ኢትዮጵያ ሊጎበኙ የሚችሉ የበርካታ የተፈጥሮና የሰው ሠራሽ ቅርሶች ባለጸጋ ናት። እነዚህን ሀብቶች ማልማት ላይ ብዙም ባለመሥራቷ ግን ከቱሪዝም ዘርፍ ማግኘት ያለበትን ያህል ጥቅም አላገኘችም። ለእዚህ ደግሞ የፓርኮች አለመተዋወቅ፣የመሰረተ ልማት አለመዘርጋትና በተለይ በርካታ ጎብኚዎችን ሊስቡ በሚችሉ የቱሪስት መስህቦች ላይ አለመሠራቱ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
የኢኮኖሚ ባለሙያው አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፤ ሀገሪቱ የቱሪዝም መስህቦቿን በተለይም በርካታ ጎብኚዎችን ሊስቡ በሚችሉት እንደ ፓርኮች ባሉት ላይ አለመሥራቷ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ አንዳትሆን አርጓታል ይላሉ። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እንደሚለይ ይጠቁማሉ።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ጎብኚዎችን ሊስብ በሚችል የቡዙሃን (ማስ) ቱሪዝም የሚያመጣ የቱሪዝም መስህብ ላይ አልተሠራም። ጎብኚዎች አፍሪካ በሚባልበት ጊዜ የዱር እንስሳትን መጎብኘት ነው የሚታያቸው። በሀገራቸው የሌለውን ለማየት ነው የሚፈልጉት። የኛ ፓርኮች ደግሞ በደንብ አልተያዙም። ትልቁ ነገር ፓርኮቹ አሉ፤ከኬንያና ታንዛኒያ ግን በጣም ወደኋላ የቀሩ ናቸው።
በዱር እንስሳት አያያዝም ሆነ በሆቴልም ይቀረናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፓርክ እንደ እነ ታንዛኒያ ሰራጌቲ ፓርክ አይደለም። ‹‹ሰራጌቲ›› ፓርክን ዓለም በሙሉ በቴሌቪዥን ያውቀዋል። እንዲህ ዓይነት የማስተዋወቅ ሥራ እኛ አልሠራንም። ፓርኮቹም ደካማ ናቸው የቡዙሃን (ማስ) ቱሪዝም ሊኖር የሚችለው ፓርኮቻችንን በደንብ ስንይዝ ነው።
‹‹እኛ ጋ ያለው ቱሪዝም ቅርስና እና ባህል ነው›› የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣ ይህን ሊጎበኙ የሚችሉት የተማሩት /ኤሊቱ/ መሆናቸውን ይገልጻሉ። እንዲህ ዓይነቱ መስህብ የሚጎበኘው ታሪክ የሚያውቅ፣ ባህልን የሚወድ የዱሮን ነገር ለማየት የሚፈልግ ሰው ነው ይላሉ። የዚህ ዓይነቱ ቱሪዝም በውጭው ሀገርም ቢሆን ብዙ አለመሆኑን ይናገራሉ። ሀገራችንን ለብዙሃን (ማስ) ቱሪዝም ምቹ ለማድረግ ፓርኮቻችንን በሚገባ መያዝ አለብን፤መሰረተ ልማቱ በደንብ መሠራት አለበት ይላሉ። በአንድ ባላ ብቻ መንጠልጠል የለብንም። ለብዙሃን (ማስ) ቱሪዝምን ረስተናል ለማለት ነው ስለ ለብዙሃን (ማስ) ትሪዝም በተደጋጋሚ የማነሳው ብለዋል።
አምባሳደር ጥሩነህ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገሮች አንጻር ሲታይ ቱሪዝምን የጀመረችው በቅርቡ መሆኑን ይጠቁማሉ። ‹‹እኛ ሁሌም ያለፈውን እንረሳለን፤ ከደርግ ጊዜ ወደህ ነው ቱሪዝም ላይ በሚገባ መሥራት የጀመርነው፤ በደርግ ስርዓት ዘርፉ ተጎድቷል፤ ራሳችንን እያወዳደርን ያለነው ግን በቱሪዝም ላይ 100 ዓመት አካባቢ ከሠሩት ጋር ነው ›› የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣ራሳቸውን መቶ ዓመት አስተዋውቀው እና አዘጋጅተው እዚህ ከደረሱት ከጎረቤት ሀገሮችና ከግብፅ ጋር ራሳችንን እያወዳደርን እንደምንገኝ ይገልጻሉ። የተነሳንበትንና የደረስንበትን አብረን ማየት አለብን። ይህ ማለት የማስተዋወቁን ነገር ዝም ብለን ማየት የለብንም ማለቴ አይደለም ይላሉ።
እንደ አምባሳደር ጥሩነህ ገለጻ፤ባለፈው ጊዜ የታጣውን ለማግኘት በማስተዋወቅ በኩል በጣም መሥራት አለብን። አሁንም በብዙ መንገድ የኢትዮጵያ ስም እየተነሳ ነው። በአሁኑ ጊዜ በረሀብ አይደለም የምትታወቀው፤በልማት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም የምትታወቀው በጦርነት ሳይሆን በሰላም ነው። ይህ ሁሉ መልካም ሁኔታ ነው። እነዚህ ሁሉ መልካም ሁኔታዎች ናቸው፤ በደንብ ግን አላስተዋወቅናቸውም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሆነውን ሳይሆን ምንም ወንጀል የማይፈጸምባት፣ በሰው ህይወት ላይ በብዛት አደጋ የማይደርስባት ሀገር ብለን በደንብ አላስተዋወቅንም።
‹‹ዋናው የምናስተዋውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ ይገባል። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ቅድም እንዳልኩት ለተመረጡ ሰዎች ነው፤ ባህል ታሪክ ለሚያውቁ ነው የተዘጋጀነው። ለብዙኃን (ማስ) ቱሪዝም አሁን ባለው ሁኔታ ተግዳሮቶች አሉ፤ በቅድሚያ እዚያ ላይ መሥራት ያስፈልጋል›› ይላሉ። እንደ ጥምቀት ፣መስቀል፣ ጨምበለላ፣ገዳ እና ኢሬቻ ያሉት የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኔስኮ መመዝገባቸው ለብዙሃን(ማስ) ቱሪዝም አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ቢችሉም ለብዙሃን(ማስ) ቱሪዝም ላይ ግን በትኩረት ሊሠራ ይገባል ይላሉ።
ሀገሪቱ ከቱሪዝሙ ዘርፍ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ አለመሆኗን የቱሪዝም ኢትዮጵያ የገበያ ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ እሸቱ ይገልጻሉ። ለዚህ ትልቁ ችግር ደግሞ ይህ ሀብት በዓለም አቀፍ ገበያ በሚገባ እንዲተዋወቅ አለመደረጉ መሆኑን ይናገራሉ። አቶ ንጉሴ የቱሪዝም ሀብቱ ብቻ አይደለም ያልተዋወቀው ኢትዮጵያን ራሷን የውጭ ዓለም የሚያውቃት በጥሩ ጎኑ አይደለም ሲሉ ያብራራሉ።
አቶ ንጉሴ ሁለተኛ ብለው የሚጠቅሱት ምክንያት ደግሞ ሀገሪቱ አላት ተብለው የሚታወቁት የመስህብ ስፍራዎችና ወደ ስፍራዎቹ የሚወስዱ መንገዶች አለመልማታቸውን በመጥቀስ የአምባሳደር ጥሩነህን ሃሳብ ያጠናክራሉ።
እንደ አቶ ንጉሴ ገለጻ፤ መልማት ማለት ሁለት ነገር ነው፤አንዱ የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ናቸው። ሆቴሎች፣ሎጆች ፣ምግብ ቤቶች በበቂ ሁኔታ የሉም። ሁለተኛው መሰረተ ልማት ነው። መንገድ ፣ውሃ፣ የኢንተርኔት ኮኔክሽን በበቂ ሁኔታ የሉም። በዚህ የተነሳም ትላልቅ የአስጎብኚ ድርጅቶች ጎብኚዎችን ወደ ሀገሪቱ ሊልኩ ይፈልጉና ሻወር የሌለው ሆቴል ነው ያለው እንደዚህ ነው በሚል ስም የሚያጠፉም ስላሉ / ብላክ ሌብል ስለተደረገ/ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርገውናል።
ያለንን ያህል እንኳ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም የሚሉት አቶ ንጉሴ ፣ የለማ አለ፤መሰረተ ልማት የተሟላለት አለ። ካለው በታች በማሳነስ ነው በሌሎች ወገኖች እየተዋወቀ ያለው። ትክክለኛ ገጽታ እየታወቀ አይደለም። እጥረት አለ፤ከእጥረቱ በላይ ምንም እንደሌለ ተደርጎም እየተወሰደ ነው። እሱ መጥፎ ነገር ፈጥሯል የሚል ሃሳብ አለኝ ይላሉ።
እንደ አቶ ንጉሴ ገለጻ፤ ችግሩን ለመፍታት መንግሥት እየሠራ ነው። በቱሪዝም ላይ የሚሠራ የራሱ ኃላፊነት እና የሥራ ድርሻም የነበረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የሚባል ተቋም ነበር። ድርጅቱ በመንግሥት በጀት የሚተዳደር ነው። ተቋሙ በሌላ ስም ቱሪዝም ኢትዮጵያ በሚል በአዲስ መልክ ተቋቁሟል። አዳዲስ ኃላፊነቶችና መብቶች ተካተውበት ነው የተቋቋመው። የራሱን ገቢ እያፈላለገም የሚሠራ ይሆናል። ሰፊ ሥራ እንዲሠራ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረውለታል። በዚህም ወደፊት ሰፊ የማስተዋወቅና የልማት ሥራ ይሠራል። በዚህም ለውጥ ይመጣል ተብሎም ይጠበቃል።
የብዙኃን (ማስ) ቱሪዝም ማለት የጎብኚዎች ብዛትን የሚያሳይ መለኪያ ነው የሚሉት አቶ ንጉሴ፣ በተፈጥሮ ሀብት የቱሪዝም ሀብቶቻችን ላይ ማተኮር አለብን የሚል መሆኑን ይገልጻሉ። የቱሪዝም ሀብታችን እኛ እንደ እነ ኬንያ እንድንሠራ የማይፈቅድልን ሁኔታ አለ የሚሉት አቶ ንጉሴ፣ፓርኮቻንን ብናይ ተፈጥሮን መሰረት ባደረገውና ሳፋሪ በሚባለው ላይ መሰረት አድርገን እንዳንሠራ ያለው ሀብት ብዙ ችግሮች እንዳሉበት በመግለጽ የአምባሳደር ጥሩነህን ሃሳብ ይጋራሉ።
እንደ አቶ ንጉሴ ገለጻ፤ሀገሪቱ ካሏት ፓርኮች መካከል በሙሉ ልብ ኑ ጎብኙ ብላ ልታስተዋውቅ የምትችለው የማያሳፍሩት ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክና ባሌ ተራራዎች ፓርክ ብቻ ናቸው። ሌሎቹ በተለይ የአዋሽ ፓርክ የፍየል መዋያ ሆኗል። በዚህ የተነሳም ለአደንም ይሁን ለሳፋሪ ለማዋል ያስቸግራል።
የብዙሃን(ማስ) ቱሪዝምን በማልማት በኩል አሁን አንዳንድ ጅምሮች እንዳሉም ይጠቁማሉ። በደቡብ ክልል እንደ ነጭ ሳር ፣ማጎ ያሉ ፓርኮችን በትስስር(ኮንሴሽን) ልምድ ካላቸው የውጭ ኩባንያዎች ጋር ለማልማት መታሰቡን በመጥቀስም፣መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ በጋራ ይዘው መሰረተ ልማቱን የሚያሳድጉበት አሠራር እየተዘረጋ መሆኑን ይጠቁማሉ። ፓርኮቹ የሆኑ ጊዜ ቱሪስቶች በብዛት መጥተው እንዲጎበኙ ለማድረግ ገበያ ማፈላለግ እንደሚቻልም ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል