ወይዘሮ ሰናይት እሸቴ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በሰሜን ሸዋ አሌልቱ በምትባል ከተማ አካባቢ ሲሆን እንደ ልጅ ከብት አግደው ተጫውተው ባሳለፏት አጭር ጊዜም እስከ ሰባተኛ ክፍል እዛው በተወለዱበት አካባቢ ተምረዋል። ገና በልጅነታቸው ነበር የአስራ አንድ ዓመት ልጅ እያሉ በቤተሰብ ግፊት ትዳር ለመመስረት የበቁት። እሳቸው የትዳርንም ሆነ የህይወትን ሚስጥር ባይረዱትም ከጥቂት ዓመታት በኋላ አከታትለው ወልደው የአምስት ልጆች እናት በመሆን የቤተሰብ ሀላፊነትን ለመሸከም ይበቃሉ።
ነገር ግን ህይወት ባሰቧት መንገድ አትሄድም። ወይዘሮ ሰናይትም ከባላቸው ጋር አብሮ ለመቆየት የማያስችላቸው ነገር በመካከላቸው ይፈጠራል። ምክንያቱ ደግሞ የልጅነት ባላቸው መጠጥ አዘውትረው መጠቀማቸው ነበር። የመጠጡ መዘዝ እቤት ከሚፈጥረው ሰላም ማሳጣት ባለፈም ለቤተሰቡ ሀብት ብክነት ዋና ምክንያት እየሆነ ይመጣል። እናም ወይዘሮ ሰናይት ነገሩ ከመሻሻል ይልቅ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ሲመጣ መክረው አስመክረው አልሆን ሲላቸው ከልጅነት ባላቸው ጋር ፍቺ ይፈጽሙና ንብረት ተካፍለው ወደቤተሰባቸው ይመለሳሉ። እዛም የተወሰኑ ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ የገጠር ኑሮ የማይሆን ሲሆንባቸው በ1983 ዓ.ም ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ ያደርጋሉ። በአዲስ አበባም ያገኙትን የጉልበት ስራ በየሰው ቤት እየሄዱ በመስራት ልጆቻቸውን ይዘው አንዲት ቤት ተከራይተው መኖር ይጀምራሉ።
አዲስ አበባ ከመጡ ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ ዘመድ «ጥሩ ሰው ነው አንቺም ብቻሽን ከምትሆኚ ለክፉም ለደጉም ሁለት መሆን ይመረጣል» ብሎ ከአንድ ፖስታ ቤት ሰራተኛ ጋር ያስተዋውቃቸውና በወግ በማእረግ በሰርግ ትዳር ለመመስረት ይበቃሉ። ነገር ግን ወይዘሮ ሰናይት በዚህኛውም ትዳር ለጥቂት ዓመታት ሰላም ሆነው ቆይተው በተከታታይ ዓመታት አራት ልጆችን ሶስት ወንድ አንድ ሴት ለመውለድ ቢበቁም ታሪክ ራሱን ደግሞ ሁለተኛ ባላቸውም እየጠጡ የመስከር አመል ስላመጡ ሌላ ችግር ይጋረጥባቸዋል። በተመሳሳይ አሁንም ሁለተኛ ባላቸውን መክረው አስመክረው አልሳካ ሲል በዚሁ ምክንያት ብቻ አራተኛ የወለዷት ልጅ ዓመት ሳይሞላት የሁለተኛውም ትዳር እህል ውሃ ያከትምና ሶስት ጉልቻቸው ለመፍረስ ይበቃል። በባለቤታቸው በፍርድ ቤት ተወስኖባቸው በወር አንድ መቶ ሃምሳ ብር እንዲቆርጡ ቢደረግም እሳቸው ግን ገንዘቡን ሳይሰጡ በዛው የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ። እናም ወይዘሮ ሰናይት ያለፈውን አስራ አምስት ዓመት ብቻቸውን ዘጠኝ ልጆቻቸውን የማሳደጉን ሃላፊነት ተሸክመው ከጎዳና ላይ የጉሊት ንግድ ጀምሮ ያገኙትን እየሰሩ ለመኖር ይገደዳሉ። በእነዚህ ዓመታት ግን ልጆቻቸውን በአግባቡ ይቆጣጠሩ ስለነበር ቤታቸው እንኳን ዘጠኝ አንድ ልጅ ያለበት አይመስልለም ነበር። በዚህ ሁኔታ እያሉ ነበር በአንድ ወቅት የህይወታቸውን አቅጣጫ የቀየረ አጋጣሚ የተፈጠረው።
ልጆቼ ሲበተኑ ቤተሰቤ ሲፈርስ ማየት አልፈልግም የሚሉት ወይዘሮ ሰናይት የልጆቻቸውን የእለት ጉርስ በመሙላት ቤተሰባቸውን ለማስተዳዳር ያገኙትን ሁሉ ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን ነገሩ ህገ ወጥና አደጋ የሚያስከትል በህግም የሚያስጠይቅ እንደሆነ ቢያውቁም የአየር በአየር ህገወጥ የስንዴ ንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ነበር። በወቅቱ ይህንን ስራ የሚሰሩት ሙሉ ካፒታሉ የእሳቸው ሆኖ ሳይሆን ከአንድ ማዳበሪያ የምትሰጣቸውን ሀያ ብር ኮሚሽን እየተቀበሉ ቤታቸውንና ልጆቻቸውን ለመደጎም ነበር። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ወደ ወረዳው አመራሮች ጆሮ ይደርሳል። በወቅቱ የነበሩት የወረዳ ሀላፊዎችም በአንዲት አስፈሪ ነገር ግን ለእሳቸውና ለቤተሰባቸው ተስፋ በሰነቀች እለት ፖሊስ አስከትለው ወደ ተጠርጣሪዋ ቤት ሲያቀኑ ወይዘሮ ሰናይት እቤት ባይኖሩም ለነጋዴዎች ሊከፋፈል የተከመረውን ስንዴ ያገኙታል። ለቁጥጥር እቤት ውስጥ የገቡት የወረዳው ሃላፊዎችና ፖሊሶች ግን በቤት ውስጥ ያገኙት የተደረደረውን የማዳበሪያ ስንዴ ብቻ ሳይሆን ከስሩ የተኮለኮሉትን ለአቅመ ኮንትሮባንድ ያልደረሱ ህጻናት ልጆችንም ነበር። ቤቱንም በደንብ ሲመለከቱት በህገወጥ መንገድ የሚዘዋወር ስንዴ የሚከማችበት ብቻ ሳይሆን የአንዲት ጥሮ አዳሪ መኖሪያ ቤት መሆኑንም ይገነዘባሉ። እናም የመጡበት አላማ እንደተጠበቀ ሆኖ እዛው ቆመው በገጠማቸው አዲስ ነገርና በህገወጥ ስም ገናና ነጋዴ ላይ መወያያት ይጀምራሉ።
ይህን ግዜ እቤታቸው የተፈጠረውን ጉድ ያልሰሙት ወይዘሮ ሰናይትም ሌላ ዙር የሚያስረክቡትን ስንዴ አሸክመው ሀገር ሰላም ብለው እቤታቸው ሲደርሱ ያልጠበቁት ነገር ይገጥማቸዋል። ከወረዳ የመጡት ተቆጣጣሪዎች ግን እሳቸውን ይዘው ከማዋከብና ንብረቱን ከመውሰድ ይልቅ በእርጋታ እነዚህ ሁላ ልጆች የማን እንደሆኑና ለምንስ በዚህ ሁኔታ እዚህ ስራ ውስጥ እንደገቡ ይጠይቋቸዋል። እሳቸውም ልጆቻቸውን በአዲስ አበባ ኑሮ ብቻቸውን በቤት ኪራይ እያሳደጉ በመሆኑ ገንዘብ ለማግኘት የሚሰሩት ስራ መሆኑን ይገልፃሉ። ጨምረውም አሁን ያሉበትንም ሁኔታ ያስረዱና የተያዘው ስንዴ በውርስ የሚወሰድ ከሆነ የሚገጥማቸውን የከፋ ችግር ለአመራሮቹና ፖሊሶቹ በመማፀን ያስረዳሉ። ከወረዳ ከመጡት መካካል የነበረው ሃላፊም ይህንን ስራ አቁመው በወረዳው ውስጥ ስራ ቢመቻችላቸው ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ይጠይቃቸውና ሲስማሙለት በወረዳው ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ስር አንዳንድ የአቅማቸውን ስራ እንዲሰሩ ያስቀጥሯቸዋል ።
በወረዳው ተቀጥረው ስራ እንዲጀምሩ ሲደረግ ደመወዛቸው ሁለት መቶ ሀምሳ ብር ብቻ ስለነበር በወቅቱ ይህንን ምን ከምን አድርጌ ይበቃኛል የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር። ነገር ግን የሚደረግላቸው አንዳንድ የቁሳቁስ ድጋፍና የአበል ክፍያ እየደጎማቸው በትርፍ ሰዓታቸውም ያገኙትን እየሰሩ አምስት መቶ ብር የቤት ኪራይ እየከፈሉ ራሳቸውን ችለው መኖር ይቀጥላሉ። በ2002 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ህዝብን መምራት ይችላሉ ብቃት አላቸው ብሎ ስላመነባቸው አስፈላጊውን ስልጠና በመሰጠት በሴቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አድርጎ ያስቀምጣቸዋል። እናም ዛሬ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አስራ ሁለት የሴቶች ማህበር ሰብሳቢ በመሆን ከአስር ዓመት በፊት በሁለት መቶ ሀምሳ ብር ደመወዝ የጀመሩት ስራ አድጎ ዛሬ የአንድ ሺ አምስት መቶ የወር ደመወዝ ተከፋይ ለመሆን በቅተዋል። ልጆቻቸው እርስ በእርስ ስለሚዋደዱና ስለሚደጋገፉ አንድ ቀን መሽቶ ባደረ የእሳቸውን ሸክም ያቀሉላቸው ነበር።
በሴቶች ጉዳይ በሰሩባቸው ጊዜያት ችግር የገጠማቸውን ባለትዳሮች በመማከር ረገድ የተዋጣላቸው እንደነበሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ሰናይት በአንድ ወቅት የገጠማቸውን ነገር እንዲህ ያስታውሱታል። በ2007 ዓ.ም ነበር ያለመውለድ ችግር የገጠማቸው ጥንዶች መለያየታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ወደሳቸው ይላካል። ወይዘሮ ሰናይትም ሴትዮዋን ያስጠሩና የተፈጠረውን ነገር ይጠይቋታል። እሷም ተስማምተን ተፋቅረን ትዳር መስርተን መኖር ከጀመርን ዓመታትን አስቆጥረናል፤ ነገር ግን መውለድ ባለመቻላችን ችግሩ ያንቺ ነው ብሎ ከቤት ትቶኝ ወጥቷል ትላለች። ወይዘሮ ሰናይትም ከሁሉም በፊት ያለሽበት ሁኔታ መታወቅ ስላለበት መመርመር አለብሽ ብለው እንድትመረመር ያደርጋሉ። በምርመራውም ውጤት ሴትዮዋ ቅሪት ሆና ትገኛለች ወይዘሮ ሰናይትም የባለቤቷን ስልክ ተቀብለው ደውለው ለማነጋገር ሞክረው ሳይሳካ ሲቀር ደብዳቤ ጽፈው እንዲገናኙ ያደርጉና ያለውን ነገር የራሳቸውን ታሪክ ምሳሌ አድርገው ይነግሩታል። ሰውየውም ያለውን ነገር በመቀበል ፈቃደኛ ሆኖ ከባለቤቱ ጋር በጋራ ምርመራ ያደርጉና የሁለት ወር ጽንስ መያዟን ሲያረጋግጥ ወደ ትዳሩ ለመመለስ ይወስናል። ከዓመት በኋላም ጥንዶቹ ልጃቸውን ክርስትና ሲያስነሱ ወይዘሮ ሰናይትን የክርስትና እናት ያደረጓቸው ሲሆን አሁንም ድረስ ከወይዘሮ ሰናይት ጋር እንደ ቤተሰብ ተቀራርበው እየተጠያየቁ ይገኛሉ።
ወይዘሮ ሰናይት ለልጆች ካላቸው ጥልቅ ፍቅርም የተነሳ ከጉልበት ብዝበዛና የህጻናት ዝወውር ጋር በተያያዘም በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ያከናወኑ ሲሆን በአንድ ወቅት ዋንጫ ለመሸለም ያበቃቸውንም ተግባር እንዲህ ይገልጹታል። ነገሩ የተፈጸመው እሳቸው በሚሰሩበት ሳይሆን በሌላ ወረዳ ነው። አዲስ አበባም ላሉትም ሆነ ገጠር ለሚኖሩት የእሳቸው ቤተሰቦች ለችግሩም ለደስታውም ቀዳሚ ተጠሪ በመሆናቸው የወንድማቸው ልጅ ከገጠር ጠፍቶ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ ይነገራቸውና ፍለጋ ይጀምራሉ። ባየ በሰማ ሲያጠያይቁ ይሰነብቱና አንድ ቀን ሰዎች «አንድ ሰው እዚሁ ክፍለ ከተማችን ውስጥ ህጻናትን ከየሀገሩ እያስመጣ የጉልበት ስራ ሲያሰራቸው ይውላል፤ ምን አልባት እዛ ከሄደ ብለው እንዲያጣሩ ይጠቁሟቸዋል።» ወይዘሮ ሰናይትም ወደተጠቆሙት ቦታ ሲሄዱ እውነትም የወንድማቸውን ልጅ ካለበት ገጠር በደላላ ተሰርቆ እዛው ቤት ገብቶ የጉልበት ብዝበዛ እየተፈጸመበት ያገኙታል። ነገሩ ግን ለእሳቸው ከወንድማቸውም ልጅ የዘለለ ሌላ አሳዛኝ ነገርን እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል። ሰውየው ከስምንት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሆናቸውን ሀያ ስምንት ልጆች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቤተሰብ አሰርቆና አታሎ በማስመጣት እቤቱ አስቀምጦ ለምግብነት የሚውል ሳንቡሳ ለማዘጋጀት በእግራቸው ሊጥ ከማስቦካት ጀምሮ የተለያዩ የጉልበት ስራዎቸን ያላቅማቸው እያሰራቸው መሆኑን ይመለከታሉ። ሰውየው ለልጆቹ ምንም ጥንቃቄ የማያደርግላቸው በመሆኑም ከመካከላቸው በፈላ ዘይት ተጠብሶ ጉዳት የደረሰበትም እንዳለ ይገነዘባሉ። እናም ይህንን ጉዳይ እንደ ሰላይ ተከታትለው ለሚመለከተው የህግ አካል በማሳወቅ ልጆቹ ወደቤተሰብ እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን እሳቸውም የዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን ይበቃሉ።
ወይዘሮ ሰናይት የአደራ ቤተሰብ በመረከብና ጠብቆ በማስተላለፍም ውጤታማ እናት ነበሩ። በወረዳው ተቀጥረው መስራት ከጀመሩ አንስቶ በርካታ ልጆችን ከቤተሰብና ከአሳዳጊ ጋር ለማገናኘትም በቅተዋል። ልጆች ጠፍተው ሲመጡ አልያም ተጥለው ሲገኙ ከፖሊስና ከሴቶችና ህጻናት ጋር በመሆን ኦፒድ የሚባል ድርጅት ፍራሽና አንሶላ ስለሚሰጣቸው ከልጆቻቸው ጋር በመሆን ይዘው እስከ ሁለትና ሶስት ወር እቤታቸው ያቆዩዋቸዋል። ህጻናቶቹን ራሳቸው ይዘው የሚቀመጡ ሲሆን ከፍ ከፍ ላሉት ግን ለዚሁ ብለው የቆርቆሮ ቤት ቀልሰዋል። በዚህ በኩልም ሁሌ የሚያስደስተኝ ስራ በማለት አንድ ገጠመኛቸውን ያስታውሳሉ። አንዲት እናት ሰው ቤት ተቀጥራ ስትሰራ ታረግዝና ልጅ ትወልዳለች ነገር ግን እርግዝናው ያልታሰበ ስለነበር ጓደኛዋ ባይከዳትም ኑሮን ለማሸነፍ ትቷት ወደ ካናዳ ይሄዳል። እናትም ህጻኗ ሶሰት ዓመት እስኪሆናት ተቸግራ ካሳደገች በኋላ መቀጠል አልችል በማለቷ ለድርጅት እንድትሰጥ ወደ ወረዳው ሴቶች ቢሮ ይዛት ስትመጣ ወይዘሮ ሰናይት ይቀበሏትና ተቸግራ ቢሆንም ውሳኔዋ ከባድ መሆኑን በመግለጽ ልጅቷ እሳቸው ዘንድ እንድትቀመጥ ያደርጋሉ። ልጅቷ ትምህርቷን እየተማረች ሶስት ዓመት ከቆየች በኋላ ግን የልጅቱ እናት የጓደኛዋን ስልክ ቁጥሩ ይዛ ስለነበር ቀጥራ ታሳራት በነበረች አንዲት ሴት አማካይነት በፌስ ቡክ ከአባቷ ጋር እንድትገኛኝ ያደርጓታል። እናትም ልጅቷ ያለችበትን ሁኔታ በመግለጽ አባትን ከወይዘሮ ሰናይት ጋር አገናኝታ ሲያነጓግሯቸው ሰውየው ልጁንም እናቱንም ለመያዝ ይስማማና በወረዳው ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ በኩል ልጁን ለመረከብ ይበቃል ። በአሁኑ ወቅትም አባት በየወሩ አምስት ሺ ብር እየቆረጠና ሌሎችም ድጋፎችን እያደረገ ሲሆን እናትም ከሰው ቤት ስራ ወጥታ ቤት ተከራይታ ከልጇ ጋር በድጋሚ አብራ ለመኖር በቅታለች። በዚህም የተነሳ ሁለቱም ጥንዶች ወይዘሮ ሰናይትን እንደ እናት እየመጡ እንደሚጠይቋቸውም ይናገራሉ።።
ወይዘሮ ሰናይት ከስኬታማ ጉዟቸው በተለየም በአስራ አምስት ዓመት ለብቻ ቤተሰብ የመምራት ግዜያቸውም የሚያስታውሷቸው አሳዛኝ ገጠመኞች አሏቸው። በአንድ ወቅት አንድ ሰው ጥሩ ክፍያ እንደሚከፈላቸው ይነገራቸውና ልብስ ለማጠብ ይስማማሉ። እናም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምረው እስከ ምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት ልብስ ያጥባሉ።። አመሻሽ ላይ ግን ባዶ ሆዳቸውንም ስለነበሩ ክፉኛ ያማቸውና ራሳቸውን ማንቀሳቀስ ተስኗቸው ልጆቻቸውን አስጠርተው ወደቤት በመሄድና ህክምና በመከታተል ወደቀድሞ ጤናቸው ይመለሳሉ። ልብሱን ያሳጠበቻቸው ሴትዮ ግን የቤተሰብ ሃላፊ መሆናቸውን ስታውቅ አዝና አስራ ስድስት ዶላርና ሌላም ነገር ሰጥታቸው ብትሄድም እሳቸው ግን ከልጆቼ ሊለየኝ የመጣ ክፉ ቀን ብለው ስለያዙት ከዛች ቀን ጀምሮ ልብስ የማጠብ ስራ ላለመስራት ይወስናሉ።
ወይዘሮ ሰናይት በአሁኑ ወቅት አንድ የልጅ ልጃቸውን ጨምረው ስድስት ልጆቻቸውን ይዘው እየኖሩ ሲሆን ሌሎቹ ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ትዳር መስርተው ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ