ዓለማችን በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል። በእነዚህ ፈተናዎች ወቅት አገራት የሚኖራቸው ትብብር ፈተናውን ለማለፍ የሚኖረው ድርሻ ቀላል አይሆንም። ዛሬም ዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ በአዲስ ፈተና ተወጥራለች፤ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ። ይህ ወረርሽኝ አህጉርም አገርም ሳይመርጥ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የዓለማችንን ህዝብ አልጋ ላይ አውሏል፤ ከ154 ሺህ በላይ ህይወት ነጥቋል፤ ቢሊዮኖችን ስራ ፈት አድርጎ በቤት ውስጥ አውሏል።
ወረርሽኙ ልዩ የሚያደርገው የቱንም ያህል በተናጠል የሚደረግ ጥንቃቄና ጥረት የተዋጣለት ቢሆንም፤ ሌላው ወገን ተመሳሳይ ጥረትና ጥንቃቄ ካላደረገ ውጤቱ አልቦ መሆኑ ነው። ከዚህ አንጻር ተጠቃሿ አገር ቻይና ነች። ቻይና በግዛቷ ቫይረሱን ተቆጣጥራ ለዓለም አብስራ ዓለምን ባስደመመች በሳምንታት እድሜ ውስጥ ኬሎች አገራት የሚመጡ ዜጎቿ ቫይረሱን ይዘው እየገቡባት መሆኑ ለተነሳው ነጥብ ጥሩ አስረጅ ይሆናል።
እውነታው ይሄ ቢሆንም በአንድ አንድ አገራት በተለይም በአሜሪካን የሚታየው የራስን ጥቅም ብቻ የማስቀደም አካሄድ በዚህ ፈታኝ ወቅት ትዝብት ውስጥ የሚጥል ተግባር ሆኗል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ በአገር ውስጥ የተነሳባቸውን የቫይረሱን መቆጣጠር አልቻሉም ወቀሳና ትችት ወደ ዓለም ጤና ድርጅት ወርውረውታል። ወትሮም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ ችግሮቻቸውን ሁሉ በማስፈንጠር የሚታወቁ ቢሆንም፤ በዚህ ደረጃ አይናቸውን በጨው ያጥባሉ ብሎ የገመተ አልነበረም።
ፕሬዚዳንቱ ወደ መንበር ስልጣን ከመጡ ወዲህ አገራቸውን ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ስምምነቶች እያስወጡና እያገለሉ ዓላማቸው ምን እንደሆነ ዓለምን ግራ ማጋባት ቀጥለዋል። በዚህ የፕሬዚዳንቱ ግራ አጋቢ አካሄድና ውሳኔ ዙሪያ ቢቢሲ ዘርዘር ያሉ መረጃዎችን አስነብቧል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባም ለአሜሪካ የማያወላዳ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቁት የአውሮፓ አገራት የትራምፕ አካሄድ እያስኮረፋቸው በመምጣቱ ከእርሳቸው ጋር መስማማት ከባድ ነው እስከማለት ደርሰዋል። ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የአውሮፓ አገራት በበቂ ገንዘብ አያዋጡም በሚል ሲተቹ ነበር። ጥምረቱ ትራምፕ ከመጡ በኋላ የድሮ የትብብር ጥንካሬው እርቆታል ይላሉ ታዛቢዎች።
ዶናልድ ትራምፕ ከዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት ጋር በይፋ መኳረፋቸውንና አገራቸወን ለድርጅቱ ያደርግ የነበረውን የገንዘብ መዋጮ እንቢ አላዋጣም ብለው በአደባባይ አውጀዋል። የአሜሪካን ውሳኔ የዓለም የጤና ድርጅትን በእጅጉ እንደሚጎዳው ሳይታለም የተፈታ ነው። ምክንያቱ ደግሞ አገሪቷ በድርጅቱ ውስጥ ያላት የገንዘብ መዋጫ ድርሻ ላቅ ያለ ነውና።
ኢንዲያ ቱዴይ ባስነበበው ትንታኔው፤ አሜሪካ ከድርጅቱ ጠቅላላ ገቢ ውስጥ 14.67 በመቶ ያህሉን ትሸፍናለች። ይህ በገንዘብ ሲሰላ ስድስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሏል። ፕሬዚዳንቱ ታዲያ የገንዘብ መዋጮዬን አቋርጫለሁ ሲሉ ይሄንን ያህል ገንዘብ መስጠት አቁሜያለሁ፤ ድርጅቱ የራሱ ጉዳይ ዓለምም እንዳሻት ማለታቸው መሆኑ እርሳቸውና መንግስታቸውን ትዝብት ውስጥ ጥሏል።
ፕሬዚዳንቱ ግን በዓለም ዙሪያ ካሉ የአገራት የትብብር መድረክ አገራቸውን ሲያርቁ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ይለናል፤ ቢቢሲ በዘገባው። ለምሳሌ ያህልም በማለት ቢቢሲ ፕሬዚዳንቱ በስልጣን ዘመናቸው ያቋረጧቸውን ትብብሮችና የቀደዷቸውን ስምምነቶች ዘርዝሮ አቅርቧል።
የመጀመሪያው “P5+1” በሚል የሚታወቀውና ብዙ የተደከመበትን ዓለምንም ብዙ ዋጋ ያስከፈለውን፣ የ2015 የኢራን የኒውክሌየር ስምምነት ትራምፕ አሽቀንጥረው ጥለውታል። ይህ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በሩሲያ እና በቻይና የተፈረመው ስምምነት በዶናልድ ትራምፕ የተናጠል እርምጃ አሜሪካ ከስምምነቱ ወጥታለች። የተቀሩት አገራት አንዳቸውም ድጋፍ አልሰጧቸውም።
ከዚያ ይልቅ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ማክሮንና የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትራምፕን ለማሳመንና ወደ ስምምነቱ እንዲመለሱ ለማድረግ ደፋ ቀና ብለው ነበር። ዶናልድ ትራምፕ ግን በእንቢታቸው ገፍተውበታል። እንዲያውም ስምምነቱን “የኦባማ ኮተት” ሲሉ አጣጥለውታል።
ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው በትንሹ ከአምስት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወይም ስምምነቶች ወይም ማዕቀፎች አገራቸውን እንዳራቁ ቢቢሲ ዘርዝሮ ገልጿል። ለመሆኑ እነዚህ ስምምነቶችና ተቋማት እነማን ናቸው?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስልን እአአ በሰኔ 2018 ጥላ ወጥታለች። ምክንያቷ ደግሞ ካውንስሉ የምንጊዜም አጋሬን እስራኤልን አስቀይሞብኛል በሚል ነው። ካውንስሉ እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የምታደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲተች ቆይቷል።
በዚያን ጊዜ በተባባሩት መንግሥታት የአሜሪካ ቋሚ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ካውንስሉ ለእስራኤል ጥላቻ አለው፤ በዚያ ላይ ግብዝ ነው ስለዚህ አባል መሆን አንሻም ብለው ነበር። እስራኤልም ይህንን የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ በደስታ ነበር የተቀበለችው። አሜሪካ የዚህ ካውንስል አባል የሆነችው በፕሬዚዳንት ኦባማ ጊዜ ነበር።
የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት
አሜሪካ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት የወጣቸው ባለፈው ዓመት ቢሆንም ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ነው። የፓሪሱ ስምምነት አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የፈረሙት እጅግ ወሳኝ የሚባል ስምምነት ነው። ስምምነቱ ላይ 195 አገራት ፊርማቸውን አኑረዋል። ስምምነቱ አሜሪካ በ2025 የበካይ ጋዝ ልቀቷን በ28 በመቶ እንድትቀንስ የሚያግባባ ነበር።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት
አሜሪካ የዚህ ፍርድ ቤት አባል ሆና አታውቅም። ነገር ግን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለፍርድ ቤቱ ትብብር አትነፍግም ነበር። በ2018 የዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተን እንዲያው ምንም አይነት ትብብር አናደርግም ብለው ያልገቡበትን ማኅበር ተችተው ከትብብሩ ወጥተዋል።
ትራንስ ፓስፊክ የትብብር ማዕቀፍ
ገና ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው ትራምፕ ፍጹማዊ ፊርማቸውን ተጠቅመው ከዚህ ማዕቀፍ ወዲያውኑ ነው አገራቸውን ያስወጡት። ይህ ከ12 አገራት ጋር የተደረገው የንግድ ስምምነት በባራክ ኦባማ ዘመን ነበረ የተፈረመው።
የንግድ ማዕቀፉ 40 ከመቶ የሚሆነውን ዓለም አቀፍ ንግድ የሚሸፍን የነበረ ሲሆን ጃፓን፣ ማሌዢያ፣ አውስትራሊያ፣ ኒው ዚላንድ ካናዳና ሜክሲኮን ያካተተ ነበር። በዚህም በአገራቱ መካከል ታሪፍ በመቀነስ ንግድን ለማጧጧፍ ያለመ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)
አሜሪካ ወደ ዩኔስኮ ቢያንስ ሦስት ጊዜ ገብታ ወጥታለች። መጀመሪያ በፈረንጆች 1984 ድርጅቱ ነጻ ድርጅቶችን ይጨፈልቃል በሚል ለቀቀች።
ከዚህ በኋላ በጆርጅ ቡሽ ዘመን ወደ ድርጅቱ ተመለሰች። በ2011 የአባልነት መዋጮ አቆመች፤ ምክንያቱ ደግሞ ፍልስጤም አባል ሆናለች በሚል ነበር።
በ2013 አሜሪካ በዩኒስኮ ድምጽ የመስጠት ስልጣኗን ተነፍጋ ቆየች። በመጨረሻም በ2017 አሜሪካ ዩኒስኮን ጸረ እስራኤል ድርጅት ነው በሚል እስካሁን እንደወጣች ቀርታለች።
አሁን ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ከኮሮናቫይረስ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከአገራቸው ሕዝብ እየቀረበባቸው ባለው ጠንካራ ትችትና ተቃውሞ ምክንያት በተራቸው የዓለም ጤና ድርጅትና ዋና ዳይሬክተሩን ሲወቅሱ ቆይተው ለድርጅቱ የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ ገልጸዋል።
ይህ ውሳኔያቸው በዚህ ወሳኝ ወቅት ድርጅቱ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ላይ ከባድ ጫናን የሚፈጥር ሲሆን፤ አሜሪካ በተቋሙ ውስጥ በሚኖራት ሚና ላይ የእራሱ የሆነ ተጽእኖ አለው። ይህም ምናልባት በሌሎች ተቋማት ላይ እንዳደረገችው ድርጅቱን ለቃ ለመውጣት የሚያበቃት ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2012
በጋዜጣው ሪፖርተር