ውድ ወገኖቼ ፣ ጥሪያችንን አክብራችሁ ወደጉባኤው አዳራሽ ስለመጣችሁ አመሰግናለሁ፤….. ውድ እንግዶቻችን ያደረግሁላችሁን ጥሪ አክብራችሁ ወደ ሰርጉ ሥነሥርዓት ለመታደም ስለመጣችሁ ሁላችሁንም በተጋቢዎቹ ሙሽሮችና ወላጆቻቸው ስም ማመስገን እወዳለሁ። …. ውድ ምዕመናን ለምስጋና ወደቤተ እምነታችን እንኳን መጣችሁልን…ወዘተ የሚሉ መታደምንና መካፈልን ምክንያት አድርጋችሁ በተገኛችሁበት እና በተገኙላችሁ ስብሰባዎች ላይ አንድም የምትሰሙት አለዚያም ለሌሎች የምታሰሙት የምስጋና ዓረፍተ ነገርን ነው ፤ ከላይ ያቀረብሁት።
አሁንም ይህን ዓምድ በቋሚነት ለመከታተል መንገድ አቋርጣችሁ ጋዜጣውን በግዥ፣ በደንበኛነት ወይም በመስሪያ ቤት አግኝታችሁ ታማኝ አንባቢ በመሆን የምትታደሙትን እናንተን አንባቢዎቼን አለማመስገን እንዴት ይሆንልኛል። ያገራችን ሰው የወለዱትን ካልሳሙለት የደገሱትን ካልበሉለት ….ይል የለ?! እናም ህይወታችን በምስጋና ካልታሸ ምኑን ኖርነው፤ እንዴትስ የህይወትን መልካም ጎንና ወለላ ከጠጣን በኋላ ሳናመሰግን ዝም ማለት ይቻለናል? እንዲያውም ይኼኔ ነው፤ ያገራችን ሰው እነ “በልቶ ዝምን”፣ ምስጋና ቢስ የሚለን።
የዛሬ ርዕሰ ነገሬም ይኸው የምስጋና ህይወት ነው። ምን በልተን፣ ምን አይተን፣ ምን ሰምተን ፣ ምን ሰርተን፣ ምን ቀምሰን … እናመስግን? ለምትሉኝ በቀጥታ ወደራሳችሁ ልውሰዳችሁ እወዳለሁ።
ጠዋት ከተኛችሁበት (ምንም ይሁን ምን የመኝታችሁ ዓይነት) አንደኛ ለመንቃት መቻላችሁና አዲስ ቀን መጀመራችሁ ምስጉን እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ምክንያቱም በተኙበት ያሸለቡ እጅግ ብዙ አሉና። የበለጠ ምስጉን የምትሆኑት ደግሞ የወገብ ህመም ሳይኖርበት፤ የትከሻ ህመም ሳይጎበኛችሁ፣ ያለሌላ ሰው ድጋፍ መነሳታችሁ፤ እኮ ነው። ጫማችሁን ሰው ሳይሰጣችሁ ማጥለቃችሁ፤ ከሁሉም ከሁሉም ደግሞ በጤናማ አተነፋፈስ ላይ ቆይታችሁ፣ ወደመፀዳጃ ቤት ኮራ ብላችሁ ጎራ ማለታችሁ ነው።
ዓረቦቹ እኮ በጤናማ ሁኔታ (የተቃጠለ አየር ይሉታል፤) ፈስ በማስወጣታቸው “አላህም ዱሊላሂ” ይላሉ፤ ድንቅ ናቸው፤ ይሄ ነገር ያቃታቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ አስባለሁና። ይህንን እየጻፍኩ እያለ አንድ ምሳሌ ትዝ አለችኝ ። እነሆ ምሳሌዬ!!
የሰውነት ክፍሎቻችን ስብሰባ ጠርተው፣ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ይጣላሉ። አእምሮ ሁሉ ነገርህን የምቆጣጠረው እኔ ስለሆንኩ ያለእኔ ሌሎቻችሁ ከንቱ ናችሁ እናም መሪነቴን የሚቀናቀን ማንም ሊኖር አይችልም፤ አለ። ልብ ደግሞ በተራው ተነሳና፣ ቀልደኛ ደም ቅዳ ደም መልሱን የምቆጣጠረው እኮ እኔ ነኝ፤ እኔ ስራ አቆምኩ ማለት ሁለመናህ ቀጥ አለ፣ ማለት ነው፤ እንዲያውም ልብ ባለበት በዚያ ነፍስ አለች ነው፤ የሚባለው፤ እኮ አለ።
ይህን የሰማ ጆሮ በዙሪያው ዓለም ያለውን መረጃ ሰምቶ ፍርድ ለመስጠት አእምሮም እንዲሰራ ልብም ስራውን እንዲያከናው ሚዛን መጠበቂያው እኔ ነኝ …እንዲያውም እኛ ጆሮዎች ነን… እግዚአብሄር በጣም አስፈላጊ ስለሆንን፤ ሁለት ያደረገን እኮ አለ። ዓይን ቀበል አደረገችና፣ ለቁጥር ለቁጥርማ እኛም አለን፤ ቁም ነገሩ ማየት ነው፤ ታውቃለህ “ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል” ፤ የተባለልን በብርሃን ለመመላለስ እኛን የሚያክል ወደረኛ የሌለን የጨለማ አጥፊዎች ነን ፤ ሁልሽም ዝም ብትይ ጥሩ ነው አለ።
እጅም ተዘረጋጋና ሰርቼ ባላበላህ ኖሮ አዳሜ በህይወት አትቆይም ነበር፤ አለና በቁጣ ተወራጨ፤ መዳበሴስ ፣ ማካፈሌስ፣ ማስጻፌስ፣ መሰንዘሬስ…ኧረ ምኑ ቅጡ የኔ ውለታ ሆ! አለ። እግር ቀበል አደረገና (ፈገግ ያለ ይመስለኛል በምኑ እንዳትሉኝ እንጂ) አሁን፣ እኔ አልንቀሳቀስም ብል እኮ አዳሜ፣ አንድም ተቸክለሽ ነበር የምትቀሪው፤ አለዚያም ትንፏቀቂያት ነበረ፤ (ፎቃቃ ሁሉ ሳይል አይቀርም)። ልብ ብላችኋል አለ ፤ በቁጣ ። ሰው ዛፍ እንዳይሆን ምክንያቱ ማንም ሳይሆን እኔ ነኝ፤ ስለዚህ እኔን ብታከብሩ ያዋጣችኋል አለ። አንጀትም ፣ ጉበትም ፣ ጸጉር እንኳን ሳይቀር ሚና እንዳላቸውና ነገር ያለእነርሱ እንደማይሳካም እንደማይሰምርም ተናገሩ። ኩላሊትም፣ ተው እንጂ ብዙ ባታናግሩኝ ይሻላል፤ ሰሞኑን በእኔ ጦስ እየሆነ ያለውን እየሰማችሁ ነውና ፣መሪነቱ የሚገባው ለእኔ ነው አለ። ምላስ ከጥርስ ጋር እየተጋጨች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ከአሳቢው እኩል ነገር መተርጎሚያቸው እኔ ነበርኩ ፣ ጣዕም ማጣጣም የሚችሉት፣ ምሬትን የሚቀምሱትና የሚያነጻጽሩት ብቻ ምን አለፋችሁ የእኔ ድርሻ የሌለበት የፈሳሽና የጋዝ የጠጣር ነገር ማጽደቂያ ማወራረጃ የትም የለም። በእኔ በኩል ያላለፈ ምግብም ሆነ መጠጥ እንዲሁም አየር ከንቱ ነውና ይህንኑ አውቃችሁ አሁኑኑ እጅ ብትሰጡና መሪያችሁ ብታደርጉኝ መልካም ነው፤ አለ።
በስብሰባው ላይ እየተወከቡና እየተንጫጩ እያለ ሁሉም በድንገት እንደመታፈን ሽቅብ ሽቅብ ይላቸው ገባ፤ ወዲያውም ምንድነው ምንድነው መባባል ጀመሩ። “ኧረ ጨነቀኝ ምንድነው፤ኧረ ሁለመናዬ ተወጣጠረ” ማለት ጀመሩ፤ ሁሉም ሁሉንም በሚያነካካ ስሜት አንዳቸው ሌላኛውን ማየት ጀመሩ። ድንገት ከርቀት ድምጽ ተሰማ እኔ ነኝ ፤ አለች ፊንጢጣ! አያችሁ፣ ያገባሻል ብላችሁ ስብሰባ እንኳን አልጠራችሁኝም፤ ግብዞቹ ሆይ!…. እንዳሻችሁ ማለት መንቀባረራችሁንና ራሳችሁን በዋናነትና ፊታውራሪነት ማሳበጥና መጋሸብም ትችላላችሁ፤ ግን ከሰውነት ክፍላችሁ የማያስፈልግና ብቸኛ የሚባል ነገር አለ እንዴ ? ሁሉም እኮ፣ ባለበት ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። እኔ መውጫ በሩን ጥርቅም ሳደርግ አዳሜ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጭ፤ ሆነብህ አይደል? እኔም የአይንን ያህል ፤ የእጅና እግርን ያህል፤ የልብን ያህል አስፈላጊ ነኝ ። እርስ በእርሳችን ካልተደጋገፍን የሰውየው ህይወት ያጥራል እንጂ፤ አይረዝምም አለቻቸው። ሁሉም እውነቱን ለመቀበል የትም አልሄዱም፤ ራሳቸውን ከመነቅነቅ ውጭ!!
ቁም ነገሩ ሁላችንም ለአንዳችን አንዳችንም ለሁላችን አስፈላጊዎች መሆናችንን ማወቁ ላይ ነው። ደስታችንና ምስጋናችንም የሚመነጨው አንድነታችን ከ ሚ ፈ ጥ ር ል ን ልባዊ ሃይል ነው፤ አለቻቸው። (ለመሆኑ የልብ ራስ የት ነው የጉበትስ? አደራ እንዳትጠይቁኝ ።) የሰው ልጅ እንዲህነቱ አጠያያቂ አይደለም፤ አጠያያቂው ነገር ህብረትን መጥላ ታችንና አንዳችን ለሌላ ኛችን ያለንን ዋጋ አለማጤኑ ላይ ነው።
ምስጋና ያለው ህይወት፣ አያላክክም። ለውድቀቱ ምክንያት ማንንም አያደርግም። ለሽንፈቱ፣ ዘመድ አዝማዱን አለቃውን፣ የትዳር አጋሩን ተፎካካሪውንና ተወዳ ዳሪውን፣ የሥራ ባልደረባውንም ሆነ ጓደኞቹን አያደርግም። ወደ ውስጥ እንጂ ወደውጭ አይዘልም። ችግሩን የሚፈትሸው በቅድሚያ ራሱ ዘንድ ነው። በውድቀቱ የሚያመሰግን ሰው ለመነሳቱ ምክንያት ራሱ ዘንድ እንዳለው ያውቃል። የሚነጫነጭ ግን የትም አይደርስ፤ አሁንም አሁንም የሚዳክረው እዚያው ነው።
የምናመሰግንበት እጅግ ብዙ ነገር አለን። ከመኝታችን የጀመርነው ምስጋና በእንቅልፋችንም ይገለጻል ፤ እጅግ ሰላማዊ እንቅልፍና እረፍት ማግኘት የምስጋናችን ምንጭ ይሆናል። ከእንቅልፍ በኋላ ያለውን ማመስገኛ ውሎ ነግሪያችኋለሁ። ለመራመድ መቻላችን፣ እቅዳችንን ለማብሰልሰል የተረጋጋ አእምሮ ስላገኘን፣ ወደ ቁርሳችን ወይም ምግባችን ስንሄድና፣ የቀረበውን ምግብ በተሰጠው ጊዜና መጠን ለመብላትና ለመጠጣት መታደል ምስጋና ቢስ እንዳንሆን ያስገድደናል።
ለዚህ አንድ አስረጅ ልስጣችሁ። እጅግ የሞላውና የደላው፤ ዘመድ አለኝ። በየጊዜው በትንሽ በትልቁ ጉዳይ ደግሶ ማብላት ይወዳል፤ ልብ በሉ ደግሶ ነዳያንንም ይሁን የተከበሩ ሰዎችን በዓመት ውስጥ በልጆቹም ሰበብ ይሁን በራሱ ምክንያት በትንሹ ሃያ ለሚያክል ጊዜ ከዓመት በዓላት ውጭ ደግሶ ማብላት ያውቅበታል። ጠረጴዛውን በምግብ ከሞላው ብፌ ዙሪያ መለስ ቀለስ እያለ፣ ብሉልኝ ጠጡልኝ ሲል ትህትናው እጅግ አስደናቂ ነው። እርሱ ግን ያበላ ፣ ይጋብዝ እንጂ ሲበላ አይታይም። ሲበላ ከታየም በጠረጴዛው ላይ ከተደረደረው፣ 26 የምግብ ዓይነት ጎመንና ጥቂት ቂጣ በ”ሲኒ እግር” ይዞ እየተንጎራደደ እባካችሁ ብሉልኝ ማለቱ ነው፤ አንድ ቀን ታዲያ ስፈራ ስቸር፤ “አንተስ አትበላም እንዴ” አልኩት፤ “ሐኪም አትብላ ብሎኝ እኮ ሁሉን መብላት ካቆምኩ ቆየሁ፤ ጨምረህ ብላ እንጂ ለእናንተው ነው የተዘጋጀው፣” አለኝ ምግቡን እያየ። ሁሉ ሞልቶ ሁሉን ለመብላት አለመቻልም አለ። ስለዚህ፣ ጠራርገህ የመብላት አቅሙና ፈቃዱ ያለህ ሁሉ ምስጋና ልታቀርብ ይገባሃል ።
በነገራችን ላይ ፈረንጆች ፤ ለየጥቃቅኑ ነገር ሁሉ ማመስገን ይችሉበታል። አንድ ጠረጴዛ ላይ ሆነው እንኳን ማንኪያ ስለተቀባበሉ፣ ጨርቅ ስለተሰጣጡ፣ ሳሙና አንዱ ላንዱ ስላቀበለው ሁሉ አንደኛው አንዱን ማመስገን ይወዳሉ። እኛ ግን ለዚህ ብዙ የታደልን አይደለንም። በምንም ምክንያት ይሁን በምን አንድ ሰው አኗኗሬን፣ አመጋገቤን፣ አስተኛኘቴን፣ ንባቤን፣ ጉዞዬን፣ የመስማት ጉጉቴን ከፍ ካደረገልኝ ካመቻቸልኝ ላመሰግነው ይገባኛል። በምስጋና ውስጥ አድራጊውን ለሌላ ደግነትና ለሌሎች ተቆርቋሪነት ማነሳሳት ልንጨምር እንችላለን። ከዚያም በላይ እኛንም ምስጋና ቢሶች ከመባል ያድነናል። ስለዚህ መመሰጋገንን መልመድ ይገባናል። ምስጋና የምድሩን ብቻ ሳይሆን የሰማዩን በረከት ያዘንብልናል።
ጉዳዩን በሐገር ደረጃ ካየነው፣ ተመሳሳይ ነው። ባህሎቻችን የሚወራረሱትና የምንግ ባባቸው ናቸውና ምስጋና ይገባናል፤ ሥነ-ምግባሮቻችን ተወራራሾች ናቸውና ደስ የሚያሰኝ ነው። ፈሪሐ- አምላክ ያለን ህዝቦች ነንና (ይህም በብዙው የሀገራችን ክፍል አኗኗር የተገለጠ ነው) ልናመሰግን ግድ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በቢሾፍቱው የአውሮፕላን አደጋ፣ ለሞቱት ለማናውቃቸው የልዩ ልዩ ሐገር ዜጎች፣ ስፍራው ላይ ተገኝተን ነጠላ ዘቅዝቀን፣ ሙሾ እያወረድን የምናለቅስ፤ የአስራ ሁለታቸውን፣ የሰላሳና አርባቸውን ዝክር ስፍራው ላይ ተገኝተን ለነዳያን በነፍስ ይማር የምናበላ ባለወርቅ ባህል ህዝብ ነን። ይህንን አይቶ አለማመስገን ደግሞ አይቻልም ። የየሰርጉ፣ የየዓውድ ዓመቱ፣ የጅጌው፤ የደቦው ፣ የወንፈሉ የእቁቡ፤ የገንፎው፣ የእድሩ፣ ምርጣ-ምርጥ ባህላችን ቢነገር ካጣነው ይልቅ ያለን ሃብት ገና ገና ለሺህና 10 ሺህ ዓመታት የሚያኖረን ነው። ይኼ ታዲያ ደስ አይልም ?
እኛ ከጎደለን ይልቅ የሞላን፤ ካጣነው ይልቅ ያገኘነው፤ ከጠጠረብን ይልቅ የላላልን፤ ከተወጠረው ይልቅ የረገበልን በብዙ እጅ የሚበልጥብን ነን። ከእዚያ ይልቅ ግን ጉድለታችን፣ እጦታችንና ውጥረታችን ላይ ስለምናተኩር ምስጋና ቢስ ህይወት እንመራለን። ስለዚህ ካንደበታችን ምሬት፣ ቁጭትና ማጉረምረም ጠፍቶ አያውቅም። የሚያስገርመው ምሬትና ማጉረምረም ደግሞ ወደ ድል በር አይወስደንም፤ በእጦት ያዳክረናል፤ ዕድሜያችንንም በብስጭት እንድንመራና ጠላት እንድናፈራ ነው፤ የሚያደርገን ። ስለዚህ የምስጋና ህይወት ቢኖረን የምንጠቅመው ራሳችንን ነው። ለዚህ ደግሞ ዋናው መንገድ ከሌሎች ብዙ አለመጠበቅና በራሳችን ላይ በአመዛኙ መደገፍ እና ባለን ለመደሰት መቻል ነው። ይህም የሚመነጨው ከአመስጋኝነት ህይወት ነው።
አሜሪካውያን ሰሞኑን የምስጋና ሳምንታቸውን አክብረዋል። እኛስ ይህ በዓል ቢኖረንስ ያልኩት አንድ ወዳጄ፣ ባለፈው ጳጉሜ ወር ላይ አንዱ ቀን “የኩራት ቀን ነው” ሲባል፣ የእኛ ሰው ክፉኛ እንዴት እንደተወራጨ አታስታውስም ? ኩራት፣ ምስጋና ፣ ሞገስ፣ ፍቅር፣ ጸጋ …የሚባሉ የምስጋናና የመወድስ አዎንታዊ ቃላትን ፣ የተፀየፍንበትን ምክንያት አላውቀውም። ግን በአንድ ነገር አምናለሁ፣ መልካም አስብ፤ መልካም ይሆንልሃል፤ መልካም ተናገር መልካም ይመለስልሃል፤ ደግ ተመኝ ደግ ይደረግልሃል በሚለው እሳቤ አምናለሁ። የተቆጣን ሰው እኮ በፈገግታ ማለዘብ ይቻላል፤ ክፉኛ ቅር ያለውን ሰው በምስጋና እንዲረጋጋ ማድረግ ይቻላል። የምንመርጣቸው ቃላት ሃይል የግንኙነታችንን አቅጣጫ ያሳምሩታል፤ ወይም ያበላሹታል።
አመስጋኝ አንደበት ቁጣን ታበርዳለች፤ ነጭናጫና አውጋዥ አፍ ግን የተሰበሰበን ይበትናል፤ የተረጋጋን ያናውጣል። ስለዚህ አላካኪና አሳባቢዎች አንሁን ፤ ይልቅ እናመስግን። በነገራችን ላይ፤ የዓምዱ ጠባብነት ይወስነናል እንጂ በዚህ ጉዳይ በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል ።
በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም ያለፈውን ሳምንት አልፈን መጥተናልና እናመስግን፤ በህይወት ስላለን ነው፤ ማመስገን የቻልነው፤ የሌሉትማ አበቁ። ዓይኖቻችሁ ጤናማ ሆነው፣ ስላነበባችሁልንም እናመሰግናለን፤ ስለዚህ የሳምንት ሰው ይበለን!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/12
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ