
እ.ኤ.አ በሚያዝያ 2019 በኢትዮጵያ እና በ2018 ህዳር ወር በኢንዶኔዥያ በቦይንግ 737 ማክስ አይሮፕላን ላይ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በተከሰተው የመከስከስ አደጋ 346 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ይታወሳል። በሁለቱ አገራት የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ ቦይንግ ከባድ ጫና ውስጥ ገብቶ ቆይቷል። ከሁለቱ ሰቆቃዎች በኋላ ሳልሳዊ ሰቆቃን ለመከላከል ላለፉት ዘጠኝ ወራት አይሮፕላኑ ከበረራ ታግዶ ቆይቷል። በመገባደድ ላይ ያለው የፈረንጆች ዓመት ሳይጠናቀቅ አይሮፕላኖቹ ዳግም አየር ላይ ይታያሉ የሚል ተስፋ ሰንቆ ነበር።
በወቅቱ ቦይንግ በአጭር ጊዜ ወደ በረራው እንደሚመለስ ተስፋ እንዳለው የገለፀ ቢሆንም፤ የዩኤስ የአየር ተቆጣጣሪዎች ግን አይሮፕላኖቹ በአጭር ጊዜ አየር ላይ የመታየት ዕድል እንደማይኖረው እየገለፁ ይገኛሉ። አይሮፕላኑ መብረር ያቆመ ቢሆንም ኩባንያው አይሮፕላኖችን የማምረት ሥራውን ግን አላቆመም ነበር። አሁን ያለው ነገር ቦይንግ እንዳሰበው ሳይሆን በተቃራኒው እየሆነ ነው። በመሆኑም ኩባንያው የማምረት ሥራውን ለማቆም ተገዷል። ከአንድ ሳምንት በኋላ በሚገባው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የማምረት ሥራውንም በጊዜያዊነት እንደሚያቆም ይፋ አድርጓል።
ኩባንያው የሰጠውን መግለጫ ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ ሰሞኑን እንደዘገበው፤ ኩባንያው ከቀናት በኋላ በጊዜያዊነት የማምረት ሥራውን ያቆማል። ቦይንግ በአሜሪካ ከሚገኙ ቁንጮ ኤክስፖርተሮች ግንባር ቀደሙ ሲሆን፤ በዓመት እስከ 806 አይሮፕላኖችን በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አቅም ያለው ተቋም ነው። ኩባኒያው አይሮፕላኖችን ማምረት በጊዜያዊነት ሲያቆም ሠራተኞቹን የመቀነስ ዕቅድ እንደሌለው የገለፀ ቢሆንም የአይሮፕላኑን ክፍሎች አምራች በሆኑት ኩባንያዎች እና በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ግን እየተነገረ ነው።
በመግለጫው መቼ ወደ ገበያ እንደሚመለስ ይፋ ያላደረገው የዓለማችን ግዙፉ የአይሮፕላን አምራች ቦይንግ ፤ የ737 ማክስ አይሮፕላንን ደህንነት አስተማማኝ አድርጎ ወደ አገልግሎት መመለስ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን የኩባንያው ኃላፊዎች በመግለጫው አብራርተዋል። በቀጣይ ጊዜያት ማሻሻያዎችን በማድረግ በበረራ ተቆጣጣሪዎች፣ በኩባንያው ደንበኞቻች እና የበረራው ተጠቃሚዎች ዘንድ አመኔታን ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርግ አብራርቷል።
እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2019 በኢትዮጵያ ከተከሰከሰ በኋላ 737 ማክስ በሰማይ ላይ መታየት ባይችልም ላለፉት ዘጠኝ ወራት የችግሩን መንስኤ ሲያጣራ ቆይቷል። ኩባንያው በደረሰው የምርመራ ውጤት መሰረትም አይሮፕላኑ ራስ-ሰር የቁጥጥር ሥርዓቱ (automated controlling system) ላይ ያለው ችግር የመከስከስ አደጋው መንስኤ መሆኑን እንደደረሰበት ይፋ ያደረገው ኩብንያው ችግር እንዳለበት የታመነበትን ራስ-ሰር የቁጥጥር ሥርዓት መልሶ ለመሥራት (ዲዛይን) በማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቋል።
እንደ ኩባንያው ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት 400 የሚሆኑ አዳዲስ 737 ማክስ አይሮፕላኖች ይገኛሉ። አይሮፕላኖቹን ለመግዛት ውል የገቡ ብዛት ያላቸው የዓለም አየር መንግዶች መኖራቸውም ይታወቃል። ነገር ግን የቦይንግ መሐንዲሶች በሶፍትዌሩ ላይ የሚታየውን ችግር ሙሉ በሙሉ እስኪቀርፉ ሲጠበቅ ቆይቷል። አይሮፕላኖቹን በአጭር ጊዜ ለደንበኞች ለማቅረብ በትኩረት እንደሚሠራ በመረጃው ተመልክቷል።
የጉዞ ኢንዱስትሪ ተንታኝ የሆኑት ሄንሪ ሃርትዌልድ በበኩላቸው ቦይንግ 737 ማክስ አይሮፕላን ማምረት ለማቆም ያሳለፈው ውሳኔ ያልተጠበቀ ነው ብለዋል። ኩባንያው ባለፈው ሰኞ ቀን የማምረት ሥራውን እንደሚያቆም ማሳወቁን ተከትሎ የኩባንያው የሽያጭ ዋጋ በ4 በመቶ አሽቆልቁሏል። የቦይንግ ውሳኔ በእራሱ ላይ እና ለኩባንያው የተለያዩ ክፍሎችን በሚያቀርበው እንዲሁም በአየር መንገዶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል ብለዋል። “ውሳኔው ከቦይንግ ጋር ግንኙነት ባላቸው አየር መንገዶች፣ የቦይንግ አካል በሆኑት 600 በሚደርሱ ኩባንያዎች እና በቦይንግ በራሱ ላይ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል”ሲሉም ሥጋታቸውን ገልፀዋል።
ላለፉት ዘጠኝ ወራት ከበረራ በመታገዱ ኩባንያው እስካሁን የዘጠኝ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ማምረት ማቆሙን ይፋ ካደረገ በኋላ የኪሣራው መጠን ሊጨምር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። የኩባንያው ምርት ማቆም በዓለም አቀፍ የቦይንግ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የራሱ ጫና ይኖረዋል ተብሏል።
የቲል ግሩፕ አቪዬሽን ተንታኝ ሪቻርድ አሉላፊያ በበኩላቸው፤ ቦይንግ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ የወሰነው የምርት ማቆም ውሳኔ ለቦይንግ አቅራቢዎች “መጥፎ እና የከፋ” እንደሆነ ገልፀዋል። በተለይም ኩባንያው አቅራቢዎችን ያሰናብታል ወይስ አይሮፕላኑ ዳግም ወደ ምርቱ እስኪመለስ ለአቅራቢዎቹ እየከፈለ ይቆያል የሚለው እጅግ አወዛጋቢ ነው ብለዋል።
የተለያዩ የአይሮፕላን ክፍሎችን አቅራቢ ኩባኒያዎች ግን እስካሁን ከቦይንግ ጋር በቅርበት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የምርት መቆም የሚያስከትለው ተጽዕኖም ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ቦይንግ 737 ማክስን በብዛት ሲጠቀሙ የነበሩ አየር መንገዶች 737 ማክስን ለመተካት ሌሎች አይሮፕላኖችን በኪራይ እየተጠቀሙ በመሆኑ እስካሁን ድረስ የአየር መንገዶች ደንበኞች ላይ የደረሰባቸው ተጽዕኖ አለመኖሩ የተነገረ ሲሆን፤ በቀጣይም አየር መንገዶቹ ሌሎች አይሮፕላኖችን በግዥና በኪራይ ስለሚጠቀሙ የአየር መንገዶች ደንበኞች ላይ የሚደርስ አሉታዊ ተጽዕኖ አይኖርም ተብሏል።
በኤንዳኡ አናሊቲክስ ማዕከል የአቪዬሽን ዘርፍ ተንታኙ ሹኮር ዩሶፍ ቦይንግ ላይ የደረሰው ኪሣራ ቦይንግን ለህዝብ ማመላለሻነት በስፋት ተጠቃሚ በሆነው የቻይና አየር መንገድ አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ባለፈው ሐምሌ ወር ቦይንግ ለመግዛት ክፍያ ፈፅመው አይሮፕላኖቻቸውን ላልተረከቡትና ተረክበው ሊጠቀሙበት ያልቻሉትን አየር መንገዶች ለመካስ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ካሳ መበጀቱን ማሳወቁ ይታወሳል። በወቅቱ አይሮፕላኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል የሚል እሳቤ ተይዞ እንደነበርም ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012
መላኩ ኤሮሴ