
የአለም መገናኛ ብዙኋን የሰሞኑ ትኩረታቸው የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተለያዩ ገፆቻቸው በስፋት ሽፋን ሰጥተውበታል፡፡በተለይም በሶስቱ ሀገራት መካከል የነበረው ድርድር ያለ ስምምነት መቋጨትና የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ዋንኛ ትኩረታቸው ነበር፡፡
ታላቁ የዜና አውታር ቢቢሲ፤ ኢትዮጵያ የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት “ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” ብላለች።በሚል ባሳለፍነው ሳምንት ሰፋ ያለ ዘገባ አስነብቧል። በዘገባው ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ሜጋ ግድብ ፕሮጀክት ላይ የአሜሪካ አቋም “ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለውም”ማለቷን ጠቅሷል፡፡
የግብፅና የኢትዮጵያ አለመግባባት ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል በሚል ፍራቻ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ አሜሪካ ድርድር እንዲደረግ ጥረት አድርጋለች በማለት ዘግቧል።ድርድሩ ያለ ስምምነት መጠናቀቅ እንደሌለበት አሜሪካ ካሳሰበች በኋላ ኢትዮጵያ እራሷን ከድርድሩ ማግለሏን አትቷል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ ውይይቱን መቀጠል እንደምትችል ተናግረው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል። ግድቡ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እንደሚሆን የጠቆመው ዘገባው፤ ለኢትዮጵያና ለአንዳንድ ጎረቤቶች ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስገኝም ገልጿል። ኢትዮጵያ ግድቡን በመጪው ሰኔ ወር መሙላት መጀመር ትፈልጋለች። ነገር ግን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የውሃ አቅርቦታቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አሳስቧቸዋል።በተለይም ግብጽ ግንባታው እ.ኤ.አ. በ2011 ዓ.ም ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ፕሮጀክቱን እንደ አንድ የአደጋ ስጋት አድርጋ እንደምትመለከተው በዘገባው ጠቅሷል፡፡
በዘገባው እኤአ በ1932 የተደረገው ስምምነት ግብፅ እና ሱዳን ሁሉንም የአባይ ውሃን የመጠቀም መብት መስጠቱን ተመልክቷል።ነገር ግን በአባይ ላይ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ግድብ 90 በመቶው ውሃውን ይወስዳል ብላ ግብፅ ስጋቷን ስትገልፅ ቆይታለች።የአፍሪካን ረዥሙ ወንዝ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ይችላል የሚል ስጋት እያየለ በመምጣቱ ምክንያት ግብፅ የግድቡ የውሃ ሙሌት ስራ በረጅም ጊዜ እንዲከናወን ትፈልጋለች።
በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል አለመግባባት የተፈጠረ ሲሆን ሁለቱም አገራት ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ነገር እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።አሜሪካ ለድርድር ለመገኘት ወስና ሶስቱን አገራት ብታደራድርም በአፋጣኝ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለበት ለኢትዮጵያ ጥሪ ማቅረቧን ዘገባው አመልክቷል።
የአሜሪካ መንግስት ስምምነቱን ሁሉም ወገኖች ካልፈረሙ የመጨረሻ ሙከራ እና የውሃ ሙሌት ስራው መጀመር የለበትም ብሏል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የአሜሪካንን መግለጫ “ያልተለመደ” እንደሆነ በመግለጽ “አሜሪካኖች ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ እንፈልጋለን።ነገር ግን ማንኛውም ሌላ ሚና ተቀባይነት የለውም፡፡” ብለዋል።ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሮይተርስ እንደገለፁት፤ አሜሪካ አለመግባባቱን ለመፍታት አስፈላጊው ጥረት ታደርጋለች፡፡
የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ማብራሪያ መስጠቱ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም የግብጽ መገናኛ ብዙኃን አወዛጋቢ ዘገባዎችን ሠርተዋል።“ዴይሊ ኒውስ ኢጂብት” የተሰኘው የዜና ምንጭ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ብቸኛው አማራጭ ድርድር እንደሆነ ሀገራቸው እንደምታምን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶክተር ኢንጂነር) መናገራቸውን ዘግቧል።ይህ የዜና ምንጭ በዚሁ ዘገባው ሚኒስትሩ በድርድሩ ጉዳይ ግብጽ ያቀረበችውን ሐሳብ ከዚህ ቀደም ውድቅ ማድረጋቸውንም አስነብቧል።
ሲ ጂ ቲ ኤን በበኩሉ፤ በግድቡ ላይ የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለግብጹ አቻቸው አል ሲሲ ገልጸውላቸዋል።ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ድርድር ከጀመሩ ዘጠነኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን አሜሪካ ጥረቷን እንደምትቀጥልም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ለግብጹ አቻቸው እንደገለጹላቸው ተዘግቧል።ሦስቱ ሀገ ራት የሕዳሴ ግድቡን የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ የተመለከተውን ሰነድ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ እንደ ሚፈርሙ ቢጠበቅም ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ለመወሰን ጊዜ እንደሚያስፈልጋት በማሳወቋ ተግባ ራዊ አልተደረገም፡፡
ይህም በግድቡ ድርድር ሰበብ የዓባይ ወንዝ ውኃ ድርሻ ላይ ውሳኔ እንዲተላለፍላት ግፊት ስታደርግ የነበረችው ግብጽ ቅር ሲያሰኝ አሜሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ ያልተገኘችበት ውሳኔ እንዲተገበር ፍላጎቷን የሚያሳይ መግለጫ ማውጣቷ ይታወሳል።“ድርድሩ ሳይጠናቀቅ ኢትዮጵያ ግድቡን ውኃ መሙላት መጀመር የለባትም” የሚለው መግለጫ “አሜሪካ ለግብጽ ያላትን ወገንተኝነት በግልጽ ያሳየ ነው” በሚል በኢትዮጵያ የዘርፉ ባለሙያዎችና በሕዝብ እየተተቸ ነው።አንዲት ሉዓላዊት ሀገር ሀብቷን የመጠቀም መብቷን በተመለከተ የማንንም ይሁንታ የማትጠብቅ መሆኗን በምክንያትነት በማንሳት ነው አሜሪካ እየተተቸች የምትገኘው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012
መርድ ክፍሉ