ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ጉለሌ መድሀኒአለም ትምህርት ቤት አካባቢ አቅንቶ ሞላ ገላጋይን ለጠየቀ ጠቋሚው ብዙ ነው። አቶ ሞላ ገላጋይ የዘመኑ እውቅ የባህል ሀኪም ነበሩ። በአካባቢውም ተሰሚነት የነበራቸውና ሰው ሲጣላ አስታራቂ፣የተከበሩና የታፈሩ አባት ናቸው። አቶ ሞላ የመጀመሪያ ትዳራቸውን የያዙት በተወለዱበት ወሎ ክፍለ ሀገር ሲሆን ከዛ በኋላ አምስት ሚስቶችም አግብተዋል። ከእነዚህ ሚስቶቻቸውም አስራ ዘጠኝ ልጆችን ወልደዋል። በአሁኑ ወቅትም ሃያ ሰባት ሴትና ሃያ ዘጠኝ ወንድ በድምሩ 56 የልጅ ልጆችን፤ እንዲሁም 20 ሴትና 10 ወንዶች በድምሩ 30 የልጅ፤ ልጅ ልጆችንም አፍርተዋል። አቶ ሞላ በተለያዩ ቦታዎች ትዳር መስርተው ልጆች ቢያፈሩም 16 ልጆቻቸው ያደጉት አዲስ አበባ በመጨረሻ ባለቤታቸው እጅ ነበር።
ዙሮ ዙሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት እንዲሉ አቶ ሞላ በ1983 ዓ.ም በቀናት ህመም ህይወታቸው ያልፋል። አቶ ሞላ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ሁሌም ለደረሱ ልጆቻቸው የሚያሳስቡት ስለቤተሰብ ፍቅር ነበር፤ ለልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ዘመድ አዝማድ ሲሰባሰብም ስለቤተሰብ አንድነት፣ መዋደድ፣ መተባባርና ፍቅር ያስተምራሉ። «ሁሌም በራችሁን አትዝጉ፤ እርስ በእርስም ተፋቀሩ የእናንተ መዋደድ ለጎረቤት፤ በሎም ለሰፈርና ለሀገር ይተርፋል፤ ያጠፋን መምከር እንጂ መቆጣት አይገባም ደግሞ አትኳረፉ ከኩርፊያ ምንም አይገኝም እያሉም ሲያሳስቡ ኖረዋል። እናም እሳቸው ቢያልፉም ቃላቸው ፍሬ አፍርቶ ያለፈውን 30 ዓመት ቤተሰቡ እንደተሰባሰበ ለመቆየት በቅቷል። በቅርቡ ደግሞ የ30 ዓመት ጉዞው ለቀጣዩም ትውልድ ይሸጋገር ዘንድ ቤተሰቡ በየሁለት ወሩ የሚዘጋጅ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።
ወይዘሮ ትርንጎ ታደሰ በወሎ ክፍለ ሀገር መቄት ወረዳ ነው የተወለዱት ለአቶ ሞላ ገላጋይ አምስተኛ ሚስት ናቸው። ከእሳቸውም ስድስት ልጆችን ወልደዋል። ከአቶ ሞላ ገላጋይ ጋር ያሳለፉትን ህይወት እንዲህ ያስታውሱታል። አራት ሚስቶች ነበሯቸው አሁንም ሁለቱ በህይወት ይገኛሉ። ትዳር ስንመሰርት እኔ ከሳቸው በእድሜ በጣም አንሳለሁ። ልጅ አልወለድኩም እንጂ ሀገር ቤት በልጅነቴ ትዳር መስርቼ ነበር። የተገናኘነውም እሳቸው ገጠር መጥተው ነው ተጋብተን አዲስ አበባ ሲያመጡኝ ሁሉንም ነገር ነግረውኝ ነበር። ውሸት አይወዱም አራት ሚስት አለኝ ብዙ ልጆችም ወልጂያለሁ አሉ። እኔ ምንም አልመሰለኝም ከመጣሁ ጀምሮ ሳሳድግ የነበረው የሳቸው ከሌሎች ሚስቶቻቸው የወለዷቸውን ልጆች ነው። እኔ በወሊድ ወቅት ልጆች የሞቱብኝ(የጠፉብኝ) ሲሆን አሁንም ግን ስድስት ልጆች አሉኝ። ቤት ውስጥ ሳሳድጋቸው የነበሩት ልጆች ግን ከ15 አንሰው አያውቁም። ቀሪዎቹ ሚስቶችም የየራሳቸው ቤት አላቸው ኑሯቸውም አዲስ አበባ አይደለም ግን ሁሉም እየመጡ ልጆቻቸውን አይተው ጠይቀውን ይሄዳሉ። የመጀመሪያ ልጄን በ1970 ዓ.ም የወለድኩ ሲሆን ባለቤቴ ሲያርፉ የመጨረሻው ልጄ የስድስት ወር ዕድሜ ነበረው።
እሳቸው ከሰው መኖር አስተምረውኛል ከዘመዶቻቸውም መካከል ሙስሊሞች ነበሩ በዛ ላይ የባህል ሐኪም ስለነበሩም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ፈውስ ፍለጋ የሚመጡም በርካቶች ነበሩ። ቤት ውስጥ አንድም ቀን ያለ እንግዳ ያሳለፍንበትን ጊዜ አላስታውስም። የዛ ልምድ ይመስለኛል ዛሬም ግቢ ውስጥ ሰው ሲበዛ ሰው ሲንቀሳቀስ ልጆች ሲንጫጩ ሳይ ደስ ይለኛል። እኔም ልጆቼም ብቸኝነት አንወድም። እሳቸው ትልቅ ስለነበሩ አከብራቸውም ነበር። አንድም ቀን ክፉና ደግ ተነጋግረን አናውቅም በጣም ነበር የምንፋቀረው። በጣም ቀልደኛም ነበሩ ልጆቻቸውን ሲመክሩ ይቆዩና ጉራጌ ስራ ይወዳል ከጉራጌ መውለድ ነበረብኝ ይሉን ነበር።አቶ ሞላ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ ያስመጧቸውና ለወግ ለማረግ ያበቋቸው በርካቶች ናቸው። ከእነዚህም መካከል በህክምና ተመርቀው በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በስራ ለይ ያሉም አሉ። እኔ ሁሌም የሚሰማኝ ሁሉም ልጆች የእኔ አብራክ ክፋይ እንደሆኑ ነው። አሁን በህይወት ካሉት ከሞቱትም የልጆቹ እናት ጋር እንደ እህትማማች ነበር የምንተየያው።
በአንድ ወቅት እኛም ቤት እንደ ማንኛውም ቤተሰብ አለመግባባት ተፈጥሮ እገጭ እጓ የምትል ትንሽ ግጭት ገጥማን ነበር። እንጀራም ዳቦም እስከመሸጥ የደረስኩበትም ወቅት ነበር። ሁሉንም ልጆች ያሳደግኳቸው እኔ ነኝ። የእኔን ያህል እናታቸውን እንኳ በውል አያውቋቸውም። እናም ግጭት በተፈጠረበት ወቅት በጣም ነበር የምጨነቀው። ጨርሶ አልተቆራረጥንም በለቅሶና በአንዳንድ ማህበራዊ ጉዳዮች እንገናኝ ነበር ታዲያ የዛኔ ፍቅራቸውን ስለለመድኩ በጣም ነበር የምረበሸው። ይህም ሆኖ ልጆቹ ብልህ ናቸው የአባታችውን ምክር አስታውሰው ነገሩን በቀላሉ በመፍታታቸው መልሰን መሰባሰብ ችለናል። እንዲህ አይነት ልምድ ሁሉም ቤተሰብ ሊኖረው ይገባል። ዛሬ ቤተሰቡ ተሰባስቦ ሳይ ተናግሬ የማልጨርሰው ደስታ ይሰማኛል ደግሞ ልጆቹ በአጋጣሚ ይሁን አውቀው አላውቅም ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከትግሬና ከጉራጌ ተጋብተዋል። ታዲያ አንዳንዴ ቤት ሲመጡ የቀበሌ ስብሰባ የሚካሄድ ነው የሚመስለው። ሰው ከእኛ ብዙ መማር ይችላል አንዳንዴ በየቤቱ የምሰማው ነገር በጣም ያስደነግጠኛል፤ ሶስት አራት ልጆች ሆነው ከአንድ እናትና አባት ተፈጥረው ተጣሉ ተካሰሱ የሚል ነገር ስሰማ እደነግጣለሁ። ምናለ እኛን መጥተው ቢያዩ የሚል ሀሳብም ይመጣብኛል ይላሉ ወይዘሮ ትርንጎ።
ወይዘሮ ሲሳይነሽ ሞላ ለቤተሰቡ አስራ ሶስተኛ ልጅ ናቸው። ያለፈውን አስራ ስድስት ዓመት ኑሯቸውን ያደረጉት በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ አካባቢ ነው፤ የሁለት ልጆች እናትም ናቸው። የአባታችን አደራ ነበረብን እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ፣ ሰው ማክበር እንዳለብንም ሲያስተምረን ኖሯል ይላሉ። ወይዘሮ ሲሳይነሽ በቤተሰቡ ውስጥ ያሳለፉትንም ጊዜ እንዲህ ያስታውሱታል፤ በልጅነታችን ታላላቅን ማክበር ታናናሾችን ደግሞ መንከባከብ ግዴታችን ነበር። በዚያ ላይ እንግዳ ከቤት ውስጥ ጠፍቶ አያውቅም። የእነሱን እግር ማጠብ በቤተሰቡ የተለመደ ተግባር ነው።አዛውንቶችን እግር አጥበን ስመን ካልተነሳን እንቆጣ ነበር።እኛ ቤት የማይመጣ ዘመድ የለም የተለያየ ብሄር፤ የተለያየ ሀይማኖት ያላቸውን እንግዶችን እናስተናግድ ነበር። አባታችን ጋር ህክምና ለማግኘት መጥተው ቤት የሌላቸው እኛው ቤት ነበር የሚያድሩት፤ ገንዘብ ሳይኖራቸው የሚመጡት እንኳን የሚታከሙበት በነጻ ነበር።አንዳንድ ጊዜ ምግብም ከቤት ነበር የሚጠቀሙት። እንዲህ ሲሆን ደግሞ አባታችን በቃ አንድ ዘመድ አግኝታችኋል ደግ በማድረጋችሁ እንዳትበሳጩ ይለናል።
እኔ ወላጅ እናቴን አላውቃትም፣ አላሳደገችኝም ያሳደገችኝ ወይዘሮ ትርንጎ ታደሰ ናት። ያሳደገችኝ ፍቅር እየሰጠች ነው። ዛሬ ላለሁበት ማንነት ለትዳሬ መቃናትም እንደ አባቴ ሁሉ የሷም ጥርት ትልቅ ቦታ አለው። ወደ ድሬዳዋ የሄድኩት ለስራ ቢሆንም አስተዳደጌና ቤተሰቤ ከማህበረሰቡ አኗኗር ጋር ለመቀላቀል ብዙ ረድቶኛል። አባታችን እርስ በእርስ እንድንተሳሰብ እድርጎን ስለነበር እኔ ስራ ስይዝ የመጀመሪያ ስራዪ ያደረኩት ታናናሾቼን መንከባከብ ነበር ። በተመሳሳይ አንዷ እህታችንም አረብ ሀገር እየሰራች ቤተሰቡን ትደጉም ነበር። ፈጣሪ ፈቃዱ ሆኖ ተሳክቶልን ሁሉም ታናናሾቻችን ጥሩ ቦታ ደርሰዋል።
ሰላም የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። በፍቅር ያደገ ልጅ ለክፉ ስራ አይተባበርም፤ ጨካኝም አይሆንም። ዛሬ አንዳንድ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን ወጣቶች ሲያደርጉ ስመለከት ቤተሰባቸው ውስጥ የነበራቸውን አስተዳደግ ነው የምረዳው። ማንም ቤተሰብ ውስጥ ቅራኔ አይጠፋም። ነገር ግን ሁሉን ነገር ቀለል አድርጎ ማየትና መቻቻል ያስፈልጋል። ትቶ ማለፍና መታገስ ለቤተሰብ ፍቅር መሰረት ነው። ድሮ አባታችን ከጉራጌ በወለድኩ ይል ነበር። እኔ ኦሮሞ አግብቻለሁ ቤታችን ትልቅ ፍቅር አለ። የአሁኑን ዝግጅት እኔነኝ የማዘጋጀው ስል ሁሉም እንሄዳለን ስላሉ 11 ሆነን ነው ከድሬዳዋ የመጣነው። ጎረቤቶቻችን ሳይቀር በእኛ ደስተኛ ሲሆኑ አያለሁ። ሁሉም ቤተሰብ በአቅሙ ብዙም ባይሆን እንደኛ የቤተሰብ ማህበር እያቋቋመ እርስ በእርሱ ቢረዳዳ ቢወያይ መልካም ነው ሲሉ ወይዘሮ ሲሳይነሽ ምክራቸውን ይለግሳሉ።
«እኛ ልጆቹ አንድም ቀን ከተለያየ ቤተሰብ እንደተወለድን አስበንው አናውቅም። አባታችን በ1983 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እስከ 1996 ዓ.ም ወራሽነት አላሳወጅንም ነበር። ስለቦታም ስለሀብትም ጥያቄ ተነስቶ አያውቅም። መጨረሻም ወደ ፍርድ ቤት የሄድነው ቦታው ለመንገድ ስራ ስለሚፈለግ አስገዳጅ ሆኖብን ነው» የሚሉት ደግሞ የአቶ ሞላ ገላጋይ አምስተኛ ልጅ አቶ አበራ ሞላ ናቸው። የአባታችን ምክር ሰውን በሰውነቱ ብቻ እንድንቀበል አድርጎናል የሚሉት አቶ አበራ “በአንድ ወቅት ልጅ እያለሁ አንድ ቀን ሌሊት በሰፈሩ የሚኖር የአእምሮ ችግር ያለበት ሰው ቤታችን በር ላይ ሆኖ ይቆረቁራል። አባታችን ሲወጣ ልጁን ያገኘዋል። ቤት አስገብቶ እኛን ልጆቹን ከአልጋ ላይ አስነስቶ እሱን እዛ ያሳድረዋል። ይሄ በወቅቱ በጣም ከባድና መስዋእትነት የሚጠይቅ ነገር ነበር። የአእምሮ ችግር ያለበትን ልጅ እቤትህ ማሳደር ይቅርና ማስገባትም ይከብዳል። እኔ እንደዚህ አይነት ደግነትና ሰዎችን መርዳትን ሁኔታዎች ሳይ ስላደኩ ታክሲ ከምሳፈርበት ጊዜ ጀምሮ ከማንኛውም ሰው ጋር በቀላሉ መግባባት እችላለሁ፤ በስራ ቦታም ከማንም በላይ ከሰው ተግባብቼ በሰላም እሰራለሁ። ይሄ ሁሉ የአስተዳደጌ የቤተሰብ ውጤት ነው” ብሏል።
አባታችን እረፍት ሲኖረው ሰብስቦ ያጫውተንና ይመክረን ነበር። እኛም እሱን ተከትለን የቤተሰብ ስብሰባ ድሮም ጀምሮ ነበር የምናካሂደው። ምንም አይነት ነገር ሲገጥመን ተሰብስበን ነበር የምንወስነው። ሌላው ቀርቶ ከልጆች መካከል ትንሽ የባህሪ ለውጥ የታየበት ካለ ሁላችንም ተሰብስበን እንነጋገራለን እንማከራለን። ምንም ነገር ቢገጥመን ቅድሚያ የምንሰጠው ለውይይት ነው። አሁን የጀመርነው ቋሚ ጉባኤ ደግሞ የቤተሰብ መገናኛና መመካከሪያ መድረክ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ነዋሪ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። የቤተሰብ ጉባኤው ሲካሄድ የቤተሰቡን አባላት በተገኙበት ሌሎች ቤተሰቡን የሚመለከቱ የጥያቄ ውድድርም እናካሂዳለን። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከእኛ ይበልጥ የልጅ ልጅ የሆኑት ህጻናት ማህበሩን በጣም እንዲናፍቁት ያደርጋቸዋል። በተጨማሪ የቤተሰብን ፍቅር የመሰባሰብንም ትርጉም ይረዳሉ። እኛ ስለ ቤተሰብ ያለን አመለካካት ጠንካራ ነው። የግል የምንለው ጉዳይ ብዙም የለንም። ያሰብነው ወይም የገጠመን ነገር ካለ እንነጋገራለን መፍትሄም እናቀርባለን። የቤተሰባችን መቀራረብ ጥሩ ትውልድ እንዲኖር አድርጓል። ከዚህ ቤተሰብ ወጥቶ ለማህበረሰብ፣ ለአካባቢ ሽማግሌ ክብር የማይሰጥ ስነ ስርዓት የጎደለው የልጅ ልጅ የለም ይላሉ።
አቶ አበበ ንጉሴ ደግሞ የሞላ ገላጋይን የልጅ ልጅ አግብተው በትዳር ቤተሰቡን የተቀላቀሉ ናቸው። ከሞላ ገላጋይ ቤተሰብ ብዙ ተምሪያለሁ ከምንም በላይ ለቤተሰብ ፍቅርን መስጠት እንደሚቀድምም ለማወቅ ችያለሁ ይላሉ። አቶ አበበ የራሳቸውን ቤተሰብ ታሪክ በማንሳትም ከሞላ ገላጋይ ቤተሰብ ያገኙትን ፍቅር እንዲህ ይገልጻሉ። እኔና ባለቤቴ ግንኙነት ከጀመረን አስራ ሰባት ዓመት አልፎናል። ከእሷ ጋር ስቀራረብና ስለቤተሰቧ በደንብ ሳውቅ ስለእኔም ቤተሰብ አስባለሁ። እኔ ጋር ከአንድ አባት የምንወለድ አስራ አራት እህትና ወንድሞች አሉኝ። ለአባቴ የመጨረሻ ለእናቴ ደግሞ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ ባጋጣሚ ከአንዷ በቀር ሁሉም ውጭ አገር ነው የሚኖሩት። አንገናኝምም፤ አላውቃቸውም። እናም ከእኔ ቤተሰብ ያጣሁትን ፍቅር ከሞላ ቤተሰብ ማግኘት ችያለሁ። በዚህም ሁሌም ደስተኛ ነኝ። ቤተሰቡ ትንሿ ኢትዮጵያ ነው ብዙ ናቸው ከተለያዩ ብሄሮች ጋር ተጋብተዋል። የሚኖሩትም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ነው። ይህን ቤተሰብ አይቶ የማይቀና የለም። በተለይ ዛሬ በሀገራችን አንዳንድ ቦታዎች እየተፈጠረ ላለው ችግር የእንዲህ አይነቱ ቤተሰብ መበራከት መፍትሄ ይሆናል ይላሉ።
ወይዘሮ ጸባኦት ሞላ ለቤተሰቡ አስራ ስምንተኛ ልጅ ናት። አባቷ አቶ ሞላ ገና ሶስት ዓመት ሳይሞላት ስላረፉ በደንብ አታስታውሳቸውም። ግን ደግሞ ከቤተሰብ ከዘመድና ከአካባቢው ነዋሪ ስለአባቷና ስለቤተሰቡ ያለፈ ህይወት ብዙ ስትሰማ ስለነበር ለቤተሰቧ ያላት ፍቅር ከፍተኛ ነው። ፍቅሯ ከቤተሰብም አልፎ ለጎረቤትና ሰፈርተኛውም ጭምር ነበር። «የእኛ ቤተሰብ ከጎረቤትም ጋር በጣም ይቀራረብ ነበር ከጉለሌ ቤት ቀይረን ሸጎሌ ስንመጣ አዲሱ ሰፈር በጣም ከብዶኝ መልመድ አቅቶኝ ነበር። እናም ወደ ድሮ ሰፈሬ ተመልሼ አንድ ዓመት የድሮ ጎረቤታችን ቤት ተቀምጨ ለመኖር ተገድጂያለሁ ትላለች።»
ወይዘሮ ጸባኦት አጠቃለይ ቤተሰቡን ለማወቅ ትልቅ ጉጕት ስለነበራትም መዝገብ አዘጋጅታ የነበሩ፤ የተወለዱ የተጋቡ እያለች የቤተሰቡን ታሪክ በመዝገብ ታሰፍራለች። የቤተሰብ ጉባኤውንም ከእህቷ ልጆች ጋር በመሆን የምትከታተለው እሷው ናት። እናም አሁን ካነሳናቸው የቤተሰብ አባላት በተረፈ ሌሎችም በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭም አሉ። ግን አድራሻቸውን ስለማናውቅ እየተገናኘን አይደለም። በመሆኑም እነሱንም በማግኘት ወደ ቤተሰቡ ለመቀላቀል እቅድ አለኝ ብላለች።
ከእነዚህም መካከል አንደኛው በ1967 ዓ.ም ከኢትዮጵያ በፖለቲካ ምክንያት ከአገር የወጣና ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገ አለ። ለተወሰነ ጊዜ የሰላምታ ደብዳቤ ይልክ ነበር። አሁን ግን የት እንዳለ አናውቅም። ስሙን ሳይቀይር አይቀርም የሚል ግምት አለን። ሁለተኛው ደግሞ አባታችን ሰሜን ሸዋ መርሀቤቴ አካባቢ ልጅ እንዳለው ተናግሯል ያለበትን ልዩ ቦታ፤ ስሙን ወይንም የእናቱን ስም ግን ስላልነገረን አናውቅም። ይህም ሆኖ ፍለጋችን አይቋረጥም ትላለች። አሁን በቋሚነት ማካሄድ የጀመርነው የቤተሰብ ጉባኤ ደግሞ ለዚህም ይረዳናል። ጉባኤው ሐምሌ ወር በ2011 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በየሁለት ወሩ የሚካሄድ ነው። ለቀጣይ ዓመት ወሎ ላሊበላ አንዷ ትልቅ እህታችን ጋር ለማክበር ቀጠሮ ተይዟል። ለአሁኑ ጉባኤ አስራ አንድ የቤተሰቡ አባል ከድሬዳዋ ሶስት ደግሞ ከላሊበላ መጥተዋል ዝግጅቱንም ያሰናዱት ከድሬዳዋ የመጡት ናቸው። የቤተሰባችን ታሪክ ለብዙዎች ምሳሌ እንደሚሆን አስባለሁ። እህትና ወንድም ወንድምና እህት ተጣሉ ሲባል ይገርመኛል። በእለት ግጭት መቀያየም ይኖራል ነገር ግን ነገር አክሮ ወደሌላ መዳረስ ግን ትልቅ ጥፋት ነው። በመሆኑም ሁሉም ለቤተሰበቡ ክብር፣ ፍቅር፣ ጊዜ በመስጠት ሰላም መፍጠር ይጠበቅበታል ሲሉ ከቤተሰባቸው ተጨባጭ ልምድ ተነስተው ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 29/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ