
ግብርና በሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና ከሰባ በመቶ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መተዳደሪያ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ የግብርና አሰራር ዘዴያችን ኋላ ቀር በመሆኑ ለዘመናት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባንን ጥቅም ሳናገኝ ቀርተናል። ባለንበት ወቅት የግብርና ማሻሻያ ከያዛቸው መርሀ ግብሮች አንዱ በአነስተኛ መሬት ላይ በተበታተነ መልክ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ዘመናዊ አሰራርን ተከትለው ወደ ገበያ መር ግብርና እንዲሸጋገሩ ማስቻል ነው። በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስተባባሪነት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሞከር በነበረው ገበያ መር ኩታ ገጠም የግብርና ልማት አርሶ አደሮች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ ተገልጿል። ህዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ‹‹ገበያ መር ኩታ ገጠም የግብርና ልማት›› ይፋ በሆነበት ወቅት አዲስ ዘመን ከትግራይ፣ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል የመጡ መልካም ተሞክሮ ያላቸው አርሶ አደሮችን አነጋግሯል።
ርዕሰ ደብር ሚካኤል ዮሀንስ በደቡብ ትግራይ አምባላጃ ወረዳ አይባ ቀበሌ የሚኖሩ አርሶ አደር ናቸው። አርሶ አደሩ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በመታገዝ በኩታ ገጠም ከሚያዋስኗቸው አጋሮቻቸው ጋር ተደራጅተው አመርቂ ውጤት እንዳገኙ ይናገራሉ። በስምንት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ የተደራጁ አርባ አርሶ አደሮች በአንድ ቀን አርሰው በአንድ ቀን እንደዘሩና በልማት ሰራተኞች በሚደረግላቸው ድጋፍ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ሁሉ ጥቅም ላይ በማዋል በአካባቢው ታይቶ የማይታወቅ የስንዴ አዝመራ ማየታቸውን ያስረዳሉ። በኩታ ገጠም ከተደራጁት አርባ እርሶ አደሮች ውስጥ አሥራ አምስቱ ሴት አርሶ አደሮች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በአነስተኛ መሬት ላይ የሚያርሱ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ከቤት ፍጆታ በዘለለ ለገበያ የሚተርፍ ምርት እንዲያመርቱ የቴክኖሎጂ እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል። በዚህም ቀደም ሲል በሄክታር ከ15 እስከ 20 ኩንታል ብቻ ያገኙ እንደነበርና አሁን ግን ከ35 እስከ 40 ኩንታል እንደሚያገኙ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በኩታ ገጠም ተደራጅቶ ማረስ ተመሳሳይ ግብዓቶችንና ሙያዊ ድጋፍ ለማግኘትም አመቺነት እንዳለው የተናገሩት አርሶ አደሩ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ሁሉ በኩታ ገጠም ተደራጅተው ቢያርሱ ምርታማነት እንደሚጨምርና ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማግኘት እንደሚቻልም ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ምርታቸው ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር የጠቀሱት አርሶ አደሩ አሁን ግን ከራሳቸው የሚተርፍ ምርት እንደሚኖራቸውና የገበያ ትስስርም እንደተፈጠረላቸው አስረድተዋል። መንግስት የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ግብርናውን ለማዘመን የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነ የጠቀሱት ርዕሰ ደብር ሚካኤል አርሶ አደሩም የሚደረግለትን ዕገዛ ተጠቅሞ ምርቱን በማሳደግ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ ወረዳ ጉርሚቾ ቀበሌ በ82 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ከተደራጁ 624 አርሶ አደሮች ውስጥ መዲና ኮርቦ አንዷ ነች። እርሷን ጨምሮ 144 እማወራዎች በኩታ ገጠም እርሻው እንደታቀፉ ትናገራለች። ኩታ ገጠም እርሻ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ከማሳደጉም በተጨማሪ የሴት አርሶ አደሮችን እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አሰራር እንደሆነም ጠቅሳለች። አርሶ አደሯ ኢቮን የተባለውን የገብስ ምርጥ ዘር በኩታ ገጠም ተደራጅታ በመዝራት ውጤታማ እንደሆነች ትናገራለች። መዲና ቀደም ሲል ከቀለብ የማይተርፍ ምርት እንደምታመርት ገልጻ አሁን ግን በግብርና ባለሙያዎች በሚደረግላት ድጋፍ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማግኘቷን ተናግራለች። ከአሰላ ብቅል ፋብሪካ ጋር የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላትም አስረድታለች።
ባለፈው የበጋ ወራትም ውሃ ገብ በሆኑ መሬቶች ላይ በኩታ ገጠም ተደራጅታ ድንች በማምረት በ75 ጊዜ ምልልስ (ቢያጆ) በመኪና ለገበያ ማቅረባቸውን ገልጻ አሁንም የገብሱ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ድንች ለማምረት መዘጋጀታቸውን ተናገራለች። በኩታገጠም ተደራጅቶ ማረስ የመሬት ብክነትን እንደሚቀንስና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም እንደሚያመችም ገልጻለች።
ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ሽንዴ ወረዳ ዋዝንግስ ቀበሌ የመጣችው አርሶ አደር ነጻነት ከበደ በዚህ መርሀግብር በመልካም ተሞክሯቸው ከተመረጡ አርሶ አደሮች አንዷ ነች። በ178 ሄክታር መሬት ላይ 273 ወንዶችና 14 ሴቶች በድምሩ 287 አርሶ አደሮች እንደተደራጁ አስታውሳ፤ ፓኬጆችን በሙሉ በመጠቀም ምርታቸው በጥራትም በብዛትም መሻሻል እንደታየበት ትናገራለች። ቀደም ሲል የሚያመርቱት ምርት ከቤት ፍጆታ በዘለለ ለገበያ እንደማይበቃ የገለጸችው አርሶ አደሯ ዛሬ ላይ የተሻለ ምርት ማግኘታቸውንና በአካባቢው ከሚገኙ ዱቄት ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው ገልጻለች። ኩታ ገጠም እርሻ ተመሳሳይ ዘር በተመሳሳይ ቀን ለመዝራት የሚያስችል እና በአንድ ጊዜ በርካታ አርሶ አደሮችን ተደራሸ ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ተናግራለች። ወደ ፊትም ግብርናውን ለማዘመን መልካም ጅምር እንደሆነ ጠቅሳለች። ጎልቾ የተሰኘ ምርጥ ዘር ስንዴን በመዝራትም በሄክታር እስከ ስልሳ ኩንታል ድረስ የሚገመት ምርት እንደምታገኝ ጠቅሳ ቀደም ሲል ከነበረው ምርት አንጻር በእጥፍ ማምረት መቻሏን ተናገራለች። የአካባቢው ምርታማነት እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት የማጨጂያና የመውቂያ ማሽኖችን የመጠቀም ልምድም እየተስፋፋ መምጣቱን ትናገራለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012
ኢያሱ መሰለ