መረዳዳት መተሳሰብ ለኢትዮጵያውያን የኖረ ባህል ነው። እንደዛሬው የመሸበትና ማደሪያ አልቤርጎ ሳይጀመር፤ አገሩን የለቀቀ ተጓዥ መንገደኛ ነኝ ካለ ከጥሬ እስከ ዶሮ ገበታ ሳይለይ አብልቶ አጠጥቶ የሚያሳድረው አያጣም ነበር። ከሲራራ ነጋዴ እስከ እለት መንገደኛ አቅሙ በፈቀደ በአገልግሉ ከሚቋጥረው እህልና ቅሉ ከሚያንጠለጥለው የሚጠጣ ነገር ውጪ ለቀናትም ለወራትም የሚያቆይ ጉዳይ ቢኖረው እግሩን ከቤቱ የሚያነሳው የሀገሩን ልጅ እንግዳ ተቀባይነትና ፍቅር ተማምኖ ነው። ዛሬ ዛሬ ከመዘመን ጋር በተያያዘ ይሄን ወርቃማ ባህል አለ ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ ባይኖርም ዘመናዊነት ባህላችንን በሰረቀባቸው ከተሞች ሳይቀር ብልጭ የሚሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያንን ማየታችን አልቀረም። ታዲያ ይህ ደግነትና እንግዳ ተቀባይነት ደግሞ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሳይሰለች ከግማሽ ምእተ አመት በላይ ዘልቋል ስንባል ምን ይሰማን ይሆን ?
ሀጂ በድሩ ሺፋ ይባላሉ።ትውልዳቸው ሰባት ቤት ጉራጌ እንድብር በምትባል አንዲት ትንሽ ከተማ ነው። ገና በልጅነታቸው ነበር እያስተማሯቸው የነበሩትን እናታቸውን በሞት ያጡት።ሀዘኑ ቢጎዳቸውም እዛው በመሆን ኑሯቸውንም ትምህርታቸውንም ለመቀጠል ሞክረው ሁለት አመት ከቆዩ በኋላ ሳይሳካላቸው ይቀራል። እናም የአራተኛ ክፍል ትምህርትቸውን አቋርጠው በ1957 ዓ.ም ከተወለዱበት አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ። አዲስ አበባ ሲደርሱም በአንዲት የአጎታቸው ልጅ መሪነት በዘመኑ ከነበረው ክፍት የስራ ቦታ ከሊስትሮነት ጀመረው ያገኙትን እየሰሩ ራሳቸውን ለመቻል መጣር ይጀምራሉ። ዋል አደር ካሉና ሀገሩንም ሰውንም ከለመዱት በኋላ ደግሞ ሰው ቤት በመቀጠር በመጀመሪያ በሶስት ብር ከዛም በስምንት ብር ደመወዝ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰሩ ይቆያሉ። ይሄ ስራ ያለመናቅና ጠንክሮ የመስራት ባህሪያቸው ብዙም ሳይቆዩ በአንድ መደብር ውስጥ ተቀጥረው እንዲሰሩ አጋጣሚውን ይፈጥርላቸዋል።
በተቀጠሩበት መደብርም ለተወሰነ ጊዜ ካገለገሉ በኋላ እዛው መደብር ለስራ ጉዳይ ይመላለሱ የነበሩና የስራ ብርታታቸውን ያስተዋሉ ህንዶች አብረዋቸው እንዲሰሩ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጥሩ ያገለግሉት የነበረው አሰሪያቸው እሳቸውን ላለማጣት ሲል ከህንዶቹ ጋር እንዳይሰሩ ያደርጋቸዋል። ነገር ግን ህንዶቹ አይናቸው አርፎባቸው ስለነበር ትንሽ ጊዜ ቆይተው እንደምንም አድርገው በማግባባት ይሰሩበት ከነበረው መደብር ያስወጡና ከእነሱ ጋር ሲኒማ ራስ አካባቢ ሹራብ በሚሰሩቡት የራሳቸው መደብር ውስጥ ጣቃ መሸጥ እንዲጀምሩ ያደርጓቸዋል። ህንዶቹ ሀጂ በድሩ የሚሰሩትን ካዩ በኋላ “አንተ ጎበዝም ታማኝም ሰራተኛ ነህ፤ ነገር ግን ገንዘብ የለህም” በማለት ኢንሹራንስ መግባት አለብህ ብለው ያስገቧቸዋል። የዛን ጊዜ እሳቸው ስለ ኢንሹራንስ ጥቅምና ጉዳት ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበራቸውም። በዚህ ሁኔታ የጀመሩትንም ስራ በማስፋፋት በራሳቸው ጥረት የተለያዩ የንግድ ስራዎችን እየሰሩ ከእለት ጉርስ ባለፈ ጥሪት ቋጥረው ወፍጮ ቤትና የተለያዩ የንግድ ስራዎችም ውስጥ መሳተፍ ይቀጥላሉ። በአንድ ወቅት የደርግ መንግስት ወረሰባቸው እንጂ አሁን ከሚኖሩበት ቤት ተጨማሪም ኮልፌ አካባቢ ሰፋ ያለ ቤት ለመግዛትም በቅተው ነበር።
የሀጂ በድሩ ስኬት በስራቸው ብቻ የተገደበ አልነበረም።ስራ በሚሰሩበት ቦታ ለአባቷ ቡና ስታፈላ ካዩዋት ወጣትም ጋር የረጅም ዘመን እቅድ በልባቸው ነድፈው ነበር። እናም ግንቦት አስራ ሰባት ቀን 1962 ዓ.ም ዛሬ ድረስ አብረዋቸው ከሚኖሩትና ጎረቤታቸው ከነበሩት ከወይዘሮ ዙሪያሽ ወርቅ በሽር ሀቢብ ጋር ትዳር ለመመስረት ይበቃሉ። የዛኔ እሳቸው የአስራ ሰባት አመት ወጣት ሲሆኑ ባለቤታቸው ደግሞ የአስራ አምስት አመት ጉብል ነበሩ። በዚህ ሁኔታ በአንዲት ክፍል ውስጥ የጀመሩት ሶስት ጉልቻም ያለፉትን ሃምሳ አመታትም አሳልፎ ስምንት ሴትና አራት ወንድ ልጆችን እንዲሁም ሰላሳ የልጅ ልጆችን ለማየት እንዲበቁ አድርጓቸዋል።
ከዚህ የህይወት ውጣ ውረድ በተጓዳኝ ደግሞ ሀጂ በድሩ ገና በልጅነታቸው አገር ቤት እያሉ አያታቸው እንዲሁም አባታቸው ያደርጉት የነበረና እሳቸውም ምኔ እድሜዪ ደርሶ አቅሜ ጎልብቶ ብለው የሚጠብቁት ሀሳብ በውስጣቸው ነበር። እናም ባሰቡት ደረጃ ሀብት ባይትረፈረፍላቸውም አዲስ አበባ ከመጡ ከአራት አመት በኋላ በወር ስምንት ብር እየተከፈላቸው በሚሰሩበት ወቅት እንደ አያታቸውና አባታቸው በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚከበረው የኢድ አልፈጥር በአል ወቅት ሰደቃ ማውጣት ይጀምራሉ። የመጀመሪያ ጊዜ ሰደቃ ያወጡትም በአንድ ብር ከሃምሳ በተገዛ ዶሮ ነበር። ይህንን የተቸገሩ የማስታወስ በጎ አድራጎትም ላለፉት ሃምሳ አንድ አመታት ሳያቋርጡና ሳይታክቱ ሲፈጽሙት ኑረዋል።በአንድ ዶሮ የተጀመረው ሰደቃም በግ ብሎ ዛሬ በበሬ እርድ ይከናወናል። ሰደቃ ማድረግ በበርካታ ሰዎች የተለመደ ቢሆንም የእሳቸው ሰደቃ ለእስልምና ተከታይ ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኑም ለሚያውቁትና ለተጠራ ብቻ ሳይሆን አስታውሶ ለመጣና እግር ለጣለው ሁሉ ነበር። ከጾም ውጪም እቤት ለመጣ ጎረቤትም ከሄዱ የሚታወቁት በዚሁ ነው።
«የመረዳዳቱን ነገር ካደኩበትና ማህበረሰብና ከቤተሰቤ የወረስኩት ነው» የሚሉት ሀጂ የተፈጠርነው አብረን በልተን አብረን ኖረን ለመሞት ነው።ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ የተለመደ ነው። እኔ እናቴ ካረፈች በኋላ ጥቂት ጊዜም ቢሆን ሲንከባከቡኝ የኖሩት ጎረቤቶቻችን ነበሩ። በዚህ ረገድ አባቴ ብዙ አስተምረውኛል።በሀይማኖታችን እንዲህ ይባላል። “ጎረቤትህን ሳታይ ገበታ አትቅረብ፤ ብትችል በቀኝ አርባ፣ በግራ አርባ ጎረቤቶችህ እንዳንተ እየበሉ እንደሆነ አረጋግጥ። የሌለው ካለ አብሮህ እንዲበላ አድርግ። ይሄ ሁላችን እንድናደርገው የታዘዝነው ነው። ሰውን ለመርዳት ደግሞ ብዙ እንዲኖርህ መጠበቅ አያስፈልግም፣ ካለው መካፈል ይቻላል። የተቸገሩን መርዳት የተቸገሩን ማስታወስ ለነፍስም ለስጋም የሚተርፍ ስራ ነው” የሚሉት ሀጂ በድሩ ወደፊትም ፈጣሪ እድሜ እስከሰጣቸው ድረስ እንደማያስተጓጉሉት ይናገራሉ።
ከአባቴ ጠንካራ ሰራተኛ መሆንን ተምሪያለሁ የሚሉት ሀጂ በድሩ በአንድ ወቅት አባታቸው የገጠማቸውንና በቀልድ መልክ የተናገሩትን እንዲህ ያስታውሳሉ። አባታቸው ልጃቸውን ለመጠየቅ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት « የሀጂ በድሩ አሰሪዎች ህንዶቹ ለምን ከሀገርዎት ይወጣሉ ሲሉ ይጠይቋቸዋል። እሳቸውም ልክ እናንተ ከሀገራችሁ ወጥታችሁ እንደከበራችሁት እኔም ለመክበር ብዪ መጣሁ» ብለው በማሳቅ እግረ መንገድም ሰርቶ ለመበልጸግ የሚከፈል መስዋእትነት እንዳለ ይነግሯቸዋል።
ሀጂ ልጆቻቸውን ባይጫኗቸውም ወደንግዱ እንዲያዘነብሉ አይፈልጉም።ማንም ሰው የፈለገውን ስራ ቢሰራ ተምሮ መሆን አለበት «ያለ ትምህርት የሚሰራ ስራ በወንፊት የተያዘ ውሃ ነው» ብለው ስለሚያምኑ ሁሉንም ልጆቻቸውን አስተምረዋል። ከቃል ተግባር ብዙ ያስተምራልና በአሁኑ ወቀት ልጆቻቸውም የእሳቸውን አርአያ እየተከተሉ በያሉበት በአቅማቸው አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ስራ ይሰራሉ። አንዷ ልጃቸው ካራ ቆሪ አካባቢ የራሷ ትምህርት ቤት ያላት ሲሆን ከ35 በላይ ልጆችን በነጻ ታስተምራለች። ሌሎቹም እንዲሁ በያሉበት የመረዳዳት ተምሳሌት ናቸው።“ይሄ እንዲቀጥል እፈልጋለሁ። አያታችንም እኛ የፈጣሪ ስንሆን ፈጣሪም የኛ ይሆናል ለገንዘብ ሳይሆን ለፍቅር ቅድሚያ ስጡ፤ ይህን ስታደርጉ የዘራችሁት ይበቅላል፤ የሰራችሁት ሁሉ ፍሬ ያፈራል፤ ይሉን ነበር። እኔ ከብዙ አመት በኋላ መልሼ ኢንሹራንስ ገብቺያለሁ።ከዛ ውጪ እስካሁን ባንክ የማስቀምጠው ብር የለኝም። ከሰፈር ሰው ሁሉ ተስማምቼ ነው የምኖረው።እኔ ቤት ሙስሊሙም ክርስቲያኑም መጥቶ ያለውን ተቃምሶ ይሄዳል። ከዚህም ባለፈ ቢያንስ በአመት ሁለት ጊዜ ገጠር እሄዳለሁ።እዛም የቻልኩትን ሳደርግ ቆይቻያለሁ።ልጄም ትምህርት ቤት ለመክፈት እቅድ አላት።ይህ ሁላ ተሳክቶ ለማየት እሻለሁ። ዛሬ በተለይ እኔ በተወለድኩበት አካባቢ በገጠር ወጣት የለም ወጣቱ ወደ አዲስ አበባ እየመጣ አዛውንትና ባልቴቶች ቀርተዋል።ስለዚህ እዚህ ብቻ ሳይሆን መጠያየቅ ያስፈልጋል”፤ ይላሉ ሀጂ በድሩ።
ለዚህ ሁሉ ደግሞ ባለቤቴ ትልቅ ድርሻ አላት የሚሉት ሀጂ በድሩ ለትዳርና ለቤተሰብ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት እንዲህ ያሳስባሉ፤ እኛ ሃምሳ አመት የኖርነው ተፋቅረን ተቻችለን ነው። ልጆች ሁሉን እናውቃለን ከሚል አመለካከት ወጥተው የአባት እናትን ምክር መስማት አለባቸው። ሶስት ጉልቻ ለመመስረት ያሰቡም ወጣቶች ከመጋባታቸው በፊት መጀመሪያ እርስ በእርሳቸው መግባባት አለባቸው። ተጋብተው ህይወት የጀመሩትም ልጆቻቸውን እያዩ ተቻችለው በትእግስት መኖር አለባቸው። በዚህ ወቅት ግቢዬ የሚመጣ ብዙ ሰው የለም።ጊዜው ጥሩ አይደለም።አትሰብሰቡ፣ መስኪድ አትግቡ የሚያስብል በሽታ መጥቶብናል። እኔ በእድሜዬ ባልደርስም ስለ ህዳር በሽታ ሰምቼአለሁ። ይሄ ከዛም የባሰ ነው። እኔ በአቅሜ የምረዳቸውን ሰዎች ባሉበት እየላኩ ነው።ፈጣሪን እየፈራን እየጸለይን መንግስትና ባለሙያ የሚለንን እየሰማን መኖር አለብን፤ በማለት ኢትዮጵያውያን ከኮሮና ራሳቸውን እንዲጠብቁ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
ባለቤታቸው ወይዘሮ ዙሪያሽወርቅ በሽር በበኩላቸው ቤታችን ውስጥ ከልጆቻችን ውጪ ሃያ ስድስት ቤተሰብ ይኖርበት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የእለት ደራሽም ነበር።ግን ቸግሮንም አስቆጥቶንም አያውቅም። እህቴን እንኳን ጠርቼ አላውቅም።ሁሌ እንደምናዘጋጅ ስለሚታወቅ የፈቀደ ከዘነበወረቅ ድረስ መጥቶ በልቶ ጠጥቶ ይሄዳል። ግርግሩ ጨዋታው ሁሉ ይናፍቀን ነበር።የሰው ፍቅር ሀብት አለን ይላሉ። ወይዘሮ ዙሪያሽ ወርቅ ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ አውቶቡስ ተራ አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት አካባቢ ነው። በልጅነታቸው ቁርአን የቀሩ ሲሆን ስድስት አመት ከሆናቸው ጀምሮ ደግሞ በደጃዝማች ኡመር ሰመተር ትምህርት ቤት ከሰባተኛ ክፍል በኋላም አርበኞች ትምህርት ቤት ገብተው ተምረዋል።
ወይዘሮ ዙሪያሽወርቅ እንደ ባለቤታቸው እሳቸውም እናታቸው በሞት ያጡት በልጅነታቸው ነበር። ነገር ግን በኋላ አባታቸው የመጨረሻ ልጅ በመሆናቸው እሷን ለወግ ለማዕረግ ሳላበቃ አላገባም ብለው ልጃቸውን ማስተማሩ ላይ ብቻ ያተኩራሉ። እሳቸው ካደጉ በኋላ ግን በእሳቸውና በዘመድ ፈቃድ እንዲያገቡ ስለገፋፏቸው አገር ቤት ገብተው አግብተው መኖር ይጀምራሉ። በዚህ ወቅት ነበር ገጠር ከአባታቸው ጋር ለመኖር በ1962 ዓ.ም ወዳሉበት ያቀኑት።ሆኖም በ1961 አዲስ አበባ በተማሪዎች ረብሻ ተፈጥሮ ስለነበር ትምህርታቸውን መቀጠል ስላልቻሉ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ። ወደ ገጠር ከመሄዳቸው በፊት ከአሁኑ ከባለቤታቸው ጋር ትውውቅ ቢኖራቸውም የፍቅር ግንኙነት ግን አልነበራቸውም።እናም አንድ ቀን ጓደኛቸው ሰርግ ላይ ታላቅ እህታቸውና ባለቤታቸው ይነጋገሩና የጋብቻውን ጥንስስ ይጀምራሉ። በነገሩ ከተስማሙበትም በኋላ ወይዘሮ ዙሪያሽ ወርቅ ወደትዳር ለመግባት ምን እቃ ገዝተሀል ብለው ጥያቄ ያቀርባሉ። አልጋ አንድ ማስታጠቢያና አንድ መዘፍዘፊያ የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል።ይሄ የዛን ጊዜ ለእሳቸው በቂ ነበርና በዚህ ሁኔታ የሃምሳ አመቱን ጉዞ “ሀ”ብለው ጀምረው ዛሬ ላይ ለመድረስ ይበቃሉ።
ወይዘሮ ዙሪያሽወርቅ እንደባለቤታቸው ሁሉ ለራሳቸው ልጆች እንደሚመክሩት ለሀገራቸው ሴት ልጆችም እንዲህ ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ። ሁሉም ልጆቻችን አማክረውን ነው የሚያገቡት።ልጆች በተለይ ሴቶች በወቅቱ ማግባት አለባቸው።በወቅቱ ካገቡ ልጆቻቸውንም እድሚያቸው ሳይገፋ በወጉ ለማሳደግ እድሉን ያገኛሉ። ዋናው ነገር ሰውን በስውነቱ መዝኖ ይሆነኛል አይሆነኝም የሚለውን መለየቱ ላይ ነው። ገንዘብና ሌላው ነገር በኋላ የሚመጣ ነው።እሱም ቢሆን ለመኖሪያ ያህል ብቻ ከተገኘ ሌላው ትርፍ ነው።
«ሀጂ በድሩ ቤት የሁላችን ቤት ነው፤ በደግነት ብቻ ሳይሆን ከሰው ተስማምቶ መኖርንም የምንማርበት ነው» የሚሉት ደግሞ ልደታ በተለምዶ ኮካ የሚባለው አካባቢ ነዋሪ የሆኑትና የሀጂ በድሩን ቤተሰብ ለሃያ ሰባት አመት የሚያውቋቸው ሼህ መደድ መሀመድ ናቸው። ሼህ መደድ ሀጂ በድሩንና ቤተሰባቸውን እንዲህ ሲሉ ይገልጿቸዋልእሳቸውም ባለቤታቸውና ልጆቻቸውም ከሰው ተግባቢ ናቸው። ቤታቸው ሰው ጠፍቶበት አያውቅም።ለደሃ ደራሽ ናቸው።ከሁሉም ተስማምተው ለሁም አስበው የሚኖሩና ሁሉን ሰው በእኩል አይን በሰውነቱ ብቻ የሚቀበሉ ናቸው። እኔ እስከማውቃቸው ብቻቸውን አይበሉም።ሰው ጠርተው የሚበሉ፤ ሰው ይራባል፤ ይቸግረዋል፤ ብለው የሚያስቡ ናቸው። ይሄ ባህሪያቸው ደግሞ ካወቅኳቸው ጀምሮ አልተለወጠም።እንደሳቸው አይነት አባት ቢበዛልን እንደ ሀገር ከንብረቱም ከፍቅሩም ብዙ እናተርፋለን ይላሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ