የልዕለ ኃያሏ አገር መሪ ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት የ36 ሰዓታት በረራ በማድረግ የህንድን ምድር ሲረግጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ተጨንቀውና ተጠበው ባዘጋጁት አስደማሚ የአቀባበል ስነስርአት በፍቅርና በስስት ተቀብለዋቸዋል፡፡ የኒውዴህሊው መንግስት አዲስ ያስገነባውና ከመቶ ሺህ በላይ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው የአለማችን ትልቁ የክሪኬት ስታዲየም በዶናልድ ትራምፕ እንዲመረቅም ተደርጓል፡፡ በዚህ የምረቃ ዝግጅትም የአገሬው ህዝብ ስታዲየሙን ከአፍ እስከገደፉ በመሙላት ለእንግዳው ድጋፉንና ክብሩን አሳይቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም በተደረገላቸው አቀባበል በእጅጉ መደሰታቸው በግልፅ ተስተውሏል፡፡ሁለቱ መሪዎች በፍፁም ደስታ በተደጋጋሚ ሲተቃቀፉና አንዳቸው አንዳቸውን ሲያሞካሹ ታይተዋል፤ተደምጠዋል፡፡በተለይ ትራምፕ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲን‹‹በሁሉም የሚወደድ ጠንካራ ፤አንድን ነገር ለማሳካት ምንም የማይሳነው››ሲሉ አድንቀዋቸዋል::
የትራምፕ ጉብኝት ህንድ በተለይ በኢኮኖሚ መንገጫገጭና በስራ አጥነት ክፉኛ በተፈተነች ወቅት መሆኑም ከቤት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚነሱ የህዝብ ምሬቶችን ለመቀልበስ ከማገዝ ባሻገር ከልዕለ ኃያሏ አገር መሪ ጋር የመሰረቱት ወዳጅነትም አለም አቀፍ ገፅታቸውን እንደሚያጎላው በርካቶችን አስማምቷል፡፡
በርካታ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ሊሂቃንም የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት በመመልከት ‹‹ከመሪዎች በፍቅር መክነፍ ጀርባ ምን ምክንያት ይኖራል›› የሚል ጥያቄን በማንሳት ሰፊ ትንታኔ በማስፈር ላይ ተጠምደዋል፡፡
ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጠናከርና ለመሪዎቹ መቀራረብ ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከልም የንግድ አጋርነት ቀዳሚው ነው፡፡ በእርግጥ አሜሪካ የሕንድ ጥብቅ የንግድ አጋር ናት። አመታዊ የንግድ ልውውጣቸው 160 ቢሊየን ዶላር ስለመድረሱ ይገለፃል፡፡ ይሁንና የሁለቱ አገራት አጋርነት በልዩነት ውስጥ የሚዳክር በተለይም የታሪፍ ጉዳይ የሚያስጨንቀው ከሆነ ቆይቷል:: ትራምፕም ቢሆኑ ‹‹የቻይናን ያህል ባይሆንም ህንድ አላግባብ እየተጠቀመችብን ነው::›› ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡
የምርጫ ጉዳይም ሁለቱን አገራት ያስተሳሰረ ሌላው ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በተለይ ትራምፕ ዳግም ተጨማሪ አራት አመታት በነጩ ቤተ መንግስት ለመቆየት ደፋ ቀና በማለት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ኒውደህሊ የመገኘታቸው ምክንያትም ‹‹ከሪፐብሊካን ይልቅ ለዲሞክራቶች ድምፃቸውን በመስጠት የሚታወቁና በአሜሪካ የሚገኙ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ህንዳውያንን ቀልብ ለመሳብ ነው፡፡›› ተብሏል፡፡
ለመሪዎቹ ፍቅር መጦዝ ዋነኛው ምክንያት ቻይና መሆኗም በርካቶችን አስማምቷል:: በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጆን ኤቼቭሪ ጄንትን ጨምሮ በርካቶች እንደሚያስረዱትም፤ በአሁኑ ወቅት ቻይና ለሁለቱም አገራት ዋነኛ ተቀናቃኝ ናት፡፡ የቻይና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት እየጎለበተ መምጣት በተለይ ለዋሽንግተን መንግስት ከባድ ራስ ምታት ነው፡፡
ህንድም ብትሆን ለቻይና ያላት ምልከታ የአሜሪካን ያህልም ባይሆን የተንሸዋረረ ነው፡፡ እንደ ዋሽንግተን ሁሉ ህንድም ቤልት ኤንድ ሮድ የተሰኘውና አገራትን በመንገድና መሰረት ልማት ከቻይና ጋር ለማስተሳሰር የተጀመረው ፕሮጀክት የሆነ ቦታ እንዲቆም ትሻለች፡፡ የሕንድ ስጋት ኢኮኖሚያዊ ብቻም አይደለም፡፡
ፕሮፌሰር ጆን እንደሚያስረዱት፤ ቻይና በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ የምታደርገው መስፋፋት ለኒው ዴሊሁ መንግስት አይመቸውም:: በእርግጥም ህንድ ከቻይና ጋር በሰሜን ምስራቅ ድንበር አካባቢ ከባድ ፍጥጫ ውስጥ ትገኛለች:: ይሁንና በፓስፊክ ምድር ከቻይና ጋር ጦር የመግጠም ፍላጎት የላትም::
ከሁሉ በላይ ግን በጎረቤቷ ቻይና የወዳጅነት ትኩረት መነፈጓ ያንገበግባታል፡፡ ከአሜሪካ ጋር የመሰረተችው ወዳጅነት ጥብቅ ሆኖ መታየቱ ታዲያ ቻይና ሳይውል ሳያድር ንቀቷን በመተው የሚገባኝን ክብር በመስጠት እጇን እንድትዘረጋና ያስገድዳታል የሚል እምነት አላት፡፡ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ ይሕ የፖለቲካ ቀመር ህንድ በአሜሪካ ፍቅር ስር እንድትሆን ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡
ሌላኛው የሁለቱ አገራት በፍቅር መውደቅ የጦር መሣሪያ ግዥ መሆኑም ይነገራል፡፡ የሳዑዲ አረቢያን ያህልም ባይሆን ህንድም የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ሸማች ናት፡፡ የትራምፕ ጉብኝት ማብቂያም በቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ስምምነት የታሰረ መሆኑም ይሕን ያጠናክረዋል፡፡
ይሕ ስምምነት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለሕንድ የጦር መሣሪያ የምታቀርበውን ሩሲያ ዳር የሚያስይዝ መሆኑ ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ከሞዲ ጋር በፍቅር በመውደቅ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ስለመምታታቸው ማረጋገጫን ይሰጣል፡፡
የኒውስ ዊክ ዴቪድ ብረናን በበኩሉ፤ ሁለቱ አገራት ወዳጅነት ፍቅር ላይ መሆናቸው ባይካድም ለወቅታዊ ችግሮቻቸው ተጨባጭ የመፍትሄ እቅድ ማሳየትና በወሳኝ ጉዳዮች ላይ አሁንም ልዩነቶቻቸውን መፍታት እንዳልሆነላቸው አብራርቷል፡፡
ይሕን ሃሳብ የሚጋሩት በአትላንቲክ ካውንስል የደቡብ እስያ ማእከል ዳይሬክተር ኢርፋን ኑረዲን፣ ‹‹ጉብኝቱ በበርካታ ያልተጨበጡ ጉዳዮች የተቋጨ ነው፣ ሁለቱ መሪዎች ቻይና ዋነኛ ፈተናቸው መሆኗን ቢስማሙም ፈተናቸውን እንዴት በተጠና እቅድ መሻገር እንዳለባቸው በተጨባጭ ማስመልከት አልቻሉም››ብለዋል፡፡
በንግድ ግንኙነቱም ቢሆን ልዩነታቸው ጠባብ አይደለም፡፡ በዚህ ጉብኝትም ምንም እንኳን መሪዎቹ በፍቅር ከንፈው በአደባበይ ቢታዩም በሁለቱ የአለማችን ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ ዘዋሪዎች መካከል ለአመታት ሲጠበቅ የነበረው የንግድ አጋር ስምምነት መቋጫ አላገኘም፡፡
ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ የሚል እሳቤ አራማጆቹ ሁለቱ መሪዎችም ጉዳዩን በሚመለከት ያሳወቁት አንዳች መረጃ የለም፡፡ ይህም ለልዩነታቸው ግልፅ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይሕን ዋቢ የሚያደርገውና መቀመጫውን ለንደን ባደረገው በቻትሃም ሃውስ ስመጥር የጥናት ባለሙያ የሆነው ጋሬዝ ፕራይዝ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ወዳጅነት በተለይ በንግድ አጋርነት ረገድ በተሳሳተ መንገድ እየተመራ ነው ሲል አስረድቷል፡፡
በእርግጥ
ሁለቱ አገራት የንግድ ስምምነት ላይ መግባባትና የመጨረሻ ውሳኔያቸውን ማሳወቅ ሲሳናቸው ይሕ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ሞዲ ባሳለፍነው
አመት አሜሪካን በጎበኙበት ወቅትና በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የአገራቱን የንግድ ውል ፈር ማስይዝ አልቻሉም:: ትራምፕም
ቢሆኑ ከምርጫ ቀድሞ በንግድ ስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይሕ እስከሆነ ደግሞ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ሁለቱ
አገራትና መሪዎቻቸው በአፍላ ፍቅር ቢሰክሩም በወሳኝ አጀንዳዎ ላይ ከመቀራረብ ይልቅ ተራርቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )