ላሌ ላቡኮ ከሁለት ሺ በላይ ህዝብ የማይኖርባት አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው የተወለደው። ላሌ ማለት በተራራ ላይ ብቻ የሚገኝ የተለየ ዛፍ ማለት ነው። መንደሯ መጠሪያ ስሟን ያገኘችው በአቅራቢያዋ ከሚገኘው ካራ ዱዝ ከሚባለው ወንዝ ነው። መንደሯ ኦሞ ወንዝ አጠገብ የምትገኝና ዙሪያዋን በደን የተከበበች ስትሆን በደኑ ውስጥ ከዓመታት በፊት እንደ ዝሆን፤ ጉማሬና መሰል የዱር እንስሳት ማየት የተለመደ ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን የአካባቢው ህብረተሰብም መሳሪያ በመታገዝ እንስሳቶችን በማደኑ፤ በመንደሯ የሚገኘው የከብት ቁጥርም በመጨመሩ፤ ይህንንም ተከትሎ ለግጦሽ ማስፋፊያ ሲባል አካባቢው በመመንጠሩና የደን ሽፋኑ እየቀነሰ በመምጣቱ የዱር እንስሳቱ ቁጥር ተመናምኗል ።
የኦሞ ቻይልድ ግብረ ሰናይ ድርጅት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ላሌ ዘጠኝ ዓመት እስኪሞላው የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በእረኝነት ነው። በእነሱ መንደርም ሆነ በአጎራባች መንደሮች ልብስ አይታወቅም። አዋቂ ወንዶች በከፊል የሚለብሱ ሲሆን ሴቶች ከፊት ለፊታቸው ብቻ ትንሽ እራፊ ጨርቅ አልያም ቆዳ ብቻ ነበር የሚያገለድሙት። ልጆች ደግሞ ምን አልባት ለመኝታ ከቆዳ የተዘጋጀ እንደ ብርድ ልብስ የሚገለገሉበትን ከመልበስ ውጭ ሁሌም ራቁታቸውን ነው የሚውሉት። ላሌም የስድስት ዓመት ልጅ እያለ የቤተሰቡ ከብቶች ያድሩበት የነበረው ራቅ ያለ ጫካ እየሄደ ከአባቱ ጋር ከብቶችን እየጠበቀ ያድራል። በአካባቢው እንደ ቆርኪ ያሉትን የዱር እንስሳት በጦርና በቀስት ማደን የተለመደ ቢሆንም የላሌ አባት መሳሪያ ስለነበራቸው ይዘውት ሄደው እሳቸው በጥይት ትልልቆቹን ሲያድኑ እሱም በዱላ በመታገዝ ግልግሎቹን ይይዛል።
የላሌ የልጅነት ዘመን ግን በጀመረው መስመር አልቀጠለም። አንድ ቀን የእሱንም፤ የቤተሰቡንም ከዛም አልፎ የብዙዎችን ሰቆቃ የሚታደግበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ላሌ አጋጣሚውን እንዲህ ያስታውሰዋል «በአካባቢው ትምህርት ቤት አልነበረም፤ ወደ አካባቢው ለመጀመሪያ ግዜ የመጡት የስዊድን ሚስዮናውያን ነበሩ። ፈረንጅ ልጆችን ይዞ ይጠፋል ተብሎ ስለሚፈራ የአካባቢያችን ሰው ልጆቹን ትምህርት ቤት አይልክም። አባቴ ነገሮችን እንዴት እንደተረዳ ባላውቅም እኔ ትምህርት ቤት እንድሄድ ፈቀደ። እናም ከትውልድ መንደሬ ስልሳ ኪሎ ሜትር ርቀት በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ ወዳለች ትውሽ ወደ ምትባል አንድ መንደር በማቅናት ትምህርት ቤት ገባሁ። መንገዱ ረጅም ስለነበር ወደ ቤተሰብ የምመጣው በየሶስት ወሩ ነው። በዚያ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤትም በስንዴ መቋጠሪያ ማዳበሪያ ላይ እየተኛሁ፤ ቁርስም፣ ምሳና ራትም የስንዴ ንፍሮ እየበላሁ ከአንድኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ተማርኩ። አጠቃላይ የነበርነው ተማሪዎች ከስልሳ አንበልጥም። ከዚሁም በተለያዩ ምክንያቶች የሚያቋርጡ ነበሩ እኔ ግን ትምህርቴን ቀጠልኩ» ይላል ላሌ።
ላሌ ከትምህርት ህይወቱ ባለፈ ዛሬ ድረስ ዓለም አቀፍ እውቅናን እንዲቸረው ያደረገውን አጋጣሚ ደግሞ እንዲህ ያስታውሰዋል። «የአስራ አምስት ዓመት ልጅ እያለሁ እንደተለመደው ሶስት ወሬን ጠብቄ የቤተሰቤን ናፍቆት ለመወጣት ወደ ትውልድ መንደሬ አቀናሁ። እዛም እያለሁ አንድ ጠዋት ሰፈር ውስጥ በእግሬ ስንሸራሸረ አንድ የሚያስደነግጠኝ አጋጣሚ ተፈጠረ። አምስት የሚደርሱ የሰፈሩ ሽማግሌዎች ከአንዲት እናት ላይ ያቀፈችውን ልጅ በጉልበት ይነጥቋታል። ልጇን የምትነጠቀው እናት ለቅሶና ሰቆቃ ደግሞ እኔን እግሬን ከእርምጃ ገትቶ ትኩረቴን እነሱ ላይ እንዳደርግ ያስገድደኛና ነገሩን መከታተል እጀምራለሁ። ሽማግሌዎቹ ህጻኑን ይዘው ሚንጊ ሚንጊ እያሉ መሮጥ ይጀምራሉ። እናትም ልጇን ለማዳን እያነባች ትከተላለች። እኔ ደግሞ የሚሆነውን ለማየት ተደብቄ ሁሉንም እከተላቸዋለሁ። በመጨረሻ ተደብቄ እያየኋቸው ሽማግሌዎቹ ጫካ ውስጥ በመግባት ያንጠለጠሉትን ህጻን ወንዝ ውስጥ ይጨምሩታል። እናትየዋንም፣ ህጻኑንም አላውቃቸውም። ነገር ግን የተፈጠረው ነገር ክፉኛ ስላሳዘነኝ በተደበቅኩበት ሆኜ አለቅሳለሁ። ወዲያውኑም ለምን ስል ራሴን ብጠይቅም መልስ ማግኘት ስላልቻልኩ አእምሮዬ ቢያርፍ ብዬ ወደ ቤት በመመለስ ጥያቄውን ለእናቴ አቀረብኩላት። እናቴ ጥያቄዬን ለመመለስ ፈርታ ዝም አለችኝ። ነገሩ በጣም ስላሳዘነኝ እናቴ መልሱን ካልሰጠቸኝ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ በዛው እንደምጠፋ ነገርኳት። እናቴም ነገሩን ለማንም እንደማላወራ ቃል ካስገባችኝና ካስጠነቀቀችኝ በኋላ በአካባቢው ያለውንና የብዙ ህጻናትን ህይወት እየቀጠፈ የኖረውን ጎጂ ባህል ከስር መሰረቱ እንዲህ ስትል ተረከችልኝ።»
በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚገኙት አስራ ስድስት ብሄር ብሄረሰቦች መካከል በካራ፤ ሀመርና በና ብሄረሰቦች ሚንጊ የሚባል ባህል አለ። በዚህ ባህል መሰረት ህጻናት ጥርስ ማብቀል ያለባቸው ከስር ነው ተብሎ ይታመናል። ስለዚህም አንድ ህጻን ዘጠኝ ወር ሳይሆነው ቀድሞ በላይኛ ድዱ ጥርስ ካበቀለ ወይንም እስከ ሰባት ዓመቱ ወድቆም ቢሆን የላይኛው ጥርሱ ከተሰበረና ከወለቀ ሚንጊ ይባላል። ያገባች ሴትም ነገሮች በባህሉ መሰረት ቡናና ማር ተይዞ ምርቃ ሳይከናወን ብታረግዝ ሚንጊ ይባላል። አንዲት ሴት ልጃገረድ ሆናም ሳታገባ ካረገዘች ሚንጊ ይባላል። እነዚህ ሶስቱ ነገሮች ከተፈጠሩ በህብረተሰቡ ዘንድ በሞት ያስቀጣሉ። ሚንጊ ማለት እርግማን ነው እነዚህ ልጆች ካልተገደሉ ድርቅ ይመጣል፤ ዝናብ ይቆማል፤ በሽታ ይገባል፤ ቸነፈር ይመታናል። በአጠቃላይ ክፉ መንፈስ መጥቶ ህዝብ ያልቃል ብለው ያምናሉ። ስለዚህ ህጻናቱ አንድም ወንዝ ይጨመራሉ፤ አልያም ከገደል ይወረወራሉ፤ ካልሆነም ጫካ ወይም ዋሻ ውስጥ አውሬ እንዲበላቸው ይጣላሉ። ዛሬ ሽማግሌዎቹ ወንዝ ውስጥ የጣሏትም ልጅ እንዲህ ስለሆነች ነው የገደሏት። አንተም ሁለት ታላላቅ እህቶችህን በዚህ ሁኔታ አጥተሃል። ወደፊት ይህ ነገር ካልቆመም ነገ ያንተም ልጆች እጣ ይሄው ነው አለችው።
ላሌ ባየውም፤ በሰማውም ነገር ውስጡ ክፉኛ ቆስሎ ስለነበር እናቱ የነገረችውን ታሪክ ሰምቶ ከመቀበልም ይልቅ ነገሩን ለመጋፈጥ ይወስናል። ከዓመታት በኋላም ትምህርቱን አጠናቆ ወደ መንደሩ ሲመለስ መንጊ በሚል የሚጣሉትን ህጻናት ለማሳደግ ይወስናል። እናት ሀሳቡን ስትሰማ መጀመሪያ ባህል ነው ተው ብላ ተከራክራ ነበር። በኋላ ግን ነገሩን ሲጀምረው ደግሞ እሱና ቤተሰቡ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ስጋት ላይ ጥሏታል። እሱ ግን በነገሩ ቀጥሎበት በይፋ «እኔ ጫካ፤ ወንዝና ገደል ልሁንና ለእኔ ስጡኝ እርግማኑንም እኔ ልውሰድ» ብሎ ሽማግሌዎቹን ይጠይቃል። በእውነትም እናቱ እንደሰጋችው ማህበረሰቡ ነገሩን በቀላል አልተቀበለውም። ይልቁንም ከላሌም ጋር ሆነ ከቤተሰቡ ጋር ቡና ላለመጠጣት በመወሰን «ቤተሰቡን ሚንጊ ነው ከእነሱ ጋር የበላና የጠጣ ይረገማል፣ ይሞተል» በማለት ማግለል ይጀምራሉ። በዚህም አላቆሙ ከመንደሯና ከአካባቢው ለማባረር አስበው የአባቱን ቤትና ሙሉ ንብረት ለማውደምም ይዘጋጃሉ፤ ይነጋገራሉ ነገር ግን ሁሉም ሳይሳካላቸው ይቀራል።
ላሌ በውሳኔው በመጽናት ስራውን ይቀጥላል። ነገር ግን ሀሳቡን የሚቀበልና የሚስማማ በመጥፋቱ እሱ በግሉ ህጻናቱ ሊገደሉ የሚል ወሬ ሲሰማ ቢሮጥም የሚደርሰው ልጆቹ ከተገደሉ በኋላ ነው። እናም አንድ ልጅ ለማዳን አንድ ዓመት ይወስድበታል። በዚህ ጊዜ ቤተሰብን ከመምከርና በግልም ከመሮጥ ባለፈ ሌላ ነገር መስራት እንዳለበት ይገነዘብና ፕሮጀክት ቀርጾ መንቀሳቀስ ይጀምራል። በፕሮጀክቱም የተስፋ ጭላንጭልን ይዞለት መጣ። ሆኖም ህጻናቱን ከሞት ይታደግልኛል ብሎ የቀረጸው ፕሮጀክት ስድስት ልጆችን ከሞት ካተረፈ በኋላ እንዲህ ማድረግ አትችልም» በማለት በተጠናከረ መልኩ ይከለክሉታል። በዚህ ወቅትም በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ አስራ አንድ ልጆች ሚንጊ ተብለው እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል። በሌላ በኩል ለእሱ ድጋፋቸውን የሚሰጡት ወጣቶች ቁጥር ደግሞ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ስለነበር እነሱ ላይ ትኩረቱን አድርጎ መስራቱን ይቀጥላል። ወጣቶቹ መንጊ ተብለው የሚገደሉትን ህጻናት መሰብሰባቸው ከታወቀ እርምጃ ሊወሰድባቸው ስለሚችል ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ በድብቅ እስከ ንጋት ነበር የሚሰበሰቡት። ነገሩን ለመቃወም የሚንቀሳቀሱትም ጥቃት ይፈጸምባቸው ነበር። በአንድ ወቅት አንዲት ህጻን ልጅ ለውሻ ተወርውራ ልትበላ ስትል ደርሰው ሊያነሷት ሲሞክሩ ለምን በሚል ወጣቶቹ ላይ ጥይት ተተኩሶባቸዋል።
ሚንጊ ላለፉት አንድ ሺ ዓመታትም የተተገበረና የማህበረሰቡንም ቁጥር ያመናመነ ሲሆን በየወቅቱ በዚህ ያልተስማሙት ከአካባቢው እንዲፈናቀሉም ሲደረግ ቆይቷል። በአንጻሩ ሀይሉ የሚባል የራሱን ልጅና መሳሪያ ይዞ ጫካ በመግባት ላሌ መቶ ያድነኝ ብሎ ልጁንም እሱንም ለመታደግ በቅቷል። የእኔም አያት በጉልበት አንድ ልጃቸውን አሳድገዋል። ስለዚህ ከጠነክርን ማስቆም እንችላለን የሚል አቋም ነበረው። ከጃኬቱ በፊት ሸሚዙ አይወልቅም የሚል ብሂል ያለው ላሌ ችግሩን ለማለፍ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅበት ያምናል። የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ደግሞ እሱ በባህሉ መሰረት በወግ በማዕረግ ያላገባ በመሆኑና የአገር ሽማግሌዎችን ለማናገር ስለማይፈቀድለት አባቱን በማሳመን እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ ለመጠቀም ይነሳል። ይህም ይሳካለትና የአባቱን ጨርሶ ወደ አካባቢው ወጣቶች ያተኩራል። ይህም ውጤታማ ይሆናል በመጀመሪያም ወደ ሽማግሌዎች ሲሄድ በብዛት ሳይሆን በትንሹ እየነጠለ ማናገር ይጀምራል። «በአንዴ ሳናግራቸው ተቃውሞ ያነሳሉ በዛ ላይ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ባህሪ አለው። መሳሪያ ይዘው እንገላለን የሚሉም ነበሩ፤ አልተሳካላቸውም እንጂ ብሏል።
ከዓመታት በኋላ አራት ህጻናትን ይዥ ወደ መንደሬ ስመለስ ነዋሪው የተወረወሩት ህጻናት በህይወት የሚኖሩ ስለማይመስላቸው «የላሌ ልጆች» መጡ እያሉ ይጮሁ ነበር። ሊወልዱ የደረሱ እናቶች ደግሞ ልጆቻቸውን እንዲያድንላቸው ይለምኑታል። ሚሽነሪ ትምህርት ቤት እስከ ሶስተኛ ክፍል ከእሱ ጋር የተማረ ጓደኛው ልጁ ልጃገረድ እርጉዝ ሆና በመገኘቷ ምክንያት ልጇ እንዲገደል በማድረጉ ይጸጸት እንደነበር ላሌ ያስታውሳል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ላሌን ትንሳኤ የምትባለው ህጻን ታሪክ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አድርጎታል። ትንሳኤ በካራ ማህበረሰብ በቆርጮ አካባቢ ነው የተወለደችው። እናቷ ያላገባች ልጃገረድ ሆና በማርገዟ ሚንጊ ተብላለች። ያን ጊዜ ደግሞ እነ ላሌ ከአስራ ስድስት በላይ ልጆችን ከሞት ታድገው ስለነበር ግንዛቤው እየተፈጠረ ነበር። በህግ በኩልም መንግስት እርምጃ መውሰድ የጀመረ በመሆኑ በፊት ለፊት ልጆቹን ወንዝ ጫካ፤ አልያም ገደል ወስዶ የሚገድል ባይኖርም ስልት በመቀየር ምግብ በመከልከል መግደል ጀምረዋል። እናም ትንሳኤ ስትጣልም የእነ ላሌ አባል የነበረ አንድ ወጣት ያነሳታል። ይህን ያዩ የአካባቢው ሰዎችም ህጻኗን ምንም ምግብና ውሃ እንዳይሰጣት ያስጠነቅቁታል። ልጁም ፊት ለፊት ህዝቡ መሳሪያ ይዞ ስለሚጠብቀው እየተደበቀ ለሁለት ሳምንት በውሃ ብቻ ያቆያታል። ከዚህ በኋላ መንግስት ይደርስና እነላሌ እንዲወስዷት ያዛል። እነ ላሌም በምግብ እጦት የተጎዳችውን ህጻን ጅንካ ሆስፒታል ይወስዷታል። ህይወቷ ሲተርፍ ትንሳኤ የሚል ስም አወጡላት።
ለ12 ዓመታት ጥረትና ትምህርት በኋላ ዛሬ በካራ ሚንጊ የሚባለው ጎጂ ልማድ ሙሉ ለሙሉ ቀርቷል። በሀመር እስከ ሰባ በመቶ ቀንሷል ። ቀደም ሲል በዓመት ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ህጻናት ይገደላሉ። ዛሬም ሀመር ውስጥ ሚንጊ በሚል የሚገዱ ህጻናት አሉ። ሆኖም በዓመት ከ20 እና ከ30 አይበልጡም ሲል ለውጥ መኖሩን አሳይቷል።
የሚገደሉ ህጻናትን መሰብሰብና ማሳደግ ከጀመርኩ በመጀመሪያ አምስት ዓመታት ልጆቼ ብሎ መጥቶ የጠየቀ ወላጅ አልነበረም፤ በክረምት ትምህርት ሲጨርሱ ቤተሰብ ሄደው እንዲጠይቁ ይደረጋል። አንዳንድ ቤተሰቦች ፍየል አርዶ ደግሶ ልጆቹን ይቀበላል። ልጆቹ ግን አባታቸውም፤ እናታቸውም ላሌ እንደሆነ ነው የሚረዱት።
ላሌ ልጆቹ ነጻነታቸውን እንዲያገኙ በማሰብ አድገው ተምረው ራሳቸውን ሲችሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማስታረቅ ስራ ይሰራል። ለዚህም ልጆቹ ቤተሰብ አውቆ ፈቅዶ ሳይሆን ማህበረሰቡ የተጫነበት ባህል አስገድዷቸው የሚያደርጉት መሆኑን በመግለጽ ቤተሰባቸውን ሳይሆን ባህሉን መቀየር እንዳለባቸውና እንደሚችሉም ይነግራቸዋል።
ላሌ ይሄን ስራ ከባለቤቱ ጋር አንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ቤቱ የጀመረው የግል እርዳታ ድርጅት ፈቃድ እስኪያገኝ ድረስ ልጆቹ ያደጉት እሱ ጋር ነበር። እስከ ቅርብ ጊዜም ሀምሳ ልጆችን በቤት ኪራይ ሲያሳድግ ቆይቷል። አሁን ከደቡብ ኦሞ ዞን መንግስት በስጠው ቦታ ላይ የህጻናት ማሳደጊያ፣ ትምህርት ቤትና መመገቢያ ቦታ እየገነባ ይገኛል። የኦሞ ቻይልድ ግብረሰናይ ድርጅት ለ26 ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል። ላሌ ልጆቹንም የሚያየው እንደሞቱ እህቶቹ ነው። ላሌ ታናሽ እህትና ወንድሞቹንም በበሽታ አልቀውበታል። እናም ሚንጊ የተባለው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና በሽታ ለእሱ ቀዳሚ ጠላቶቹ ናቸው። በመሆኑም «እኔ የብሄር ወይንም የሀይማኖት ጠላት የለኝም» የሚለው ላሌ ወደ ፊት በበሽታ ለህልፈት የሚዳረጉ ወገኖቹን ለመታደግ ሆስፒታል እንደሚገነባና በጤናውም ዘርፍ ሰፊ ዘመቻ ለማድረግ ማሰቡን ይናገራል። በአሁኑ ጊዜም ላሌ በሀመር፣ ካራናና በና አካባቢዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ለተማሪዎች ያቀርባል፤ የተጎዱ ትምህርት ቤቶች እንዲታደሱ ያደርጋል። ዛሬም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባለመቀረፉ ከመንግስት ጋር በመሆን ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል። በቅርቡም በአካባቢው ትምህርት ቤት ለማቋቋም አስቦ በሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር ግንባታውን የጀመረ ሲሆን አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 12 ሚሊየን ብር እንደሚፈጅም ይናገራል።
ላሌ በመምህርነት ከተመረቀ በኋላ በጀርመን በመንፈሳዊ ትምህርት፤ በአሜሪካ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል። እንዲሁም የናሺናል ጂኦግራፊ፤ ኒዮርክ ሎዋል ቶማስ አዋርድና የዓመቱ በጎ ሰው ተብሎ ለመሸለም የበቃ ሲሆን በእሱ ስራ ላይ የሚያጠነጥነው «ኦሞ ቻይልድ ዘሪቨር ኤንድ ቡሽ» የሚለው ፊልምም በርካታ ሽልማቶችን አስገኝቶለታል። ለዚህ ሁሉ ከፈጣሪ ቀጥሎ መማሬ ጠቅሞኛል የሚለው ላሌ ከምንም በፊት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ጨምሮ የትኛውንም ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ መማር እንደሚገባ ያሳስባል። ለዚህም በተለይ እሱ እንደተወለደበት አካባቢ በርካታ ማህበራዊ ችግሮች ባሉበትና ትምህርት ባልተስፋፋበት አካባቢ መንግስትም ሆነ እርዳታ አድራጊዎች ከሁሉም በፊት ትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ የአቅማቸውን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያሳስባል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 13/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ