መነሻውን በሀገረ ቻይና ዉሃን ግዛት አድርጎ ሁሉንም የዓለም ከፍል እያዳረሰ ያለው የኮሮና ቫይረስ እስካሁን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት በመዳረግ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ያልጋ ቁራኛ ያደረገ ሲሆን በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ስጋት ሆኖ በመስፋፋት ላይ ይገኛል።
ቫይረሱ ባለፉት ጥቂት ወራትም ከጤና ስጋትነትና ከአንድ አገር ችግርነት ተሻግሮ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎችን በመላው ዓለም መፍጠሩን ቀጥሏል። በኢትዮጵያም የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (Covid-19) መከሰቱ በይፋ ከተነገረበት መጋቢት ሶሰት ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ከነዚህም መካከል ህብረተሰቡ ራሱን ከቫይረሱ እንዲጠብቅ ግንዛቤ መፍጠር፤ የትምህርት ተቋማትን መዝጋት፤ የሰዎችን እንቅስቃሴ መገደብ፤ የሀገሪቱ ድንበሮች ከሎጀስቲክ አቅርቦት ውጪ ላልተወሰነ ጊዜ ለሰዎች ዝውውር ዝግ እንዲሆኑ ማድረግ፤ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሰዎችን ንክኪ ለመቀነስ እንደየመስሪያ ቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ እየታየ ከፊል ሰራተኞች ከቤታቸው ሆነው ስራቸውን የሚሰሩበት መንገድ እንዲመቻች ማድረግ እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት የሚከናወኑ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎችም ምእመናኑን ለቫይረሱ ተጋላጭ በማያደርግ መልኩ እንዲፈጸሙ ሲያሳስብ ቆይቷል።
ይህም ሆኖ የቫይረሱ ስርጭት በአስጊ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኝ በመሆኑ ከቀናት በፊትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅም ደርሷል። ከመንግስት በተጨማሪም ዜጎች በቤት ውስጥ እንዲቀመጡና በህክምና ባለሙያዎች የሚነገሩና መውሰድ ያለባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲተገብሩ በህክምና ባለሙያዎችና በሃይማኖት አባቶች ምክር እየተለገሰም ይገኛል። ቫይረሱን ለመከላከል ከሚወሰዱት የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል ቀዳሚውና አዋጩ በቤት ውስጥ መቆየት መሆኑ በተደጋገሚ ይነገራል።
በዚህ ረገድ በቤት ውስጥ የምናሳልፈው ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከመከላከልም ባለፈ የቤተሰባችንን ግንኙነት ለማጠናከር ልንጠቀምበት እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዎሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ክቡር እንግዳወርቅ ያስገነዝባሉ። ዶክተር ክቡር እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት የመንግስት ሰራተኞችና በግል ስራ ላይ ያሉ አንዳንዶችም የኮረና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ለመቀነስ ከሚደረገው ትግል ጋር በተያያዘ እቤት የሚውሉበት ሰአት እየበዛ መጥቷል። ይህም በሚስትና በባል፤ በወላጆችና በልጆች መካከል ለሚኖረው ግንኙነት የራሱ አንድምታ ያለው ነው።
ሰዎች ይህ ችግር ከመከሰቱ በፊት በነበራቸው ህይወት ቀን የተለያዩ ስራዎችን ሲሰሩ ውለው ወደ ቤታቸው የሚመለሱት አምሽተው ስለሚሆን ከትዳር አጋሮቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ያሳልፉት የነበረው ጊዜ ውሱን ነበር። አንዳንዶች ተመሳሳይ ጊዜ የዓመት ፈቃድ ወስደው እቤት ውስጥ የሚቀመጡ ቢሆንም ቀድመው የሚያውቁ በመሆኑ የሚሰሩትን ነገር የሚያዘጋጁ ሲሆን በሌላ በኩል ምንም የማይሰሩ እንኳን ቢሆን እንደልባቸው ከቤት ውጪ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ የሚፈጥረው የጎላ ተጽእኖ አልነበረም። የኮሮናን ስርጭት ለመከላከል የተጀመረው በቤት መዋል ግን የራሱ የሆኑ የተለዩ ገጽታዎች ያሉት ነው። እነዚህም ሙሉ ቤተሰቡ በአንድ ጊዜ እቤት ውስጥ የሚቀመጥ መሆኑ፤ በቤት ውስጥ ያለውም እንቅስቃሴ የራሱን ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑ፤ በጊቢ ውስጥ ካሉ ሌሎች ነዋሪዎችም ሆኑ ዘመድ አዝማድ ጋር የሚደረግ ግንኙነት ገደብ ያለው መሆኑ ናቸው። በመሆኑም ጊዜው እንደሌሎች የእረፍት ጊዜያት የሚታይ አይደለም። ይህም ሆኖ ይህንን ሰፊ ጊዜ በመልካም ግንኙነት ብቻ በበጎ መልኩ በመጠቀም ለማሳለፍ ራስን ማዘጋጀትና የባለሙያዎች ምክር እየተከታተሉ መተግበር ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ሲሆን በሶስት ጉዳዮች ላይ ግን የሁሉም ትኩረት የሚያስፈልግ ይሆናል። የመጀመሪያው የባልና ሚስት ግንኙነትን የሚመለከተው ነው። በዚህ ረገድ እቤት መዋሉ በበጎ ጎኑ ሲታይ ረጅም ጊዜ ከቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ መቻሉ ጥንዶች በአንድ በኩል እስካሁን ሊያደርጓቸው ይፈልጉ የነበሩ ነገር ግን በስራ መብዛት ምክንያት ጊዜ በማጣትሳያደርጓቸው የነበሩ መልካም ነገሮችን ለቤተሰቦቻቸው ለማድረግ ለምሳሌም ለትዳር አጋር ፍቅር ለመስጠት አብሮ ለማሳለፍ እድሉን ያገኛሉ።
የተለያየ ሙያ ያለውም በቤት ውስጥ ሊሰራ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ካለ ስራውን በመስራት ቤተሰቡን ለመደገፍ ይችላል። ይህ ማለት ግን በሁሉም ቤተሰብ ወስጥ ጊዜውና ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ማለፍ ይችላሉ ማለት ስላልሆነ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ነገሮችም ይኖራሉ። ከነዚህም መካከል በቅድሚያ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ አንድ ሰው ስራ የሚውልበትን ጊዜ የሚጠቀምበት ለገንዘብ ማግኛ ብቻ አለመሆኑ ነው። ስራ ለአንዳንድ ሰዎች ከቀኑ ረጅሙን ጊዜ በጥሩ አካባቢ የሚያሳልፉበት፤ ራሳቸውን የሚገልጹበት፤ አእምሯቸውን የሚያዳብሩበት፤ ወገናቸውን የአገል ግለውና ረድተው የሚመለሱበት ሊሆን ይችላል።
በዚህ አይነት መልኩ የቀደመ ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ለነበሩ ሰዎች እቤት መዋሉ በራሱ የሚፈጥርባቸው ተጽእኖ አለ። በተጨማሪ ልንሰራ አቅደነው የነበረ ነገር ባለማድረጋችንና አቋርጠን እቤት በመዋላችን በራሱ ሊፈጠር የሚችል ድብርትና ብሰጭት የስነ ልቦና ጫናም ይኖራል። ይህንን ስሜት አውጥተን ትዳር አጋራችን አልያም ልጆቻችን ላይ ካንጸባረቅነው እቤት ውስጥ ያለውን የሰላም ድባብ የሚረብሽ ስለሚሆኑ በጥንቃቄና በማስተዋል መጓዝ በቤተሰብ ውስጥ ካሉ ሰዎችም ጋር በተረጋጋ መንፈስ መነጋገር ይሚጠበቅ ይሆናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እቤት መዋሉ በሁለት ጥንዶች መካከል በገንዘብ አጠቃቀም ረገድም የሚኖር ክፍተቶችንም ለማየት ያስችላል። አንድ ሰው አቤት በመዋሉ በሆቴል ከፍሎ ከሚመገበው ለትራንስፖርት ወይንም መኪና ከነበረው ለነዳጅ እንዲሁም ሻይ ቡና የሚልበትና ሌሎችንም ወጪዎቹን ለመቀነስ ይችላል። በተጨማሪ በጥንዶች መካከል የወጪ አወጣጥንም በቅርብ ለመገንዘብ የሚያስችል ሲሆን ጥንዶቹ ክፍተቱ ካለ የት ላይ እንዳለ በቀላሉ ለመለየት ጥሩ ጊዜ ነው። ስራ የሚውሉ እናቶችም እቤት ውስጥ በመዋላቸው ከሰራተኛ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማየት እድሉን በማግኘት የበጀት ብክነትን ለመቀነስ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
ባልም እቤት በመዋሉ የሚሸመቱ እቃዎችን ለእነዛ የሚወጡ ወጪዎችን ዋጋ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚያገለግሉ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ስለሚያስችለው ተቀራርቦ በመነጋገር መለወጥ መስተካከል ያለበትን ለማስተካከል በር ይከፍታል። እዚህ ላይ ምግብ ማብሰልን እንደ አንድ የጊዜ ማሳለፊያ መጠቀም ይቻላል፡፡ በዚህ በኩል አንዳንድ ቤተሰቦች ስራ ፈተው በመቀመጣቸው ገቢያቸው የሚቀንስም ካለ በዛ የሚከሰተውን ክፍተት ለመዝጋት ይረዳቸዋል።
ከቤተሰቡ መካከል አልኮል የሚያዘወትሩም ካሉ አጋጣሚውን በሁለት መልኩ ሊጠቀሙበት ይችላሉ የመጀመሪያው በቀጥታ የሚወስዱትን አልኮል በማቆም ወይንም በመቀነስ ከቤተሰባቸው ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍና ወጪያቸውን መቀነስ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ በዘላቂነት ከሱስ ለመላቀቅ የሚፈልጉ ከሆነ ደግሞ አጋጣሚውን መጠቀም ይረዳቸዋል። ሌላው ጉዳይ የወላጆችና የልጆችን ግንኙነት የተመለከተ ነው። በቅድሚያ ወላጆች እቤት በመዋላቸው ልጆቻቸውን ለማስጠናትና በቅርበት ለመከታተል እድሉን ያገኛሉ ። በሌላ በኩል ደግሞ በልጆችና በወላጆች መካከል የሚነሱ መነታረኮችን በተወሰነ የሚያስቀረው የልጆች ትምህርት ቤት መዋል በመሆኑ እነዚህን ጊዜ ማሳለፊያዎች በአንድ ጊዜ እርግፍ አድርጎ እቤት መዋሉ በጸባይ አለመግባባት መሰለቻቸት ሊፈጠር ይችላል። ከልጆች ጋር ረጅም ሰአት መዋሉ ወላጆች የማያውቋቸውን የልጆች ባህርያት ለመገንዘብ እድሉን እንዲያገኙ ያስችላል። በተለይም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች በትምህርት ላይ ሆነው የተለያዩ ሱሶች ውስጥ የገቡ ያሉ ሲሆን አብዛኛው ቤተሰብ ደግሞ እነዚህ ልጆች ያሉበትን ሁኔታ አያውቅም።
ልጆቹ የለመዱትን ነገር ለመተው ፈቃደኛ እንኳን ቢሆኑ አስፈላጊውን ክትትል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ አይኖርም። በመደበኛው አካሄድ እነዚህን ልጆች ካሉበት ሱስ ለማላቀቅ ረጅም ጊዜ ይፈልጋል፤ የቴራፒ የባለሙያ እርዳታ ያስፈልጋል ይህንን ሳያሟሉ በአንድ ጊዜ እቤት ዋሉ አትውጡ የትም አትሂዱ ሲባል ሱሳቸውንም ህክምናውንም ስለማያገኙ የሚፈጠርባቸው ተጽእኖ ጠንካራ ከመሆኑ ባለፈ የመነጫነጭና አላስፈላጊ ነገሮችን ለማድረግ ሊሞክሩ ይችላሉ። በዚህ አይነት በልጆቹ ላይ የሚመለከቱት ነገር በሙሉ ጥሩ ላይሆን ስለሚችል ግጭት ሳይፈጠር የልጆቹንም ችግር በመረዳትና መፍትሄ በማፈላለግ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ይጠበቃል።
ለዚህም ልጆችን በትእግስት ቀርቦ በማነጋገር እንደ ሲጋራ ጫት ያሉ ነገሮችን የሚያዘወትሩ ልጆች ሲገጥሟቸው የቀኑን ጊዜ ከቤት ሳይወጡ በእንቅልፍ እንዲያሳልፉ ፤ የአካል ብቃት እንቅስቅሴ እንዲያደርጉ፤ ሙዚቃ እንዲያዳምጡ፤ ፊልም እንዲያዩ መጽሀፍ እንዲያነቡና ሌሎች ሃሳባቸውን ለመቀየር የሚረዷቸውን የሚወዷቸውን ነገሮች እንዲከውኑ ማነሳሳት ይገባል። እንዲሁም እንደ ሻይ ቡና ያሉ በማህበረሰቡ ለድብርት ማስለቀቂያ የተለመዱ ነገሮችን በማቅረብ ቀስ በቀስ ለመላቀቅ እንዲላመዱ መሞከር ይጠበቃል።
በሶስተኛ ደረጃ በአካባቢያችን ካሉ ነዋሪዎች ከጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ጋር የሚኖረን ግንኙነት ነው። በዚህም ረገድ እያንዳንዱ ሰው እቤቱ ሲውል ከሌሎች ጋር የሚኖረውን ግንኑኙት ገድቦ መሆን አለበት። በኢትዮጵያ አኗኗር በአንድ ጊቢ አልያም በአንድ ቤት ውስጥ የተለያዩ ቤተሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። በአንድ አካባቢም ዘመድ አዝማድና በጣም የሚቀራረቡ ቤተሰቦች አብረው ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን አንድ ጎረቤት ወይም ዘመድ ወደ አንድ ወዳጁ ቤት ቢሄድ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሳይሆን በርካታ ነገሮችን ይዞ ሊሄድ ስለሚችል ከሰላምታ ጀምሮ እንደ ድሮ ተቀብሎ ማስተናገዱ የሚታሰብ አይሆንም።
በዚህ ረገድ በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ወጥቶ የሚመለስ ሰውም ካለ ተመሳሳይ ነው። አሁን ያለው ሁኔታ ህብረተሰቡ ቡና የሚጠራራበት የተለመዱና ሰብሰብ ተብለው የሚከወኑ ባህላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎችን የሚያደርግበት አይደለም። በመሆኑም በተቻለ መጠን ከሰው ርቆ ያለውን ጊዜ ማሳለፍ የግድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚመጣ የሚሄድ ሰው ካለ ደግሞ ከላይ እንደተባለው በባለሙያዎች የተነገሩትን ነገሮች ሙሉ ለሙሉ ያለምንም ማመንታትና ይሉኝታ መተግበር ይገባል።
እነዚህን እንቅስቃሴዎች ማድረግ በአንዳንድ ሰዎች አስተሳሰብ የማህበረሰብን የኖረ እሴት እንደማፍረስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ምን አልባትም አንዳንዶቹ እንቅስቃሴዎች አውሬ ሆንሽ አውሬ ሆንክ የሚያስብሉም ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በቀዳሚነት መታሰብና መታወቅ ያለበት ዛሬ ይሄንን ጥንቃቄ በማድረግ ነገ እኛንም ሆነ የምንወዳቸውን በህይወት ለማየት የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል መሆኑን ነው። ይሄ ነገር እስከ ዘላለም የሚቆይ አይደለም።በሰው ልጆች ምርምርና ጥረት በፈጣሪ ፈቃድ ማለፉ አይቀርም ስለዚህ አሁን ላይ ሰው ምንም ቢለን ሳንሸበር ነገን በማሰብ የሚበልጠው የሰው ልጅ በህይወት መኖሩ በመሆኑ በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ባይቀበሉንም ጨክነን በባለሙያ የተነገረንን መከወን አለብን። ከዚህ ውጪ ፍቅርን ለመግለጽ የግድ አካላዊ ግንኙነት መኖር የለበትም፡፡ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በስልክና ማህበራዊ ሚድያ መገናኘት እንችላለን ። እነዚህ ነገሮች ግን የኖረ የመረዳዳት ባህላችንንም ሆነ ሰብአዊነታችንን የሚነኩ መሆን የለባቸውም። ችግሩ ሰፊና ከባድ እንደመሆኑ በአካባቢያችን ያሉ የእለት ጉርስ የማይኖራቸውንም ማሰብ የሚጠበቅብን ሲሆን ይሄን የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህላችንን የሚገድቡ ነገሮችን ማድረግ የለብንም። በዚህ ወቅት በማንኛውም ሁኔታ ተቸግረው እርዳታችንን የሚፈልጉትን እጃችንን ልናጠፍባቸው አይገባም።
ማድረግ የፈለግነውና የምንችለው ነገር ካለ በጥንቃቄ እቃም፣ ብርም መቀባበል የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን ። በቫይረሱ የተያዘ ሰው አልያም ቤተሰብ በአካባቢያችን ካለም ማግለል የእንድ በሽታ ሌላው አስከፊ ገጽታ በመሆኑና መልሶ በሽታን ማስፋፋት ስለሚሆን ከማግለል መቆጠብ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም በኤች አይቪ ኤድስና ሌሎች በሽታዎች እንደታየው ህመሙ በራሱ ሳይሆን ሰዎች ስለ ህመሙ ላይ ባላቸው ግንዛቤ ተመርኩዘው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሌላ ጦስ ይዞ ሊመጣ ይችላል።
አንድ በህመሙ የተጠቃ ሰው ሲገለል ያዩ ሌሎች ሰዎች በአጋጣሚ ተጠቂ ቢሆኑ ህመሙ እኔ ላይ መከሰቱን ባሳውቅ ተመሳሳይ መገለል ይደርስብኛል ብለው በማሰብ ህመማቸውን ይደብቃሉ። ይሄ ደግሞ ወደ ሌሎች እንዲተላለፍ ለቫይረሱ በር የሚከፍት ሲሆን እነሱም ህክምና እንዳያገኙ ያደርጋል። ስለዚህ መደረግ ያለበት ባለሙያዎች የሚነግሩንን ጥንቃቄ እየወሰድን በሰብአዊነት ህመምተኞች ህክምና የሚያገኙበትን፤ ፍቅር የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ነው።
ባጠቃላይም ከተፈጠረው ዓለም አቀፍ ችግር ራስን ተከላክሎ ሌሎችንም ለማዳን ከምንም በፊት በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን እየተከታተሉ በአግባቡ መተግበር ይጠበቃል። ባለሙያዎቹ እንደሚናገሩት በሽታው ከባድ ከመሆኑ ባሻገር በቀላሉ ከአንድ ሰው ወደሌላው ሊተላለፍ የሚችል ነው። እቤት ዋሉ ሲባልም ሰብሰብ ብሎ ከጓደኛ ከሰፈር ሰውና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ሲጫወቱ መዋል ማለት አለመሆኑን በመገንዘብና እቤት የመዋልን ዋና ዓላማ ከግንዛቤ በማስገባት ራስንም ቤተሰብንም ብሎም አካባቢንና ሀገርን ከጥፋት መታደግ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ
የቤት ውስጥ ውሏችን ምን ይመስላል?