ወይዘሮ ቤዛዊት ኑርልኝ በላይ ትባላለች፡፡ ውልደቷና እድገቷ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በትግራይ ክልል አለማጣ ከተማ ነው። መነሻ ምክንያቱን ባታውቀውም የማየት ችሎታዋን ያጣችው ደግሞ ገና በልጅነቷ ነፍስ ሳታውቅ ነው። የልጅነት ጊዜዋን ሳታጣጥም የገጠማት ፈተና ከባድ ቢሆንም ሁሉንም ነገር እንደ አመጣጡ በማስተናገድ ራሷን ለተሻለ ህይወት ለማብቃት ስትጥሩ ኖራለች።
ህይወት ባሰቧት መንገድ አትጓዝም እንዲሉ ከብዙ ዓመታት ፈተናና ጥረት በኋላ ወይዘሮ ቤዛዊት የራሷን ቤተሰብ የመመስረት ዕድሉን ብታገኝም ነገሮች ግን እሷ ባሰበቻቸው መንገድ መቀጠል አልቻሉም። እናም እሷ ስትወለድ ከደረሰባት ችግር ጋር በተያያዘ አባቷ ከቤተሰቡ እንደተነጠሉት ሁሉ ከልጇ አባት ጋር ሊስማሙ ባለመቻላቸው ትዳራቸውን ለማፍረስ ተገደዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ብቻዋን እናትም፣ አባትም፣ ሆና ልጇን እያሳደገች ትገኛለች። «ቤተሰብን ለብቻ ማስተዳደር ከእናቴ ተምሬያለሁ» የምትለው ወይዘሮ ቤዛዊት ያሳለፈችውን ጊዜ እንዲህ ታስታውሳለች።
የማየት ችሎታዬን ያጣሁት በልጅነቴ ነው። ያን ጊዜ ግን ችግሩን ብዙም እረዳው ስላልነበር ያን ያህል አልጨነቅም። ከእኔ በላይ ስለኔ ትጨነቅ የነበረችው እናቴ ነች። ይሄ ችግር ሲደርስብኝ ቤተሰቦቼ በተለይ እናቴ ለከፋ ጭንቀት ተዳርጋ ነበር፡፡ ለማሳከምም፤ ለመንከባከብም ኃላፊነት የነበረባት እሷው ብቻ ናት። ይህ ሁሉ ሲሆን አባቴ የችግሩን ምንጭ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ምክንያት በማድረግ ከእናቴ ጋር የጀመረው እሰጥ አገባ እየተካረረ ይመጣና ቤተሰቡን ለእናቴ በመተው ወደ ተወለደበት ቀዬ ያቀናል።
እናቴም የዓይኔ ህመም ሊድን እንደማይችል ካወቀች በኋላ በእሷ አመለካከት ይሄ ችግር የደረሰበት ሰው የመጨረሻ ዕጣ ፈንታው እቤት ውሎ ተጧሪ መሆን ነው የሚል ስለነበር እቤት ተገድቤ እንድቀመጥ በማድረግ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረጓን ትቀጥላለች።
ታዲያ በአንድ ወቅት ይህንን ነገር የሰሙ በአካባቢያችን ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ወደ ሻሸመኔ በመሄድ ትምህርቴን መቀጠል እንዳለብኝ ለቤተሰቦቼ ያሳስባሉ። እናቴ ግን ተምራስ ምን ሊቀየር? ይልቅስ ልጄ የማታወቀው ሀገር ሄዳ የባሰ ችግር ይገጥምብኛል ብላ አምርራ ትቃወማለች። ነገር ግን በወቅቱ ይህንን ማድረግ ግዴታ መሆን ስለነበረበት ኃላፊዎቹ እናቴን አስረው ለትምህርት ወደ ሻሸመኔ እንድሄድ ያደርጋሉ።
እኔም ወደ ሻሸመኔ ካቀናሁም በኋላ ለተከታታይ አራት ዓመታት ክረምትን ጨምሮ ቤተሰቤን ሳላይ እዚያው ሻሸመኔ ለመቆየት ቻልኩኝ። ሌላው ቀርቶ በክረምት ትምህርት ባለመኖሩ ሌሎቹ ልጆች ወደ ወላጆቻቸው ሲሄዱ ከሠራተኞችና ከሥራ ኃላፊዎች ጋር በየቤታቸው እየወሰዱኝ ስታሳልፍ እንደነበር ታስታውሳለች።
በዚህ ሁኔታ «ሻሸመኔ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት» እስከ ስድስተኛ ክፍል ለመማር ቻልኩ። የሻሸመኔ ቆይታዬ በትምህርቱ ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገር ደስተኛ የሆንኩበት ነበር። ትምህርት ቤቱ ለዓይነ ስውራን ተብሎ የተዘጋጀ በመሆኑ ብዙ ነገሮች የተሟሉለት ነው። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በተመሳሳይ ዕድሜ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበርን በመሆኑ ቅርርብና እርስ በእርስ እንፋቀራለን። አዳሪ ትምህርት ቤት በመሆኑም በአብዛኛው ጊዜ ግንኙነት የነበረን ከመምህራኖች፤ ሠራተኞችና ተማሪዎች ጋር ብቻ ነው። ይህም ሆኖ የነበሩት መምህራን በጣም ስለሚወዱንና ተነሳሽነት ስለነበራቸው ከብሬል ጀምረው በደንብ እንድንማር ይከታተሉን ስለነበር ሁላችንም ውጤታማ ነን።
ከዚህ በኋሏ ወደተወለድኩበት ራያ ተመልሼ ትምህርቴን ለመቀጠል ስል ሌላ ያላሰብኩት መሰናክል ገጠመኝ። የአካባቢው ህብረተሰብ በተለምዶ ዓይነ ስውር ለብቻው ተለይቶ ነው የሚማረው የሚል አመለካከት ስለነበረው በአካባቢው ያለው ትምህርት ቤት ተቀብሎ ለማስተማር ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል። ነገር ግን እስከ ስድስተኛ ክፍል በመማሬ የተፈጠረውን ሁለንተናዊ ለውጥ ያስተዋለችውና ተስፋ የሰነቀችው እናቴና ሌላውም ቤተሰብ ክልከላውን በጽኑ በመቃወም ክልል ድረስ በመሄድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረጉት ትንቅንቅ በ«አለማጣ ታዳጊዋ ኢትዮጵያ» ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርቴን እንድቀጥል ሁኔታዎች ተመቻቹልኝ።
ትምህርቴን በዚህ ሁኔታ ብጀምርም የትምህርት ቤቱ ዝግጅት አካቶ በመሆኑና የልዩ ፍላጎት ትምህርትን ግብአት ያላሟላ በመሆኑና ከብሬል ጀምሮ መሰረታዊ የሆኑት የዓይነ ስውራን መማሪያ ቁሳቁሶች ባለመኖራቸው እንደ ሻሸመኔው ውጤቴን ጠብቄ መቀጠል አልቻልኩም። ይህም ሆኖ በሻሻመኔ ትምህርት ቤት በነበርኩበት ወቅት የትምህርትን አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ትምህርት ለዓይነ ስውራን አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆኑን ተረድቼ ነበር። በመሆኑም በቤተሰብና ጓደኛ ድጋፍ አስፈላጊውን መስዋእትነት እየከፈልኩ መማሬን ቀጠልኩ። ይህም ሆኖ አካቶ ትምህርት እኩል ሰምተህ እኩል ጽፈህና እኩል አንብበህ የምትዘጋጅበት በመሆኑ ሙሉ እውቀቴን በመጠቀም እንደ ቀደመው ጥሩ ውጤት እያስመዘገብኩ ለመቀጠል የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አልነበረም ትላለች።
አካል ጎዳተኞች ህብረተሰቡ አይችሉም የሚል አመለካከት ስላለው በየእንቅስቃሴያችን ጣልቃ ይገባብን ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ለመሳሳት እንኳን ዕድል አልነበረንም። በዚህም የተነሳ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት አስቸጋሪ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ፡፡ በሻሸመኔ የነበረኝንም ትዝታ ለመመለስ በየቀኑ ማስታወሻ እጽፋለሁ። መላመድ ሲመጣና ሰውም ነገሮችን እየተገነዘበ ሲሄድ እኔም ከሰዎች ጋር ያለኝንም ቀረቤታ ሆነ ህይወትን ቀለል አድርጌ መመልከት እንዳለብኝ ስረዳ ነገሮች እየተስተካከሉ መጡ።
እናቴም ምንም እንኳ የመማሬን ነገር መጀመሪያ ተቃውማ የነበረ ቢሆንም ትምህርት ከጀመርኩና በኋላ ግን ፍሬውን ለማየት ብዙ ስለምትጓጓ ማንም እንዲናገረኝ፤ ከዓላማዬ እንዲያሰናክለኝ አትፈቅድም። ኃይለኛም ስለነበረች እቤት ውስጥም ከሁለት ወንድሞቼና ከሁለት እህቶቼ ለእኔ ብቻ የተለየ ትኩረት በመስጠት ሁሉም እንዲንከባከቡኝ ታደረግ ነበር። ይህም ፍሬ አፍርቶላት ዛሬ ከሁሉም እህትና ወንድሞቼ በትምህርት የተሻለ ደረጃ የደረስኩት እኔ ብቻ ነኝ።
የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ስወስድም ሦስት ነጥብ ስድስት በማምጣት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ዕድሉን አገኘሁ። እናቴም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተደሰተችው በዚህ ወቅት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲም የህግ ትምህርቴን ለሦስት ዓመታት እየተከታተልኩ ሳለ ሌላ ያልታሰበ ድገተኛ ክስተት አጋጠመኝ። እናቴ አረፈች። ብዙውን ኑሮዬን ስትኖርልኝ የነበረችው የእናቴ ሞት ለእኔ ከባድ በመሆኑ ነገሮችን በቀደመ መስመር መቀጠል ባለመቻሌ ትምህርቴን ለማቋረጥ ተገደድኩ።
ይህም ሆኖ የዩኒቨርሲቲው ባይሳካልኝም ትንሽ ከተረጋጋሁ በኋላ «ተስማሚ የቴክኖሎጂ መዕከል ለዓይነ ስውራን» የሚል ተቋም በመግባት ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። በተቋሙ የሚሰጠውን የሦስት ወር መሰረታዊ የኮምፒዩተር ስልጠና ወስጄ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቤ እዚያው በመምህርነት እንድሠራ የቀረበልኝን ጥያቄ ተቀብዬ ቀጠልኩ። በተቋሙም ለሦስት ዓመት ያህል ስሠራ ራሴን ከመጥቀሜ ባለፈ ሌሎች ዓይነ ስውራን ከቴክኖሎጂ ጋር በመገናኘት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ታግዘው ከጥገኝነት እንዲላቀቁ ለማድረግ በመቻሌ ሁሌም ደስታ ይሰማኛል።
በእነዚህ ዓመታት ባፈራሁት ጥረትም ቀን ቀን እየሠራሁ ማታ ማታ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መማር ጀምርኩ። ይኼኛውም ጉዞ ግን መሰናክል አላጣሁም ተቋሙ ቅሬታ በማቅረቡ ወይ ከትምህርት ወይ ከሥራ አንዱን ለመምረጥ ተገደድኩ። ውሳኔ ከባድ እንደሆነ ባውቅም ትምህርቴን ለመቀጠል ወሰንኩ። እንደፈራሁትም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የፋይናንስ ችግር ገጠመኝና ቀድሞ የህግ ትምህርት ስንማር እንተዋወቃቸው የነበሩ ጓደኞቼ እየደገፉኝ በ2008 ዓ.ም በቋንቋና ስነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ድግሪዬን ለመያዝ በቃሁ።
የመጀመሪያ ድግሪዬ ስማር ደግሞ እዚያው አብሮኝ የሚማር ዓይነ ስውር ወጣት ጓደኛዬ ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀምሬ ነበር። በጓደኝነት የተወሰነ ጊዜ ከቆየን በኋላ መጸነሴን አወቅሁ፡፡ እናም ለጓደኛዬ ስነግረው በዚህ ጊዜ ልጅ መውለድ የለብንም በሚል ሳይቀበለው ቀረ። በእርግጥ ከጅምሩም ጓደኝነታችን ጠንካራና ቤተሰብ ለመመስረት የሚያስችል ዓይነት አልነበረም። ይህም ሆኖ የልጅ እናት ለመሆን በቃሁ። ልጅ የመውለዱ ጉዳይ ታስቦበት የነበረ ባለመሆኑ ጽንሱን እስከማጨናገፍ ድረስ አስቤ ለህክምናው ቀብድም ከፍዬ የነበረ ቢሆንም እዚህ ከደረሰ በኋላ ወደ ኋላ መመለሱ ለማንም አይበጅ የሚል ሃሳብ መጣብኝ።
መቼም ቢሆን ልጁ ተወለደም ተጨናገፈም የችግሩ ተሸካሚ ሴት ብቻ ናት፡፡ ስለዚህ ውሳኔውንም መወሰን ያለብኝ እኔው ብቻ ነኝ ብዬ በራሴ መንገድ ነገሮችን ቀጠልኩ። እናም ቤተሰብ ሳይመሰረት የተጀመረውን ቤተሰብ የማስተዳደር ሌላ ኃላፊነት ከፊቴ ተደቀነ። በአንድ በኩል ሥራ የለም፤ በሌላ በኩል የቤት ኪራይ፣ ቀለብና ልጅ ማሳደግ ኃላፊነት ከፊቴ ተደቅኗል። በዚህ ወቅት ከፈጣሪ ቀጥሎ ከጎኔ የነበሩት የቀደሙ ወዳጆቼ ብቻ ነበሩ። እነሱ ስትማሪ መደገፋችን ብቻ በቂ አይደለም አንቺ ሥራ ሠርተሽ እንጀራ ቆርሰሽ እስክትበይ መጨረሻሽም ጥሩ ሲሆን ማየት አለብን ብለው ድጋፋቸውን ቀጠሉልኝ። እኔ ግን ሁሌም እናቴን አስታውሳለሁ በገጠር ኑሮ አራት ልጆቿን ማሳደግ ችላለች፡፡ ይሄ ለእኔ ብርታትና ጎልበት ነው ስል እዕምሮዬን አሳምነዋለሁ። ከእንጀራ መጋገር ውጪ አንዲት እናት የምትሠራውን ሁሉ ሠርቻለሁ፤ እሠራለሁም።
አንዲት ነፍሰጡር ሴት በቤትም ሆነ በሆስፒታል ብትወልድ ቤት ከገባች በኋላ በቤተሰብ መታረስ ያስፈልጋታል፡፡ እኔ ግን ይህንን ወግ ለማየት ዕድሉን አላገኘሁም። ለዕለት ከዕለት እንቅስቃሴም በቤት ውስጥ የሚረዳኝ ቤተሰብ አልያም ዘመድ ወዳጅ አልነበረም። ድሮም እናቴ ቤት እያለሁ ልጅ ማሳደግ እንዴት እንደሆነ የማይበት ዕድሉ አልነበረኝም።
ለሕፃናት ልብስ እንዴት እንደሚቀየር፤ ዳይፐር እንዴት እንደሚደረግ እንኳን ስለማላውቅ ሁሉም ነገር አዲስ ነገር ነበር የሆነብኝ። እናም ጎረቤት እየጠራሁ እንዲተባበሩኝ አደርግ ነበር። በአንድ ወቅት አንዲት አከራዬ እስከ መቼ በደጋፊ ትኖሪያለሽ ብለው ብዙ ነገሮችን አሳዩኝ። በዚህ ሁኔታ በየማስታወቂያውና መስሪያ ቤቱ ሥራ በመፈለግም፣ ልጅ በማሳደግም፣ አንዳንዴ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠትም ሁለት ዓመት አሳለፍኩ። በመጨረሻም ላይነጋ አይጨልምም እንዲሉ ትምህርት ቢሮ የሥራ ማስታወቂያ አውጥቶ ተወዳድሬ ማለፍ ቻልኩ። ይሄ ደግሞ በጓደኞች ድጎማ ቆሞ ለነበረው ቤተሰብ የተስፋ በር ከፈተ። በአሁኑ ወቅት በበላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ዘጠነኛ ክፍል የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርት ሆኜ እየሠራሁ እገኛለሁ።
በልጅነቴ ስለኔ ችግር ከእኔ በላይ ትጨነቅ የነበረችው እናቴ ናት፡፡ ያኔ እኔ ብዙውን ነገር አልረዳውም፡፡ ነገ ምን ይጠብቀኛል ምን እሆን ብዬ አላስብም፡፡ እሷ ግን እኔ ከሌለሁ ምን ትሆናለች ብላ ሙሉ ህይወቷን የሰጠችው ለእኔ ነው። ያልተማረችው እናቴ ዛሬ ላለሁበት ደረጃ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ይህም ቤተሰብ ለልጅ እድገት ወሳኝ መሆኑን ለመረዳት አስችሎኛል። አባቴን ሰባተኛ ክፍል ልገባ ስል አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ያገኘሁት፡፡ የአባት ፍቅር ሳላገኝ ነው ያደኩት።
በወቅቱ ወደ ቤተሰቦቹ ወስዶ ሊያሳድገኝም ቢፈልግም እናቴ እስከአሁንም ያሳደግኳት እኔ ነኝ አሁንም እኔ አለሁ ብላ ከለከለችው፡፡ እኔም ለምን አባቴ ጋር አልሄድም ብዬ ከእናቴ ጋር ክርክር ገጥሜ ነበር፡፡ እናቴ ግን ፈቃደኛ አልነበረችም። ይህም እናቴ ምን ያህል መስዋእትነት እንደከፈለች ብቻ ሳይሆን ልትከፍልልኝም እንደተዘጋጀች እንድረዳ አስችሎኛል። በአጠቃላይም ደረጃው ቢለያይም አንድ ቤተሰብ እንደ ቤተሰብ እንዲቀጥል በሁሉም ወይንም በተወሰኑ የቤተሰቡ አባላት የሚከፈል መስዋእትነት እንዳለም ለመረዳት ችያለሁ።
አሁን እኔ ልጄን ብቻዬን እያሳደግኳት ቢሆንም አባቷን እንድታጣ ግን አልፈልግም። ሌላው ቢቀር ፍቅር እንዲሰጣት እፈልጋለሁ፡፡ የስነ ልቦና ችግር እንዲገጥማት አልሻም። በእርግጥ በዚህ የኑሮ ውድነት ቤት ኪራይ ከፍሎ ልጅ አሳድጎ ለሠራተኛ ከፍሎ መኖር ከባድ ነው፡፡ ከዚህም በላይ አንድ ቤተሰብ ቤተሰብ ለመባል ከቁሳዊ ፍላጎት ባለፈ ልጆች እናትና አባታቸውን እያዩ አብረው መኖር መቻል አለባቸው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ቤተሰብ በተለያየ መንገድ ሊመሰረት ይችላል፡፡ አንድ ሰው ጥሩ ባል ወይንም አንዲት ሴት ጥሩ ሚስት ላትሆን ትችላለች፡፡ ልጅ ከተወለደ ግን እንደ አንድ ቤተሰብ ጥሩ አባት አልያም ጥሩ እናት መሆን የግድ ነው።
ሆኖም ቤተሰብ አብሮ ለመኖር ካልተስማማ የግድ በአንድ ቤት ተሰባስቦ መኖር ባይኖርበትም፣ መጠያየቅ መገናኘት ግን ይቻላል። እኔ ይሄም ሃሳብ ስላለኝ ምንም እንኳ እስከአሁን የተለወጠ ነገር ባይኖርም ዛሬም ድረስ ልጄ ከአባቷ ጋር እንድትገናኝ እየደወልኩ እሞክራለሁ። አንድ ቀንም እንደ ቤተሰብ እንደምንሰባሰብ ተስፋ አለኝ። በእኔ በኩል ግን ዛሬ ቤቴ ሙሉ ነው፡፡ አሁን ከልጄ ጋር አዲስ ዓለም ነው የጀመርኩት። ልጄ ማያ ትባላለች እንደ ስሟ ለእኔ መመልከቺያዬም ናት፡፡ አሁን ሦስት ዓመት ሆኗታል፡፡ ቀን ቀን ከሠራተኛዋ ጋር ትውላለች ማታ እኔ ስገባ ቤታችን ሞቆ ነው የሚያመሸው። ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ ልጄ ትምህርት ስትጀምር በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ሁለተኛ ድግሪዬን ለመሥራትና ያቋረጥኩትንም የህግ ትምህርት ለመጨረስ እቅድ አለኝ።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 6/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ