በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የምሕረት ወር እንደሆነ የሚታመነው የረመዳን ጾም በመደጋገፍ በመተሳሰብና ይቅርታ በማውረድ የሚሰነበትበት ነው።ህዝበ ሙስሊሙ ረመዳን ሊገባ ቀናት ሲቀሩት ጀምሮ ከፈጣሪው ለመታረቅና በምድር ሰላምን በሰማይም ድህነትን ለማግኘት ከቤተሰብ እስከ አካባቢ የተቀያየመ ካለ ይቅር ተባብሎ ጾሙን ይጀምራል፡፡ ወሩ እስኪወጣ ድረስም በመከባበር በመፈቃቀርና በመረዳዳት የሚያሳልፈው ይሆናል፡፡ በዚህ ወር ከዚህ ቀደም የሚዋሽ የሚቀጥፍና ሌሎች ጥፋቶችንም የሚሰራ ቢኖር የሚታረምበትና ለፈጣሪው ታማኝ ለመሆን በጾም በጸሎት በመትጋት የሚያሳልፈው ግዜ ነው።
የረመዳን ወር ለሕዝበ ሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ታዋቂ ነው፡፡ ቴምር፣ ሳንቡሳና ሌሎችም የረመዳን የማፍጠሪያ ምግቦች ረመዳን በማኅበረሰቡ ዘንድ የተለየ ቦታ እንዲኖረው ያደርጉታል፡፡ ሾርባና ሌሎች የተለያዩ ጣፋጭ ምግቦችም የረመዳን ድምቀት ናቸው፡፡ በማፍጠሪያ ግዜ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችም ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር አብረው መአድ ሲቀርቡ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል። የዘንድሮው የረመዳን ወርም ከሌላው ግዜ በተለየ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አለም ብዙ ጸሎት የተደረገበት፤ ብዙ መረዳዳትና መተሳሰብ የታየበት እንደሆነ በማስታወስ ከፍቺውም በኋላ ከቤተሰብ እስከ ሀገር የተጀመረው ፈጣሪን የመፍራትና የመተሳሰብ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሀገር ሽማግሌና የሰላም ኮሚሽን አባል የሆኑት አቶ አህመድ ዘካሪያ ያሳስባሉ።
አቶ አህመድ ዘካሪያ እንደሚናገሩት በእስልምና ሀይማኖት አስተምህሮ መሰረት የረመዳንን ቅዱስ ወር ለመቀበል መንፈሳዊና አካላዊ ዝግጅቶች ይደረጋሉ። በዚህ ረገድ መንፈሳዊው ዝግጅት የሚጀምረው ሰብአዊ ተነሳሽነትን በማዳበር፤ በቤተሰብና በማሕበረሰብ ባህሪ ላይ በጎ ተጽእኖ በሚፈጥር ሁኔታ ለሰዎች ምህረት በማድረግና ርህራሄን በማሳየት እንዲሁም ከዘመድ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከርና ለበጎ ስራ በመሽቀዳደም ነው። ማህበራዊ ህይወትንና አንድነትን ለማጠናከር ከሚሰሩ ስራዎችም መካከል ለተቸገሩ ምግብ ማብላት፤ ምጽዋት መስጠትና ለሰው ልጆች በሙሉ ርህራሄንና ፍቅርን ማሳየት ይጠቀሳሉ። የዚህ አይነቱ መረዳዳትና መደጋገፍ የሚጀምረው ደግሞ ከቤተሰብ ነው። በተጠናቀቀው የረመዳን ጾም ወቅት ከመቼውም ግዜ በተለየ ይህ ነገር በስፋት አንደ ሀገር ሲተገበር ቆይቷል። ለዚህ ደግሞ ከሀይማኖቱ አስተምህሮ በተጨማሪ የኮሮና ወረርሽኝ የፈጠረው ቀውስ አንዱ ምክንያት ነው። ወረርሽኙ በርካታ ዜጎች ከስራ ገበታ እንዲነሱ ያደረገ በመሆኑ ብዙ ቤተሰብ የእለት ጉርስ ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነበት መጥቷል። እስካሁን ለዚህ እየተደረገ ያለው ምላሽ አበረታች ነው።ነገር ግን ችግሩ መቼ እንደሚያቆም ስለማይታወቅ በችግር ምክንያት ቤተሰብ እንዳይበተን ልጆች ለርሀብ ብሎም ለጎዳና ህይወት እንዳይዳረጉ በጾም ወቅት በስፋት የተጀመረው የመደጋገፍ ስራ ችግሩ አስኪቀረፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
በረመዳን ጾም ወቅትም ሆነ በፍቺው እለት በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ጾማቸውን የሚገድፉት በህብረት አንድ መአድ ላይ ቀርበው ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች በጉርብትና የሚኖሩና ተወላጅ የሆኑ ቤተሰቦችም እንደ አንድ ቤተሰብ በአንድነት የሚያከብሩበት ሁኔታ ያለ ሲሆን ገበታ ሲቀርቡም አዋቂ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆችም ለየብቻ ነው። ዛሬ ዛሬ ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ቴሌቪዥን ስልክና ሬድዮ ላይ ግዜ ማጥፋት ሳይጀመር እነዚህ የማፍጠሪያ ሰአቶች እርስ በእርስ ለመወያያትና ሀሳብ ለመለዋወጥ የሚያገለግሉም ነበሩ። ዛሬም ቢሆን የሀይማኖቱ አስተምህሮ ባይሆንም በኢትዮጵያና በተወሰኑ ሌሎች ሀገራትም ባሉ የእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ከማፍጠር በኋላ በተመሳሳይ ጫት በመቃም የሚያሳልፉት ግዜ ለውይይትና ሀሳብ ለመለዋወጥ የሚያገለግል ነው። በእስልምና ሀይማኖት ዘንድ ደግሞ ለእረፍት ተብሎ የተሰጠ ግዜ ባለመኖሩ እነዚህ ግዜያት የተሻለ የቤተሰብ ግንኙነትና ትስስር ለመፍጠር የሚያስችሉ ናቸው።
አቶ አህመድ ጨምረው እንዳብራሩት በረመዳን ጾም ወቅት ከምግብ ብቻ ሳይሆን አይንም ጆሮም መጾም ስለሚኖርበት በተቻለ መጠን ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ላለማየትና ላለመስማት ራስን ተገቢ ካልሆኑ እንቅስቃሴዎች ለመቆጠብና ከክፉ ነገር ለመጠበቅም ከብዙ እንቅስቃሴዎች ተገድቦ የሚቆይበት ወቅት ነው። ይሄ ማለት ግን ለሌሎች በተለይ ለተቸገሩ የሚደረግን ድጋፍ የሚያግድና ከቤተሰብና ከዘመድ ወዳጅ ጋር ያለን ግንኙነት የሚያላላ ሳይሆን በተለየ መልኩ በንጹህ ልብና ፍቅር ለመቀራረብ የሚያስችል ነው። ወሩ ቁርአን የወረደበትና በየግዜው ምህረት የሚደረግበት እንደመሆኑም ከህዝበ ሙስሊሙ በርካታ መልካም ስራዎች የሚጠበቁበት ነው። በተጨማሪም ወሩ ህዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪ ጋር የሚታረቅበት በሰውም ዘንድ ከቤተሰብ ጀምሮ በጎረቤትም ሆነ በአካባቢ አለመግባባትና ቂም ከነበረ እርቅ የሚፈጠረበትና ሰላም የሚወርድበትም ነው።
በሀይማኖቱ አስተምህሮ አንድ አማኝ በዚህ ወቅት የሚጾመው ጾምና የሚጸልየው ጸሎት ለፈጣሪው እንዲደርስለት ከፈለገ ከፈጣሪም፤ ከፍጡርም፤ ከራሱም እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር እንዲታረቅ ይጠበቃል። ለምሳሌ በክርስትና እምነት አንድ ሰው ከወዳጁ ከተቀያየመ ጀምበር ከመጥለቋ በፊት መታረቅና ይቅር መባባል እንዳለበት እንደሚያስቀምጥ ሁሉ፤ በእስልምና እምነትም የሀይማኖቱ ተከታይ የተቀያየመው ሰው ካለ እርቅ ሳያወርድ ሶስት ቀን መቆየት እንደሌለበት ተቀምጧል። በዚህ መሰረት በተለየ የረመዳን ጾም ሲገባ ደግሞ አማኙ የሚጾመው ጾምና የሚጸለየው ጸሎት ከፈጣሪ ዘንድ ደርሶ ዋጋ እንዲያገኝ ከቂም የጸዳ ንጹህ ልብ ይዞ ይቅርታ ተባብሎ የጾሙን ወቅት መጨረስ ይጠበቃል። ይህም የሚደረገው በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም ሰው ጋር ዘመድም ሆነ ቤተሰብ ይቅር በመባባልና ያለፈውን ነገር በመተው ቀድሞ ወደ ነበረው ሰላም በመመለስ መሆን አለበት።ሌላው ቀርቶ በረመዳን ወቅት ለልጆች የተለየ ቦታ የሚሰጥ ሲሆን ልጆች የቱንም ዓይነት ጥፋት ቢያጠፉ በረመዳን እጁን የሚያነሳባቸው፣ የሚቆጣቸው ቤተሰብ አይኖርም፤ ይልቁንም ወላጆች ሰከን ብለው በመምከርና በመገሰጽ ያስተምሯቸዋል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ እነዚህን የመተሳሰብና ይቅር የመባባል ተግባራት በበለጠ ተነሳሽነት እንድናደርግ እያስገደደን ይገኛል። ምንም እንኳን በሽታው በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተና ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን መላውን አለም ስጋትና ሰቀቀንን ያላበሰ ቢሆንም፤ ለኢትዮጵያውያንም የራሱ ገጽታ ያለው ነው። ቫይረሱ በሀገር ውስጥ መገኘቱ ይፋ ከመደረጉ በፊት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በርካታ ለመስማት የሚከብዱና ለማየት የሚቀፉ ነገሮች ተፈጽመዋል። ባለፉት ሁለት አመታትም ህዝቡ ከመረዳዳት ከመተሳሰብና ከመደጋገፍ ይልቅ በትንሽ በትልቁ ሲጋጭ፤ ሲሰዳደብና በምድርም በሰማይም ተቀባይነት የሌላቸውንም አጥፊ ተግባራት እርስ በእርሱ ሲፈጽም ከርሟል።
ባለፉት ጥቂት ወራት ደግሞ ኮሮና ምክንያት ሆኖ ሁሉም ወደ ቀልቡ በመመለስ ዘር ሀይማኖትና ጎሳ ሳይለይ በመቻቻል በመረዳዳት በመተባበር የመጣበትን መጥፎ ግዜ ለማሳለፍ እየጣረ ይገኛል። አብዛኛው ሰውም ወደ ቀልቡ በመመለስ መንፈሳዊነት ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል። በተለይ በጣቶች ዘንድ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይስተዋል የነበረው ስሜታዊ እንቅስቃሴ በአንድ ግዜ እንዲረግብና ወጣቶች በርህራሄ በመሞላት የተቸገሩትን ለመርዳት ሲንቀሳቀሱ እያየን እንገኛለን። ቀድሞውንም እነዚህ ነገሮች ሊከሰቱና በዜጎች መካከል መቃቃርን ከዚያም አልፎ የተለያዩ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥፋቶችን ሲያስከትሉ የነበረው በቤተሰብና በሀይማኖት አባቶችም ዘንድ ሆነ በዘመናዊው ትምህርት ስነ ምግባርን በተመለከተ ተገቢው ስራ ባለ መሰራቱ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውም ሰው በልጅነቱ የሚይዘው ስብእና የቀረ ህይወቱን የሚከተለው መሆኑን እያንዳንዱ ቤተሰብ መገንዘብ አለበት። ልጆች በቤተሰብ ውስጥ እያሉ መልካም ስነምግባር ይዘው በጥሩ ስብእና እንዲያድጉ ከተደረጉ ይህንን ባህሪያቸውን ካደጉም በኋላ በስራ በትምህርትና በማህበራዊ ህይወት ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲገናኙ የሚያንጸባርቁት ይህንኑ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ወላጅ በቃል ከመናገር ባለፈ በተግባርም ሰው ማክበርን መቻቻልንና፤ መረዳዳትን፤ እንደ ንብረቱና ትምህርቱ ሁሉ ለልጆቹ ማውረስ ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ ደግሞ የአንድ ቀን ስራ ሳይሆን የየእለት የዘወትር ተግባር ቢሆንም በተለይ በረመዳን ወቅት የመሰባሰቡና የመነጋገሩ እድል ሰፊ በመሆኑ በተለየ መንገድ ሊጠቀምበት ይገባል።
በእምነትም በኩል የሀይማኖት አባቶች ሃላፊነታቸውና አስተማሪነታቸው ለምድር ብቻ ሳይሆን ለሰማይም መሆኑን መረዳት አለባቸው። የፈጣሪ አገልጋይና በመንፈስ ከሞት በኋላ ያለው ህይወት የሚሰማቸውና እንደሌላው ሰው ወደ ምድሩ ሳያደሉ ተከታዮቻቸውንም ለሰማያዊ ህይወት የሚያጩ መሆን ይጠበቅባቸዋል። የሰማያዊው ህይወት የሚገኘው ደግሞ የሰው ልጅ በምድር ሳለ በሰራው መልካም ስራ በመሆኑ የመቻቻልን የመደጋገፍን ተግባሮች ማስተማርና በተግባርም ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። እንደ እምነት አባትነታቸውም ፈጣሪያቸውን በመፍራትና ለፈጣሪያቸው ትእዛዝ በመገዛት ያጠፋውን በመገሰጽ የተጣላውን በማስታረቅ ለሀገርም ለህዝብ የሚበጀውን የቀናውን መንገድ የመጥረግ ስራ የሚጠበቀው ከእነሱ ነው። እነሱም እንደ ቤተሰብ እነዚህን ስራዎች ከአመት አመት መስራት ያለባቸው ቢሆንም እንደዚህ ምእመናኑ ጆሮውንም ልቡንም በሚሰጥባቸው የጾምና የበአላት ወቅት ደግሞ የበለጠ ተደማጭነት ስለሚኖራቸው ሊጠቀሙበት ይገባል።
በአለማዊ ትምህርት ረገድም ቢሆን በኢትዮጵያ እየተሰጠ ያለው ትምህርት መሰረታዊ የስብእና ጥያቄዎችን የሚያሟላ መሆን አለበት። በዚህ ረገድ ባለፉት ሀምሳ አመታት እንደ ሀገር የመጣንበት መንገድ ስነ ምግባር ላይ ትኩረት ሳይሰጥ መብትና ግዴታ ላይ ብቻ በማተኮሩ መንፈሳዊ ስሜት ሳይኖረው ቁሳዊና ስሌት ላይ ብቻ የተመረኮዘ ትውልድ እንዲፈጠር በር ከፍቷል። ነገር ግን ወፍ ለመብረር ሁለት ክንፍ እንደሚያስፈልጋት የሰው ልጅም ሚዛናዊ ሆኖ ለመኖር መብትና ግዴታ የሚያስፈልገው ቢሆንም የሰው ልጅ መንፈሳዊና ስጋዊ እንደመሆኑ አመክኖኣዊ የሆነውን መንገድ ብቻ መከተሉ ትክክል አይደለም።
በመሆኑም መንፈሳዊ የሆኑት ነገሮች ላይም በማተኮር የተሟላ ሰብእና ያለው ትውልድ መፍጠር የሚጠበቅ ይሆናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በአንድ በኩል እንደ ተቋም የተቀመጠውን የትምህርት ፖሊሲና የትምህርት አሰጣጥ ሂደት የተማሪና መምህር ግንኙነት መፈተሽ የሚገባ ሲሆን፤ በመምህራን በኩል ደግሞ እንደ አንድ ዜጋ ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥም ቢሆኑ ለተሰጣቸው ሃላፊነትና አደራ ቅድሚያ በመስጠት ከእያንዳንዱ ትምህርት በተጓዳኝ ሰላምን ፍቅርን መረዳዳትና መቻቻልን ማስተማር ይገባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደመሆናችን ንግግራችንና ጭቅጭቃችን ከሀገር እስከ አለም አቀፍ በሚያገባንም በማያገባንም እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም ይህንን በመረዳት የማይመለከተንን በመተው ከመወቃቀስ ወጥተን ያለውን የሀሳብ ልዩነት እንዴት እናስተናግደው ብለን መመካከርና መወያየት ይጠበቃል። ወጣቱ ደግሞ ለሚፈጠረው ችግር ምክንያት ብቻ ሳይሆን የችግሩም ተቋዳሽ ሁሌም በአለማዊውም በመንፈሳዊውም ጉዞ አንድነትን፣ ህብረትንና መደጋገፍን አንዲያስቀድም ማስተማርና አርአያ መሆን ይጠበቃል። ለዚህም አካባቢውን እንዲያውቅ ከተፈጥሮም ጋር እንዲታረቅ መደረግ አለበት። ዛሬ በስፋት እየተተገበሩ ያሉት የችግኝ ተከላ ስራዎች የአየር ብክለት ቁጥጥር የመሳሰሉት ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ለሌላው ክፉ ስራ ግዜ እንዳይኖረው የሚያደርጉ ናቸው ይላሉ አቶ አህመድ ዘካርያ።
የኮሮና ወረርሽኝ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስም ህዝበ ሙስሊሙ በጾም ወቅት ሲያደርገው የነበረውን የተቸገሩትን የመርዳት የተራቡትን የማብላትና የታረዙትን የማልበስ ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ከዚሁ በተጓዳኝ ደግሞ መንግሥት ያሳለፈውን መመሪያና የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ከመስማት ባለፈ ወደ ተግባር በማውረድ ራሱንም ቤተሰቡንና አካባቢውን ከመጣው መቅሰፍት መጠበቅ እንደሚኖርበት አቶ አህመድ ዘካሪያ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ