ቤተልሄም ትባላለች። እድሜዋ አስራ ሶስት ዓመት ነው። በአንዲት ሁለት ሜትር በሶስት ሜትር በማትሞላ የአፈር ቤት ውስጥ ከእናቷ ጋር ነው የምትኖረው። ቤቷ ለእሷና ለእናቷ ሳሎን መኝታ ቤት፣ ምግብ ማብሰያ፣ እንዲሁም ሁሉም ነገር ነች። ቤተልሄም ለመጣው ለሄደው ሁሉ ፍጹም ፈገግታ ታሳያለች። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እናቷን በአትኩሮት ስትመለከት ትቆይና ደግማ ደጋግማ እንደመሳቅ ትላለች። ግን አትናገርም፤ አትንቀሳቀሰም፤ ራሷን ችላ የምታደርገው አንዳች ነገር የለም። እጇንም፣ እግሯንም ማንቀሳቀስ አትችልም። ዘወትር ፊት ለፊቷ የተቀመጠችውን አነስተኛ ቴሌቪዥን ብቻ አይኖቿን እያንከራተተች በአትኩሮት ትከታተላለች። ከዛች ጠባብ ቤት ውስጥም ይሁን ከውጭ ድምጽ ከሰማች በፍጥነት ድምጹን ወደሰማችበት አቅጣጫ ፊቷን ታዞራለች። የሷ ትልቁ አካላዊ እንቅስቃሴ ይሄ ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ረዘም ላለ ጊዜ ብቻዋን እቤት ውስጥ ከቆየች ብቻ የምታለቅስ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ያለፉትን ስምንት ዓመታት አሳልፋለች። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ እናትም አባትም እህትም ሆና ከአጠገቧ ሳትለይ የምትንከባከባት ደግሞ እናቷ እታፈራሁ አለሙ ናት።
ወጣት እታፈራሁ አለሙ ተወልዳ ያደገችው በአንኮበር ወረዳ ካራ መገን በምትባል አንዲት አነስተኛ መንደር ነው። አፈር ፈጭታ ውሃ ተራጭታ ባደገችበት መንደርም እስከ ስድስተኛ ክፍል ስትማር ቆይታለች። ግና በአንዲት ያልተባረከች ቀን የህይወቷን አቅጣጫ የሚቀይር አጋጣሚ ተፈጠረ። ነገሩ የተከሰተው እንዲህ ነበር። አንድ ቀን አገር ሰላም ብላ ትምህርት ቤት ውላ ስትመለስ አንድ የአካባቢዋ ነዋሪ ወጣት ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ጠልፎ እየደበደበ ይወስዳታል። በአካባቢው ነገሩን ያዩ ሰዎች ስለነበሩና ለቤተሰብ ስለተናገሩ ጉዳዩ ወደ ህግ ያመራል። እናም ወደ ቤተሰቧ እንድትመለስ የተደረገ ሲሆን እሱ ክስ ተመስርቶበት ወደ ማረሚያ ቤት ይገባል። ወጣቱ እስር ቤት ቢገባም ያፈቅራት ስለነበር የማታገባኝ ከሆነ ስወጣ አንዳች ነገር አደርጋለሁ እያለ እንደሚዝት እታፈራሁ ትሰማለች ። በአንድ ወገን ከሱ ጋር መሆን ስለማትፈልግ፤ በሌላ በኩል በእሷ የተነሳ ችግር ሲፈጠር ማየት ስላልፈለገች ለነፍሷም ለስጋዋም በመፍራት ነገሮች እስኪረጋጉ በማለት በ1995 ዓ.ም አንድ ጠዋት ተነስታ ወደ አዲስ አበባ ታቀናለች።
አዲስ አበባ ስትደርስም ከሷ ቀድማ መጥታ የነበረች አንዲት አብሮ አደግ ጓደኛዋን አፈላልጋ ታገኝና እሷ ጋር ውላ አድራ የሰው ቤት ሰራተኝነት ትቀጠራለች። የሚያሰሯት ሰዎች ጥሩዎች ናቸው። እንደ ልጅም ተንከባክበው ያሰሯት የነበር ቢሆንም ለዓመታት የሚከፈላት ገንዘብ ዝቅተኛ ስለሆነባት ያንን ቤት ትለቅና አማራጭ ፍለጋ ወደ ሌላ ማማተር ትጀምራለች። እናም በአንድ ደላላ አማካይነት ሌላ ቤት በተሻለ ክፍያ ተነጋግራ ትጀምራለች። አዲስ የገባችበት ቤት ግን ለእታፈራሁ መልካም ገድ ያለው አልነበረም። የቤቱ አስተዳዳሪዎች እናትና አባት የሚውሉት ስራ ነው። አንዲት ልጃቸውም ጠዋት ወጥታ ማታ ነበር የምትመለሰው። በዚህ መሀል እቤት ውስጥ የሚውሉት እሷና አንደኛው የቤቱ ልጅ ብቻ ነበሩ። ልጁ ደግሞ የተለያዩ ደባል ሱሶች ተጠቃሚ ነው፤ ያጨሳል፣ ይቅማል፣ ይጠጣል። አንዳንዶቹን ነገሮችም እቤት ውስጥ ተደብቆ ያደርግ ነበር። እናም እታፈራው ስራ ከጀመረች ሳምንት እንኳን ሳይሞላት በአንዲት እድለቢስ ቀን ልጁ ስራ ስራዋን እያለች ባለበት ወቅት ሳታስበው አስገድዶ ይደፍራታል። እሷ ለቤተሰቡም አዲስ ስለነበረች በጣም ተደናግጣ ጥቂት ቀናቶችን ካሳለፈች በኋላ ልጁ እንዳትናገር ያስፈራራት ስለነበርና እነዚህን አይነት እኩይ ተግባሩን እንደማያቆም ስትገነዘብ ቤቱን ለቃ ትወጣለች።
ከዚህ በኋላ ጥቂት ቀናት ቆይታ አዲስ ቤት ፈልጋ ስራዋን ትጀምራለች። አዲስ የገባችበት ቤት ለእሷ ጥሩ ነበር። ክፍያቸውም አይጎዳም፣ የሚያስቸግራትም የለም። በዚህ ሁኔታ ለአራት ወራት ከቆየች በኋላ ግን ያላሰበችው እዳ አብሯት አንዳለ ትገነዘባለች። ትኩረት ያልሰጠችው የወር አበባዋ መቅረት። ለካስ ፀንሳ ነበር። ነገሩ ስላስደነገጣትም፣ ስላስፈራትም ለሚያሰሯት ቤት እናት ደብቃ ትናገራቸዋለች። እሳቸውም የተፈጠረውን ነገር በሙሉ እንዲነግሯት ያደርጉና ልጁ በሽማግሌም ይሁን ክስ ተመስርቶም ቢሆን መጠየቅ እንዳለበት፣ እሷ ግን ማስወረድ ምናምን የሚል ሃሳብ ሳታስብ ልጁን መውለድ እንዳለባት ይነግሯታል። የማስወረዱን ጉዳይ ብትስማማበትም እስከዛሬም ለእሷ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት አስገድዶ ከደፈራት ልጅ ጋር ያለውን ነገር ግን በዝምታ እንዲቆይ ትወስናለች። በዚህ ሁኔታ ስምንት ወር እስኪሞላት እዛው አሰሪዎቿ ቤት ቆይታ እጇ ላይ ያላትን ብር በመያዝ ገርጂ ጊዮርጊስ አካባቢ ቤት ተከራይታ በመውጣት ቤተልሄምን ትወልዳለች። እርጉዝ እያለች የተፈጠረውን ነገር ለቤተሰቦቿ አሳውቃ ስለነበር ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ ያርሳታል። ቤተልሄም ክርስትና እስክተነሳ ድረስ በሰላምና በጤና የሰነበተች ቢሆንም አራተኛ ወሯ ላይ መጣ ሄድ የሚል ህመም ይጀምራታል። እናም በወቅቱ ወደ ህክምና ስትወስዳት ያመማት ማጅራት ገትር እንደሆነ ይነገራትና አስፈላጊው ህክምና እየተደረገላት በየካቲት አስራ ሁለት ሆስፒታል ሁለት ወራትን ታሳልፋለች።
በእነዚህ ጊዜያቶች ግን በየእለቱ ረጅሙን ጊዜ በጣም በማልቀስና በመወራጨት ነበር የምታሳልፈው። ጡት መጥባትም ሆነ ምንም ምግብ መውሰድም አቁማ ምግብ የሚሰጣት በአፍንጫዋ በተሰካ ግሉኮስ ነበር። በዚህ ሁኔታ በሆስፒታሉ ከቆየች በኋላ ትንሽ ትንሽ ድምጽ ማሰማት ስትጀምር አየሩም ሲቀየር ለውጥ ታመጣ ይሆናል በማለት ከሆስፒታል አውጥታ ወደ ገጠር ቤተሰቦቿ ጋር ትወስዳታለች። እዛም ጸበሉንም የሀበሻውንም መድሃኒት እየሞከረች ለአንድ ዓመት ካቆየቻት በኋላ እድሜዋ ሁለት ዓመት ሲሞላ በዚህ ሁኔታ እዛ መቆየት ስለሌለባትና የጠበቀችውንም ለውጥ ስላላገኘች የተቻለውን አንዳች ነገር ለመሞከር በማለት ተመልሳ ወደ አዲስ አበባ ታቀናለች።
አገር ቤት በነበረችበት ወቅት መጨረሻ ትሰራበት ከነበረችው ቤት እናት ጋር በስልክ ትገናኝ ስለነበር ጸበሉንም ሆነ ህክምናውን እሳቸው ቤት ተቀምጣ እንድትሞክር ፈቅደውላት እንደ መጣች እዛው ቤት አርፋ የቀደመ ስራዋን እየሰራች ለሁለት ዓመት ትቀመጣለች። በእነዚህ ጊዜያቶችም የሰማ ሁሉ የጠቆማት ቦታ በመሄድ የባህላዊንም ዘመናዊውንም ህክምና ስትሞክር ብትቆይም ቤተልሄም ላይ የሚታይ ለውጥ ማየት አልቻለችም። እናም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ህጻኗን ሳል ሲያማት በሚያሰሯት እናት ድጋፍ ይዛት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ታቀናለች። ሆስፒታል ስትደርስም ከወር በኋላ መጥታ እንድትከታታል ይቀጥሯታል። አብረዋት የሄዱት እናት ብዙ ተጨቃጭቀው ምርመራ እንድታገኝ ያደረጉ ሲሆን እግረ መንገድም በእለቱ የገጠማትን ሳል ብቻ ሳይሆን አላንቀሳቅስና ከአልጋ አላስነሳት ላለውም በሽታ ህክምናዋን ትጀምራለች። እናም እየተመላለሰች ለዶክተሮቹ ብታሳይም የተጠየቀችውን ምርመራም ብታደርግም የፊዚዮቴራፒ ህክምና ካገኘች ተስፋ ስለሚኖራት እሱን ትሞክር ከሚል ምክር ውጪ አሁንም ለቤተልሄም በሽታም ሆነ መድሀኒት ሳይገኝላት ይቀራል።
ከዚህ በኋላ ነበር ነገሮች ባሉበት መቀጠል ስላልቻሉ ወደ እንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ በጸበል ለመሞከር በማሰብ አንዲት ትንሽዪ ቤት ተከራይታ ልጇን እያስታመመች መኖር የጀመረችው። እናም ያለፉትን ስምንት ዓመታት ከአካላዊ እድገት ውጪ ምንም የጤና ለውጥ የማታሳየውን ህጻን ይዛ እዛው በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ቤት ተከራይታ ትከትማለች። በእነዚህ ዓመታተም ቤተልሄም ረጅም ሰአት ስለምትተኛና ያን ያህል ስለማታስቸግራት አዝላት እየሄደች ልብስ አጠባና እንጀራ መጋገር የመሳሰሉትን የጉልበት ስራዎች እየሰራች ታሳልፋለች። የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት እንድትወስድ በታዘዘውም መሰረት ጉርድ ሾላ ሳአሊተ ምህርት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ቸሻየር ፋውንዴሽን በሚባል ድርጅት ለአንድ ዓመት ያህል በሳምንት ሁለት ቀን በነጻ ስታሳክማት ብትቆይም ከመንገዱ ርቀት የተነሳና ለሸክምም ሆነ ለታክሲ ያለው ውጣ ውረድ አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲሁም በዓመታት ህክምና ውስጥ ምንም ለውጥ ባለማየቷ ለማቋረጥ ትገደዳለች። እናም በየእለቱ ቤተልሄምን ጸበል ማሰጠመቋን ትቀጥላለች።
ከወራት በፊት ደግሞ በድጋሚ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምናዋን መከታተል ያስጀመረቻት ቢሆንም ቤተልሄም ግን ምንም ለውጥ ማግኘት አልቻለችም። ሃኪሞቹም ከዓመታት በፊት የነገሯትን በመድገም ዛሬም ፊዚዮቴራፒውን መከታተል እንደሚኖርባት ይነግሯታል። በድጋሚ ካዛንቺስ አካባቢ ሁለተኛ ዙር የፊዚዮቴራፒ አገልግሎቱን ብትቀጥልም እሷም ስራ መስራት ስላለባት ትንሰፖርቱም አስቸጋሪ በመሆኑ በተመደበው ፕሮግራም መሰረት ሳይሆን በቻለች ጊዜ ብቻ የፊዚዮቴራፒውን ህክምና እንድትከታተል ታደርጋታለች። የቤተልሄም ማደግ ግን ያመጣው ችግር ህክምናውን በቀላሉ እንድትከታተል አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን እንደልብ ይዛት መንቀሳቀሰም ስለማትችልና ምንም እንኳን የማትንቀሰቀስ ቢሆንም እቤት ውስጥ ዘግታባት ለመሄድ ስለማትችል ለእለት ጉርስ ለማግኘት የምትሰራውንም ስራ እያደናቀፈባት መጣ። የእታፈራሁና የቤተልሄም ቤት ኪራይም ሆነ የቤት ወጪ የሚሸፈነው ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ወንድሞቿ ሊጠይቋት ሲመጡ ከገጠር ይዘውላት ከሚመጡት ጤፍና አንዳንድ እህሎች ውጭ እሷ በየቀኑ ተሯሩጣ በምታመጣው ገቢ ነው። እናም አብዛኛው ስራ እየተቋረጠ በመምጣቱ ቤት ኪራዩም የሚበላውም እየጎደለ ይመጣል። ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ አንዲት ልብስ ስታሳጥባት የነበረች ሴት ችግሯን በመረዳት በየወሩ ደመወዟን እንደምትከፍላት ስራውን ግን በተመቻት ጊዜ እየመጣች እንድትሰራ ሁኔታዎችን ታመቻችላታለች። ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ በቅርበት የሚያውቋት ግለሰቦችም ቋሚ ባይሆንም ባገኙ ጊዜ በሚያደርጉላት ድጋፍ የእሷንም የልጇንም የእለት ቀለብ በመሸመት ለመኖር ትገደዳለች።
እታፈራሁ የዘገየች ቢሆንም የልጇ ህመም እየጠና ሲሄድና በአንዳንድ ነገሮች አስቸጋሪ እየሆኑባት ሲመጡ መልኩን እንኳ በትክክል የማታስታውሰውን አስገድዶ የደፈራትን ልጅ ለማግኘትና አስፈላጊውን የህግ ውሳኔ ለማስወሰን በማሰብ ወደ ቤቱ አቅንታ ነበር። ነገር ግን የዛኔ እሷም አላወቀችው ሆኖ እንጂ አሰሪዎቿ ቤት ተከራይተው ይኖሩ ስለነበር ለቀው መሄዳቸውንና ጊዜው ከአስር ዓመት በላይ ስለሆነው እንኳን ያሉበትን እነሱንም የሚያስታውስ አጥታ ትመለሳለች።
መፍትሄ ባገኝ በማለትም የነዋሪነት መታቂያ ባወጣችበት ወረዳ ወደሚገኘው ሴቶችና ህጻናት ቢሮ በመሄድ ድጋፍ እንዲደረግላትም ታመለክታለች። እነሱም ወደ ከተማ አስተዳደሩ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ይልኳታል። ቢሮው ተቀብሎ ጉዳዩን ካየ በኋላ መካኒሳ ስለ እናት የሚባል በጎ አድራጎት ድርጅት መኖሩን በመጠቆም ወደዛ እንድትሄድ ደብዳቤ ጽፎ ይሸኛታል። ደብዳቤውን ይዛ ወደተባለችው ቦታ ብታቀናም ድርጅቱ እርዳታ የሚያደርገው ለሚማሩ ተማሪዎች ብቻ በመሆኑ ሊያስተናግዷት እንደማይችሉ በመንገር ያሰናብቷታል። እንዲህ እንዲህ እያለች በርከት ያሉ ሙከራዎችን ብታደርግም ከአንዳቸውም ጠብ የሚል ነገር በማጣቷ በራሷው ትግል ኑሮዋን ለመቀጠል ትገደዳለች።
ከረጅም ጊዜ በኋላ ደግሞ በቅርቡ እሷ የምትኖርበት ወረዳ ይሰራ የነበረ አንድ እሷን የሚያውቃት ልጅ ሽሮ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው የወረዳው ሴቶችና ህጻናት በመሄድ አንዳንድ ድጋፎች እንዲደረግላት እንድትጠይቅ ይነግራታል። በተደጋጋሚ ወደተለያዩ አካላት በመሄድ ላቀረበችው ጥያቄ ከወሬ ውጪ ምንም ተደርጎላት ስላልነበር የሰነቀችው ተስፋ ባይኖርም ለመሞከር ብላ ወደዛው ታቀናለች። እዛም ደርሳ ያለውን ነገር በማስረዳት ያላትን መረጃ ታቀርባለች። እነሱም ከሳምንት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሶስት መቶ ብር ይሰጧታል።
ከዚህ በኋላ ልጅቷን ይዛ እንደልብ መንቀሳቀስ ስለማትችል ያላት እድል ቤተልሄም ባለችበት አካባቢ አንድ ቦታ ተቀምጣ እንጀራ መጋገር ባልትና ማዘጋጀት የመሳሰሉትን ለመስራት በመሆኑ ለራሷ እቅድ ይዛ ተቀምጣለች። ግን ይሄም ቢሆን መነሻ ጥሪት የሚጠይቅ በመሆኑና እሷ ባለችበትና በየቀኑ ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮ በማይሞላበት ሁኔታ አስቸጋሪ ሆኖባታል። ይህም ሆኖ እታፈራሁ አንዳንዴ የግድ አስፈላጊ ሲሆን ቤት ዘግታባት የምትሄድ ቢሆንም የቀረ ይቀራል እንጂ ረጅም ሰአት ቤተልሄምን ብቻዋን እንድታሳልፍ እንደማትተዋት ትናገራለች።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ