‹‹ … ወደ ክልል ስመጣ በእኔ ዕቅድ አይደለም፣ ወደሚንስትርነት ስመጣም አልተነገረኝም። እኔ ባለሥልጣን የመሆን ህልምም ዕቅድም አልነበረኝም። የእኔ ፍላጎት የምወደውን መምህርነት መቀጠል ነበር። ለምን ወደ ሹመቱ የሚል ጥያቄ አቀረብኩ ። ሆኖም የተሰጠኝ ምላሽ ‹‹መቼ አገራችሁን ልታግዙ ነው፣ እስከታመነብሽ ድረስ አገርሽን ማገልገል አለብሽ›› አሉኝ አሁን በህይወት የሌሉት አቶ ምግባሩ ከበደ። ከዛም አገርን በዚህ ሰዓት ማገዝ የሚለውን ሐሳብ ተቀበልኩ….›› ይላሉ የዛሬ የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› እንግዳችን ዶክተር ሂሩት ካሳው።
በአሁኑ ወቅት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ናቸው። ቀደም ባሉት ጊዜያት የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ነበሩ። በባህልና ቋንቋ ዘርፍም ተሳትፎ አድርገዋል። በጥቅሉ በቋንቋ፣ በማስተማርና በባህል ዘርፍ ውስጥ ለ25 ዓመታት አገልግለዋል። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት የአማረኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም ዳይሬክተር ፣ ለሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ ለ6 ዓመታት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም ለ15 ዓመታት ያህል ደግሞ ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት አገልግለዋል። ለመሆኑ የዶክተር ሂሩት የህይወት ተመክሮ ምን ያስተምራል? እንደዚህ አቅርበነዋል፦
የሥራ ሀሁ…
ዶክተር ሂሩት ካሳው ተወልደው ያደጉት በቀድሞው አጠራር ጎንደር ክፍለ አገር በአሁኑ የደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ አካባቢ ‹‹ቀፎየ›› በምትባል መንደር ነው። የተወለዱት በገጠራማው ክፍል ይሁን እንጂ በልጅነት ዕድሜያቸው አባታቸው የመንግሥት ሠራተኛ ስለነበሩ ወደ ከተማ የመሄድ ዕድል ነበራቸው። የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን እስከሚማሩ ድረስ የቆዩት ግን በእስቴ ነው። አብዛኛውን የልጅነት ዕድሜያቸውን ያሳለፉት፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በደብረታቦር ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው የከፍተኛ ትምህርት ለመማር ደግሞ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅለዋል።
ዶክተር ሂሩት ሥራ የጀመሩት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቱሉቦሎ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማስተማር ነው። ከቱሉ ቦሎም ወደ ወሊሶ ሄደው ሠርተዋል። ጉራጌ ውስጥ በምትገኝ እንጅባራ የምትባል ከተማ ውስጥም ለስድስት ወራት ያህል አገልግለዋል። ለብዙ ዓመታት ያገለገሉት ግን ሰበታ ከተማ ውስጥ ነው። ከሰበታ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በመማርም በኢትዮጵያ ቋንቋና ሥነ ጽሁፍ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። የሁለተኛ ዲግሪ ዕድል ያገኙትም ሰበታ እያስተማሩ ነበር። የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንደጨረሱም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአማረኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ማስተማር ጀመሩ። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ አሁንም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለመማር ዕድል ገጥሟቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። ጥረት ከዕድል ጋር ይሏል ይሄ ነው።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ከመሆናቸው በፊት ለ25 ዓመታት ያህል ያገለገሉት በመምህርነት ነው። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እያሉ የአማረኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም መስርተዋል። የተቋሙ ዳይሬክተር በመሆንም ለአማረኛ ቋንቋና የባህል ዘርፎች መበልፀግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ሹመትን እንደ መርዶ
‹‹ሚንስትር መሆኔን የሰማሁት ተሿሚዎች በተወካዮች ምክር ቤት ቃለመሃላ ሲፈጽሙ እንደማንኛውም ሰው በቴሌቪዢን መስኮት ነው›› የሚሉት ዶክተር ሂሩት፤ ጊዜውም አጭር ስለነበረ ቃለመሃላ እንኳን በጊዜው መፈፀም እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
በወቅቱ በአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ነበሩ። የሚንስትርነት ሹመት የተሰጣቸው ጥቅምት ወር ላይ ነው። እርሳቸው ግን ከአንድ ወር በኋላ ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለመመለስ አስፈላጊውን ዝግጅት
እያደረጉ ነበር። መጀመሪያው ወደ ክልል ቢሮ የመጡት የክልሉን ህዝብ እና መንግሥት በእውቀታቸው ማገዝ አለብኝ ብለው በማሰባቸው ነበር። ይሄንን ቃል ሲገቡ ደግሞ ለሁለት ዓመት በሚል ነበር። እንዳሉትም ቃላቸውን በመፈፀማቸው ወደመጡበት ዩኒቨርሲቲ ለመመለስ ራሳቸውን እያዘጋጁ ነበር።
‹‹ወደ ክልሉ ልሥራ ብዬ ወስኜ ስመጣም እስከመቼ ዩኒቨርሲቲ ተቀምጠን ዳር ሆነን እየተቸን ? ዳር ሆነን የአድናቆት ወይም የተቃውሞ ድጋፍ እናደርጋለን፤ ገባ ብለን ማገዝ አለብን የሚል አቋም ነበረኝ›› የሚሉት ሚኒስትሯ፤ ታምኖብን አግዙን ከተባልን ሄደን ማገዝ አለብን የሚል ቀና ሀሳብ እንደነበራቸው ይናገራሉ። በወቅቱ ወደ ክልል እርሳቸውና አንድ ሌላ ተጨማሪ ሰው ነበር የተጠሩት። ጥሪው ህልማቸው ባይሆንም አንዴ ከመጣ በኋላ ግን ማገዝ እንደሚኖርባቸው ለራሳቸው ቃል ገቡ። በአጋጣሚ ወደሚንስትርነት የታጩ ጊዜ ጠረጴዛቸውን ሁሉ አጽድተው ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ክልሉን ለማገዝ የገቡትን ቃል በማጠናቀቃቸው ነበር። ስለዚህ ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው ለማስተማር ወስነው ነበር።
በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ሹመቱን በድንገት ሰሙ። ከፍላጎታቸው ተቃራኒ ስለነበር ‹‹ለምን ወደሹመት›› የሚል ጥያቄ አቀረቡ። የተሰጣቸው ምላሽ ግን ‹‹መቼ አገራችሁን ልታግዙ ነው፣ እስከታመነብሽ ድረስ አገርሽን ማገልገል አለብሽ›› የሚል ነበር። ጥያቄው ደግሞ አሁን በህይወት በሌሉት አቶ ምግባሩ ከበደ የቀረበ ነበር። እርሳቸውም ጥያቄውን ተቀምብለው በሃሳቡ መስማማታቸውን ገለፁ።
በዚህ ወቅት አገርን ማገዝ አስፈላጊ እንደሆነም ይናገራሉ። አስቸጋሪ ፈተናዎች የተደቀኑበት ወቅት በመሆኑም ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር ወጥታ ወደ መልካሙ መንገድ እንድትሻገር እገዛ እንደሚያስፈልጋት ያምናሉ። በክልል እያሉም ይህን መሰል አመለካከት ነበራቸው።
ህልም፣ ባልም- መምህርት
‹‹አሁን የሆንኩት መሆን የምፈልገውን አይደለም›› ይላሉ አጋጣሚውን ሲናገሩ። ከልጅነታቸው ጀምሮ መሆን የሚመኙት እና ትልቁ ፍላጎታቸው መምህር መሆን ነበር። መምህርነት ይወዱታል፤ ያከብሩታልም። እስካሁን የሚኮሩበት ጊዜም መምህር የሆኑበትን ወቅት ነው። ‹‹አሁንም ሚንስትር ሆኜ ህልም የማየው ስለአስተማሪነቴ ነው። ስለሚንስትርነቴ ህልም አይቼ አላውቅም›› ይላሉ ሃሳባቸውን ጠንከር ባለ መልኩ ሲገልፁት።
ሴቶች የትም ቦታ ሆነው መሥራት እንደሚችሉ ግን ያምናሉ። እሳቸውም በተቀመጡበት ቦታ አቅማቸው የፈቀደውን እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ። የምርጫ ጉዳይ ከመጣ ግን ቀዳሚው ፍላጎታቸው መምህር መሆን ነው። አገርን በዚህ ሰዓት ማገዝ ምርጫ ውስጥ የሚገባ አይደለምና እውቀታቸውን ለዚሁ አላማ እያዋሉት ነው።
እናትነትና ሥልጣን
‹‹ሴት ሥራ ይኑራት፤ ሥልጣን ትያዝ …ተብሎ ብዙ ጊዜ ሲነገር እሰማለሁ ። እኔ ግን ሴት የመንግሥት ሥራ ስትይዝ፣ ሥልጣን ላይ ስትወጣ ቦታውን የምትይዘው ለአገር ስለምትጠቅም እንጂ ራሷን ለመጥቀም አደለም›› ይላሉ፤ የተሳሳተ ግንዛቤ መኖሩን እያሰመሩ። ሴት የምትጠቀመው በቤቷ ተቀምጣ ልጆቿን ማሳደግ፣ ቤተሰቧን መያዝ ብትችል መሆኑንም እንደሚያምኑ፤ የገቢ ምንጭ ካላጣች ተጠቃሚ የምትሆነው ልጆቿን በአግባቡ አሳድጋ ለአገር ጥሩ ዜጋ ማፍራት ስትችል መሆኑንም፤ ወደ መንግሥት ሥራ በተለይ ወደ ሥልጣን ትምጣ ሲባል ግን መቶ በመቶ አገር ለመጥቀም እንጂ ራሷ ብቻ ስለምትጠቅም አይደለም ይላሉ።
ወደ ሥራ፣ ሥልጣን ስትመጣም የቤተሰብ ጉዳይ ምንም ቢሆን ከእሷ ስለማይወጣ ተጨማሪ ዕዳ መሆኑንም ያነሳሉ። ሴት ልጅ የፈለገ ቢሆን ከቤተሰብ ሃላፊነት ነፃ መሆን አትችልም። ምንም ቢሆን እንኳን ማርገዝ፣ መውለድንና ማጥባትን መተው እንደማይቻል ይገልፃሉ። አርግዞ ወልዶ ልጅ ማሳደግ በላይ ደግሞ ከባድ ሃላፊነት እንደሌለ ነው የሚናገሩት።
‹‹በአንድ አገር ውስጥ ትልቁ ምሰሶም ይሄው ነው›› ይላሉ ዶክተር ሂሩት፤ ይሄንን ከባድ ሃላፊነት ተሸክሞ ለአገር ብቁ ዜጋ የማብቃት ትልቅ ሃላፊነት አለብን። የቤተሰብ ሃላፊ መሆን በጣም ብዙ ሸክም አለው። የቤተሰቡ ጣጣ እንኳን ቢቀር ማህበራዊ ሃላፊነቱ በራሱ ከባድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሥልጣን ተሸከሚ ማለት የቤቷን ሥልጣን ማን ተሸክሞላት ነው የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳ ይናገራሉ፤ የጉዳዩን ከባድነት ሲገልፁ። ስለዚህ ለእርሳቸው ሴት ባለሥልጣን ስትሆን አገር ትጠቅማለች እንጂ እሷ እና ቤተሰቧ ተጎጂ ናቸው የሚል አመለካከት አላቸው።
‹‹ሴት የተለየ ተሰጥኦ አላት ብዬ አምናለሁ›› ይላሉ ሚኒስትሯ፤ በራሳቸውም ሲያዩት ብዙ ነገር በአንድ ጊዜ ማከናወን እንደሚችሉ ይናገራሉ። ቤተሰብ ማስተዳደር፣ ማህበራዊ ጉዳይን እና የመንግሥት ሃላፊነት መወጣትን በምሳሌነት ያነሳሉ። ሌላው ሴት ዴሞክራት ናት፣ ሃቀኛ ናት፣ ሥራን ሠርታ ለውጥ ለማምጣት እንጂ ወንበር ይዛ ለመቀመጥ አትጨነቅም። ስለዚህ ሴቶች ወደ አመራርነት ሲመጡ አገር ይጠቀማል፤ ሰላም ይመጣል፤ ሙስናና አድሎን መቀነስ ይቻላል ይላሉ። ሁሉም ሰው በእኩልነት፣ በፍትሐዊነት፣ እስከ ሰብአዊነት ማክበር ጭምር የዘለቀ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ሴቶች ይሄንን ይወጣሉ ሲባል ከመጡበት ነገር አንፃር ማየት ይቻላል። ሴት ልጆቿን እኩል እያሳደገች፣ እያስተናገደች ስለምትመጣ የእዛ ልምድ ወደ ሀገር ይመጣና አገርን በእኩልነት ትጠቅማለች። ብልሹ የሚባል ሥርዓትን ማስተካከል ትችላለች ይላሉ።
ሽልማቱ የማን ነው?
‹‹በፓስፊክ ኤርያ ትራቭል ራይተርስ አሶሴሽን የ2019 በሚል የተሰጠን ሽልማት ሁለት ነው›› ይላሉ ዶክተር ሂሩት፤ አንዱ እንደ አገር ለተቋሙ ሌላው ደግሞ ተቋሙን ለሚመራው አካል ነው። እንደ ሀገር የተሰጠው ‹‹ቤስት ዴስትኔሽን አርኪኦሎጂ ዴስትኔሽን›› የሚል ነው። ይሄ ከቱሪዝም ሀብት አንፃር ወደ አገራችን የሚመጡ ቱሪስቶች ኢትዮጵያ በመሬት ውስጥ የታሪክ ቅርሶች የበለፀገችና ጥንታዊ የታሪክ አገር ናት በሚል በሰጡት ምስክርነት የተገኘ ሽልማት ነው።
‹‹የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እና ደብሊው ቲቲ ሲ›› በየዓመቱ ጥናት ያደርጋሉ። እያንዳንዱ አገር የት ደረጃ ላይ ነው የሚለውን አጥንተው ለአገሮች ይፋ ያደርጋሉ። ይህንን ጥናት ለዓለም መንግሥታት ጭምር ለዕቅድ መረጃ የሚሰጡ ናቸው። መረጃው ሲወሰድ በአርኪኦሎጂ እና ታሪክ ኢትዮጵያ እንደተመሰገነች ይናገራሉ። ኢትዮጵያ የዓለም ጥንታዊ ታሪክ ባለቤት መሆኗን፣ ታላላቅ የታሪክ ገድሎች እና ድሎች እንዳሏት፤ በአርኪዮሎጂም ከሉሲ የሰው ልጅ መገኛነት ጀምሮ ላለው ምስክርነት ያገኘችበት ነው።
ሁለተኛው ሽልማት ደግሞ ለሚንስትር የተሰጠ ነው። በሚንስትር ደረጃ ሲሰጥ ደግሞ ለመሪ የሚሰጥ ሽልማት ነው። የዚህም መረጃው ከዓለም ቱሪዝም ድርጅት የተወሰደ ነው። መረጃው 1ኛ ኢትዮጵያ ብዙ የቱሪስት መስህብ ያላት አገር ናት። መስህቦቿንም አልምታለች የሚል ነው። በዚህ ውስጥ የሚታየው የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ መንገዶች ውሃ፣ መብራት፣ መዳረሻዎች፣ ማረፊያ፣ መዝናኛ፣ የመፀዳጃ ስፍራዎች አሉ ወይ? ይሄንን በማልማት ጥሩ ደረጃ ላይ ናት ወይ? የሚለው ነው። ያሏትን መስህቦች፣ ራሷን እንደ አገር በማስተዋወቅ ጥሩ ደረጃ ላይ ናት። በመስኩ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል የሚል ነው። የዚህ ድምር ውጤት ከቱሪዝሙ ጥሩ ውጤት እያገኘች ነው ማለት ነው። ይሄ የ2019 ጥናት ውጤት ነው። በ2019 ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይሄ የአገር ውስጥ ገቢን ሳይጨምር ነው። በተጨማሪ የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ የቱሪስት መስህቦች መልማታቸውን ይናገራሉ ሚኒስትሯ።
በሁለተኛነት የሚያነሱት ደግሞ ኢትዮጵያ በተለያየ የዓለም አገራት ዓይን የምትገባ መሆኑን ነው። በተለይም ከቱሪዝምና ከባህል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ሀብቱ ስላላት ትኩረት እንደምትስብ ይናገራሉ። በዓለም ላይ የተወሰዱ ትልልቅ የሚባሉ ሊታዩ የሚችሉ ቅርሶችን እንኳን ተጽዕኖ ፈጥሮ የማስመለስ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከአፄ ቴዎድሮስ ሽሩባ ቁንዳላ ጀምሮ ዘውድ እስከማስመለስ ደርሰናል ይላሉ።
በዩኒስኮ የማይዳሰሱ ቅርስ ላይ ብዙ ቅርሶች እየተመዘገቡ ናቸው። ጥምቀት በሌሎች ዓለማት ቢኖርም የተመዘገበው ግን የአገራችን ብቻ መሆኑን ያነሳሉ። የኢትዮጵያ ጥምቀት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል። በዓለም ላይ ለምዝገባው 47 የማይዳሰስ ቅርስ ቀርቦ ከእነዚህ ቅርሶች የተመዘገቡት 5 ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያ እዛ ውስጥ እንደገባች ይናገራሉ። ሚኒስትሯ ይሄ እንደአገር ለመሥሪያ ቤቱ፣ እንደመሪም ለሃላፊው ትልቅ ውጤት ነው። እነዚህ ሁሉ ተዳምረው በግል ተሸላሚ መሆናቸውንም ይገልፃሉ። ይሄ ሽልማት ግን በመስኩ ከላይ እስከታች የተሳተፉ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ድምር ውጤት መሆኑን ከማንሳት አልተቆጠቡም። ሽልማቱ የርሳቸው ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን ይናገራሉ።
ገጠመኝ
ፓርላማውን በቴሌቪዥን እንጂ በአካል አላውቀውም ይላሉ ዶክተር ሂሩት ። ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርላማ የዘጠኝ ወር ሪፖርት አቅርቡ ተባለ። አሁን በዛ በማያውቁት ወንበር ላይ ተቀምጠው ሊያቀርቡ ሆነ። አውዱ ከበድ እንደሚል ይናገራሉ፤ ስለ ሁኔታው ሲያነሱ። በቦታው መባል ያለበትንም ሆነ የማይባለውን ለመለየት ከብዷቸው ነበር። ምንም ልምድ የሌለው ሰው ደግሞ ቢያንስ ከዚህ ቀደም የነበሩ ነገሮችን ሁሉ ቢያውቅ ጥሩ ነው ብለው ያስባሉ። እርሳቸው ሁሉንም እንደ መምህርነት ያስቡት ነበር። ስለዚህ የተለየ ዝግጅት አላደረጉም። አስተማሪ ሆነው ትልልቅ ኮንፈረንሶች ላይ ጥናቶች ያቀርባሉ። በክፍል ውስጥ ማስተማር ብዙ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ መገኘት አለ። የዘጠኝ ወር ሪፖርት ታቀርቢያለሽ ሲባሉ የተዘጋጁት በሪፖርቱ ላይ ብቻ ነበር።
በአቀራረቡ ዙሪያ ቅድመ ሁኔታዎችን የነገራቸው የለም። እሳቸውም አልጠየቁም። አስተማሪ መሆን ፕሮቶኮል የሚባሉትን ነገር ሁሉ ያስረሳል ይላሉ። ጭንቀትን እንደሚያርቅ እየተናገሩ። በሰዓቱም አንድ ኮንፈረንስ ላይ የሚገኙ ያክል ነበር ተዝናንተው የሄድት። በመድረኩ ላይ አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ መሐል፣ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ በሌላው አቅጣጫ ደግሞ ሚንስትር ዴኤታዎች ተሰይመዋል። አፈጉባኤው እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋን ሚንስትሯ ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ ጋብዙ ብለው አዘዙ። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢም ዶክተር ሂሩት ሪፖርቶዎትን አቅርቡ ብለው ጋበዟቸው። እሳቸውም ክብርት ወይዘሮ አበባ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አመሰግናለሁ ብለው ወደ ሪፖርቱ ሊገቡ ሲሉ አዳራሹ በሳቅ ተሞላ። እርሳቸውም ለምን እንደሳቁ ስላልገባቸው የድምጽ ማጉያው አልሰማ አለ ብለው ወደ ማይኩ ተጠጉ። በድጋሚ ቤቱ በሳቅ ተሞላ። ነገሩ ጭራሽ አልገባቸውም። ሪፖርቱን ወደ ማንበቡ ገቡ። በመግቢያቸው ላይ ግን የተከበሩ አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የተከበራችሁ የምክር ቤት አባለት ብለዋል።
መምህር ጥያቄ ሲጠየቅ ወዲያው መልስ ይሰጣል። እሳቸውም እንደዛ ነበሩ። ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ሲቀርላቸው ወዲያው መልስ ይሰጣሉ። ጥያቄዎቹ ተሰብስበው አንድ ላይ መመለስ ነበረበት፤ ያን አላደረጉም። በእርግጥ እነሱም አልተከፉም፣ ተደስተዋል። እሳቸው ግን ይሄንን ሁሉ የተረዱት በኋላ ነው። የመምህርነት ልምድ ምን ያህል እንዳገዛቸው የተገነዘቡበት ቀን ነበር። በምክር ቤቱ ያደረኩትና አባላቱን ያሳቀው ነገር የተነገራቸው ከወጡ በኋላ ነው። ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን እሳቸው ስህተት ሠርተው ነበር ብለው አያምኑም።
‹‹እንዳቀርብ ሪፖርቱን የጋበዘኝን ሰው ማመስገን ስህተቱ ምን ላይ እንደሆነ አሁንም ድረስ አልገባኝም›› በማለት በወቅቱ አባላቱ ያሳቃቸውን ሁኔታ ይገልፃሉ። መመስገን ያለበት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ነው በሚል ነው የተሰጣቸው ሂስ። ይሄ እንግዲህ እንደተሾሙ የገጠማቸው ፈገግ የሚያሰኝ ጊዜ ነበር።
አገራችን የት ትደርሳለች ?
‹‹ትበለፅጋለች፤ ኢትዮጵያ አሁን የምትፈልገው ሦስት ነገሮችን ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ። 1ኛ ፍቅር 2ኛ ሰላም 3ኛ ደግሞ ታታሪ የሥራ ባህል ያለው ህዝብ›› ይላሉ ዶክተር ሂሩት፤ ለምሳሌ ጋዜጠኛው በጋዜጠኝነቱ ህዝብን ማስተማር፣ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ከቻለ ተቀምጦ ከማውራት ህዝብን ከማጋጨት ወጥቶ ወደ ሥራ ከገባ ሀብትም፣ ቴክኖሎጂም ቀስ ብሎ ይደርሳል። በሦስቱ ብቻ ኢትዮጵያ ማደግና መበልፀግ ትችላለች የሚል እምነት እንዳላቸውም ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ታታሪ፣ ቅን ሠራተኛ ህዝብ ብቻ ነው የሚያስፈልጋት የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። ምክንያቱም ሲያስቀምጡ ደግሞ ‹‹ለመበልፀግ ግቢያችንን ከመቆፈር ብንጀምር ውጤታማ እንሆናለን። የደጃችንን መሬት ቆፍረን እንኳን ጎመን መዝራት ስንችል ይህን አናደርግም። ጓሮ ተደብቀን በፌስቡክ ወንድም ከወንድሙ ማጋጨትን ነው የምንሠራው›› በማለት በጠንካራ አገላለፅ ከዚህ ወጥተን ፍቅር፣ ሰላም፣ የሥራ ባህልና ታታሪነትን ይዘን መንቀሳቀስ ከጀመርን ቴክኖሎጂው በራሱ እግር ይመጣል የሚል ሃሳባቸውን ያጋራሉ።
ከምግብ አብሳይነት በላይ
ዶክተር ሂሩት ዛሬ ትልቅ በሚባለው ሃላፊነት ማማ ላይ ተቀምጠዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ባለቤት፣ ልጆች አሉ። ይሄንን ቤተሰብ በእናትነት ሚና ምግብ እያበሰሉ እየተወጡት ነው ? ጥያቄውን ወደ እኔ መልሰው ወረወሩ። ‹‹እኔን ነው የምትጠይቂው›› አዎ እርሶን። በጣም አስገራሚ ሳቅ ሳቁ። ደግመው ደጋግመው ሳቁ። ጥርሳቸው ብቻ ሳይሆን አይናቸው ጭምር። ቀጠሉ በሳቁ የታጀበ ምላሻቸውን ‹‹በእውነት ለመናገር ከሆነ ምንም ነገር ሰርቼ አልመግብም›› አሁንም ሳቁ ቀጠለ። ምክንያቱ ግን እንዲህ ነው ሲሉ ቀጠሉ…
‹‹አጋጣሚ ሆኖ እንጂ ቀደም ሲልም የተለየ ባህሪ አለኝ›› በማለት ያ ባህሪያቸው ወጥ መሥራት፣ እንጀራ መጋገር … የመሳሰሉ በልምድ የሴቶች የሚባሉ ሥራዎችን እንደማይሠሩ ነገሩኝ። ልጅ ሆነውም እንደማይወዱ ይናገራሉ። በቤታቸው ካሉ ልጆች ሥራ ብዙም ሳይሰሩ ካደጉት ውስጥ ይመደባሉ። ከአካባቢው ልጆች አንፃር እርሳቸው የተለየ አስተዳደግ ነበራቸው። አብዛኛውን ጊዜያቸውን በድግግሞሽ ሥራ አላሳለፉም። ሆኖም እንጀራ መጋገር፣ ወጥ መሥራት የሚባሉትን ሙያዎች ያውቃሉ። በብዛት ይሠሩ የነበረው ግን ጽዳት ነው። በቤት ውስጥም የሚታወቁትም ሲፈልጉና ውስጣቸው ሲፈቅድ ብቻ ሥራ እንደሚያግዙ ነው። ሲያሻቸው ጥሩ እንጀራ ይጋግራሉ ጥፍጥ ያለች ወጥ ይሠራሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በቤት ውስጥ በጽዳት ታዋቂ ነበሩ። ከልብስ አጠባ እስከ ቤት ጽዳት ይሠሩ ነበር። ዕቃ ማጠብ የመጀመሪያ የሥራ ምርጫቸው ነበር።
‹‹በልጅነቴ በጣም አመፀኛ ነኝ። የሴት ሥራ አልወድም ያ አመጽ ደግሞ ጠቅሞኛል። በድሮ ጊዜ የሴት የሚባሉ ሥራዎችን እንዳልሠራ ያደረገው አባቴ ነው። አባቴ 24 ሰዓት እንዳነብ፣ እንድጽፍ ነው የሚፈልገው›› በማለት እርሳቸውም የአባታቸውን ፍላጎት ማሟላት ምርጫቸው እንደነበር ይናገራሉ። ይህን ፍላጎት ለመፈፀም ደግሞ ከእናታቸው ይሸሹ እንደነበር ይናገራሉ። በዚህ በዚህ እናታቸውን እንዳላረኩ ይሰማቸዋል። የአባታቸውን ፍላጎት ደግሞ ፈፅመዋል። ሆኖም የአባታቸውን መስመር ሲይዙ እናታቸው እንደደገፏቸው አልሸሸጉም። ምክንያቱም እንደሌሎቹ እናቶች ሥራ ካልሠራሽ ተብሎ ቅጣት አይጠብቃቸውም ነበር።
ሴት ልጅ ለትዳር የምትመረጥበት አንዱ መመዘኛ የቤት ውስጥ ሙያ አላት የሚል ቢሆንም ዶክተር ሂሩት ግን እንዲህ ይላሉ ‹‹በጣም የሚገርመው ደግሞ ‹ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ › የሚባል አባባል አለ። ትዳር ይዤ ወልጄም የራሴን ቤት ከመሰረትኩ በኋላም ወጥ ሥሪ እንጀራ ጋግሪ የሚለኝ ባለቤት አይደለም ያጋጠመኝ›› ፤ እንዲያውም እንዲማሩ የሚያግዛቸው፣ በመምህርነት ሲሠሩም ህፃናት ልጆቻቸውን እየተንከባከበ ለዚህ እንዳበቋቸው ይገልፃሉ። የባለቤታቸውን ጥንካሬም ሲገልፁ ‹‹ወጥ መሥራት ሲኖርበት ሠርቶ፣ ገበያ ገብይቶ፣ ወፍጮ ቤት ሄዶ ልጅም አሳድጓል›› ይላሉ። በተለይ ከ1988 እስከ 1997 ድረስ የሴት የሚባሉት ሥራዎችን ሁሉ እየሠራ እንዳስተማራቸው ይናገራሉ። ያ የሴት ሥራ የሚሉት ልምዳቸው ባለቤታቸው ጋር ደርሶ ከቤት ውስጥ ሥራ ነፃ መሆናቸውን ይናገራሉ። አሁንም ሲፈልጉ እንጂ ሥራዬ ብለው እንደማይሠሩ ይናገራሉ።
ዶክተር ሂሩት አራት ልጆችን ወልደዋል። ዛሬ ሁለቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ በየደረጃው በትምህርት ላይ ናቸው። ‹‹ለልጆቼ ጥሩ እናት ነኝ። ፍቅርን በቃላት መግለጽ አይቻልም እንጂ በጣም ነው የምወዳቸው፤ እነሱም በጣም የሚወዱኝ እና የሚሰስቱኝ ናቸው። ይሄንን ከድርጊታቸው አስተውላለሁ›› ይላሉ፤ ለልጆቻቸው አርአያ መሆንን ይፈልጋሉ። እርሳቸውን እንዲከተሉ፣ ራሳቸውን ጠንካራ እንዲያደርጉ ምኞታቸው ነው። አንድ ሥራ ብቻ እንደማይሠሩ ይናገራሉ። እረፍት አልባ ናቸው። በእንቅልፍ አይታወቁም፤ ተቀምጠው አይውሉም። ልጆቻቸውም የሚያውቋቸው በእረፍት አልባ ሴትነቴ ነው። እነሱም ይሄንን የሥራ ባህል እንደሚወስዱ ያምናሉ። ከዚያ ውጭ ሰው ማክበር፣ ደግነት ከቤተሰብ የወረሱት ነው። ልጆቻቸውም ይሄን እንደሚተገብሩ ያምናሉ።
የሚኒስትሯ መልክት
ኮሮና ለአገራችንም ሆነ ለህዝባችን ትልቅ ጠላት ይላሉ። የጋራ ጠላት እንደሆነም ይናገራሉ። በኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም መስክ፣ በባህል፣ በሃይማት… ላይ የተጋረጠ አደጋም እንደሆነም ይገልፃሉ። ከተደማመጥን የመንግሥት እና የጤና ሚንስትር መልዕክቶችን መተግበር ከቻልን ደግሞ የምንቆጣጠረው መሆኑን ተናግረው ይህንኑ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ይገልፃሉ። ለዚህ ሕብረት ያስፈልጋል ይላሉ። አንድ ሆኖ ተረዳድቶ፣ አዳዲስ ሐሳቦችን በየሥራ ዘርፉ አመንጭቶ እና ተግብሮ ጉዳቱ ቅስም ሰባሪ ከመሆኑ በፊት ልናቆመው ልናቆመው እንደሚገባና እንደምንችል አምናለሁ ይላሉ። ለዚህ ግን መደማመጥ ወሳኝ መሆኑን በምክረ ሃሳባቸው ይገልፃሉ። ‹‹ቅድሚያ ለሚያስፈልገው ቀድሞ መስጠት ይገባል›› መቋጫ መልክታቸው ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2012
አልማዝ አያሌው