በጠቅላላ ህክምና ፣ በውስጥ ደዌ ፣ በሳንባና በጽኑ ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ያደረጉ ናቸው፡፡ ዛሬ ደግሞ በኮሮና ዙሪያ እንዲሰሩ ከተመረጡ ሲኒየር ዶክተሮች መካከል አንዱ ሆነው የአገራቸውን ሕዝብ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ለሙያው ትልቅ ክብር እና ሕዝብን በቅንነት የማገልገል ሰብአዊነት እንዳላቸው ከንግግራቸው ለመረዳት ብዙም አይከብድም፡፡ ወደሙያው ሲገቡ ለሀገራቸውና ለሕዝቡ በገቡት ቃል ብቻም ሳይሆን ከዚያም ከፍ ባለ ደረጃ ራሳቸው ሞተው ሌሎችን ለማገልገል ቆርጠው የተነሱ ናቸው። በዚህ አስከፊ ታሪካዊ ወቅት በመስራታቸው «ደስ ብሎኝ ነው ይህንን እያደረኩ ያለሁት» ሲሉ ደጋግመው ይናገራሉ፡፡
«አንድ ሰው በጥንቃቄ ጉድለት ካልሆነ በስተቀር የችግሩ ሰለባ አይሆንም፡፡ በዚያ ላይ ይህ ዕድል መኖራችንን ለአገራችን የምናሳይበት ነው፡፡ ስለዚህም ለአገሬ ሕዝብ የምችለውን አድርጌ ብሞት ለእኔ ደስታ እንጂ ኀዘን የሚሆንበት አጋጣሚ የለም፡፡ ወታደር ቤተሰቡን ትቶ ሲዘምት አገሩን ከራሱ አብልጦ ስለሚወድ ነው፡፡ ለእኛ የጤና ባለሙያዎችም ይሄ አጋጣሚ የወታደርነት ማዕረግን የምንቀዳጅበት ነውና ወደንና ደስ ብሎን ሕዝባችንን ለማዳን ልንሰራበት ይገባል» ይላሉ፡፡ እናም ይህ የህክምና ጊዜ እንዴት መታለፍ እንዳለበት፣ የእስከዛሬው የሕይወት ጉዟቸው ምን እንደሚመስል አውግተውናልና አንባብያንም ከሕይወት ልምዳቸው ትቋደሱ ዘንድ የዛሬ «የሕይወት እንዲህ ናት» አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል፤ዲያቆን ዶክተር ዳዊት ከበደን፡፡
ባለራዕዩ ነጋዴ
በቤት ውስጥ ስምንት ልጆች ይኖራሉ። ሁሉም ከትምህርት በኋላ ቤቱን የሚደጉሙበት ሥራ ይሰራሉ። ስለዚህም ታዳጊው ዳዊትም የዚህ ሥራ ተሳታፊ ነበር። በየጠጅ ቤት፤ በኬላዎችና መኪኖች በሚቆሙበት ቦታ ሁሉ ቆሎ እያዞረ ይሸጣል። ፓስቲና ዳቦ፣ ብርቱካንና… በማዞር ለፈላጊው ማህበረሰብ ያቀርባል። በትውልድ አካባቢው ጅማ ከተማ አጂፕ ሰፈር ውስጥም እነዚህን ነገሮች ይዞ በመገኘት ፈጣን ነው። የሰራውን ያህል ሰርቶ ያገኘውን ሳንቲም ይዞ ወደቤት በመመለስ ለእናቱ ያስረክባል። በገንዘቡ እናት ቤተሰቡን ማስተዳደር፣ መመገብ ሌላም ሌላም አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለቤተሰቡ ማሟላት አለባቸውና ዳዊትም ይሄ ጎዶሎ እንዳይበል የራሱን የልጅነት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
አባቱ በልጅነታቸው በማረፋቸው ይሄን ችግር እንደተጋፈጡና የኑሮን ተራራ በጋራ ለመወጣት መገደዳቸውን ያስታውሳሉ። ኢኮኖሚያዊ ችግሩን በጋራ ለማሸነፍ ጥረት እያደረጉ እናት ደግሞ በሥነምግባር ተኮትኩተው፣ በትምህርት በቅተው ለሀገርና ለወገን የሚተርፉ ልጆች እንዲሆኑላቸው ጥረት ያደርጋሉ። ዳቦና ቆሎ ሲሸጡ በማህበረሰቡ ዘንድ «ዱርዬ» እየተባሉ ከሚፈረጁት ጋር ቢውሉም እነርሱ ግን ሥነሥርዓት ያላቸው፣ታዛዥና ታታሪ እንዲሆኑ አድርገው እንዳሳደጓቸው አጫውተውናል።
ቤተሰቦቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ሁሉም የነገደውን አምጥቶ ለእናቱ በሚሰጠው ገንዘብ እንደሚተዳደሩ ያጫወቱን ዲያቆን ዶክተር ዳዊት፤ ብዙዎቹን የሚነገዱ ነገሮች እናታቸው በቤት ውስጥ አዘጋጅተው ይሰጧቸዋል። በዚህም ገና ሲወጡ ብዙ ምክሮችን ይለግሷቸው እንደነበር አይረሱትም። በተለይም ከሰው ጋር መጣላትና መሳደብን አጥብቀው ይጠላሉና ይህንን እንዳያደርጉ ያስጠነቅቋቸዋል። እነርሱም ይህንን የእናታቸውን ምክር ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ይህ ደግሞ ብርታት ሰጥቷቸው ደንበኞቻቸው እንዲበራከቱ እንዳገዛቸውም አልሸሸጉም።
ጎረቤትና የአካባቢ ሰዎች እንደ ወላጅ አድርገው እንዳሳደጓቸው የሚናገሩት እንግዳችን፤ «ከየት መጣነቴን ማንም ባይረዳው ደስ ይለኛል። እኔን የሚገልጠኝ ኢትዮጵያዊነት ነው። ምክንያቱም በአደኩበት አካባቢ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ጉራጌው፣ አማራው ከአገር አልፎ ኤርትራውያን ጭምር ቤተሰብ ሆነው ስላሳደጉኝ ከዚህ ነኝ ማለት አይመቸኝምና ነው»ይላሉ።
ባለታሪኩ፤በልጅነት ብዙም የጨዋታ ጊዜ አልነበራቸውም። ሰዓት ካገኙም የሚጫወቱ ልጆችን መመልከት እንጂ ተሳታፊ አይደሉም። ስለዚህ በባህሪያቸው ጭምት ከሚባሉት ተርታ የሚመደቡ ናቸው። ለእርሳቸው ጨዋታ፣ ሰዓትም ማሳለፊያቸው ሥራና ንባብ ነው። በዚህም ጓደኞቻቸው «ቸካዩ»የሚል ቅጽል ስም አውጥተውላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
እናታቸው ልጆቻቸውን ወደ ሥራና ትምህርት ቤት ካሰማሩ በኋላም በቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውኑ እንደነበር የሚያነሱት ባለታሪኩ፤ እግዚአብሔር ልዩ ጸጋ ሰጥቷታል። በዚህም ሰዎችን በተለያየ መንገድ ታክማለች። ለአብነትም ወጌሻና የባህል አዋላጅ በመሆኗ ለተቸገረ ሁሉ ትደርሳለች። ይህ ደግሞ ብዙ ነገሮችን እንዳስተማራቸውና የልጅነት ፍላጎታቸው ሕክምና ላይ እንዲያርፍ እንዳደረገም ነግረውናል።
ያልተታከተበት ጥናት
ተማሪዎች እረፍት ሲወጡም ከማንበብና ጥያቄዎችን ከመስራት የማይርቁት እንግዳችን፤ ሁልጊዜ እውቀታቸውን የሚያጎለብቱበትን መንገዶችን መከተል ያስደስታቸዋል። በዚህም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተከታተሉበት ጅሬን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት የሚፎካከራቸው አልነበረም። ከአንድ ልጅ በስተቀር። እርሱንም ቢሆን በፍቅር አሸንፈውት የራሳቸው በማድረግ የዛሬ መድረሻቸውን እንዲያመቻችላቸው አድርገውታል።
ጓደኛቸውና ከወንድሞቻቸው በላይ የሚወዱት ልጅ መሰለ ሀየሎም የሚባል ሲሆን፤ እርሱ ባይኖር አሁን ላሉበት ደረጃ እንደሚበቁ እርግጠኛ እንዳልነበሩ ያነሳሉ። የሕይወቴ ዋስትናም ነበር ይሉታል። በጣም ጎበዝ ተማሪ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የትምህርት ቤቱን የአንደኝነት ደረጃ ለመያዝ እልህና ፉክክር ውስጥ ይገቡም ነበር። ሆኖም ይህ እንደማያዋጣ የተረዱት ባለታሪኩ ከእናታቸው መልካምነትን ተምረዋልና ከተፎካካሪያቸው ጋር ተቀራርበው አብረው ለማጥናት ይስማማሉ። ከዚያማ የጠነከረ አንድነታቸውን በሁሉም ዘርፍ ማሳየታቸውን ቀጠሉ።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅሬን መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቀጠሉት ዲያቆን ዶክተር ዳዊት፤ የሳይንስ ትምህርቶችን አጥብቀው ይወዱ ነበር። በዚህም በቆይታቸው የተሻለው ውጤት በሳይንስ ትምህርት ላይ ነው። ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ አራት ነጥብ በማምጣትም የመቀሌ ዩኒቨርስቲን በፕሪ ኢንጂነሪግ የትምህርት መስክ ተቀላቀሉ። ይሁን ና ከሶስት መንፈቅ ዓመት በላይ በዚያ አልቆዩም። ምክንያቱም በጣም ታመው ነበር። ስለዚህም ለቤተሰብ ቅርብ ሆነው እንዲማሩ በማሰብ ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተቀየሩ። ጅማ ከተዛወሩ በኋላ ደግሞ በጣም የሚወዱትንና የልጅነት ህልማቸው የሆነውን ትምህርት መስክ እንዲቀላቀሉ ሆነዋል። በጠቅላላ ህክምናም በማዕረግ ተመርቀው ትምህርቱን አጠናቀዋል።
ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይወስደናል። ይሄ ከሁለት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ሲሆን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመግባት በውስጥ ደዌ ስፔሻላይዝድ አድርገዋል። ሦስት ዓመት የአገልግሎት ክፍያቸውን ከጨረሱ በኋላ ደግሞ ተመልሰው በመምጣት ሌላ ትምህርት ተምረዋል። ይህም የሳንባ ሰብ ስፕሻሊስት ለመሆን የበቁበት ነው።
ትምህርት በቃኝ የማይሉት እንግዳችን፤ በተማሩበት ትምህርት ቤት እያስተማሩ፣ ሕክምናውን እየሰሩም ሌላ ትምህርት ደግሞ ተምረዋል። ይህኛው የትምህርት መስክ ከሌሎቹ ጠንከር ያለ እንደነበር ያስታውሳሉ። ምክንያቱም በአገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ በውጭ አገር ትምህርቱን የሚሰጡት የውጭ ዜጎች ስለነበሩ ትንሽ ፈትኗቸው እንደነበር ያነሳሉ። ያም ሆኖ ግን በተሻለ ውጤት ማጠናቀቃቸውን ይናገራሉ።
ትምህርቱ የጽኑ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ሲሆን፤ እስከአሁን ድረስ እያገለገሉበት ይገኛሉ። ከዚያ በኋላ መማር ቢፈልጉም ብዙ የሚጨምሩት እንደሌለ ስለሚያውቁ አልቀጠሉበትም። ከዚያ ይልቅ በሙያው እየሰሩ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ይከታተላሉ። በምርምር፣ በተግባር ሥራ እና በሥልጠና የበለጠ ሙያቸውን ማጎልበት ላይ ተጠምደዋል።
እንግዳችን፤ በርካታ ሥልጠናዎች ወስደዋል። በተለይም በአገሪቱ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከሰቱ የነበሩ የሕክምና ዘርፎች ላይ በስፋት ሰልጥነዋል። ሰርተውባቸዋልም። ከእነዚህ መካከል ቲቪና ኤችአይቪ፣በክሊኒካል ኢፒዶሞሎጂና በአመራርነት በዋናነት የወሰዷቸው ሥልጠናዎች የሚጠቀሱ መሆናቸውንም አጫውተውናል። በዚያ ላይ እውቀት የሚገኘው በትምህርት ብቻ ሳይሆን ምርምሮችንም በመስራት ነውና ይህንን ለማድረግ ሰፊ ዕድል አላቸው። ስለዚህም ዕድሉን እየተጠቀሙበት መሆኑን ይናገራሉ።
ዲያቆን ዶክተር ዳዊት፤ የተማሩት ዘመናዊውን ትምህርት ብቻ አይደለም። በሌላው ምዕራፍ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ የአብነት ትምህርትን ተምረዋል። በዚህም የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያምን፣ አንቀጸ ብርሃንን፣ ይወድስዋ መላዕክት፣ መዝሙረ ዳዊት፣ መልካመልኮችንና ቅዳሴንም በሚገባ አጥንተዋል። ከዚያ የድቁንና ማዕረግ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። በዚህም ሙያቸው ቤተ ክርስቲያንን በመቅደስ አገልግለዋል።
ታታሪው ሀኪም
መስራትን የተለማመዱት ገና ልጅ እያሉ ነው። ቤተሰብ መተጋገዝን ስላስተማራቸው ያኔ ቆሎ፣ ብርቱካንና ዳቦ በመሸጥ ያጠራቀሙትን ገንዘብ ለሚፈልጉት ነገር በማዋል የመስራትንና አብሮ የመብላትን ባህል ለምደውታል፤ ኖረውበታልም። ከዚያ ተምረው ለአገራቸው የተቻላቸውን ለማበርከት ሕክምናው ላይ መስራታቸውን ቀጠሉ።
በውጤት ከሆነ የተሻለ ቦታ የመመደብ አቅሙ ነበራቸው። ነገር ግን በችግር ተቆራምደው ለዚህ ያበቋቸው ቤተሰቦች ላይ ከዚህ በላይ ሸክም መሆን አልፈለጉም። ስለዚህም በቀጥታ ወደ ኦሮሚያ ጤና ቢሮ በማምራት መቱ ካርል ሆስፒታል ዶክተር ያስፈልገዋልና እዚያ እንዲመድቧቸው ጠየቁ።
መቱ ካርል ሆስፒታል ሠራተኛ እንደሚያስፈልገው ያወቁት የጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ ትምህርት ሲወጡም ሆነ አንዳንድ ሥራዎችን ሲሰሩ እዚያ ይሄዳሉና ነው። ስለዚህም እርሳቸው የዚህ ዕድል ተጠቃሚ በመሆናቸው የቀጣይ ጉዟቸውን በእዚያ እንዲሆን አድርገዋል። ስለዚህም የጤና ቢሮውም ፈቃዱን ሰጥቷቸው ተመድበው ጠቅላላ ሐኪም በመሆን ሁለት ዓመት ሰሩ። ጎን ለጎን ደግሞ የውስጥ ደዌ ክፍልም ኃላፊ ሆነው አገልግሎት ሰጥተዋል።
የሆስፒታሉ ኤችአይቪ ኤድስ አስተባባሪ በመሆንም ሰርተዋል። ከዚያ ወደ ትምህርት በመሄዳቸው ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ነው ወደ ሥራ የገቡት። ያስተማራቸው መቱ ካርል ሆስፒታል በመሆኑ ወደ ሆስፒታሉ በመመለስ በዋናነት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሆነው ማገልገላቸውን ቀጠሉ። ከዚያ በተጨማሪም የውስጥ ደዌና የጽኑ ሕክምና ክፍሉ ኃላፊ በመሆንም ሰርተዋል።
ለትምህርት ወደ ጥቁር አንበሳ በመምጣታቸው ምክንያት ተማሪም ሠራተኛም በመሆን ማገልገላቸውን ቀጠሉበት። በዚህም በጥቁር አንበሳ ከሁለት ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ የጽኑ ሕሙማን ክፍሉ ዳይሬክተር ሆነው ማገልገል ጀመሩ። በተጨማሪ የአይ ሲ ክፍሉ ዳይሬክተርም ናቸው።
ብዙ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በዚህ መስሪያቤት እንደሆነ ያወጉን ዲያቆን ዶክተር ዳዊት፤ ለአንድ ዓመት ያህል ሆስፒታሉን የጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ሆነውም አገልግለዋል። ወደ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል እስከተዛወሩበት ጊዜ ድረስ ሁለት ክፍሎችን በዳይሬክተርነት እየመሩ፤ በመምህርነት፣ በሕክምና እና በተመራማሪነት እየሰሩ ነበር። ከዚያ ባሻገር የድህረምረቃ ተማሪዎች ትምህርት ክፍል አስተባባሪም ናቸው።
ዛሬ ደግሞ ኤካ ኮተቤ ጀነራል ሆስፒታል ውስጥ ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪም በመሆን ሕክምና እየሰጡ ይገኛሉ። በሕክምና ትምህርት ደረጃዎችን ከፍ እያደረጉ ሲኬድ ብዙ መስራትን ይጠይቃልና አሁን የሕክምና ቡድኑን የማስተባበር ኃላፊነትን ጨምረው እየሰሩ እንደሆነ አጫውተውናል።
ደዌና ፈውስ
«ሕክምና ለዘመናት የኖረ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሙያ ነው። እንዲህ በተደራጀ መልኩ ሳይሰራበት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደምናገኘው በእነ ሉቃስ አማካኝነት ሕክምና ሲከናወን ቆይቷል። በዚህም ብዙዎች መፈወስ ችለዋል። ዛሬም ጥበብን ለሰው ልጆች ሁሉ አምላክ በማደሉ የተነሳ በሕክምና ባለሙያው አማካኝነት ፈውስን ይሰጣል። ስለዚህም እኛ ሐኪሞች ምክንያት ነን። ስለዚህም ወደ ህመምተኛ ስንጠጋም ሆነ እነርሱን ስናግዝ የአምላክን ፈቃድ እየፈጸምን እንደሆነ ሊሰማን ይገባል።» ይላሉ ዲያቆን ዶክተር ዳዊት። ሰዎችን ለመርዳት የተሰጠንን ጸጋ አለመጠቀም አለማወቅ ነው። ሌሎችን ማገዝና ከችግራቸው እንዲላቀቁ ያለማድረግ ፍላጎትም ነው። እናም ሕክምና የተሰጠን ጥበብ ማበልጸጊያ፣ ለሰዎች መኖሪያና አገርን መታደጊያ ነው። ስለዚህም ባለሟሉ ይህንን መጠቀም ሲችል ሕክምና እውን ሆነ ማለት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
ህመምን በተመለከተ ሲያነሱ ደግሞ እንዲህ ይላሉ። ህመም የተፈጥሮ ኡደት ነው። ሰው ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል እንደምንለው ሁሉ ይታመማልም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ጾታ፣ ዕድሜና ማንነት አይገድባቸውም። በሁሉም ሥነፍጥረት ላይ ይደርሳሉ። ስለሆነም ሕክምናና ህመም በተፈጥሮ ሂደት ውስጥ የሚከወኑ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። እንዴት ይሰናሰላሉ ከተባለ ደግሞ ሙያውና ህመሙ ተገናኝተው ፈውስ ሲገኝባቸው ነው። በሕክምና ሙያ ላይ የሚያስደስተውና ደመወዝ የሚሆነው ህመምተኞች በባለሙያው ተረድተው ፈውስን ሲያገኙ ነው። ምርቃቱ ዘወትር ክፍያ ነው። እናም ይህንን አምኖ መስራት ሲቻል ተናበዋል ማለት ይቻላል።
ዲያቆን ዶክተር ዳዊት፤ የህመምተኞች ምስጋና ለሌላ የተሻለ ነገር ያነሳሳል፤ ያበረታልም። በዚያው ልክ ደግሞ ሕይወታቸው ሲያልፍ ማየት ከውስጥ የማይጠፋ ጸጸትን ይሰጣል። በተለይ ማድረግ እየተቻለ በተለያዩ ምክንያቶች ማድረግ አለመቻል ከተፈጠረ ሁሌም የማይጠፋ ጸጸትን ከልብ ውስጥ ያስቀምጣል። ይህ ደግሞ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ዘወትር ያጋጥማል። መሣሪያው ሲኖር መድኃኒቱ፤ መድኃኒቱ ሲኖር ደግሞ የመሣሪያ እጥረት ይገጥማል። በዚህም የሰዎች ሕይወት ያልፋል። እናም ሀኪሙ ዘወትር እንዲያዝን ያደርገዋል። ግን ሌሎችን ማዳን ግዴታው ስለሆነ ይህንን ትቶ ለሌላ ተስፋ ይነሳል ይላሉ በሕክምና ሕይወት ምን ያህል ከባድና አስጨናቂ እንደሆነ ሲያስረዱ።
ሕክምና ሲነሳ በየጊዜው የሚመጡ አዳዲስ ክስተቶችን ማንሳት ግድ ነው። በዚህም አሁን ዓለምንም ሆነ አገራችንን እያሰጋ ያለው ኮሮና ቫይረስ ይጠቀሳል። ይህ ወረርሽኝን በቀላሉ መቀነስ የሚቻለው የሥነልቦና ጫናን በመቀነስ ሲሆን፤ ጭንቀትና ፍራቻ ከጠፋ መከላከሉ ላይ በሚገባ እያንዳንዱ ግለሰብ መስራት ይችላል። ሆኖም በፍራቻ ብቻ የሚጓዝ ከሆነ አደጋው የከፋ ይሆናል። በዚህም አሁን በምንሰራበት ሁኔታ መጀመሪያ በሕክምናው የሚደረገው የሥነልቦና ጫናውን መቀነስ ላይ ነው። የሥነልቦና ጫናን መቀነስ ህመምተኛውን እንዲያገግም ዕድል ይሰጣል። ሲኒየር ሐኪም እነርሱን እንዲያግዝ እየተደረገ በመሆኑና እነርሱም ይህንን በማወቃቸው ተስፋ እንደሚሆናቸው አምነው የተባሉትን እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል። ይህ ደግሞ ማገገም ብቻ ሳይሆን የሚድነውም እንዲበዛ ይረዳል ብለውናል።
የራስ ፈተና
በጎ ነገር ሲሰራ ብዙ ጊዜ የተሳሳተ ምልከታ ይፈጠራል። በዚህም ካርል ሆስፒታል በሚሰሩበት ጊዜ የራሳቸውን ክሊኒክ ከፍተው ስለነበር በእረፍት ጊዜያቸው እዚያ ይሰራሉ። ሆኖም ይህ ሥራቸው ያልተመቻቸው ሰዎች ይነሱባቸዋል። ህመምተኞችን አያይም፤ በሥርዓት አያክምም እና መሰል ቅሬታዎችንም ያቀርቡባቸው እንደነበር ይናገራሉ። እርሳቸው ግን የምሳ ሰዓታቸውን ጭምር ሆስፒታሉንና ህሙማኑን ያገለግሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የራሳቸው ክሊኒክም ቢሆን የሚሄዱት ከ12፡30 በኋላ ነበር። ሆኖም የሰዎች ምልከታ ግን እርሳቸው ከሚያስቡት በተቃራኒው ነውና ብዙ ነገር ይሏቸው እንደነበር ያነሳሉ። ሆኖም የሰው ሕይወት እንጂ ገንዘብ አይበልጥም የሚለው እምነታቸው ነውና ነገሩን ወደጎን በመተው አምሽተው ጭምር ሰዎችን ለመርዳት ይታትሩ እንደነበር አውግተውናል። ግን በሥራቸው እየተደሰቱ ባለመሆኑ ከቦታው ለመልቀቅ እንዳስገደዳቸው ያነሳሉ።
ጽኑ ሕክምና ላይ ያለው ፈተናም አንዱ ችግር እንደነበር ያወሳሉ። በተለይም በማህበረሰቡ ዘንድ በጣም የታመመ ሁሉ እዚያ ክፍል ውስጥ ይግባ ብለው ማመኑ ከብዙዎች ጋር ያጋጫቸው ነበር። ሆኖም እዚህ ክፍል ውስጥ መግባት ያለበት በጣም የታመመና የሚጠቀም መሆን እንዳለበት ስለሚያውቁና የእርሳቸው ውሳኔ ብቻ አለመሆኑን ስለሚረዱ ለማስረዳት እንደሚሞክሩ አጫውተውናል።
ኮሮና እና ፈተናው
ብዙ መለማመድና መተው ያለብን ነገሮች አሉ። በተለይ ለበሽታው ተጋላጭ የሚያደርጉ ባህሎችን እየተከፋንም ቢሆን ማቆም ግዴታችን ነው። ለአብነት በጋራ መብላትን ለጊዜውም ቢሆን ማቋረጥ ያስፈልጋል። እኔም ሆንኩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ብቻ መብላትን ፈጽሞ አይሞክሩትም። ጾሙን ማደርንም ይመርጥ ይሆናል። ነገር ግን ለሚያልፍ ነገር የማያልፈውን ችግር መቀበል የለብንምና እየመረረንም ቢሆን ልንተገብረው ይገባል ይላሉ።
አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፤ አለመነካካትና መሰል መከላከያዎችን ማህበረሰቡ ብቻ ሳይሆን የሕክምና ባለሙያዎችም ገና አልተለማመዱትም። በዚህም ከስህተት መመለስና አርአያ መሆን ላይ ክፍተት መኖሩ አንዱ ፈተና እንደሆነም ያነሳሉ።
«ወደ ሕክምናው ስንገባ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ጓደኛም እዚህ እንዳትመጣ ሊል ይችላል። ብዙ ጓደኞቼም ኮተቤ ከገባህ መገናኘታችን ይቆማል ብለዋል። በእነርሱ ዓይን ደግሞ ትክክል ናቸው። ምክንያቱም አንድ ሐኪም ራሱን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ሊያሲዝ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በመሆኑም መራቁ አማራጭ ነው።›› ያሉን እንግዳችን፤ ለዚህም በሕክምና ጣቢያው አካባቢ በሕክምናው ዙሪያ የሚሰሩት ሐኪሞች መኖሪያ ተዘጋጅቶላቸው እየሰሩ መሆናቸውን አውግተውናል። እርሳቸው ወደዚሁ የሕክምና መስጫ ቦታ የመጡት ከሳምንት በፊት በመሆኑ ቦታ እስኪገኝ ድረስ ቤተሰብ ጋር እየተመላለሱ እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ ቤተሰብ ባይፈራም እርሳቸው ግን እየተሳቀቁ እንደሚያደርጉት አጫውተውናል። በሥራው ግን ደስተኛ መሆናቸውን እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ። ‹‹ለዓመታት ይህንን ማድረግ የምንችልበት አጋጣሚ አልተፈጠረም። ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ነው ተመሳሳይ ነገር የተፈጠረው። ስለዚህም ትውልዱ ታሪክ ሆኖ የሚያወራው ነገር ላይ መሳተፍ መቻሌ ዕድለኝነት ነው።» ሲሉ ይናገራሉ።
ቤተሰብ
ባለቤታቸውን ያገኟት መቱ ካርል ሆስፒታል በሚያስተምሩበት ጊዜ ነው፤ እርሷ የጤና ሳይንስ ተማሪ ነበረች። በዚያ ላይ ሆስፒታሉ ውስጥ በተደጋጋሚ ለልምምድ ስለሚመጡም ትውውቃቸው እንዲጠነክር ሆኗል። በይበልጥ ግን ለትዳር ያበቃቸው ነገር ከማህበራቸው አባላት ውስጥ አንዷ ጋር ተከራይተው እንዲማሩ በሚሆንበት ጊዜ እርሷ እዚያ በማረፏና እርሳቸውና ሌሎች ጓደኞቻቸው በዚያ ቤት ስለሚሄዱ የመገናኛ ጊዜያቸው በመስፋቱ ነው፡፡ በዚህም የበለጠ ውስጣቸውን የሚገላለጹበት ዕድልን አገኙ። የጋብቻ ጊዜያቸውንም አፋጥነው አንድ ላይ የመሆን ጊዜያቸውን አቀረቡ። ከዓመት በኋላም ጓደኝነቱን በጋብቻ ደመደሙ።
የሦስት ልጆች አባት የሆኑት እንግዳችን፤ ከባለቤታቸው ጋር በትዳር ከተሳሰሩ 13 ዓመት ሞልቷቸዋል። ግን በስፋት በሥራ ላይ ጊዜያቸውን ስለሚያሳልፉ ለልጆቻቸውም ሆነ ለባለቤታቸው ጊዜ እየሰጧቸው እንዳልሆነ ያነሳሉ። ጎረቤቶቻቸውንም ቢሆን በጨለማ ወጥተው በጨለማ ስለሚገቡ ብዙም አያውቋቸውም። ስለዚህም ማህበራዊ ተሳትፏቸው የሚከናወነው በሥራ ቦታቸውና በሚሳተፉበት ማህበር ብቻ ነው። በዚህም ባለቤታቸውም ሆነች ልጆቻቸው እየተከፉባቸው በመሆኑ ለማሻሻል ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ነግረውናል።
መልዕክት
ኮሮናን በተመለከተ አገሪቱ ላይ የተዛባ አመለካከት አለ። እኛ ኢትዮጵያውያንን አይነካንም፤ ጥቁሮችን አይገድልም ወዘተ ይባላል። ነገር ግን በአሜሪካ ብቻ ከመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል። እኛም ጋር ቢሆን በፍጥነት የመያዙ መጠን ቀጥሏል። ስለዚህም እንደሚይዘን አምነን መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ሁሉም የድርሻውን መወጣት ላይ መስራትም አለበት የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
በአንድ ሰው ምክንያት ቤተሰብ ከዚያም አገር ሊጎዳ እንደሚችል የሚያነሱት ዶክተር ዳዊት፤ ወረርሽኙ እየሰፋ ከሄደ ደግሞ ለዓለምም የምንተርፍበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህ ደግሞ መልካም ስማችንን ያጎድፈዋልና ለራሳችን መሆንን ባንሻ እንኳን ለቤተሰባችንና ለአገራችን ስንል መጠንቀቅን ቅድሚያ እንስጠው ይላሉ። ዛሬ እኔ የማደርገው ጥንቃቄ ሌሎችን ይጠብቃል ብሎ መስራትም እንደሚገባ ይመክራሉ።
«ዛሬ ለሌሎች መኖር ዋጋ የምንከፍልበት ጊዜ በመሆኑ ኮሮናን ታሪክ ለማድረግ እንስራ» የሚሉት ባለታሪኩ፤ ከራሳችን ምቾት ቀንሰን ፣ ካለን አካፍለን ለሌሎች መስጠትንም ልንለምድ ይገባል። ወረርሽኝ በአገሪቱ ሲከሰት ይህ የመጀመሪያ ስላልሆነም ቀደምቶቻችን እንዴት እንዳለፉት ተረድተን ታሪክ ሰሪ መሆን አለብን። በብዙ ሺህዎች በወረርሽኝ ምክንያት ሞተውብን ያውቃል። ስለዚህም ያንን ላለመድገም መጣጣር ግዴታችን እንደሆነ ማመን ይኖርብናልም ይላሉ።
ያለፈውን ታሪክ ዛሬ ላይ ሆነን እንድናወጋው ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል። ዛሬ ደግሞ እኛ የታሪክ አሻራ አስቀማጭ አድርጎናልና የታሪክ ጠባሳውን መቀነስና ማቆም ኃላፊነት አለብን። ስለዚህም «ታሪክን የሚያኖር ብቻ ሳይሆን ታሪክን አውጊም ጭምር እንድንሆን እንስራ። መልካም ባህሎቻችንን ለመጠበቅ መልካም ተግባርን ማከናወን ግዴታ ነው። ለዚህ ደግሞ ዘመኑ የጠየቀውንም ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግን ይኖርብናል። በተለይም የለመድናቸውንና የኖርንባቸውን ባህሎች ደግመን እንድንጠቀምባቸው ከፈለግን ዘመኑን የዋጀ ሥራ መስራት አለብን። አታድርጉ የተባልነውን ባለማድረግ ችግሩን ማሳለፍ ግዴታችን ነው። በእርግጥ ይህንን ማድረግ ምቾትን ይነሳል። ሆኖም «ጊዜ እስኪያልፍ ያለፋል» ነውና ነገሩ ወደማድረጉ ቢገባ ይጠቅመናል። ኮሮና እንደ ኅዳር ወረርሽኝ ሁሉ ያልፋልና ያን ጊዜ እየተረክን ባህላችንን እንተገብረዋለን፤ የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው። እኛም ከኮሮና ወረርሽኝ ለመዳን ምክራቸውን እንቀበል። ተቀብለን እንተግብር በማለት በዚሁ ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው