የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ ይታወቃል፡፡ መንግስት ይህ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የግብርና ግብአቶችን በማቅረብ፣ ባለሙያዎችንና አርሶ አደሮችን በማሰልጠን፣ በዘርፉ ለሚደረጉ ምርምሮች ድጋፍ በማድረግ ፣ወዘተ. እየሰራ ነው፡፡
የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ይህ ድጋፍ እንዳለ አምነው፣ አነስተኛ አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነታቸውን ይበልጥ ማሳደግ የሚያስችላቸው የፋይናንስ ድጋፍ እንደሌለ ይጠቁማሉ፡፡ እንዲያውም ሀገሪቱን ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የፋይናንስ ድጋፍ የማይደረግባት ብቸኛ ሀገር ብለውም ይጠሯታል፡፡ ባንኮች በግብርና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ እንጂ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ፋይናንስ እንደማያቀርቡም ያመለክታሉ፡፡
ያነጋገርናቸው አንዳንድ የባንክ ባለሙያዎች እንዳሉት፤ የፋይንናስ ድጋፍ ለማቅረብ በአርሶ አደሮች ዘንድ ተግዳሮቶች ይስተዋላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የእርሻ ሥራ የዝናብ ጥገኛ ነው፤ ዝናብ ከጠፋ ምርቱም ይጠፋል፡፡ ግብርና ከሌላው የበለጠ ለችግር የተጋለጠ ነው፡፡ እንደ አንበጣ መንጋ አይነት የሰብል ተባዮችና ወረርሽኞች ሰብል ያወድማሉ፡፡
ባንኮች የሚያበድሩት የህዝብ ገንዘብ መሆኑን ባለሙያዎቹ ጠቅሰው፣ ብድሩ ሲሰጥ እንደሚመለስ ማረጋገጥ የግድ መሆኑን ይገልጻሉ›› ያሉት ኃላፊዎቹ፣ ኋላ ቀር አስተራረስና አመራረት እንዲሁም ያልዘመነ አሰራር የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡
የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር የብድር ትንተና እና ፖርትፎሊዮ አስተዳደር ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ቶሌራ እንደሚሉት፤ አርሶ አደሮች ብድር ለማግኘት ባንክ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ በተበጣ ጠሰ መሬት የሚገለገሉ፣ ዋስትና ማቅረብ የማይችሉና የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው ናቸው፡፡
ብድር መጠየቅ ቀርቶ የተወሰነ ገንዘብ በባንክ የማስቀመጡ ልምዳቸውም አልዳበረም ሲሉም አቶ ደሳለኝ ይገልጻሉ፡፡ ለልዩ ልዩ ኢኮኖሚዎች የተሰጡ የብድር አይነቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ለእዚህም ከ50 ቢሊዮን በላይ መያዙን ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ የግብርናው ብድር 100 ሚሊየን ብር ሊሆን እንደሚችል አመልክተው፣ ይህም በጣም ትንሽ የሚባል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
አቶ ደሳለኝ ለአንዳንድ ኮሜርሻል አካባቢዎች የብድር አቅርቦት የሚሰጥበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቅሳሉ፡፡ ሁመራ፣ ወለጋ ጉቲ የሚባል አካባቢ፣ ጅማ የቡና እርሻና ተክል አምራቾች ለቦታቸው ካርታ እንዳላቸው ተናግረው፣ ይህ እየተመዘገበ ብድር እየወሰዱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ለቅባት እህሎችና ገበያ ተኮር ሰብሎች በቆሎ፣ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ አምራቾች ብድር እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግም ወደ መቂ አካባቢ ፍራፍሬ እና አታክልቶች ተቀናጅተው የሚሠሩ ብድር እንደሚወሰዱ ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ፤ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን እንዲጠቀሙ መንግሥት ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ወደ አርሲ፣ ባሌ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች እንደ ኮምባይነር ያሉ መሣሪያዎችን ለመግዛት ጠይቀዋል፡፡ ለኮምባይነር ግዢ እና ሌላም የግብርና መሣሪያ ለሚገዛ ሰው ብድር እንሰጣለን፡፡ ይህን የሚያደርጉት ግን በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
ተንቀሳቃሽ ንብረት እንደ በሬ፣ ግመል ወዘተ… ሊሆን ይችላል በመያዣነት አያያዙ ባንኮች ብድር የሚሰጡበት አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን ጠቅሰው፣ ‹‹ከተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና ምዝገባ ጋር ተያይዞ የሚወጣውን ፖሊሲያችንን በዚያው መሠረት ለማሻሻል ተቀብለን ለመስራት ዝግጁ ነን፡፡›› ይላሉ፡፡
አቶ ደሳለኝ እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ ይዞታውን አሲይዞ ብድር የሚወስድ ከሆነ የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሊኖር ይገባል፡፡ አርሶ አደሩ ይህን እንዲያደርግ ግንዛቤውን ማዳበር ይገባል፡፡ ስለምርቶቻቸውም መረጃዎች ሊኖሯቸው ያስፈልጋል፡፡ ይህም ባንኮች ብድር ለመስጠት አቅም እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር የብድር ትንተና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ ሰምዬ “እርሻ ለችግር የተጋለጠ ስለሆነና የመድን ሽፋንም ስለሌለው ብዙ ባንኮች ደፍረው አይገቡበትም፡፡›› ይላሉ፡፡ አርሶ አደሮቹ ለዋስትና የሚበቃ ነገር እንደሌላቸውም ያመለክታሉ፡፡
እንዲያም ሆኖ ንብ ባንክ ለአርሶ አደሩ ብድር የሚያቀርባበቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ “የሰብል ምርት የሚያመርቱ ደንበኞች ወለጋ፣ ጎንደር መተማ አካባቢ በመኬናይዝድ እና በባህላዊ እርሻ የሚጠቀሙ ደንበኞች ብድር ሰጥተን ምርታቸውን የሚያሳድጉበትን ነገር አመቻችተናል፡፡ አንዳንዶቹ ራሳቸውን አብቅተው የወሰዱትን ብድር መልሰዋል፤ በተደጋጋሚ ብድር እየወሰዱ ራሳቸውን እያሳደጉ ያሉም አሉ፡፡” ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
እንደ አቶ ዓለሙ ገለጻ፤ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ጎንደር አካባቢ ለሰብል አምራቾችም ሆነ ለእንስሳት አድላቢ ደንበኞች ብድር እየሰጠ ጥራት ያላቸው ከብቶችንና ሥጋ ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ አድርጓል፤ በዚህም ለውጥ ያሳዩ አሉ ፡፡ በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማሩ ገበሬዎችን በገንዘብ ብድር እየደገፈ ይገኛል፡፡ በቢሾፍቱም ዶሮ አርቢዎች በተደጋጋሚ ብድር ወስደዋል፤ በዚሁ ከተማ አትክልትና ፍራፍሬ አምርተው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ እንዲሁም በወተት ላሞች እርባታ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችም የባንኩ ብድር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የቅባት እህሎችን እንዲሁም ጥጥ የሚያለሙ አርሶ አደሮችም የድጋፉ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ባንኩ በራሱ 50 በመቶ ችግር ተጋርቶ ቀሪውን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ኮርፖሬሽን (IFC) ጋር ስምምነት በመፈፀም ለአርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አቶ ዓለሙ ይጠቅሳሉ፡፡ በእዚህም አርሶ አደሮቹ ምርታቸውን ያሳደጉበትና ለላኪነት የበቁበት ሁኔታ እንዳለም ያብራራሉ፡፡ የኤክስፖርታቸው እያደገ መምጣትን ተመልክተው ሌሎች ባንኮች አርሶ አደሮችንና ኅብረት ሥራ ማኅበራቸውን ለመደገፍ ፍላጎት እያሳደሩ መምጣታቸውን ይጠቁማሉ፡፡
«ወደ ሊሙ፣ ጅማ፣ ቦንጋ፣ ዲላ፣ ይርጋጨፌ፣ አለታወንዶ የሚገኙ ቡና አብቃይ ገበሬዎች ማንም ብድር በማይሰጣቸው ጊዜ አበድረናል፡፡›› ያሉት አቶ ዓለሙ፣ የብድር አገልግሎቱን መስጠት የተጀመረው ከ10 ዓመት ወዲህ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ባንኩ ከቡና ማምረት ተነስተው ባለቡና ማጠቢያ ማሽን የሆኑና ምርታቸውን ለገበያ የሚያቀርቡ ብዙ ደንበኞች እንዳሉትም ነው ያመለከቱት፡፡
በባንክ ባለሙያዎቹ መረዳት እንዳሉት አርሶ አደሩን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በይዞታ ማረጋገጫ፣ በግብርና ማዘመን፣ በቁጠባ ፋይዳ ወዘተ ላይ ማዘጋጀት ይገባል፡፡ እንደ በሬ፣ ግመል፣ እና የመሳሰሉትን ተንቀሳቃሽ ሀብታቸውን አስይዘው መበደር እንዲችሉ በመንግስት የወጣው አዋጅ መሬት ላይ እንዲያርፍ መንግስትም ባንኮችም አጥብቀው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ