በህይወትህ ጠንክረህ በመስራትህ አንዳች ስኬት ሲገጥምህ ያንተን ሞራል ከማነሳሳት ባለፈ ሌሎች ዓይኖች ወዳንተ እንዲያማትሩ ምክንያት ትሆናለህ። ይሁንናም በጥረትህ ወቅት የገጠመህን ተግዳሮት እያሰብክ ከቆዘምክ እናም እንዲህና እንዲያ ባይሆን ኖሮ የስኬታማነቴ ጊዜ ከዚህ ይፈጥን ነበር፤ ብለህ ማሰላሰል ከጀመርክ ፤ ድልህ ግማሽ ይሆናል። አዎንታዊነትህ በአሉታዊነት ጥላ ሥር ያርፍና ጭጋጋማ ይሆናል። ይህ እንዳይሆን ከፈለግህ አዎንታዊ አስተሳሰብን፣ የህይወትህ መሪ ቃል አድርገህ ፣ ራስህን ለማሻሻል አዘጋጅ። ቀናነት የአንተ የራስህ ምርጫ ጉዳይ መሆኑን እወቅ።
1) መለወጥ አለብኝ፤ በል። ለውጥ ግላዊ ነው፤ ስለዚህም ላለመለወጥ ምክንያት መሆን አልችልም በል።
2) መለወጥ እችላለሁ፤ በል። ለውጥ ይቻላል፤ ለሌሎች የሆነ ለውጥ ለእኔ በእርግጥ ይሆናል ማለት መቻልን እወቅ።
3) በለውጡ እንደምሸለም አምናለሁ። ለውጥ አትራፊ ነው፤ አዎንታዊ ለውጥ ከቶውንም ኪሳራ የለውም። ሰው ከክፋት ወደ ደግነት፣ ከአሉታዊነት ወደ አዎንታዊነት አስተሳሰብ ሲመጣ ቢያተርፍ እንጂ አይከስርም።
ቀና መሆን አዎንታዊ አስተሳሰብ በውስጥ ከማሳደግ የሚመነጭ ነው። ቀናነት በሥራ ሥፍራ ፣ ቀናነት በስብሰባ ላይ፣ ቀናነት በኀዘንና ሰርግ ላይ፣ ቀናነት በወንፈል ሥራ፣ ቀናነት በመስሪያ ቤት፣ ቀናነት በመኖሪያ ቤት ፣ ቀናነት በሐገር ላይ ፣ቀናነትን በዓለም ላይ ሁሉ ማሳየት ይቻላል።
እኔ ለብቻዬ የተቀመጥሁ፣ ደሴት አይደለሁም ፤ እኔ ለራሴ ከማስፈልገው ባልተናነሰ መልኩ ለሌላው ወንድሜ፣ ለወላጆቼ፣ ለጎረቤቴ፣ ለሰፈርና ለከተማዬ አስፈልጋለሁ። የአስፈላጊነቴን ያህልም አደርጋለሁ፤ ማለት የሚችል ልብ ይኑርህ።
ይህ ብቻ አይደለም ቀና ሰው በክፋት የተወረወረን ፍላጻ እንኳን በስህተት ነው እንጂ በእኔ ላይ የተወረወረ አይደለም የሚል ልብ ያሳደገ ሰው ነው።
አንድ ጊዜ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ ክፍል ውስጥ አጠገቤ የነበረች ልጅ ታለቅሳለች። ምን ሆነሽ ነው ብዬ በወረቀት ጻፍኩላት። አሞኛል፤ በዚህ ላይ፣ ፈተናው ከበደኝ፤ ብላ መለሰችልኝ። ወዲያው ወደልቤ፣ ፈተናውን ለእርሷ መስራት አሰኘኝ፤ ግን ልቤ አይሆንም አለኝ። በቃ አሞኛል ብለሽ አስፈቅጂና ውጪ፤ አልኳት።
ደደብ ነህ ! አለችኝ።
ፈተናውን እያስተጓጎለችኝ ነውና ወደፈተናዬ ፊቴን አዞርኩ። ጀርባዬን ደለቀችው። ደነገጥኩ፤ ግን ስለተናደደች ነው፤ ብዬ ተውኳት። የፈተና ወረቀቴን ለመስጠት ስዘጋጅ ዝቅ ባለ ግን ጠንከር ባለ ድምጽ ደነዝ፣ አለችኝ። መለስ ብዬ አይቻት ወጣሁ።
ፈታኙ ወረቀቱን እየተቀበለኝ፣ ምነው ፊትህ የተደናገጠ መሰለ፤ አለኝ። “ምንም፣ ቲቸር…” ብዬ ፈገግ ለማለት ሞከርኩ።
ከፈተናው በኋላ ግን ፣ ላገኛት ጠበቅኳት። እንደወጣች ቁጣ በተሞላው ድምጽ መልሱን ስጠኝ፤ ስልህ ለምን ዘጋኸኝ? አለችኝ። አላስቀዳሽም በቃ ሁለተኛ እንዳታስቢው ስላት ፤ ፈገግ ብላ ሁለታችንም ነው፤ የወደቅነው እኮ አለችኝ። እሱን እናየዋለን ፤ ስላት ታየው የለ? ብላኝ ተለያየን ።
የፈተናው ወረቀት ሲመጣ መምህሩ ፣ ለምን ሁለት የመልስ ወረቀት ሰጠህ ሲለኝ ደነገጥኩ። በአንደኛው 18 ከ20 አግኝተሃል፤ በአንዱ ደግሞ 8 ከ20 አለኝ። የምሰጥህ ዝቅተኛ ያመጣህበትን ወረቀት ነው አለኝና ሁለተኛ እንዲህ ያለ ብልጠት እንዳይደግምህ፤ አለኝ። በመጨረሻም ይህንን ማን እንዳደረገ ሳውቅ ከንዴት ይልቅ ብልጠቷ ገረመኝ። አንዳንድ ሰው እኔ ከወደቅሁ፣ ሌላውም ይውደቅ፤ አብረን እንወድቃታለን እንጂ ማን አልፎ ማን ይቀራል የሚል ልብ አለው። ዞር ብዬ ሳያት ከንፈሯን በጥርሷ ነክሳ በድል አድራጊነት፣ ሁለት አውራጣቶቿን ቀስራ፣ አሳየችኝ ። ወደ ወንበሬ እየተመለስኩ ስለተናደድሽ ነው፤አይደል እንዲህ ያደረግሽው? አዎ፤ አለችኝ።
ዳግመኛ በጉዳዩ ዙሪያ አላነገርኳትም ፤ በጥንቃቄ አመቱን ዘለቅሁት። በኋላ በሥራ ዓለም ከተሠማራን በኋላ ፣ ተገናኘንና ያን ጊዜ ለምን ዝም አልከኝ ፤ ስትል ጠየቀችኝ። ያኔ ከእኔ የጠበቅሽው፣ ስናደድ፣ ስቆጣና ሳዝን ማየት ነበረ፤ አንደኛ እሱን ከለከልኩሽ። ሁለተኛ ፣ ብመታሽ ኖሮ እስከዛሬ ትረሽው ነበረ። የዕድሜ ልክ ትምህርት እንደሆነሽ አስባለሁ። ይሁንናም ሁለቱንም ከመከልከል ሌላ ቢቻል መልሴ ሊሆን የሚገባው “ በቃ ይቅርታ አድርጌልሻለሁ ፤” ማለት ቢሆን መልካም ነበረ፤ አልኳት። “መተው ነገሬን ከተተው” እንዲሉ አባቶች፣ በመተዌ ነው፤ ዛሬም መነጋገር የቻልነው አልኳት ። ቢረፍድም ይቅርታ ተጠያየቅን ። ቀናነት ለአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ይጠቅማልና።
አንድ ሰው ቀናና አዎንታዊ አስተሳሰብን ሲመርጥ ክፉ አድራጊውን ፣ አንደኛ በአስተሳሰብ ይበልጠዋል። ሁለተኛ ራሱ፣ ደስተኛና ሰላማዊ ይሆናል። ሶስተኛ፣ በዝምታው ወይም በይቅርታው በዳዩን ያስደንቀዋል፤ ባይደነቅ እንኳን “ምነው ባላደረግሁት ኖሮ፤” ብሎ ያስቆጨዋል፤ በሌላ ሰው ላይ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይሰነዝር ትምህርት ይሆነዋል።
አሉታዊ አስተሳሰብን ገንዘቡ ያደረገ ሰው በእኔ መንገድ፣ ሃሳብ ፣ ቅኝት፣ መስፈሪያ ካልሆነ ሁሉም ነገር ልክ አይደለም ብሎ የሚያስብ ነው። የአሉታዊነት ሰማይ ከዋክብት የሌሉበት ድቅድቅ ጨለማ ነው። ይህን ባህሪ ያዳበረ ሰው፣ በብርሃን መመላለስን አይመርጥም ፤ በነገር ሁሉ ጠርጣሪነት፣ አለመረጋጋት፣ ትዕቢትና ሁሉን አውቃለሁ ባይነት የተፀናወተው፣ ገታራ ሰው ነው።
ስለዚህ ቀና ሰዎች ፣ ራሳችንን በአዎንታዊ አቋም ላይ ስናደርግ ከላይ ከተገለጹት መልካም ያልሆኑ ባህሪያት ከልክለናል ማለት ነው። በዚህም በአሰራርም ሆነ በአኗኗር ተጠቃሚነታችን ወደር አልባ ነው፤ የሚከተሉትን ጠቃሚ እርምጃዎች በመውሰድም ከአስቸጋሪ ቁመና ላይ በመውጣት የህይወት ጉዟችንን ማስተካከል እንችላለን።
1) ትሁት እንሁን፡- “ብዙዎቻችን ታላቅ ነገርን ማከናወን አንችል ይሆናል፤ ነገር ግን ትናንሽ ነገሮቻችንን በታላቅ ፍቅር መስራት እንችላለን” ሲባል ሰምቻለሁ። እናም ማናቸውንም ነገር በፍቅርና በትህትና ለማከናወን ከተዘጋጀንና ከገፋንበት የተሳካልን ዓላማ አስፈጻሚዎች እንሆናለን። በትህትናችን የሚቀርብን ነገር የለም።
2) ጥሩ ተማሪ እንሁን ፡- በችግሮቻችን ያለፍንባቸውን ወልጋዳና ጠማማ ጉዞዎች በማሰብ የቀደመው እንቅፋት መልሶ እንዳይመታን አስተዋይ ተማሪዎች እንሁን ። ከተቸገርንበት ነገር የምንማር እንጂ በችግራችን ባህር ውስጥ የምንንቦጫረቅ ምስኪኖች መሆን የለብንም ። እንዲያውም ብልህ ከሞኝ ውድቀት ይማራል እንጂ አዳልጦ በጣለው መሬት ላይ ተመልሶ አይንጋለልም ።
እናም አሁንም ራሳችንን ካለፈው መልካምም ሆነ መጥፎ አጋጣሚ እናስተምር። ለመማር ያልተዘጋጀ ሰው አይሻሻልም ፤ ሌሎችን ማስተማር ብቻውን ራስን አያሻሽልም።
3) ጽኑ እንሁን፡- በነገርህ እና በአሰራርህ ሁሉ ላይ አሉታዊ ሃሳቦች እንዳይወርሱህ ተጠንቀቅ። ካልገመትከው ስፍራ አንዳች ፍላጻ ቢወረወርብህ ይሁነኝ ብለህ ለእርሱ ስፍራ በመስጠት አትበሳጭ። አትርበትበትም ፣ ቢከፋህም መከፋትህን ዋጥ አድርገህ ይዘህ ለመፍትሔው ራስህን አዘጋጅ እንጂ፣ ችግሩን እያገላበጥክ አትወዛወዝ፤ ለማንም ደግሞ ያጋጠመህን ነገር ደጋግመህ በመናገር በደልህን አታውጋ፤ ብዙው ሰው (80 ከመቶው ሰው) ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ አገልግሎትና የደረሰብህን ላልደረሳቸው ከማዳረስ ያለፈ ፋይዳ የለውም። የችግሩን መንስኤ ካጣራህ በኋላ ለመፍትሔው ያለህን ስፍራ ወስደህ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋገር።
ጽኑ ሰዎች የማይለዋወጥ ተክለ-ሰብዕና ያላቸው ስለሆነ አመለካከታቸውም በአዎንታዊነት የተሞላ ነው።
4) ዕይታችንን እንጠብቅ፡- ይሄ ብዙ ጊዜ ለመሪዎች የሚመከር ነው። መሪዎች እይታቸውን ሲጠብቁና ዓላማቸውን ሲገነዘቡ የሚመሩትን ሃይል በመግራት የመጨረሻውን መስመር አብረው ያቋርጣሉ፤ እንጂ አይሰናከሉም ። ለእያንዳንዱ ችግር መልስ ለመስጠት እያጎነበሱ ከዓላማቸው አይዘናጉም፤ ከጉዟቸው አይደናቀፉም። ስለዚህ፣ እይታን መጠበቅ፣ ለጋራ ጉዞ ብቻ አይደለም፤ በጋራ ለማመስገንና ለመመረቅም (ሪቫን ለመቁረጥ) ይረዳናል።
ከዓመታት በፊት የተማርኳትን በልቤ ከትቤ ይዣለሁ ። እርሱም ዝንባሌ የምርጫ ጉዳይ መሆኑን ነው፤ መባሉን አምንበታለሁ። ዛሬም ይህንን ሃሳብ አደንቃለሁ፤ ስለዚህ አዎንታዊ ዝንባሌን አዳብሬ እየኖርኩ ነው፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን ሆኜ “ይህም ለበጎ ነው” ማለትን ተለማምጃለሁ። ስለዚህ አሉታዊ ዝንባሌ ያዳበሩ ሰዎችን ሳገኝ ምርጫቸው ነውና አላዝንም። ህይወት በምርጫ ባትመጣም (መርጠን አንወለድምና) ፤ አኗኗር ግን የምርጫ ጉዳይ መሆኑን አጥብቄ አምናለሁ። ስለዚህ አኗኗራችንን እንዲህ ከቃኘነው ነፍሳችን በደስታው ቅኝት ውስጥ ታዜማለች፤ ታመሰግናለች፤ ታርፋለች። በዚህም ከሌሎች ጋር ህብረት ማድረግ ይሆንልናል፤ ማህበራዊነትና ለሌሎች መቆርቆር ገንዘባችን ይሆናል ፣ ሰብዓዊነት በድርጊት ይገለጻል። እናም ምርጫው የግላችን ነው ። አዎንታዊ አስተሳሰብን ማዳበር ወይም አሉታዊ አስተሳሰብን የመኖሪያ ምርኩዝ አድርጎ መጓዝ! እኔ አዎንታዊ አስተሳሰብን መርጫለሁ፤ እናንተስ?
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 11/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ