” ለመከላከል እየተረባረብን ያለነው ኖቨል ኮሮና ቫይረስን ብቻ አይደለም። የመረጃ ወረርሽኙን Infodemic ጭምር እንጂ። ” የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ይህን የተናገሩት በማህበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያው ሀሰተኛው ፣ የተዛባው ሆነ ትክክለኛው መረጃ የትየለሌ በመሆኑ ሕዝብ፣ መንግስት፣ ፖሊሲ አመንጭዎች፣ ረጂ ድርጅቶች፣ የተግባቦት ልሒቃን፣ ወዘተ . በአሰስ ገሰስ የመረጃ አረንቋ መዋጣቸውን እና ከጤናም አልፎ የኢኮኖሚና የደህንነት ስጋት መደቀኑን በመታዘብ ነው። ከወረርሽኙ የኖቨል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ- 19) ይልቅ የመረጃ ወረርሽኑ አየሩን፣ ምድሩንና ባህሩን ብቻ ሳይሆን ቨርቹዋል የሆነውን ዲጂታል ዓለምንም አዳረሰው። በዚህም ሕዝቡ የሚይዘው የሚጨብጠው አጣ። ግራ ተጋባ።
ትክክለኛውን ከተዛባው መረጃ መለየት ተሳነው። ሽብር ተስፋፋ። ይህን ተከትሎ ፍርሀት ነገሰ። ወረርሽኙ ገና ከውሀን ግዛት ሳይንቀሳቀስ ሕዝበ አዳም በፍርሀት ራደ። መፅሐፉ” እመን እንጂ አትፍራ” ማለቱን ለማስታወሰ አእምሮን ጉልበት ከዳው። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ሮዝቬልት በታላቁ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ጊዜ ” የምንፈራው ራሱን ፍርሀትን ነው። ” የሚለውን አጀጋኝ ምክርም በጀ አላለም። የዓለም የጤና ድርጅት ሕዝቡ፣ ሀገራትና መንግስታት ተደራሽ፣ ተአማኝና ትክክለኛ መረጃ ከየት ማግኘት እንዳለባቸው ግራ በመጋባታቸው ለአልተገባ ፍርሀትና ጭንቀት እየዳረጋቸው እንደሆነ ስለታዘበ ከኮሮና ቫይረስ ባልተናነሰ የመረጃ ወረርሽኙ አሳስቦኛል ለማለት ተገደደ።
የኒዎርክ ታይምሱ ዘጋቢ ቤን ዚመር የኢንፎደሚክ ስረወ – ቃሉ ( ኢቲሞሎጂ ) እ አ አ ከ2003ቱ የኮሮና ቫይረስ ቤተሰብ” ሳርስ ” SARS ወረርሽኝ የሚመዘዝ መሆኑን ያወሳል። ኢንፎደሚክ ከኢንፎርሜሽን የመጀመሪያዎቹን ፊደላት፣ ከኤፒደሚክ ደግሞ የመጨረሻ ሆሄያት በማዋሀድ የተፈጠረ ውህድ ቃል ነው። ቃሉን የፈጠረው የፖለቲካ ሊቁ ዴቪድ ሮዝኮፍ ሲሆን በዋሽንግተን ፖስት ስለ ” ሳርስ ” ባስነበበው መጣጥፍ (ኦፕ – ኤድ) ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሞበታል። ልክ እንደዛሬው ኮሮና ቫይረስ” ሳርስ ” የተከሰተ ጊዜም በተመሳሳይ ሁኔታ ሀሰተኛ፣ የተዛባና ቅንጣት እውነተኛ መረጃ ጋር ተዛንቆ ግራ እስከማጋባትና ፍርሀት እስከመንዛት ደርሶ ነበረ ። የዓለም ጤና ድርጅት መነሻም ከዚህ አመክንዮ የተቀዳ ነው።
ቤን በዚሁ ጹሑፉ የ” ኢንፎርሜሽን ” ስረወ – ቃል ወደ ኋላ ተጉዞ እ አ አ ከ1904 እንደሚሳብ ይገልፅና በስፋት ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ግን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋትን ተከትሎ እ አ አ ከ1970 ወዲህ ነው። በአብነትም ኢንፎስፌርን፣ ኢንፎስትራክቸርን ፣ ኢንፎሜኒያን፣ ኢንፎግራፊክን፣ ኢንፎርመርስያልን ፣ ኢንፎቴይመንትነንና ኢንፎሆሊክን ያነሳሳል። ” ዴሚክ ” የሚለው ምዕላድ ስረወ – ቃል ከጥንታዊቷ ግሪክ ዘሩን የሚስብ መሆኑን ያስታውስና ” ዴሞስ ” ሕዝብ ማለት ሲሆን ” ኤፒደሚክ ” ደግሞ በሕዝቡ በስፋት የተጋባ ማለት ነው። ” ፓንዴሚክ ” ደግሞ በበርካታ ሀገራትና አህጉራት በስፋት የተዛመተን ወረርሽኝ ይወክላል ። ” ፓን ” በግሪክ ሁሉን ማለት ሲሆን ፓንዴሚክ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርሁት ሁሉን ያዳረሰ ወረርሽኝ ማለት ነው ። አሁን ሀገራችንን ጨምሮ በመላው ዓለም የተከሰተው የኖቨል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ፓንዴሚክ ነው።
የፖለቲካ ሊቁ ዴቪድ ሮዝኮፕ” ኢንፎ ” እና ” ዴሚክን” አጣምሮ በ2003 እ አ አ ላይ” ኢንፎዴሚክ “የሚለውን ውህድ ቃል ለመጠቀም ያነሳሳው በወቅቱ ተከስቶ ከነበረው ” ሳርስ ” ወረርሽኝ ይልቅ ወሬው፣ አልቧልታው በበይነ መረበ Internet በከፍተኛ ፍጥነት ተዛምቶ በሕዝቡ ዘንድ የፈጠረው ሽብርና ያስከተለው ፍርሀት መሆኑን ያስታውሳል። ቃሉ ከተፈጠረ በሁለት ዓመቱ በስፋት ጥቅም ላይ በመዋሉ በዚሁ ዓመት በታተመው የኦክስፎርድ የአሜሪካ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ሊካተት ችሏል። በአቬን ፍሉ፣ በስዋይን ፍሉ፣ በሳርስ፣ በኢቦላ ወረርሽኞች ወቅት ከበሽታው ይልቅ አሉባልታው በስፋትና በፍጥነት ተዛምቶ በሕዝቦችና በሀገራት ሽብር ፈጥሮ ስለነበር” ኢንፎዴሚክ ” በስፋት ጥቅም ላይ መዋሉን ይሄው የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ያትታል። እንደኛ በማንነት፣ በጥላቻና በደባ ፖለቲካ ተፈጥርቆ ለተያዘ ግን ከወረርሽኙ በፊትም ሆነ በኋላ የመረጃ ወረርሽኙ ላልተወሰነ ጊዜ ተቆራኝቶን ይቆያል ።
የቃሉ ፈጣሪ ሮዝኮፕ በአጭር ጊዜ ውስጥ ” ኢንፎዴሚክ “እንዲህ ታዋቂ መሆኑ ሳያስገርማቸው አልቀረም። ሆኖም ዲቃላው ቃል የመረጃ በተለይ የተዛባ መረጃ ስርጭት በሰዎች የእለት ተእለት ኑሮ ላይ ምን ያህል አሉታዊ ተዕፅኖ እንደሚያሳድር ግንዛቤ ለመፈጠር ረድቷል ይላሉ። ይሁንና እንደኮሮና ያሉ የሕዝብ ጠንቅ ወረርሽኞችን ለመከላከልም ሆነ ለመቆጣጠር የመረጃ ወረርሽኙን በመመከት ለሕዝቡ ተአማኒነት ያላቸውን የመረጃ ምንጮች ተደራሽ ማድረግ አብሮ ሊሰራበት ይገባል። ዛሬ በአለማችንም ሆነ በሀገራችን ወጥ የሆነ የመረጃ ቋት የለም ማለት ይቻላል ። በመረጃ አደረጃጀትና አሰረጫጨት የካበተ ልምድ፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ያላት አሜሪካ ሳትቀር ዶናልድ ትራምፕ በአፈተት በቲውተር በሚያዥጎደጉደው አቅላይና አዘናጊ የተዛባ መረጃ እየተወዛገበች ትገኛለች።
ወደ ሀገራችን መለስ ቀለስ ስንል የጤና ጥበቃ፣ የጠቅላይ ሚንስቴርና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የሚያወጣጧቸው መረጃዎች ወጥ መሆን ስለሚገባቸው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ወረርሽኙ በፍጥነትና በስፋት የሚዛመት ስለሆነ በጤና ሚንስቴርም ሆነ በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩቱ ሳምንታዊ ሳይሆን ዕለታዊና እንደ አስፈላጊነቱም በቀን ሁለት ሶስቴም ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠትና ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ ምክሮችና መተግበሪያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅተው ወደስራ መግባት አለባቸው ። ለዚህ ማህበራዊ ሚዲያውና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ የማይተካ ሚና አላቸው።
የዓለም የጤና ድርጅት ( ደብሊው ኤች ኦ ) በተለይ የመረጃ ወረርሽኙን ለመከላከል ከማህበራዊ ሚዲያዎች (ፕላት ፎርምስ) ጋር ተቀራርቦ በመስራት አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል ። ድርጅቱ ጠቃሚና ትክክለኛ መረጃዎችን እንዲያደርሱ ከቲዊተር ፣ ፌስ ቡክ፣ ቴንሴንትና ቲክ ቶክ ጋር ከመስማማቱ ባሻገር ከጎግል ጋርም በቅንጅት በመሰራት ላይ መሆኑ ተመልክቷል ። በስምምነቱ መሰረት ማንኛውም ሰው ጎግል ላይ ገብቶ ስለ ኮሮና ቫይረስ መረጃ ሲፈለግ ቀድሞ የሚከፈተው ፣ የሚያገኘው በዓለም የጤና ደረጃ ተረጋገጦ የተሰነደን እውነተኛ መረጃ ነው። ዩቲውብና ፌስ ቡክ ላይ ስለወረርሽኙ መረጃ ሲበረብሩ ቀድሞ የሚመጣልዎ የዓለም የጤና ድርጅት ያጠናቀረው መረጃና መመሪያ ነው።
ድርጅቱ ከዚህ ጎን ለጎን የተዛቡና ሀሰተኛ የሆኑ መረጃዎችን የማጣራት ስራ (ፋክት ቼኪንግ ) እንደ አይጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤ ኤፍ ፒ) ካሉ ዜና አገልግሎቶችና ከቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ ነው። የተዛበ መረጃ አለማቀፍ ክስተት ቢሆንም ስርጭቱ ግን ከሀገር ሀገር ይለያያል። በአፍሪካ ዜናዎች በስፋት የሚሰራጩት በፌስ ቡክ፣ ቲዊተር፣ ዩቲውብ፣ ወትስአፕ፣ ወዘተ . ቢሆንም እንደ ሬዲዮ፣ ጋዜጣና ቴሌቪዥን ያሉ መደበኛ ሚዲያዎች ተመራጭ የዜና ምንጭ የሆኑባቸው አካባቢዎችም አሉ ። ዞሮ ዞሮ የመደበኛ ሚዲያ ጋዜጠኞች ማህበራዊ ሚዲያዎን በምንጭነት ሊጠቀሙ፣ ሊከታተሉ (ሞኒተር) ሊያደርጉ ስለሚችሉ እንክርዳዱን ከስንዴው መለየት የሚያስችል የክህሎት ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል።
በኤ ኤፍ ፒ የአፍሪካ መረጃ የማጣራት ኃላፊ ኒና ላምፓርሲክ በብዛት በማህበራዊ ሚዲያው የሚዘዋወሩ አሉባልታዎች ወይም ጭምጭምታዎች በኮቪድ 19 መነሻና ወረርሽኙ በአፍሪካ በስፋት እየተሰራጨ መሆኑ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ትናገራለች ። ሆኖም እውነተኛ መረጃን ተደራሽ በማድረግ የተጋነኑና በማህበረሰቡ ዘንድ ሽብር የሚለቁ መረጃዎችን መከላከል ይቻላል ። መንግስትም ሆና ባለድርሻ አካላት ወቅታዊና እውነተኛ መረጃዎችን ከስር ከስር የማድረስ ኃላፊነት አለባቸው። እግረ መንገድ ሕዝብን ካልተገባ ፍርሀትና ውዥንብር መከላከል ይቻላል። ዳሩ ግን ትክክለኛ መረጃን የማድረስ ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው ጉዳይ ሳይሆን የሁሉንም ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑ ሊጤን ይገባል ።
አንድ መረጃ ከማጋራት ወይም ከመለጠፍ በፊት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይሁን ለሌላ ተግባር በምንጭነት ከመጠቀም በፊት ከሌሎች ምንጮች ጋር ማመሳከር የተቀናጀ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል። የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን የምንጠቀም ሰዎች ስለምናጋራው ጽሑፍ ፣ ምስልና ድምፅ ቆም ብለን ማሰብ፣ ለዋቢነት ፣ ለአጋዥነት ስለምንከፍተው ድህረ ገፅ፣ ጦማር ታማኝ ምንጭ መሆን አለመሆን ማጣራት በማስከተል አስተያየት ( ኮሜንት ) ከመስጠታችን በፊት ማውጣት፣ ማውረድና ማመዛዘን ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ከቻልን ሀሰተኛ ፣ የተዛባና የጥላቻ መረጃ ዘርጋፊዎችንና ለፋፊዎችን በሒደት ማስቆም እንችላለን።
እንደመውጫ
ወግ አጥባቂው የእንግሊዙ ” ዴይሊ ቴሌግራፍ ” ጋዜጣ ዘጋቢ ኒክ ስኳዬርስ ለጣሊያኑ ” ፕሬስ ጋዜት ” እንደተናገረው ፣ በጥር ወር በቻይናዋ ውሀን ጠቅላይ ግዛት የኖቨል ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ አንስቶ ያለእረፍት ሌት ተቀን እየሰሩ ካሉ ባለሙያዎች ሐኪሞች ቀዳሚ ሲሆኑ ጋዜጠኞች ይከተላሉ። ለጋዜጠኞች በነጻነት ተዘዋውሮ መዘገብ አዳጋች ቢሆንም ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ የማይተካ ሚና ስላላቸው ሕዝብን የማሳወቅ ፣ የማንቃትና የማቆፍጠን ኃላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብ ራሳቸውን በመጠበቅ ስራቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባ ይመክራል። በጣሊያን ሚላን ለሚገኝ ጋዜጣ በፍሪላንስነት የሚፅፈው አሌሲዎ ፔሮኒ በበኩሉ ” ከወረርሽኙ በፊት መረጃ በቀላሉ ይሰጡን የነበሩ ግለሰቦችና ተቋማት ዛሬ በቀላሉ የማይገኙ ሆነዋል። ” በማለት ወረርሽኙ በጋዜጠኞች ላይ ያሳደረውን ጫና ይገልጻል። ራሱን “የጋዜጠኞች ድምፅ ” ብሎ የሚጠራው” ኮሎምቢያ ጆርናሊዝም ሪቪው ( ሲ ጄ አር) ” አንዳንድ ጋዜጦች ከአሁኑ አምዶቻቸውን በዜና እረፍት መሙላት መጀመራቸውን በመግለፅ ወረርሽኙ በሙያው ላይ እያሳረፈ ያለውን ዱላ በማስረጃ ያወሳል።
ከቻይና በመከተል ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እያደረሰባት በምትገኘው ጣሊያን የሚሰሩ 30 የፈረንሳይ ጋዜጠኞች በተለይ ለሀገረ ፈረንሳይ በፊርማቸው አረጋግጠው ባስተላለፉት (ፔቲሽን ) ወረርሽኙ ምን ያህል የከፋና ከተጠበቀው በላይ መሆኑን በአይናችን በብረቱ አረጋግጠናል። ሆኖም ዓለም በተለይ ፈረንሳውያን ግን አደገኝነቱን በቅጡ የተረዱቱ አይመስልም ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል። ይህን መጣጥፍ እያሰናደሁ እያለ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንድ ጋዜጠኛ፣ ” የከተማ አውቶቡሱ፣ መሸታ ቤቱ፣ ምግብ ቤቱ ዛሬም በሰዎች እንደተጨናነቁ ናቸው። ለንደን እየሰማች አይደለም፣ እንዝህላልነቱ፣ ቸልታው ከኮሙኒኬሽን ስልቱ ከሆነ እንደገና ሊፈተሽ ይገባል። ” ብላለች ። በመዲናችን አዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ያለው ኬረዳሽነት ከዚህ የተለየ አይደለም ማለት ይቻላል ።
የግልም ሆነ የመንግስት፣ ኢቲቪ ሆነ ፋና ፣ አዲስ ዘመን ሆነ ሪፖርተር፣ የሀይማኖትም ሆነ የማንነት ፣ ቃለ አዋዲም ሆነ አስራት፣ ዲምጺም ሆነ እ ኤም ኤን ፣ ቃናም ሆነ ብስራት ያለምንም ልዩነት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በመናበብና በመቀናጀት ይበልጥ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ሲያደርጉ ግን የመረጃ ወረርሽኙ ሰለባ እንዳይሆኑ አበክረው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። የደቡብ ኮሪያ መንግስት ወረርሽኙ በሀገሩ ከተከሰተበት ሰዓት ጀምሮ ግልፅና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ዘርግቶ በመንቀሳቀሱ ለዓለም መንግስታት በአርዓያነት እየተጠቀሰ ነው ።
የክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መንግስት ይህን የደቡብ ኮሪያ መንግስት ፈለግ ቢከተል ብዙ ያተርፋል። ወረርሽኝ የማንም ጥፋት ወይም ስህተት አይደለም። የእናት ተፈጥሮ ፍርጃ እንጂ። ስለሆነም መሸፋፈን፣ መደባበቅና ማለባበስ ወረርሽኙ በስፋት እንዲዛመትና ሕዝቡም እንዲዘናጋ በር ከመክፈት ውጭ ሌላ ጥቅም የለውም ።
” ወረርሽኝን የመከላከል ጉዳይ የህክምና ቴክኖሎጂ ኃላፊነት ብቻ አይደለም። የመረጃ ንፅህና ጭምር እንጂ ። ” ኢዝሀን ታሩር ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com