በአድዋ ከተማ አድሀቂ ዜሮ ሰባት ሃየሎም ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፍዮሪ ሀብተ ማርያም ከሰተ ከሶስት አመት በፊት ነበር በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ችግር ተከትሎ ትዳር መስርተው ቤት ሰርተው በሰላም ይኖሩበት ከነበረው ከጎንደር አብደራፊ ከተማ አብርሃ ጅራ ወረዳ የተፈናቀሉት። በወቅቱ ችግሩ አሳሳቢ ስለነበር ቤት ንብረታቸውን ጥለው አራት ልጆቻቸውን ይዘው ከእናታቸው ጋር ወደ ትግራይ ያቀናሉ። ባለቤታቸው ደግሞ በትግራይ ያፈሩትም ሆነ ያስቀመጡት ንብረት ስላልነበራቸው አቅማቸው የፈቀደውን ሰርተው ኑሮን በማሸነፍ ቤተሰባቸውን ለመደገፍ ወደሱዳን ይሰደዳሉ። ወይዘሮ ፍዮሪም ትግራይ ገብተው ከእናታቸው ጋር በመሆን ለተፈናቃይ የምትሰጠውን በአንድ ሰው 15 ኪሎ ስንዴ እየተቀበሉ አራት ልጆቻቸውን ማሳደጉን ይቀጥላሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ ይደግፏቸው አይዞሽ ይሏቸው የነበሩት እናታቸው ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ነገሩ ሁሉ እየከፋ ይመጣል። ባለቤታቸውም የት እንደደረሱ ሳይታወቅ የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ። መቶ ኪሎ የማትሞላ ስንዴ እየተቀበሉ አራት ልጅ ይዞ በቤት ኪራይ መኖር የሚያዛልቅ ካለመሆኑም ባሻገር አንድ ቀን ሁሉም ነገር መስመር ስቶ እኔም ልጆቼም ለጎዳና መዳረጋችን አይቀርም እያሉ በመሳቀቅ ላይ ሳሉ በቀበሌ በኩል እርዳታ ሊደረግላቸው እንደሚችል መረጃ ይደርሳቸዋል።
በዚህ አይነት ነበር በወረዳው በኩል ከዋይድ ሆራይዘን ፎር ችልድረንስ ጋር ተገናኝተው አንድ ልጃቸውን በማስተማር ለሷ ቀለብ የሚሆን ወጪ እንደሚሰጣቸው የተነገራቸው። እናም ሰባት መቶ ሀምሳ ብር በልጃቸው ስም እየተሰጣቸው ለእሷም የትምህርት ወጪዋ እየተሸፈነላት መኖር ይጀምራሉ፡፡ ገንዘቡ ብዙ ባይሆንም በወቅቱ እሳቸው ከነበሩበት ችግር አንጻር ምጥ የመገላገል ያህል በመሆኑ ትልቅ እረፍት ያገኛሉ። በዚህ ሁኔታ እያሉም ምን አልባት ለመንቀሳቀስ፤ ሰርቶ ለመግባት ካሰቡ የሶስት ወር ክፍያውን በአንድ ግዜ እንስጥዎትና እንዳቅምዎ ወደ ንግድ ቢገቡስ የሚል ጥያቄ ይቀርብላቸዋል።
ወይዘሮ ፍዮሪም እኔም መንገዱ መላው ጠፍቶኝ እንጂ እስከመቼ የእናንተን እጅስ ስጠብቅ እኖራለሁ ብለው የራሳቸውን ዝግጅት ይጀምራሉ። ለልጃቸው ይሰጥ የነበረውም ክፍያ ወደ ስምንት መቶ ብር ያድግና የሶስት ወር ተቀብለው ወደ ንግድ ስራ ይገባሉ ። በሩ የተከፈተላቸው እናትም ከዚህም ከዚያም ብለው በከሰል የጀመሯትን የችርቻሮ ንግድ የመጣው ይምጣ ብለው በእቁብም በብድርም ተደግፈው ወደ ትንሽ ሱቅ በማሳደግና በማስፋፋት እዚህ ደርሻለሁ ብለው ለድርጅቱ ያሳውቃሉ። የድርጅቱ ኃላፊዎችም እኒህ እናት ትንሽ ድጋፍ ቢጨመርላቸው ቤተሰባቸውን ካለበት አደጋ ለመታደግ አቅም እንዳላቸው በመረዳት ሀያ ሶስት ሺ ብር ይሰጧቸዋል። ከጨለማ አወጡኝ የሚሉት ወይዘሮ ፍዮሪ አሁን ለቤት ኪራይ ከምከፍለውና ለልጆች ከማበላው አልፌ እንዳቅሜም ጥሪት መቋጠር ጀምሪያለሁ። ዛሬ ልጆች ቢያምብኝ ታክሲ የምጠራበት ብር ከእጄ አይጠፋም ሃሳብ ስለቀነሰልኝም እንቅልፍ ተኝቼ ማደርም ጀምሬያለሁ ይላሉ።
በተመሳሳይ በአድዋ ከተማ አድሀቂ ዜሮ ሰባት ሃየሎም ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አበባ ገብረ አምላክ ባለቤታቸው ከሞቱ 38 አመት ሆኗቸዋል። ወይዘሮ አበባ ነዋሪነታቸው በአስመራ ከተማ የነበረ ሲሆን በ1983 ዓ.ም በሀገሪቱ የተከሰተውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለመመለስ ይገደዳሉ።ወደ ሀገራቸው ሲመጡ ግን በእሳቸው ስም ቤትም ቦታም አልነበራቸውም። የወለጋ ተወላጅ የሆኑት ባለቤታቸውም ያስቀመጡት መሬትም ሆነ ቤት ስላልነበራቸው ረጅሙን የህይወት ጉዞ ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው በጡረታ ገንዘብ በቤት ኪራይ ይጀምሩታል።
በዚህ አይነት ከሀያ አመት በላይ ሲኖሩም ሁለት ልጆቻቸውን ለማሳደግ አልሰነፉም ነበር። ሰው ቤት እንጀራ በመጋገር ልብስ በማጠብ እንደተገኘም የቻሉትን ሁሉ የጉልበት ስራ እየሰሩ ኑሮን መግፋቱን ይያያዙታል። በዚህ መንገድ ካሳደጓቸው ልጆቻቸው አንደኛው የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆኖ ራሱን ችሎ የወጣ ሲሆን የመጀመሪያ ልጃቸው ግን ሁለት ልጆች ከወለደች በኋላ በመሞቷ ወይዘሮ አበባ ሌላ የልጅ ልጆቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነት እሳቸው ጫንቃ ላይ ያርፋል። በዚህ ግዜ የእርጅና መምጣትና የስራ እንደልብ አለመገኘት ለወይዘሮ አበባ ሁሉንም ነገር እያወሳሰበባቸው የቤተሰባቸውም ህልውና አደጋ ላይ እየወደቀ ይመጣል።
ለረጅም አመታት ሲቀበሏት የነበረችውም የወታደር ባለቤታቸው ስድስት መቶ የጡረታ ደመወዝ የኑሮ ውድነት ዋጋ እያሳጣት መጥቶ ዛሬ ቤት ኪራይም ለመሸፈን ተስኗታል። ከቤት ኪራይ ውጪ ደግሞ መብራትና ውሃም መክፈል ይጠበቅባቸዋል።ይሄኔ ነበር በስሚ ስሚ የደረሳቸውንና የቤተሰባቸውን ተስፋ ያለመለመውን መረጃ ይዘው ወደ ቀበሌ ያቀኑት፡፡እናም ቀበሌው አንድ ልጃቸውን በተረጂነት ለማስተማር ከድርጅቱ ጋር አገናኝቷቸው በየወሩ የስምንት መቶ ብር ተደጓሚ ያደርጋቸዋል። በደንቡ መሰረትም ድርጅቱ የስራ ፍላጎታቸውንና አቅማቸውን ስላየ በሰጣቸው የሶስት ወር አንድ ግዜ ክፍያ ደረቅ እንጀራና ከሰል መሸጥ ይጀምራሉ። አሁን ደግሞ ይህን ንግዳቸውን ለማስፋፋት የኤሌክትሪክ ምጣድ አስገብተዋል። «አሁንም ጉልበቴ ደህና ነው እነዚህን የልጄን ልጆች ለቁም ነገር ማድረስ ይጠበቅብኛል» የሚሉት ወይዘሮ አበባ ከሰል ሳሙና ክብሪት የመሳሰሉትን አጠቃላይ ችርቻሮ ንግድ ለመስራት እቅድ እንዳላቸውና ለዚህ የሚሆን ድጋፍ ካገኙ በአጭር ግዜ ውሰጥ ቤተሰባቸውን ከሀሳብና አሁን ካለበት ችግር ማላቀቅ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
የዋይድ ሆራይዘን ፎር ችልድረንስ አድዋ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ከቢረ ግደይ «የድርጅቱ አላማ እየደገፉ መኖር ሳይሆን ማብቃት በመሆኑ እንደነዚህ አይነት ቤተሰቦች ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለድርጅቱም ተስፋ የሚሰጡ በመሆናቸው የሚቻለው ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል» ይላሉ። ድርጅቱ ሁለት ዋና ዋና ፕሮግራሞችን ያከናውናል የሚሉት አስተባባሪው የድርጅቱን አላማና እንቅስቃሴ እንደሚከተለው ያብራራሉ።
የድርጅቱ የመጀመሪያው አላማ ተማሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የማብቃት ስራ መስራት ነው ። ተማሪዎችን ማብቃት ሲባል ግን ድጋፉ የሚደረገው ለሙሉ ቤተሰቡ ነው። በአብዛኛው ተማሪዎች ከትም ህርት ገበታቸው የሚሰናከሉትና በትምህርታቸውም ውጤታማ የማይሆኑት በተገቢው መንገድ ትምህ ርታቸውን ለመከታተል የሚያበቃ ከቤተሰብ ሊሟላ ላቸው ያልቻለ ነገር በመኖሩ ነው።ስለዚህ ድጋፉ ለተማሪው ብቻ ቢደረግ ተማሪው ከቤተሰቡ ጋር የሚኖር በመሆኑና የእለት ከእለት እንቅስቃሴው ከቤተሰቡ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ለብቻው የሚደረግ ድጋፍ ውጤታማ የመሆን እድሉ ጠባብ ነው። ስለዚህ በተደጋፊው ልጅ ስም በየወሩ ስምንት መቶ ሰባ ብር ለቤተሰብ ይደጎማል። ይህም ሆኖ ገንዘቡ ሲሰጥም የአንድን ቤተሰብ ሙሉ ለሙሉ ወጪ የሚያስተዳድር አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ መሰረታዊ ነገሮችን እንዲሸፍን በሚል ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ከገንዘቡ በተጨማሪ ለተማሪው የሚያስፈልገው እንደ ደብተር እስኪቢርቶና ቦርሳ ያሉ የትምህርት መሳሪያዎችና ሳሙናና ሶፍት የመሳሰሉት የጽዳት መጠበቂያ ቁሳቁሶችም እንደየሁኔታው በአመት ሁለት ወይንም አንድ ግዜ ለተማሪዎቹ ይሰጣል።
ከላይ የሚሰጠው ድጋፍ የሚደረግበት ዋና አላማ ቤተሰቡ በራሱ እንዲተዳደር ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ለማስቻል ነው። በመሆኑም ቤተሰቡ በቋሚነት መቋቋም ስላለበት ከተረጂዎች መካከል ተመርጦ ብቃት ያለው ሊሰራ የሚችል የቤተሰብ አባል ሲገኝ በአንድ ግዜ የሚሰጥ ከ18 እስከ ሀያ ዘጠኝ ሺ ብር የሚደርስ ድጋፍ የሚደረግበትም አካሄድ አለ።ድጋፉ ቤተሰቡ ራሱን ችሎ እንዲወጣና እርዳታውን በግዜ ሂደት ለማስቆም የሚረዳ ሲሆን በመጀመሪያ ግን ከትንሽ ጀምረው እንዲያድጉና ራሳቸውን እንዲችሉ ለቤተሰቡ የሶስት ወር በአንድ ግዜ እየተሰጠው በተሰማራበት መስክ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የማረጋገጥ ስራ ይሰራል። በዚህ በኩል በአሁኑ ወቅት 124 ተጠቃሚዎች ያሉ ሲሆን 58ቱ በአክሱም 66ቱ ደግሞ በአድዋ ከተማ ይገኛሉ። ድጋፉ ሲጀመር ለሁለቱም ከተሞች እኩል ኮታ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በአክሱም ይረዱ ከነበሩት ልጆች መካከል ዩኒቨርሲቲ የገቡ በመኖራቸው አሁን በአክሱም ከተማ ያሉት ተረጂዎች ቁጥር ሊቀንስ ችሏል ።
ከእነዚህ 124 ተጠቃሚዎች ቤተሰብ የጤና እክል የገጠመው ካለ ሙሉ የህክምና ድጋፍ ይደረግለታል። በተጨማሪ ጠንከር ላሉ ህክምናዎች ቅዱስ ዮሴፍ ከሚባል አሜሪካ ካለ ድርጅት ጋር በመተባበር በየአመቱ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ዶክተሮች እየመጡ በአድዋ ሆስፒታልና አጸደ ማርያም በሚባል በዋይድ ሆራይዘን በተሰራ ክሊኒክ ነጻ የህክምና ግልጋሎት ያገኛሉ። ለታካሚዎች ህክምናውም ሆነ መድሀኒቱ በነጻ የሚሰጥ ሲሆን የሚመጡት ዶክተሮች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ለሀገር ውስጥ የህክምና ባለሙያዎችም ከፍተኛ የልምድ ልውውጥና የእውቀት ሽግግር የሚፈጥር ነው።
ተቋሙ ከዚህ በተጨማሪ አልፋ (አክቲቭ ለርኒንግ ፎር አፍሪካ) የሚባል ፕሮግራም አለው። በዚህ ፕሮግራምም እድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ አስራ አራት አመት የሆኑና እድሜያቸው ቢያልፍም የትምህርት እድል ያላገኙትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። በፕሮግራም የሚካተቱ ልጆችም ስፒድ ስኩል በሚባል አካሄድ በፍጥነት ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ክፍል ትምህርት በአንድ አመት ጨርሰው በሁለተኛው አመት አራተኛ ክፍል እንዲገቡና ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ተቀራራቢ ክፍል ደርሰው እንዲማሩ የሚያስችል የራሱ አልፋ የሚባል ካሪኩለም ያለው ፕሮግራም ነው። በዚህም በአሁኑ ወቅት ወረላህ በሚባል በአንድ ወረዳ ብቻ እየተሰራ ሲሆን 600 የሚደርሱ ተማሪዎች አገልግሎቱን እያገኙ ናቸው። በዚህ ፕሮግራም የሚማሩት ልጆች በአንድ ክፍል ሰላሳ ብቻ ሲሆኑ በሀያ ክፍል ትምህርቱ እየተሰጣቸው ይገኛል።
ለዚህም ሀያ ሁለት አስተማሪዎች የተመደቡ ሲሆን ሁለት ተቆጣጣሪዎች አሉ። የዚህ አመት የመጀመሪያው ዙር እንደ አንደኛ ክፍል የሚታየው የሶስት ወር ትምህርት ተጠናቆ ውጤታቸው የገባ ሲሆን ሁለተኛው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ከሶስት ወር በኋላም ሶስተኛውን ሲያጠናቅቁ ለቀጣይ አመት አራተኛ ክፍል ገብቶ ለመማር በቂ ዝግጅት ይኖራቸዋል። ለእነዚህም በተመሳሳይ ከደብተርና እስኪሪብቶ ጀምሮ ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ በድርጅቱ በኩል ይቀርብላቸዋል።ይህ ፕሮግራም ጄኔቫ ግሎባል ከሚባል ድርጅት ጋር በትብብር የሚሰራ ሲሆን ከዚህ ቀደም መረብ ለሃ በሚባል ወረዳም ሲሰራበት የነበረ ሲሆን እስካሁንም 6 ሺ 650 የሚደርሱ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።እነዚህ ልጆች የትምህርት ገበታ ላይ ባይቀመጡም እድሜያቸው ከፍ ያለ በመሆኑ አካባቢያቸውን በአግባቡ የተገነዘቡ በመሆናቸው በትምህርቱ ላይ የሚፈጠርባቸው ጫና የጎላ አይሆንም።
እነዚህን ተረጂዎች የመምረጥና በኮታው መሰረት የማቅረቡን ስራ የሚሰራው የከተማው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ነው። ይህም ሆኖ ከቢሮው ጋር ባለው ስምምነት መሰረት የድርጅቱና የቢሮው ማህበራዊ ባለሙያዎች ያለውን ነገር በአንድነት በመሄድ ያያሉ። እናም የድህነት ሁኔታ፤ የቤተሰብ ሁኔታ (አጋዥ አለመኖር) እና የመሳሰሉት የሚታዩ ሲሆን ሁለት ተመሳሳይ የችግር ደረጃ ላይ ያሉ ሴትና ወንድ ተገኝተው ባለው ኮታ መሰረት መውሰድ የሚቻለው አንድ ከሆነ ሴቷ ትመረጣለች። በተመሳሳይ የአካል ጉዳት ላለበትም ቅድሚያ ይሰጣል።
ተቋሙ ስራ ከጀመረ አስራ ስድስት አመት የሆነው ሲሆን በመጀመሪያ ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ብር የሚሰጣቸው 400 ተደጋፊዎች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል በንግድ ስራም በትምህርትም ራሳቸውን የቻሉ አሉ። ነገር ግን ከግዜ በኋላ ገንዘቡ በቂ ስለማይሆንና መሰረታዊ የቤተሰብን ችግር የሚፈታ ባለመሆኑ ቁጥሩን ቀንሶ ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል በማስፈለጉ በአድዋ ላለፉት ሰባት አመታት 135 ተጠቃሚዎች ብቻ እንዲኖሩ ተደርጎ ላለፉት አራት አመታት ደግሞ ተመርቀው የሄዱም በመኖራቸው አሁን ያሉት 124 ብቻ ናቸው።
ድርጅቱ ዋና አላማው ቤተሰቡን እየደገፈ ለማኖር ሳይሆን አብቅቶ የራሳቸውን ህይወት ለማስቀጠል ቢሆንም በህብረተሰቡ በኩል ከፍተኛ የዘላቂ ተረጂነት ስሜት ይስተዋላል። የተገኘውን በመቆጠብና አማራጭ በመፈለግ በኩልም ክፍተት አለ ተማሪዎቹም ቢሆኑ ራሳቸውን ችለው ቤተሰባቸውን ለመታደግ በትምህርታቸው ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል በዚህ መሰረት ከሁለት ግዜ በላይ የወደቁት ይሰናበታሉ በዚህ በኩል እስካሁን ሰባት ልጆች ተሰናብተዋል።መንግስት የሚፈለገውን ድጋፍ እያደረገልን ይገኛል ያሉት ኃላፊው ነገር ግን ተረጂዎችን ከተረጂነት መንፈስ ለማላቀቅ ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ሙሉ መዋቅሩን ተጠቅሞ የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅበትም ያሳስባሉ።
«ድርጅቱ በከተማዋ ችግር ያለባቸውን ቤተሰቦች በመደገፉ እኛንም ህብረተሰቡንም ተጠቃሚ እያደረገ ነው» የሚሉት ደግሞ በአድዋ ከተማ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክላይ ፍስሀዪ ናቸው። እንደ አቶ ተክላይ ማብራሪያ የአድዋ ከተማ የተለያዩ የገጠር ወረዳዎች የያዘች ስትሆን ከእነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ ፍልሰት አለ ከሚመጡት መካከል ደግሞ ያለ እድሜ አርግዘው የወለዱትን ልጅ ጥለው የሚጠፉ አሉ። አንዳንዶችም ትምህርት ሳይጀምሩ እድሜያቸው ያለፈ በመሆኑ ከተማ ሲመጡ እነሱን በመደበኛ ትምህርት የሚያስተናግድ አይገኝም።ይሄ ድርጅት ባይኖር እነዚህ ልጆች የሚጠብቃቸው ጎዳና ነበር ያ ደግሞ ለከተማዋ አስተዳደርም ለማህበረሰቡም ችግር ነው። የእነዚህ ልጆች ጥበቃ አለማግኘት ደግሞ ችግሩ ማህበራዊ በመሆኑ ህብረተሰቡንም መንግስትንም የሚመለከት ነው። በዚህ ረገድ ዋይድ ሆራይዘን ፎር ችልድረንስ አድዋ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸውን ልጆች በመደገፍ ሊደርስባቸው ከሚችለው ችግር እየታደጋቸው ይገኛል። ድጋፉ ደግሞ በቤተሰብ ወይንም በአሳዳጊ በኩል የሚደረግ በመሆኑ የሚሰጠው ጥቅም ለመላው ቤተሰብ ሲሆን ድጋፉን ለማግኘት ሁሉም መኖር ስላለባቸው ቤተሰብን ተፋቅሮና ተሳስቦ እንዲኖር የሚያስችል ነው። በተለይ ቤተሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው በድጋፍ የማቋቋም ስራ እንደከተማ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉትና አቅም ቢኖር በመንግስት ሊሰራ የሚገባው እንደሆነም ይገልጻሉ።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ