄን ማስተማር፤ ብሎም በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚያደርሱትን ጥቃቶች ማስቆም እንዳለባቸው መምከር ይጠበቅባቸዋል። እንደ ሃይማኖት ተቋምም ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ለኮሮና እንዳደረጉት ሁሉ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ከመንግሥትም ጋር በመተባበር የቤት ወስጥ ጥቃትን ለመቀነስ መሥራት አለባቸው።
በመገናኛ ብዙሃንም በኩል የሴቶች ቀን የመሳሰሉትን የበዓላት ዘገባዎችን ከማቅረብና አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ እነሱን ተከትሎ ማራገብ ብቻ ሳይሆን አጀንዳ አድርገው በተከታታይ ያለማቋረጥ ህዝብን ማስተማርና መንግሥት እንዳይዘናጋ ማሳሳብ አለባቸው። ዓመታዊ ቀናት መከበራቸው ችግር ባይኖረውም ወጥነት ሊኖረው ይገባል። በተጨማሪ በከተማ ብቻ ሳይወሰኑ እየተከታተሉ ገጠሩንም በማዳረስ የተሸፈኑ ወንጀሎችንም የማጋለጥ ሥራ መሥራት አለባቸው።
የቤት ውስጥ ጥቃትን በዘላቂነት ለማስቆም ግን በቅድሚያ እንደ ማህበረሰብ የሴትንና የወንድን እኩልነት ማመንና መቀበል ይጠበቃል። ይሄ ጥያቄ የመብት ጥያቄ እንጂ የቅብጠት፤ የውድድር አልያም የቅናት ተደርጎ መወሰድ የለበትም:: ሴት ከወንድ የምትለይበት አንዱ ወንድ ከሌላው እንደሚለየው መሆኑ ግንዛቤ መያዝ አለበት። ይህም ሠፊ ሥራና ረጅም ጊዜ የሚወስድ እንደመሆኑ አብዛኛው ሥራ መሠራት ያለበት የነገ አገር ተረካቢ በሆነው ትውልድ ላይ ነው። ከቤቱ ሴት ልጅ ስትከበር እናቱ ስትከበር እህቱ ስትከበር እያየ ያደገ ልጅ ለሴቶች የሚኖረው ክብር የተስተካካለ ነው። በአንፃሩ አባት እናቱን አላግባብ ሲማታ ሲሳደብ ያየ ደግሞ ያንን መንገድ የመከተል ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ እያንዳንዱ ቤተሰብ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም በማሰብ ልጆቹ ከጥቃት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ራሳቸውም ጥቃት ፈፃሚ ሆነው እንዳይገኙ የማድረግ ሃላፊነት አለበት ሲሉ የሕግ ባለሙያዋ ወይዘሮ ቤተልሄም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ